Saturday, 05 November 2022 11:55

ኮንጎ ሬድ ቴስት...የፕሪክላምፕሲያ መመርመሪያ…

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 በእርግዝና ወቅት ስለሚፈጠር የደም ግፊት ወይም ፕሪክላምሲያ እና ኢክላምሲያ[Pre-Eclampsia and Eclampsia] ምንነት፣ ምልክት እና እራስን ከከፋ አደጋ ለመከላከል መደረግ ስለሚገባቸው ጉዳዮች በቀደመው እትም ላይ አቅርበናል። በዚህ እትም ላይ ይህን በሽታ ለመመርመር በሙከራ ላይ ስለሚገኘው ኮንጎ ሬድ ቴስት ስለተባለ የህክምና መሳሪያ እናስነብባቹሀለን።     
የጽንስ እና የማህጸን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ገሊላ ኪዳኔ ጎባ “በከፍተኛ ደረጃ በአለም ላይ ጥናት ከሚደረግባቸው በሽታዎች ውስጥ አንዱ ፕሪክለላምሲያ ነው” በማለት ስለበሽታው አሳሳቢነት ተናግረዋል። በምክንያትነት ያስቀመጡት በሽታውን በገንዘብ የተሻለ አቅም ያላቸው ሰዎች እንኳን ሊከላከሉት ያልቻሉት መሆኑን ነው። እንዲሁም በሽታው በምን ምክንያት እንደሚከሰት አለመታወቁ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። ስለዚህ በሽታውን ቅድሞ መከላከል ካልተቻለ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ቅድመ ምርመራ በማድረግ ህክምና ለመስጠት ዝግጅት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል የህክምና ባለሙያዋ።
በሽታው በአለም አቀፍ ደረጃ ሆነ በሀገራችን ለእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ይገኛል። ይህ በሽታ በእናቶች ላይ የከፋ ጉዳት እንዲያስከትል ምክንያት ከሆኑት ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የምርምራው ሂደት እና ውጤታማነት ላይ ችግር መኖሩ ነው። ዶ/ር ገሊላ እንድሚናገሩት አንዲት ነፍሰጡር እናት ላይ በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የደም ግፊት መኖሩን በምርመራ ለማረጋገጥ የሚያስፈልጉ ወይም መሟላት ያለባቸው ሶስት ነገሮች አሉ።
ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት የእራስ ምታት፣ የማቅለሽለሽ፣ ብዥ የማለት እና የመድከም ስሜት ሊኖራት ይችላል። ይህ ደግሞ በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የተለመዱ ስሜቶች ስለሆኑ አንዲት እናት ይህን ስሜት ለህክምና ባለሙያው ላትገልጽ የምትችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችል ዶ/ር ገሊላ ተናግረዋል።
የደም ግፊት መጠን ማንኛውም ጤነኛ ሰው ከሚኖረው 90 በ140 ከፍ ማለቱን ማረጋገጥ ይገባል። የደም ግፊቱ መጠን ቢያንስ በ6 ሰአት ልዩነት ሁለት ጊዜ መታየት ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለ6 ሰአት ያህል አንዲትን ነፍሰጡር እንድትጠብቅ ማድረግ ከባድ ይሆናል ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ።
በላብራቶሪ በሚደረግ የሽንት ምርመራ አልቡሚን በተባለ ፕሮቲን እንዲሁም በተለያየ የደም ምርመራ መሰረት የዚህ በሽታ ተጠቂ የሆነች ነፍሰጡር ትለያለች። ነገር ግን ይህ ምርመራ ማግኘት በማይቻልበት አከባቢ የሚኖሩ ነፍሰጡሮች አገልግሎቱን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ባለሙያዋ ጠቁመዋል።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ “ይህ የፕሮቲን ምርመራ የራሱ የተወሰኑ ችግሮች አሉት” ብለዋል። ችግር ብለው ያስቀመጡት አንዳንድ ጊዜ በላብራቶሪ ምርመራ በሽታው እያለ ውጤቱ ግን በተቃራኒው የበሽታውን አለመኖር የሚያሳይበት አጋጣሚ መኖሩን ነው።
