Monday, 07 November 2022 00:00

ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ---

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

     “--በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም መንግስት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ እርምጃውን ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በራቀና ትክክለኛ ጉዳትን ባገናዘበ መንገድ ያደርገው ዘንድ ማሳሰብ እሻለሁ፡፡ ይበልጥ የማሳስበው ግን ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማሻገር መንግስት ትንፋሽ አጥቶ ይሰራ ዘንድ ነው።”
      
        ላለፉት ሃምሳ ዘጠኝ ቀናት ያለ ማቋረጥ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ ውጊያ ላይ ተጥዶ የቆየው የኢትዮጵያ መከላከያና ጥምር ሃይሉ በከፈሉት እጅግ ውድና ድንቅ መስዋዕትነት፣ የእነ ደብረ ጽዮን ቡድን (ትሕነግ) ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጣ ተደርጓል፡፡ በድርድር ጠረጴዛውም ላይ ትጥቁን ለኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል በአንድ ወር ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለማስረከብ ተስማምቶ ፈርሟል። ይህን ድል ለእናት አገር ላስገኙ በልዩ ልዩ መንገድ በጦርነቱ አስተዋጽኦዋቸውን ላበረከቱ ሁሉ ልባዊ አክብሮቴን ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ እገልጣለሁ።
በትሕነግ የክፋት እጅ ላይ ወድቀው ለሃያ ሰባት አመታት የምድር ፍዳ ሲያዩ ለኖሩት ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራና ለራያና ኮረም አላማጣ ህዝብ የሚሰማኝን መሪር ሀዘን በዚህ ጊዜ ሳልገልጥ ማለፍም የሚሆንልኝ አይደለም። ፈጣሪ የተገደሉትን ነፍሳቸውን ይማረው እላለሁ።
በማይካድራና ለጎኮማ ይሁነኝ ተብሎ በዘር ተለይተው የተገደሉ (የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መቃብር ቆፍሮ ያወጣቸው ከሃምሳ ሰባት ሺህ በላይ በትሕነግ በግፍ የተገደሉ) ወገኖች ሁሉም፣ ደበኛና ሴረኛ የሆነው ትህነግ፣ ማንነቱና ምንነቱ ይበልጥ እንዲታወቅ ያደረጉ መስዋዕቶች ናቸውና እነሱንም ማሰብ በዚህ ሰዓት ተገቢ መስሎ ይታየኛል። የሁሉም መስዋዕትነት ድምር ለዛሬ ትህነግ መውደቅ አድርሶናልና። የኢትዮጵያ መንግስት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ የነበረውን ድርድር በተመለከተ የእለት ተእለት ሂደቱን አይደለም፣ ከሦስት ቀን አንድ ቀን እንኳ ይህ እየሆነ ነው ብሎ የተናገረበት ጊዜ አልነበረም። ከሁለት ቀን በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ከፍተኛ ጫና እየተደረገብን ነው” ሲሉ የጠቆሟት ሃሳብ ብቻ እንደ ጉድ የታየችም ነበረች። መንግስት አይንገረን እንጂ ማን አለብን ያሉ አገሮች በተለይም አሜሪካ ድርድሩ ማሟላት አለበት የምትለውን አራት ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጣም ነበር። በድርድሩ መጨረሻ ላይ የታየው ውጤት ግን ከአሜሪካ ዕቅድና ሃሳብ ውጭ ሆኖ ተገኘ እንጂ፡፡ በእውነቱ መንግስት ከያዘው አቋም ውልፊት ባለማለት፣ ትህነግ በህግ እንዲገዛና ትጥቁንም እንዲፈታ ከስምምነት  ላይ መደረሱ በአክብሮት የሚታይ ነው። ላሳየው ጽናትም ምስጋና ይገባዋል፡፡ በተለይ የትጥቅ ማስፈታቱ እርምጃ በራሱ በመንግስት የሚፈጸም መሆኑ ለውጭ ጣልቃ ገብነት መንገድ የዘጋ ነውና ድርብ ድል ነው፡፡  
ትጥቅ ማስፈታቱ ከምድር በላይ የሚታየውን ከባድና መካከለኛ መሳሪያ ወይም በእያንዳንዱ የትህነግ ሰራዊት እጅ የሚገኝን የግልና የቡድን መሳሪያ በመሰብሰብ ብቻ መወሰን የለበትም። በየቦታው የተቀበሩ መሳሪያዎች መውጣት ይኖርባቸዋል። ይህን ትህነግ ፈቅዶ ቢያደርገው መልካም ይሆናል። ካልሆነም የፌደራል መንግስቱ በዚህ ጉዳይ ቸል ሊል አይገባም።
በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋምና በማንኛውም የትግራይ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ሕግ የማስከበር ሥራ ማከናወን ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠው ተግባርና ትሕነግም ማስረከብ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ በስምምነቱ ተጠቅሷል።
ይህ ሁሉንም የስምምነቱን ሃሳቦች ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስፈልግ ጉዳይ ነው። የትግራይ ሕዝብ ለዘመናት ያጣውን እድል መልሶ ያገኘው መሆኑን የሚለካበትና የሚመዝንበትም አጋጣሚ ነው። በዚህ በኩል ከመንግስት የሚታይ ጥንካሬ ጦርነቱን በጦር ሜዳ ከማሸነፍ፣ በድርድር ጠረጴዛ ከመርታት በላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊደከምበት የሚገባ ስራ ነው።
ትሕነግ አንድ አማጺ ቡድን ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ አማጺ  ቡድን ሊሆን አይችልም። መንግስት ነው። መንግስት በመሆኑ የአማጺው ቡድን የሚሰራቸውን ወንጀሎች ሊሰራቸው አይችልም። የሕግም የሞራልም ተጠያቂነት አለበት። ስለዚህም በስምምነቱ የተካተቱ ውሳኔዎች በፍጥነት ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ አለበት። በውድም በግድም።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስለ ስምምነቱ ለጋሞ ጎፋ ህዝብ ባደረጉት ንግግር፤ “ትግራይን ለመገንባት አብረን እንቁም” የሚል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በጦርነት የተጎዳችው ትግራይ ብቻ  አይደለችም። አማራና አፋር ክልልም ተጎድተዋል። እንኳን እነሱ ጦርነቱ ከተካሄደባቸው አካባቢዎች ከጦር ሜዳ በብዙ ርቀት የምንገኝም ሰዎች በልዩ ልዩ መንገድ ጦርነቱ ጉዳት አድርሶብናል። ከጣት ጣት ይበልጣል ሆኖ እንጂ።
ስለዚህም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ለማቋቋም መንግስት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ እርምጃውን ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በራቀና ትክክለኛ ጉዳትን ባገናዘበ መንገድ ያደርገው ዘንድ ማሳሰብ እሻለሁ፡፡ ይበልጥ የማሳስበው ግን ስምምነቱን ወደ ተግባር ለማሻገር መንግስት ትንፋሽ አጥቶ ይሰራ ዘንድ ነው።

Read 8933 times