Print this page
Saturday, 29 October 2022 11:40

"ህወሓት የውክልና ጦርነት ስለሚዋጋ ድርድሩ 99 በመቶ አይሳካም”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(5 votes)

ድርድሩ ባይሳካ መንግስት ምዕራባዊያንን ምክንያት አልባ የሚያደርግ ሥራ መስራት አለበት

ነገ ይጠናቀቃል የተባለው የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ፍሬ ያፈራል ብለው እንደማይጠብቁ ምሁራን ተናገሩ፡፡ ምሁራኑ የሰላም ንግግሩ በነገው ዕለት ይጠናቀቃል ወይም ፍሬ ያፈራል ብለው የማይጠብቁበትን ምክንያት ገልፀዋል፡፡ የማህበረሰብ አንቂው አቶ ስዩም ተሾመ፣ በድርድሩ ዙሪያ ላነሳንላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፤ ህውሃት የራሱን ሳይሆን የውክልና ጦርነት ስለሚዋጋ 99 በመቶ የሰላም ንግግሩ ፍሬ ያፈራል ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡ “ህውሃት ባንዳ ነው፤ የራሱ ጦርነት የለውም፤ የራሱ ጦርነት ብቻም ሳይሆን የራሱ ጭንቅላት የለውም፤ የጠላትን አጀንዳ ይዞ እየተዋጋ ስለሆነ በድርድሩም ሆነ በጦርነቱ ሂደት መወሰን ይችላል ብዬ አላምንም” ብለዋል።
“የጦርነቱን ሂደት እንኳን ብናይ አንድ ቡድን ጦርነት የሚጀምረው ሊያሸንፍ በሚችልበት ሁኔታ ነው” ያሉት አቶ ስዩም፤ ህውሃት ግን ጦርነቱን የጀመረው 360 ዲግሪ ነው፤ ይህ ማለት በአፋርም፤ በአማራም፤ በኤርትራ በኩልም ነው። ይሄ ቀጠናውን ለማሸበርና ለማወክ በተልዕኮ የተጀመረ ጦርነት እንጂ አሸንፎ አንድ ደረጃ ላይ ለመድረስ የተጀመረ ጦርነት አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
አቶ ስዩም አክለውም፤ “የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ሀይል አዛዥ የነበረው ጀነራል አበበ ተ/ሃይማኖት ፤”360 ዲግሪ ጦርነት ተጀመረብን፤ ይህንን ጦርነት ማሸነፍ አንችልም፤ ስለዚህ ወደ ኋላ አፈግፍገን ወደ ጉሬላ ጦርነት መሄድ አለብን” ብሎ አስተያየት መስጠቱን አስታውሰው፤ “ደብረፅዮንም ሆነ ታደሰ ወረደ ይሄን ሃሳብ ደጋግመው መናገራቸው የሚያሳየን ጦርነቱ የህውሃት የራሱ ሳይሆን የጋላቢዎቹ መሆኑንና ለማወክና ለመበጥበጥ እንጂ ለማሸነፍ ያልተጀመረ መሆኑን ነው” ሲሉ ሀሳባቸውን ያጠናክራሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ጦርነቱ የራሱ የህውሃት ካልሆነ ድርድሩም የሱ ሊሆን ስለማይችል ህውሃት በድርድሩ ላይ ወሳኝ ሆኖ ውጤት ይመጣል ብለው እንደማይጠብቁና በእርሳቸው ግምት 99 በመቶ እንደማይሳካ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ስዩም ገለፃ ከደቡብ አፍሪካው  ንግግር ይልቅ ሐሙስ ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና በአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መካከል የተካሄደው የስልክ ውይይት ውሃ የሚያነሳና የሚልቅ ነው ብለዋል። የሁለቱ የስልክ ውይይት ባለመግባባት የተጠናቀቀ ይመስለኛል ያሉት አቶ ስዩም፤ ይህን ግምታቻውን ያጠናከረላቸው ደግሞ ስለ ስልክ ውይይቱና ንግግሩ በሁለቱም በኩል መግለጫ አለመሰጠቱ ነው፡፡ “ከደቡብ አፍሪካው ድርድር ይልቅ ሁለቱ የጦርነቱ ባለቤቶች ማለትም ኢትዮጵያና አሜሪካ በመሪዎቻቸው በስልክ የተነጋገሩት ሀሳብ ግዘፍ እንደሚነሳባቸው አቶ ስዩም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ የሁለቱ ሚኒስትሮች የስልክ ውይይት