Monday, 31 October 2022 00:00

የነገውን መከላከያ ኃይላችንን ለማየት ያብቃን!

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ የመከላከያ ቀን ባለፈው ጥቅምት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ተከብሮ ውሏል። እለቱ የመከላከያ ቀን የሆነው ግርማዊ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ አውሮፓ ስርዓት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ያቋቋሙበትና የመጀመሪያውን መከላከያ ሚኒስትር የሾሙበትን ቀን በማስታወስ ነው።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴና ከዚያም ወዲህ በነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት አልፎ አልፎ እንዲህ አይነት የመከላከያ ሰራዊትን አገራዊ አገልግሎት ለማሰብና ለማክበር የሚውሉ ቀናት የነበሩ ቢሆንም፣ እነሱ እግር የተከሉ አልነበሩም። የዘንድሮው ግን እግር ይተክላል፣ መሰረት ያኖራል ተብሎ ይጠበቃል። የመከላከያ ሰዎች በመገናኛ ብዙሃን ሲናገሩ እንደሰማሁት፤ አጀንዳውን ወደ ሚኒስትሮችና ተወካዮች ምክር ቤት በመውሰድ በህግ የታወቀ ብሔራዊ በአል እንዲሆን ለማድረግ እንደሚጥሩ ነው። ፈጣሪ ይርዳቸው ብያለሁ።
ለእኔ የመከላከያ ቀን ተከብሮ መዋል ለአመታት ይሁነኝ ብዬ በህሊናዬ ያላመላለስኳቸውን፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ከሻቢያ ጋር ሲዋጉ የወደቁትን ትልቅ ወንድሜን ምክትል መቶ አለቃ ዳኛቸው አስረስንና የትልቅ እህቴን ልጅ ወታደር ንጉሤ ቦጋለን ለማስታወስና ለማክበር አገልግሎኛል። እንዲህ ያለ ታሪክ በየቤቱና በየመንደሩ ስላለ፣ የበዓሉ ቋሚ መሆን ስለ አገርና ስለ ቤተሰብ ታሪክ ለማውሳትና ለመተረክ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አምናለሁ። ሃሳቡን ላቀነቀኑትና እዚህ ላደረሱት ወገኖች ያለኝን ከፍ ያለ አክብሮት የምሰጠው ከልብ ነው።
ዕለቱን ለማክበር በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ለመታደም እድል አግኝቻለሁ። “የጥንካሬያችን ምንጭ ህዝባችን ነው” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ ፕሮግራም፣ ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ተካተዋል። የፎቶ ትርኢትና “የእሳት ቀለበት” በሚል ርዕስ በመከላከያ ጥናትና ምርምር ማዕከል ወታደራዊ ንድፈ ሃሳብ ጥናት ክፍል ክትትል የተዘጋጀው መጽሐፍ ምረቃ። በዋና አዘጋጅነት አቶ  ያለው አክሊሉና በምክትል አዘጋጅነት አቶ ገበየሁ ዋለልኝ አገልግለዋል። በጦር ሜዳ ውጊያ የዋሉ 44 መኮንኖችና 1,685 ሰዎች በሀሳብ ሰጭነት ተሳትፈዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሮቹ አቶ አበባው አያሌው እና አቶ መኩሪያ መካሻ ስለ መጽሐፉ ያላቸውን  እይታ ለታዳሚው አጋርተዋል፡፡ ከመገረሜ ብዛት እጄን  በአፌ እንድጭን ያደረገኝ፣ አንድ በምረቃው ስነ-ስርዓት  የተገኙ ሰው፣ ስም ጠቅሰው በሸክላ ተቀርፆ ለማዳመጥ የቻልኩት  በማለት፣ “በትግራይ ምድር የዘረኝነት መንፈስ ይዘው የሚነሱ ሰዎች ይኖራሉ። በጊዜው የሚገታቸው ካላገኘ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥፋት ምክንያት ይሆናሉ” ሲሉ የተናገሩት ሀሳብ ነው። ያቀረቡት ቃል በቃል ባይሆንም ይህ የተነገረውና ሰውየው የተናገሩት በሸክላ የተቀረጸው ትህነግ ከመመስረቱ ጥቂት ዓመታት፣ ምን አልባትም ከአምስት እስከ አስር ዓመት ቀደም ብሎ ሊሆን እንደሚችል ገምቻለሁ።
