Monday, 24 October 2022 00:00

እጀ ሰባራ ላለመሆን

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

ዶክተር ዐቢይ አህመድ መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በፓርላማ በተሾሙ ጊዜ፣ ለምክር ቤቱ አባላት ያደረጉት ንግግር በራዲዮና በቴሌቪዝን በተከታተለው ህዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተቀባይነት አስገኝቶላቸዋል። ወጣቶች የእሳቸውን ፎቶ ይዘው የድጋፍ ሰልፍ ወጥተዋል።
ጠ/ሚ ዐቢይ በአውሮፓና በአሜሪካ ባደረጉት ጉዞም፣ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከፍ ያለ ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። አንዳንዶች ከወገብ ጎንበስ ከጉልበት በርከክ ብለው እስከ ምድር ዝቅ ብለው ክብር እስከማሳየት ደርሰዋል።
ሁሉም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ድጋፋቸውንና አድናቆታቸውን የሰጧቸው እንደ እኔ ዐቢይን፣ በአብይነት አይተው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተናገሩትን አምነው ተቀብለው ነው። ጠ/ሚ ዐቢይ፣ በስራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስት እንዲሻሻል ያደርጋሉ የሚል ስሜት በህዝቡ ዘንድ ነበር። ዘርን መሰረት ያደረጉትን ክልሎች ለአስተዳደርና ለእድገት በተመቸ መንገድ እንደገና ያዋቅራሉ የሚል ተስፋ በዚያ ህዝብ ውስጥ ነበር። ግን አልሆነም።
ከሕዝቡ ተስፋ ጋር የሚስማማ ሃሳብ ይኖራቸዋል። በሌላ በኩል ከዚህ ጋር የማይገጥም ሃሳብ፣ “ለአንድ ሕዝብ ተብሎ ሕገ-መንግስት አይሻሻልም” ብለው በአደባባይ በተናገሩ ጊዜ ሰምተናል። ጠ/ሚ ዐብይ ሰው መሆናቸው የግል እምነትና አስተሳሰብ ቢኖራቸውም፣ የፓርቲ አባልና መሪ እንደሆኑም ማስታወስ ያስፈልጋል። ወደው ፈቅደው የተቀበሉት የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ፣ የፓርቲያቸው አላማና ተልዕኮ አስፈጻሚ በመሆናቸው በራሳቸው እምነትና አስተሳሰብ በነጻነት እንዳይራመዱ ሊገድባቸው እንደሚችል መገንዘብ አይከብድም።
በእርግጥ፣ ዋና እና አጋር የተባሉ የፖለቲካ ድርጅቶችን በአንድ ወጥ ፓርቲ ለማዋሐድ ያደረጉት ጥረት አይዘነጋም። ነገር ግን፣ የተለያዩ ቀለም ያላቸውን ጨርቆች ገጣጥሞ ከመስፋት ያለፈ ብዙም ውጤት ሲያመጣ እስካሁን አላየንም።
ጠ/ሚ ዐቢይ፣ በመጀመሪያዎቹ ወራት በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋገር መሄዳቸው፤ በአወንታ የሚታወስ ክስተት ነው። ይሁን እንጂ፣ አሁን ላይ ሆነን ስናስበው ግን፣ሥልጣናቸውን በሚገባ ሳያደላድሉ እና ሳያረጋጉ ወደ አሜሪካና ወደ አውሮፓ ለመጓዝ መድፈር ነበረባቸው ወይ ያስብላል። አይመስኝም። ይህም ብቻ አይደለም።
የመንግስትን ስልጣን እንደያዙ እንደ ለእነ ደብረጽዮን (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ጓዛቸውን ነቅለው መቀሌ ላይ እንዲመሽጉ አይፈቅዱላቸውም ነበር። ደርግ እንዳደረገው ሁሉ ጠቅላይ ሚስትር ዐቢይም የትሕነግ ባለስልጣናትንና ለእነርሱ ያደሩ በየፖለቲካ ድርጅቱ የሚገኙ ሰዎችን ልቅም አድርገው እስር ቤት ባጎሯቸውም ነበር።