የደቡብ አፍሪካው ንግግር በውጤት እንደማይጠናቀቅ ጠቋሚ ነው ያሉት አቶ ስዩም ፤ሌላው ማሳያ የቻይናው ልዑክ፤ የአውሮፓው ልዑክ፤ የራሺያው ልዑክም ሆነ የቱርክ ልዑክ ወደ ደቡብ አፍሪካ ባልሄደበት ሁኔታ የአሜሪካው ልዑክ ተወካይ ብቻ ለምን ደቡብ አፍሪካ መሄድ አስፈለገው ብለው ከጠየቁ በኋላ፤ ጦርነቱ የውክልና መሆኑን ተወካይ ደግሞ በድርድሩ የባለቤቱን ያህል ወሳኝ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል። ስለዚህ ከደቡብ አፍሪካው ንግግር ይልቅ የዶ/ር ዐቢይ እና የብሊንከን የስልክ ውይይት የጦርነቱ ባለቤቶች ማን እንደሆኑ የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ባለመግባባት ከተቋጨና ከከሸፈ የሰሜኑ ጦርነት እጣ ፈንታ ምን ይሆናል በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄም ሲመልሱ፤ በመጀመሪያ ለህውሃት ጦርነት ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ማጤን አለብን ይላሉ፡፡ ለህውሃት ጦርነት ማለት የድርድር ስትራቴጂ ነው ሲሉም ራሳቸው መልሰዋል፡፡ ለዚህ ሀሳባቸው መነሻ ያደረጉት ደግሞ የህውሃቶቹ አመራሮች እነ ታደሰ ወረደና ደብረፅዮን የሰጡትን መግለጫ ነው፡፡ “የእነዚህ ሰዎች እስከ መጨረሻው እንዋጋለን፤ የጎሬላ ጦርነት እንጀምራለን፤ ትግራይ መቀበሪያችን ትሆናለች፤ እንደዚህ እንደዚያ እናደርጋለን እያሉ  የሚፎክሩት በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ነው ያሉት አቶ ስዩም ይህ ፉከራና ሽለላ ጦርነቱን የድርድሩ መጠቀሚያ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ድርድር ተብሎ ከአንዴም ሶስት ጊዜ ተኩስ አቁም ማድረጓን ያስታወሱት አቶ ስዩም፤ ይህም የተደረገው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደርና ሀገሪቱንም ሆነ ህዝቡን ከጥፋት ለማዳን ሲባል ነበር፤ ሆኖም ከህውሃት በኩል ሶስቱንም ጊዜ ተተኩሶብናል፤ ይሁን እንጂ አሜሪካኖቹ አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ተኩስ አቁም ነው እየጠየቁ ያሉት፤ እኛ ብናቆምም ለአራተኛ ጊዜ ወያኔ ይተኩስብናል ሲሉ፤ ከህውሃት ባህሪና ተሞክሮ ተነስተው ስጋታቸውን ገልፀዋል። “ድርድር ሲባልና ተኩስ አቁም ሲደረግ፤ ለወያኔ የጦር ዝግጅትና ፋታ ማግኛ ጊዜና እድል መስጠት ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡
ታዲያ ጦርነቱ በዘላቂነት እንዲፈታና ሰላም እንዲመጣ ምን መደረግ አለበት ብለን ለጠየቅናቸው ሲመልሱም፤ “አንድም በድርድር ካልሆነም በጦርነት ህውሃትን ትጥቅ ማስፈታት ብቻ ነው ሰላም የሚያመጣው” ሲሉ ዘላቂ ያሉትን መፍትሄ ጠቁመው፤ የድርድሩ አስኳል ጉዳይ ህውሃትን ትጥቅ ማስፈታት ላይ ማተኮር አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡ “ህውሃት በጦርነትም ሆነ በድርድር ትጥቅ እስካልፈታ ድረስ አሸባሪነቱን አያቆምም ያለጦርነትና ሽብር ደግሞ ህልውናው አይቀጥልም” ብለዋል፡፡
ሁለቱ ወገኖች በድርድሩና በንግግሩ ባይስማሙና ሂደቱ ቢከሽፍ እነ አሜሪካ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? በሚልም ጠይቀናቸው እንደሚከተለው መልሰዋል፡፡
