Sunday, 23 October 2022 00:00

የዜማ አገር ዜማ እየራቀው ነው።

Written by  እዝራ ኬ
Rate this item
(1 Vote)

 የዘፈንና የግጥም ንባብ፣ ዜማና ከበሮ እየተምታታ ነው።
- ሮፍናንን መተቸት፣ የዘመኑን ትውልድ መተቸት አይሆንም?


  “ሙዚቃ… የድምጽ እና የፀጥታ አንድነት ነው” የሚል ጽሁፍ ሲያዩ፣… “እንዴ! እውነትም!” ብለው የሚደነቁ ይኖራሉ።
“እና ምን እንሁንልህ” ብለው የሚያላግጡና የሚዘባበቱም አይጠፉም።
 “እንዴት?” የሚል ጥያቄ የሚጭርባቸው ሰዎች መኖራቸውም አይቀርም።
“እንደዚያ ይባላል!” ብለው ነገሩን አቅልለው በእንጭጩ ለመቅጨት የሚመኙም ሊኖሩ ይችላሉ።
“ሙዚቃ ማለት የድምጽ እና ፀጥታ ጥምረት ነው? ሊሆን ይችላል። ላይሆንም ይችላል። ግን፣ ሙዚቃ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ?” የሚሉ የማጣጣያ ጥያቄዎች ቢመጡም አይገርምም።
በአንድ በኩል፣ ለውጥ  አያመጣም።
ስለሙዚቃ መፈላሰፍም ሆነ መዘባረቅ፣ የሙዚቃ ምንነት ላይ ለውጥ አያመጣም። ሳይንስም ሆነ ጥንቆላ፣ አስትሮሚም ሆነ አስትሮሎጂ፣ በእውኑ ዓለም ህልውና ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም።
ተፈጥሯዊ ምንነትን ሊቀየር አይችልም- ትክክለኛ እውቀትም ሆነ ጭፍን  እምነት። እውነትን መናገርና መመስከር፣ ሐሰትን ማንሾካሾክና ማዛመት፣ እውኑን ዓለም የመገንባት ወይም የማፍረስ አቅም የላቸውም። በተፈጥሯዊ ምንነት ላይ ትርፍና ኪሳራ አያመጡም።
ስለ ሙዚቃ መመራመርና መዘባረቅ፣ በእውቀት መፈላሰፍና በዘፈቀደ መለፍለፍ፣ በሙዚቃ ምንነት ላይ ቅንጣት ጠብታ አይጨምርም፣ ቅንጣት ሽራፊ አያጎድልም።  ለውጥ አያመጣም።
በሌላ በኩል ሲታይ ግን፣… ትልቅ ለውጥ፣ ተዓምረኛ ልዩነት ያመጣል።
“ነገር ግን” ብሎ ማሰብ ሁል ጊዜ ያስፈልጋል።
ማወቅ እና አለማወቅ፣ ማሰብና አለማሰብ፣ ሳይንስና ጥንቆላ፣ አስተዋይነትና ጭፍንነት፣… በተፈጥሯዊ ምንነት ላይ ኢምንት ታህል ለውጥ አያመጡም። በሰው አእምሮ ላይ፣ በሰው ተግባርና ማንነት ላይ ግን፣ ተዓምረኛ ሃይል አላቸው።
መቼም፣ ሙዚቃ ወይም ዘፈን የተለያዩ ድምጾች በስልት እየተደራረቡና እየተከታተሉ የሚጓዙበት የሚጎርፉበት ጅረትና ፏፏቴ ይመስላል። ይሄ እውነት ነው። ሰምቶ ማረጋገጥ ይቻላል። ነገር ግን፣  ከድምጽና ከጸጥታ ቅመሞች የተቀናበረ ዘፈን ሰምታችሁ ታውቃላችሁ? ጸጥታ ከተፈጠረ ምናልባት ዘፈኑ ስላለቀ ሊሆን ይችላል። የመድረክ ዝግጅት ከሆነማ፣ አንድ ዘፈን ሲያልቅ ሌላ እስኪመጣ ድረስም የጸጥታ እድል የለም። በመሸጋገሪያ ሙዚቃ ይሸፍኑታል። በዘፈን መሃልማ የምን ጸጥታ?
ማንም የሙዚቃ አድማጭ ሊመሰክር ይችላል። በዘፈን መሃል፣ አንዲት የፀጥታ ፅበ ማግኘት ያስቸግራል።