ዶ/ር ገሊላ ጎባ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ኤሌኖን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ለ20 አመታት ያህል ለዚህ በሽታ መመሪመሪያ የሚሆን የህክምና መሳሪያ ሲሰሩ ቆይተዋል። እናም በአሁኑ ወቅት ኮንጎ ሬድ ቴስት የተባለ የህክምና መሳሪያ ለሙከራ አቅርበዋል። ይህ የህክምና መሳሪያ የኢክላምሲያ በሽታ ምልክት የሆነውን በሽንት የሚገኘውን ፕሮቲን ለይቶ የሚያሳይ ነው። ከዚህ ቀደም ከነበሩት የመመርመሪያ መሳሪያዎች በተሻለ መልኩ በቀላሉ በሽታውን ለመለየት ይረዳል። የፕሪክላሚሲያ በሽታ አንዳንድ ጊዜ ምልክት ሳያሳይ ቆይቶ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ብዙዎችን ለሞት የሚዳርገውም ቶሎ ህክምና ስለማያገኝ ነው። ስለሆነም በሽታው ጉዳት በሚያደርሰው የኢክላምሲያ ደረጃ ላይ ሳይደርስ ፕሪኢክላምሲያ ተብሎ በሚጠራው ያልከፋ ሁኔታ ላይ ሳለ እንዲታወቅ ይህ መሳሪያ ይረዳል። በቤት ውስጥ የእርግዝና ምርመራ ከሚደረግበት የህክምና መሳሪያ ጋር ኮንጎ ሬድ ቴስት በመጠን እና በአጠቃቀም የመመሳሰል ነገር እንዳለው ዶ/ር ገሊላ ተናግረዋል። ስለሆነም መሳሪያው በህክምና ተቋማት ሙከራ ከተደረገበት በኋላ በግለሰብ ደረጃ በቤት ውስጥ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ የመፍጠር እቅድ መኖሩን ባለሙያዋ አክለዋል።
ኮንጎ ሬድ ቴስት የተባለው የኢክላምሲያ በሽታ መመርመሪያ መሳሪያ በተለያዩ ሀገራት በህክምና ተቋማት ውስጥ በሙከራ ላይ ይገኛል። ህንድ፣ ሜክሲኮ እና ባንግላዲሽ መሳሪያው ከተሰራበት ሀገረ አሜሪካ በተጨማሪ ሙከራ ተደርጎ ስኬታማ ከሆነባቸው ሀገራት ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኤሌኖን (university of Illinois)፣ ጤና ጥበቃ ሚንስቴር እንዲሁም የኢትዮጽያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ የህክምና መሳሪያው ሙከራ እንዲደረግበት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
“ይህ ለኢትዮጵያ ትልቅ እድል ነው። ምክንያቱም ብዙ ጊዜ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሲፈጠሩ የተፈጠረው ነገር ይበልጥ ከሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው በኢኮኖሚ በተሻለ ደረጃ ላይ ላሉ ሰዎች ወይም የማህበረሰብ ክፍሎች ነው” ብለዋል ዶ/ር ገሊላ ጎባ። ይህ መሳሪያ ግን በአሜሪካ ሲተዋወቅ ጎንለጎን ይበልጥ ተጎጂዎች በሚገኙባቸው እንደ ህንድ፣ ናይጄሪያ እና ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራትም እንዲተዋወቅ እየተሰራ ይገኛል እንደ ዶ/ር ገሊላ ንግግር።
የማስተዋወቅ ወይም መሳሪያውን ስራ ላይ ለማዋል ለሚደረገው ሙከራ ግብአት የሚሆን ጥናት ለማካሄድ በኢትዮጵያ በ3 አከባቢዎች ማለትም በአዲስ አበባ፣ ደብረ ብርሀን እና ጅማ ስራ ተጀምሯል። የጥናቱ ዋና አካላት የጤና ተቋም፣ የህክምና ባለሙያ እና እናቶች ናቸው። 