የፎቶ ትርኢቱ በመከላከያ ሚኒስትርነትና በጦር ኃይሎች ኤታማዦርነት ያገለገሉትን ሰዎች የያዘ ነው።  
ለአይነት የመጀመሪያውን  የጦር ሚኒስትር ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ድል ነግዴ፣ በ1928 ዓ.ም የጣሊያንን ወረራ ለመመከት የኢትዮጵያን ጦር የመሩ ከአዲስ አበባ ጀምረው የተጓዙትን ራስ ሙሉጌታ ይገዙን፣ በጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ በተመራው እና በከሸፈው መፈንቅለ መንግሥት የተገደሉትን ሜጀር ጀኔራል ሙሉጌታ ቡሌን፣ ይህን ኩዴታ ካከሸፉት አንዱ የሆኑት  ሜጄር ጀነራል መርዕድ መንገሻ፤ ከዘመነ-ደርግ አቶ አያሌው ማንደፍሮን፣ ከትሕነግ/ ኢህአዴግ ሜጄር ጀነራል ሳሞራ የኑስ፣  ከዘመነ ብልፅግና ጄነራል ሰዓረ መኮንን፣ አቶ ሞቱማ መቃሳንና ብቸኛዋንና የመጀመሪያዋን ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድን መጥቀስ ይቻላል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ፣ አገሪቱ ባለችበት በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ፣ ኢትዮጵያን የሚመጥን፣ ጦርነት ሲመጣ የሚመክት ብቻ ሳይሆን ጦርነት እንዳይቀሰቀስና ባለበት እንዲቀር ማድረግ የሚችል ሰራዊት እየተገነባ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የክብር እንግዳው የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው፤ ያገርን ዳር ድንበር፣ ነፃነትና ሉአላዊነትን ለማስከበር ለሚከፈለው መስዋዕትነት ጎን ለጎን “ከውጊያ በኋላ ምን ማድረግ አለብን?” ብሎ እራሱን መጠየቅና ማዘጋጀት እንዳለበት አጠንክረው አሳስበዋል። መከላከያው በእጁ ያሉትን መሳሪዎች በመፈተሽ፣ የጎደላቸውን በማሟላት እራሱን  ማሳደግ እንዳለበት የጠቆሙት ዶ/ር ሙላቱ፤ ወደ ሲቪሉ የመጡት ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጀመሪያ የተገኙት ከመከላከያ ተቋማት መሆኑን አስረድተዋል። አያይዘውም ምናልባት ለወደፊት በሚከበረው የመከላከያ ቀን “የመከላከያ ግኝት” ተብሎ አንድ የምርምርና የፈጠራ ውጤት የምንተዋወቅበት ቀን ሊመጣ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል። “የተፈጥሮ ጀግንነታችን ብቻውን በቂ አይደለም። በዘመኑ ቴክኖሎጂ መታገዝ አለበት” ሊጠቀስ የሚገባው የዶ/ር ሙላቱ  ቃል ነው።
መከላከያው ከዘመኑ የውትድርና ሥራ ጋር በእኩል ፍጥነት ይራመድ ዘንድ በተጨማሪ አጥብቆ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይም አለው። ይኸውም የቋንቋ እውቀት ነው፡፡
በግርማዊ ንጉሠ ነገስት ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ዘመን ለአየር ኃይል ብቻ ተብሎ የታተመ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍ ማንበቤን አስታውሳለሁ። መከላከያ የበሰለ ሰው ማፍራት ይቻለው ዘንድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን በአረብኛ፣ በስዋሂልኛና በፈረንሳይኛም ጭምር እንደዚሁ በርትቶ ሊሰራ ይገባዋል። በተለይ አረብኛ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሊታሰብበትና ሊሰራበት የሚገባ ነው። እንዲህ እንዲህ ሲሆን ነው በእርግጥም የዛሬዋንና የነገዋን ኢትዮጵያን የሚመጥን የመከላከያ ኃይል የሚኖረን። ዘመኑ የመረጃ ነው። መረጃ ደግሞ የሚገኘው በቋንቋ ነው። ቋንቋ እንደ አንድ የመከላከያ የጦር መሳሪያ ታይቶ ዋጋ ሊሰጠው እንደሚገባ የማሳስበው በአክብሮት ነው።
የነገውን መከላከያ ኃይላችንን ለማየት ለሁላችንም እድሜ ይስጠን!

Read 8874 times