ከአዲስ አበባ ወጥቶ መቀሌ የመሸገው የትህነግ አመራር፣ በመከላከያ ውስጥ የነበሩ የክልሉን ተወላጆች፣ የድርጅት አባሎችና ደጋፊዎች “ወደ ክልላችሁ ኑ” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፎ አሰባሰበ። ለሁለት ዓመት ከስምንት ወር በየጦር ክፍሉ ተዋጊና አዋጊ ሰዎችን ሲያሰለጥን ከርሞ በበቂ ተዘጋጅቻለሁ ብሎ በአሰበበት ጊዜ በክልሉ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላው ጫፍ የኢትዮጵያን ድንበር በመጠበቅ ላይ በነበረው የአገር መከላከያ ላይ “መብረቃዊ ጥቃት” ሰነዘረ። የቻለውን ያህል ያለ እርህራሄ ገደለ። ጥቃቱ እንደሚፈጸም አስቀድሞ መረጃ የደረሳቸው አንዳንድ የጦር ክፍሎች ራሳቸውን አደራጅተው ተከላከሉ። ሌሎችም ወደ ኤርትራ ግዛት ገብተው ተመልሰው ትህነግን መልሰው ማጥቃት ያዙ።
ትህነግ በከፈተው ልክ ማዕከላዊው መንግስት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ወሰደ። በአስራ ሰባት ቀን ውስጥም የእነደብረ ጽዮንን የትግራይ ክልላዊ መንግስት አስወግዶ የራሱን ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር መመስረት ቻለ።
መንግስት በብዙ መሰዋዕትነት ያገኘውን ድል የትሕነግን ጠባይ ጠንቅቆ ባለማጥናት፣ ከጠላት ኃይል በላይ የፖለቲካ ስራ ባለመስራት ለስህተት ተጋለጠ። ይባስ ብሎም ለትሕነግ ፍጹም ታማኝ የሆኑ ሰዎችን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ ቦታ ሰጠ። በስንት በመስዋዕትነት ያገኘው ድል መጠበቅ እንዳይቻል የሚያደርግ ሁኔታ ተፈጠረ።
የትሕነግ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ የክልሉ ሰዎች እጃቸውን በመከላከያው ላይ አነሱ። ሰራዊቱ ከተከፈተበት ጥቃት ለማራቅና ከክልሉ የሚገኙ ገበሬዎች የክረምት እርሻቸውን እንዲያርሱ በማሰብ መንግስት ጦሩን አወጣ። ትህነግ ግን ጦሩን ከኋላ ከኋላ እየተከተለ ለመውጋትና አልፎም ወደ አማራና አፋር ክልል ዘልቆ ለመግባት ቻለ። በደርዘን የሚቆጠሩ ዞኖችና ወረዳዎች የጦር ሜዳ ለማድረግ ጊዜ አልወሰደበትም። እስከ ደብረሲና በመዝለቁ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ዶ/ር ዐቢይን ጦር ግንባር ገብተው አዋጊ እንደሆኑም እናስታውሳለን።
ካለፈው ወር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት መከላከያ ሰራዊትና ጥምር ጦሩ በልዩ ልዩ አቅጣጫ የእነ ደብረ ጺዮንን ሰራዊት በመምታት ወደ ትግራይ ክልል እየገባ መሆኑ ታውቋል። አንዳንዶች “ምታ በዝምታ” እያሉ የሚገልጡት በዚህ እንቅስቃሴ በርካታ አካባቢዎች ከትህነግ እጅ እየተላቀቁ መሆናቸው እየተገለጸ ነው።
ቀስ በቀስ ከነደብረ ጽዮን ሰራዊት አላቆ ትግራይን በቁጥጥሩ ስር ለማድረግ እየተጓዘ ያለው መከላከያና ጥምር ጦር ከዚህ ቀደም ያጋጠመው ዓይነት ችግር ድጋሜ እንዳያጋጥመው በብርቱ የታሰበበት ይመስላል።
የታሰበበት እንደሆነም የሚያመለክቱ ነገሮች እንዳሉም ምልክቶች እየታዩ ናቸው። የጦሩን ተንደርድሮ ወደ ከተማ አለመግባት ከጥንቃቄ እርምጃዎች አንዱ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