“እነ አሜሪካ፤ ማስፈራራታቸውንም ይቀጥላሉ፤ አንድ የሚገርመኝ ነገር ግን የኢንተርናሽናል ክራይለስ ግሩፕ ባቀረበው ሪፖርት ላይ የባይደን አስተዳደር ከዚህ ቀደም ወስኖት የነበረው የሌጂቲሚቲ ቦርደር ማለትም በኢትዮጵያና በኤርትራ መሪዎች ላይ ጥሎት የነበረውን ማዕቀብ በድጋሚ አንስቶ ተግባራዊ ያድርገው ማለቱን ገልፀው፤ ለምን ነበር የሌጂቲሚቲ ቦርደር የተወሰነው? ለምንስ ነበር እስካሁን ተግባራዊ ያልተደረገው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አቶ ስዩም ይህንኑ ጥያቄም አሜሪካኖቹ ማዕቀብ ቢጥሉ ሊያጡት የሚችሉት ነገር እንዳለ ያውቃሉ ሲሉ ይመልሳሉ፡፡
“የኢትዮጵያን መንግስት እስከ ጥግ መግፋት በራሱ ኢትዮጵያን ወደ አሜሪካ ተቀናቃኝ  ሀያላን ሀገሮች ማለትም ወደ ሩሲያና ወደ እነቻይና መግፋት ነው ያሉት አቶ ስዩም፤ ይህ ማለት በጂኦፖለቲክሱም አንደኛ በአፍሪካ ደረጃ ሁለተኛ በቀይ ባህር ደረጃ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ፖለቲካው ደረጃ አሜሪካኖች የኢትዮጵያን ድጋፍ እያጡት ይሄዳሉ ማለት ነው- ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ድርድሩ ባይሳካ ለድርድር ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱት የህወሃት አመራሮች ወደ መቀሌ ተመልሰው ውጊያውን ይቀጥላሉ ብለው ያምናሉ በሚል ላነሳንላቸው ጥያቄም፤ “ሰሞኑን የሚወጡት መረጃዎች የኢትዮጵያ ጦር መቀሌን እየተጠጋ ነው የሚል ነው” ያሉት አቶ ስዩም፤ አሉላ አባነጋ አየር ማረፊያ ከመቀሌ ራቅ ብላ በምትገኘው ኩይሃ እንደመገኘቱና አካባቢው በጦርነት ላይ እንደመሆኑ የህወሓት አመራሮች መጥተው እዚህ አረፉ ማለት አንድም ራሳቸውን ለአደጋ ማጋለጥ ነው፤ አንድም እጅ መስጠት ነው የሚሆነው ሲሉ አመራሮቹ ተመልሰው ወደ ሀገር ይገባሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ከዛ ይልቅ ከሰሞኑ አንዳንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከካናዳ መሪዎች ጋር ያደረጓቸው የስልክ ንግግሮችና ሲናፈሱ ከነበሩ ወሬዎች አንጻር የህወሓቶች መጨረሻ ካናዳ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው አቶ ስዩም ተሾመ ተናግረዋል።
ሌላው በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው የህግ ባለሙያው አቶ ውብሸት ሙላት፣ ነገ እሁድ የሚጠናቀቀው የደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር (ድርድር) በውጤት ይጠናቀቅ እንደሆነ አንስተንላቸው፤ “በመጀመሪያ ይህንን ሂደት ድርድር ከምንለው ሽምግልና ብንለው ይሻላል፤ ምክንያቱም ሌላ ሶስተኛ አደራዳሪ አካል አለ” በማለት ጀምረዋል።
በዚህ የሽምግልና ሂደት ላይ የተሰጠው መግለጫ ግራ የሚያጋባ ነው ይላሉ፤ አቶ ውብሸት። ለዚህም ምክንያታቸውን ሲገልጹ፤ ሽምግልናውን እሁድ ያልቃቅ ብሎ መወሰን ምን ማለት ነው? ወይስ ቀድሞ የተጠናቀቀ ነገር ይኖር ይሆን? በማለት የጠየቁ ሲሆን ከዚህ ይልቅ እስከ እሁድ ይቆያል ቢባል ትንሽ ስሜት ይሰጥ ነበር ብለዋል። እሁድ ይጠናቀቃል ብሎ ቀን መቁረጥ ግን ሂደቱ ላይ ችግር ያለ መሆኑን ያመላክታል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ገልጸዋል።
የሆነ ሆኖ እስከ እሁድ በሚቀጥለው ድርድር ምን ምን መደራደሪያ አጀንዳዎች እንደቀረቡበት አናውቅም ያሉት የህግ ባለሙያው፤ መጀመሪያ የድርድሩን ፕሮሲጀር መወሰን፣ ቀጥሎ አጀንዳው ላይ መስማማት፣ ከዚያ ደግሞ አጀንዳዎቹ ላይ መነጋገር ነው ቅደም ተከተሉ መሆን ያለበት ሲሉ አስረድተዋል። በእኔ እምነት ድርድሩ እስከ እሁድ ይጠናቀቃል ብዬ አላስብም ሲሉም ተናግረዋል።