45 የመንግስት እና የግል የህክማና ተቋማት ተካታች ይሆናሉ። በጥናቱ ላይ ከ3ሺ በላይ ነፍሰ ጡር እናቶች ታሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ከ5 ወር በላይ የሆኑ ነፍሰጡር እናቶች ማለትም የፕሪክላምሲያ ምልክት የሚያሳዩ እንዲሁም ምልክቱን የማያሳዩ ነፍሰጡር እናቶችም ጭምር በጥናቱ ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። ይህም አሁን ካለው የህክምና መሳሪያ ጋር ለማነጻጸር ይረዳል እንደ ዶ/ር ገሊላ ገለጻ። እንዲሁም በሽታው ምልክት ሳያሳይ በእናትየው ላይ ሊኖር የሚችልበት እድል ስለሚኖር ለማረጋገጥ ነው። ጥናቱ ፍቃደኛ ሆነው በተገኙ ነፍሰ ጡር እናቶች ላይ ብቻ ነው የሚሰራው። በተጨማሪም የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋት ሁኔታ ላይ ያለች ነፍሰ ጡር ሴት የፕሪክላምፕሲያ ምልክት አሳይታ ቢጠረጠር እንኳን ቅድሚያ ህክምናውን ማግኘት ስለሚገባት ጥናቱ ላይ ተስታፊ አትሆንም። በአንዲት ነፍሰ ጡር እናት ላይ ይህ ጥናት ሲደረግ ከእርግዝናዋ መጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ ልጅ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ ያካትታል። ማለትም ጥናቱ የእናቲቱን ሄድት ይከታተላል። ስለሆነም በአጠቃላይ ጥናቱን ወይም መረጃውን አሰባስቦ ለመጨረስ የ6 ወራት ጊዜ ይፈጃል።     
ኮንጎ ሬድ ቴስት የህክምና መሳሪያ ላይ ለሚደረገው ጥናት መረጃ ለሚያሰባስቡ እና ለሚያስተባብሩ የህክምና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከተማ ከመስከረም 9 እስከ 11 ለ3 ቀናት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል። በስልጠናው ላይ ያገኘናቸው በደብረ ብርሀን አየር ጤና ጣቢያ የሚሰሩት ሚድዋይፍ ዋሴ ጉልላት ከገጠራማ አከባቢ ለሚመጡ እናቶች ይህ መሳሪያ ይበልጥ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል። ይህንንም ያሉት በሽታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ የማንቀጥቀጥ እና የመጣል ሁኔታ ሲኖረው ከባእድ አምልኮ ጋር የማያያዝ  እና ህክምና ለማግኘት ፍቃደኛ ያለመሆን ሁኔታ በመኖሩ ነው። ስለሆነም እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር በሽታውን አስቀድሞ በማግኘት እናቶች ለከፋ ጉዳት ሳይዳረጉ ህክምና እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ።
በጅማ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት የማህጸን እና ጽንስ ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ደምሰው አመኑ “በጥናቱ መሰረት የህክምና መሳሪያው ውጤታማ ከሆነ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ታካሚዎች በይበልጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ” በማለት መሳሪያው ለኢትዮጵያ የሚኖረውን ጥቅም ተናግረዋል። ይህንንም ያሉት የመጀመሪያ ደረጃ የህክምና ተቋማት የህክምና መሳሪያ እጥረት እንዳለባቸው በመጠቆም ነው።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ድልአየሁ በቀለ በበኩላቸው ይህ ጥናት ውጤታማ ሆኖ በሽታው የከፋ ደረጃ ላይ ሳይደርስ የሚገኝ ከሆነ በሽታው የሚያስከትለውን ችግር እንደሚቀርፍ ተናግረዋል። ስለሆነም ጥናቱ ከጠናቀቀ በኋላ ውጤታማነቱ ታይቶ በአለም አቀፍ ደረጃ በአለም የጤና ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ ጤና ሚንስቴር እውቅና ከተሰጠው በስራ ላይ የሚውል ይሆናል።  


Read 16326 times