ከተማ ይዞ አስተዳደር መዘርጋት፣ በአንድ አውደ ውጊያ፣ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለውን ቦታ ይዞ እንደመልቀቅ ሆኖ መታየት የለበትም። በከተማ ውስጥና በአካባቢው ልዩ ልዩ አስተዳደራዊ አገልግሎት የሚፈልግና የሚገባው ሕዝብ እንዳለ ማወቅ ግድ ነው። የእርሱን ጥያቄዎች መመለስና በዚያውም የህዝቡን ድጋፍ ለማግኘት መጣር አስፈላጊ ነው። መንግስት ለትግራይ ህዝብ ልዩ ልዩ እርዳታ ለማድረስ መንገዶች እየከፈተ መሆኑ የሚመሰገን ጅምር ነው።
ትሕነግ ለአለፉት አርባ ሰባት ዓመታት የትግራይን ሕዝብ በብቸኝነት በፈለገው አቅጣጫ ሲመራ የኖረ ድርጅት በመሆኑ በመፈራትም ሆነ በማክበር በህዝብ ስሜት ውስጥ ያለው ቦታ ተቃሎ ሊታይ አይገባም። ቀደም ብሎ ሴቱን በሴት፣ ወጣቱን በወጣት ማኅበር አደራጅቶ፤ ከቁጥጥሩ እንዳይወጡ ያደረገ በመሆኑ በገጠር ገበሬውንና በከተማ የከተማ ኗሪውንና የመንግስት ሰራተኛውን ሁሉንም በልዩ ልዩ አደረጃጀት በመያዝ ከቁጥጥሩ እንዳይወጡ አድርጓቸው ኖሯል።
ከ1997 ዓ.ም አገር አቀፍ ምርጫ በኋላ ደግሞ በሕዝብ ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ቁጥጥር አንድ ለአምስት በሚል አደረጃጀት በመፍጠር የባሰ አጥብቆት እንደነበር የታወቀ ነው። ስለዚህም መንግስት ወደ ክልሉ በሚገባ ጊዜ ይህን አደረጃጀት አስቀድሞ በመበጣጠስ፣ ሰዎች ግላዊ ነጻነት አንዲሰማቸው እና በመንግስት እንዲያምኑ ማድረግ ይኖርበታል። ይህን የድርጅቱን ጥልፍልፍ የማሰሪያ ገመድ መበጠስና መበጣጠስ ያለበት ትግራይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባና በሌሎችም አካባቢዎች በሚገኙ የድርጅቱ የደጀን ኃይል ላይም ጭምር ነው።
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት መንግስት ወደ ትግራይ ክልል በሚገባበት ጊዜ፣ መንግስታዊ መዋቅሩን ለማቋቋም የሚያስችሉትን ሰዎችን እየመለመለና እያሰለጠነ መሆኑ ለማወቅ ተችሏል። መመስገን ያለበት እርምጃ ነው። ግን የሚመለምላቸው ሰዎች ከትህነግ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሚገኙ ብቻ መሆን የለባቸውም። ከተቀዋሚ ፓርቲ ተመርጠው የተወሰዱት እነአቶ አብርሃ ደስታ ምን እንዳደረጉ ማስታወስ በቂ ነው።
ትሕነግ የትግራይና የዓለምን ሕዝብ እያነሳሳ ያለው በኤርትራ ጦር ተወረናል በማለት ነው። መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም። አንድም ነገር አለመናገሩ ደግሞ ለትሕነግ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን መካድ አይቻልም። ግድ “አካፋን አካፋ” ማለት አለበት። ትሕነግ ኤርትራ ወደ ትግራይ ክልል ገባች የሚለው በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት ለኤርትራ በተሰጠው አካባቢ ከሆነ ይህ የነስዩም መስፍን ስራ ውጤት እንጂ የመንግስት ድክመት አለመሆኑን በጥቁርና ነጭ ማሳየት ያስፈልገዋል። ትሕነግ እንዲዋሽ ጊዜም ቦታም መሰጠት አይኖርበትም።
ስለዚህም መንግስት እየደከመበት ያለው ጉዳይ ፍሬ ይሰጥ ዘንድ መሰረቱን የበለጠ እያስተካከለ መሄድ ይኖርበታል። የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ መመከት እንደ ውጊያው ሜዳ ሁሉ የመንግስት ዓይን ከፍ ያለ ቦታ ሊሰጠው ይገባል - እጀ ሰባራ ላለመሆን።
ቸር ወሬ ያሰማን!

Read 8926 times