በሁለቱም ወገኖች መካከል የተራራቀ ፍላጎት ነው ያለው የሚሉት አቶ ውብሸት፤ በኢትዮጵያ በኩል ቅድሚያ ትህነግን ትጥቅ ማስፈታትና ከዚያ በኋላ ባሉት ነገሮች ላይ የመነጋገር አቋም የሚኖር ይመስለኛል ብለዋል። ጦርነት ባስነሳው ትህነግ በኩል ደግሞ ለምሳሌ የሰብአዊ እርዳታዎች ያለገደብ  ይግቡ፣ የመንግስት ጦር የትግራይ ክልልን ለቆ ይውጣ የሚሉ ጉዳዮችን አንስቷል ያሉት የህግ ባለሙያው፣ እነዚህ የተራራቁ ፍላጎቶች ታርቀው በዚህ በአጭር ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብዬ  አላምንም ብለዋል።
“ይህ ካልሆነ ጦርነቱ ይቀጥላል ማለት ነው” ያሉት የህግ ባሙያው፤ የሰላም አማራጭ ካልተሳካ በወታደራዊ አማራጭ ሰላም እንዲመጣ ይደረጋል ብለዋል።
ድርድሩ በስምምነት ካልተቋጨ እነ አሜሪካ ማዕቀቦችን  በኢትዮጵያ ላይ ይጥሉ እንደሆነ የተጠየቁት አቶ ውብሸት እነአሜሪካ ከበፊትም ጀምሮ የነበራቸው አቋም ይታወቃል ጦርነቱ የተለያዩ ደረጃዎች ስለነበሩት፣ ጦርነቱ  በተደረገ ቁጥር የሚዲያዎቻቸው ፍሬም አደራረግ አንዳንድ የምዕራብ ድርጅቶች አጀንዳ አቀራረጽና እነ አሜሪካና  አውሮፓ ህብረት የሚይዟቸው አቋሞች የታወቁ ናቸው ካሉ በኋላ፣ በተለይ ህወሓቶች በገፉና ደብረሲና በደረሱ ጊዜ አሜሪካኖች ያደረጉትን አስታውሰዋል። ስለሆነም እነ አሜሪካ በማስፈራራትም ሆነ በተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶች ጫና ለመፍጠር መሞከራቸው አይቀርም፤ ሲናገሩ የነበሩትም ይህንኑ ነው የሚሉት አቶ ውብሸት፤ አንዳንድ ድርጅቶቻቸውም አቋማቸውን ይዘው ወጥተው አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል ብለዋል።
ይህን ይህን ስናይ ወደ ማዕቀብና ወደ ሌሎች እርምጃዎች ሊሄዱ እንደሚችሉ የተናገሩት የህግ ባለሙያው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ይህ እንዳይሆን ማድረግ ይችላል ባይ ናቸው።
እንዴት ለሚለው ጥያቄ ሲመልሱም፤ “መንግስት ነፃ ለወጡ አካባቢ ህብረተሰቦች እርዳታ በመስጠት፣ የህክምና አገልግሎት፣ የመብራት አቅርቦት፣ የባንክ አገልግሎትና የመሳሰሉትን በመጀመር የሰብአዊ ችግሮች ጉዳይ ብዙ አጀንዳ እንዳይሆን ማድረግ ይችላል ሲሉ መንግስት  ሊከውናቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል በርከት ያሉ ቦታዎችን በመያዝ አማጺው የትህነግ ቡድን ብዙ ስጋት እንደማይሆን ማሳየትም ሌላው ጫናውንና ማዕቀቡን መከላከያ መንገድ ነው ያሉት አቶ ውብሸት፤ ትህነግ እንደገና አንሰራርቶ ለእነሱ ጥቅም ማስፈጸሚያ ቡድን መሆን እንደማይችል ተስፋ ማስቆረጥና በበርካታ ጉዳዮች አሜሪካኖችን ምክንያት አልባ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
 የሰላም ንግግሩ ባይሳካ ለድርድር ወደ ደቡብ አፍሪካ የሄዱት የህወሓት አመራሮች ወደ መቀሌ ተመልሰው ውጊያ ይቀጥላሉ ብለው ያምናሉ ወይ ስንል የጠየቅናቸው የህግ ባለሙያው፣ “ይህንን የሚያውቁት ራሳቸው ናቸው፤ ነገር ግን ከዚህ በላይ የነሱን መመለስና አለመመለስ የሚወስነው መቀሌ ያለው ሁኔታ ነው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊቱ በሁሉም አቅጣጫ መቀሌን እየከበበና እየተጠጋ ነው የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ወደ መቀሌ ላይመጡ ይችላሉ ያሉት አቶ ውብሸት፤ ምንም እንኳን ከአውሮፕላን ሲወርዱ ችግር ሊደርስባቸው ባይችልም በራሳቸው ፍርሃት ውስጥ መግባታቸው ስለማይቀር ጉዳዩን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ይወስነዋል ብለዋል።

Read 12358 times