ምናልባት፣ የሙዚቃ ባለሙዎች የሚያውቁት ሌላ አይነት ጸጥታ ይኖር ይሆን? ጸጥታ መፍጠር አስፈላጊ ቢሆን ኖሮ፣ ሙዚቀኞች ጉዳቸው ነበር የሚፈላው። ዘፈን መሀል ሁለት ሶስት ቦታ ብቻ ለአፍታ ጸጥታ መፍጠር ቢሞክሩ፣ ሙዚቃውን ከመስበርና ከማደናቀፍ የዘለለ ጥቅም የለውም።
የተመረጡ የድምጾችን በዓይነትና በመጠን አማርጦ፣ ፍጥነትንና አሰላለፍን መስመር አስይዞ፣ የድምጾችን ይዘትና መልክ በመቀነስ ወይም በመጨመር፣ አከታትሎ ወይም አደራርቦ በማቀናበር የሚገኝ የድምጽ ውሕደትና ጅረት ነው- ሙዚቃ።
የሙዚቃ ባለሙያዎች፣ የተመረጡ የድምፆችን በዓይነቶችን በስልት አቀናብረው እንዴት ከመነሻ እስከ መድረሻ እንደሚያስኬዱት ሊነግሩን ይችላሉ።
ስንት ድምፆችንና ስንት ጸጥታዎችን ተጠቅመው፣ እንዴት ደባልቀውና ቀላቅለው ሙዚቃውን እንደሚሰሩት ብንጠይቃቸው ግን፣ በስካር ስሜት የምናወራ ሊመስላቸው ይችላል። ቅዠት ውስጥ ገብተን እየቀባጠርን እንዳይሆን ይገምቱም ይሆናል።
ምናልባት፣ የሙዚቃ አድማጮች የማያውቁት፣ የሙዚቃ ባለሙያዎችም የማያተኩሩበት፣… የፊዚክስ አዋቂዎች ሊነግሩን የሚችሉት ልዩ የሙዚቃ ምስጢር ይኖር ይሆን?
ዘፈኖችን አጥንተው፣ የሙዚቃ ድምጾችን በዘመናዊ መመርመሪያ መሳሪያ አማካኝነት ፈትሸው፣ “የድምጽና የፀጥታ ቅንብር” መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ አይችሉም? የሳይንስ ሰዎች ይችላሉ።
ግን ማን ይሰማቸዋል?
 በድምጾች መሃል “ፀጥታዎች” እየተዛነቁ እየተነሳነሱ የሚፈጥሩት ሙዚቃ የለም። የሙዚቃ አድማጮች፣ የሙዚቃ ባለሙያዎችና የሳይንስ ሰዎች እንደየአቅማቸው ማመሳከርና መመስከር ይችላሉ። እውነታ ነውና።
አንዳንዴ ግን፣ እውነታ ከቁም ነገር አይቆጠርም። “የተቃራኒዎች አንድነት” የሚል ኮሙኒስቶች ፍልስፍና ወይም ፈሊጥ እንደ ወረት በነገሰበት የያኔውን ዘመን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። በዚህ ፈሊጥ ሳቢያም ነው ሙዚቃ የድምጾችና የፀጥታዎች ውህደት ነው የተባለው።
ዛሬ ደግሞ፣ ሌሎች ፈሊጦች በርክተዋል።
አንዳንዱ የግጥም ንባብን ከሙዚቃ ጋር ካላዜምኩ ብሎ መከራውን ያያል- “ግጥም በጃዝ” ይላል።
ገሚሱ ደግሞ፣ ሙዚቃና ከበሮ ይምታታበታል። ሙዚቃን ከዜማ ጋር ያፋታል። ዘፈንን ግጥም ንባብ ያስመስለዋል። ሮፍናን ይህን ነው የኔ ትውልድ የሚለው?
የሙዚቃ መሳሪያ ዓይቶች ጥቂት ናቸው ይባላል። የክር እና የትንፋሽ።
ያው፣… የዋሽንት ዘር ናቸው የትንፋሽ መሳሪያዎች። ሌሎቹ፣… ክራር፣ ጊታር፣ ቫዮሊን፣ ፒያኖ፣… የክር መሳሪያዎች ናቸው። የክር መሳሪያዎች ሁሉ መነሻ፣… ክራር (በገና) እንዲሁም መሰንቆ ናቸው ይላሉ- ሙዚቃ መሳሪያ ታሪክ አጥኚዎች።
በእርግጥ ከበሮም እንደ ሙዚቃ መሳሪያ ይቆጠራል። ግን፣ ግን፣ የምናጨበጭብበት መዳፍስ፣ የሙዚቃ መሳሪያ ልንለው ነው? በዱላ የእንጨት ወለሉን ወይም ጀሪካኑን መደብደብስ። የድሮ የትምህርት ቤት ደወልስ? ብረት ወይም ልዩ አለት ዛፍ ላይ አንጠልጥሎ በብረት ወይም በድንጋይ መምታትስ?
በእርግጥም፣ የከበሮ አይነቶች፣ ምንም ቢበዙ፣ ዜማ አይወጣቸውም። እንደ ክራር ወይም እንደ ዋሽንት ራሳቸውን ችለው ሙዚቃ ለመፍጠር አያገለግሉም። ግን ያግዛሉ። “ድጋፍ ሰጪ” እንበላቸው?
ደግሞም፣ እነ ከበሮ በሙዚቃ ውስጥ አገልጋይ አጃቢ ከመሆን ያለፈ አገልግሎት አልነበራቸውም። የላቸውም አልተባለም። አልነበራቸውም።
ዛሬማ፣ ዜማ በከበሮ እየተሸነፈ ነው። ቢያሸንፍም ግን፣ ያለ ዜማ ምን ዋጋ አለው?
እንደ ዘመናችን የግጥም ንባና የከበሮ ግርግርን እንደ ዘፈንና እንደ ሙዚቃ የምንቆጥር ብንሆን፣ የቱንም ያህል የከበሮ አፍቃሪ ብንሆን፣ የከበሮ ምት የቱንም ያህል ብንራቀቅበት ዜማ አይወጣውም።
በተቆርቋሪነት ስሜት እየተንጨረጨርን፣ “ከበሮ” ድንቅ ዜማ ነው፤ የአፍሪካ መመኪያ ነው” ብለን ብንጮህ፣ በስሜት ብንጨስ ለውጥ አያመጣም። እውነታውን መቀየር አይችልም።
በከበሮ ማዜም አይቻልም። ለዜማ መጫወቻ የተሰራ ከበሮ የለም።
የክር እና የትንፋሽ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ያጅባል። መረማመጃቸው ነው- ለነ ክራር ለነዋሽንት፣ ለነጊታርና ለነሳክስፎን፣ ለፒያኖና ለኦርጋን”፣ ለቫዮሊንና ትራፔት።
የዜማ አገልጋይ ሲሆን ነው የከበሮ ክብሩ። ከበሮ የነገሠ እንደሆነ ግን፣ ዜማ ይሟሽሻል። የተበጣጠሰ ይሆናል። ለዚህም ነው፤ የሮፍናን ስራዎች ላይ፣ ብዙም የዜማ ፈጠራ የማናገኘው።
ይሄ ሲባል ግን፣ ሮፍናንን ለመተቸት አይደለም። ማን ይደፍራል?
ሮፍናንን መተቸት፣ ትውልዱን መተቸት አይሆንም? በዚያ ላይ፣ ከአፍሪካ 30 ወይም 50 አዲስ አርቲስቶች መካከል ሮፍናን እንደሚገኝበት “በፎርብስ-አፍሪካ” እትም ላይ ተጠቅሷል።
በዚያ ላይ፣ ከታዋቂ የአሜሪካ የሙዚቃ ኩባንያ ጋር የስራ ኮንትራት ለመፈረም የበቃ አርቲስት ነው።
በዚያ ላይ፣ ከተለያዩ ነባር ልማዳዊ ዜማዎች ላይ፣ ቀንጨብ ቀንጠስ እያደረገ ወስዷል። ተጠቅሞባቸዋል። ሮፍናንን መተቸት፣ የብሔር ብሔረሰብ ሙዚቃዎችን እንደ መሳደብ እንዳይቆጠር ያሰጋል።
ቢሆንም ግን፤ ኢትዮጵያ፣ የዜማ አገር ናት። ሌሎች የአፍሪካ አገራት፣ “በራፕ” ልክፍት ተይዘው ሲሰክሩ፣ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ተገዳድራለች።
አሁን ግን እንጃ። ዜማ እንደ ዋዛ ሆኗል። እንደ ጠላት ሳይቆጠርስ ይቀራል?
የዜማ አገር ዜማ ሲርቀው ማየት ያሳዝናል።

Read 2757 times