Saturday, 12 November 2022 11:38

የናይሮቢው የሰላም ንግግር ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሰኞ በመንግስትና በሕወሓት ወታደራዊ አመራሮች መካከል በናይሮቢ የተጀመረው ንግግር ረቡዕ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ህትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ አልተጠናቀቅም። ውይይቱ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ የናይቢው ንግግር የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አዛዦች፣ የህወሓት ሃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን ሌሎች ታጣቂዎች የኤርትራና የአማራ ክልል ከትግራይ የሚወጡበት ጊዜ ግን አሳሳቢ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር፤ የህውሓት ሃይሎች በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ እንደሚፈቱ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል። በዚህ ንግግር ለውይይት ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል እንደ ኢንተርኔት፣ ቴሌኮም፣ መብራና ባንክ ያሉ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ  እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ማስጀመር ይገኙበታል።  በትግራይ  መሰረታዊ መድኃኒቶች ማለቃቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት፤ ወደ ክልሉ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ከአጋሮቻችን ጋር እየተጠባበቅን ነው ብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ተደራዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ክልሉ በስፋት መጓዝ መጀመራቸውንና 35 የምግብ ሸቀጦችንና 3 መድኃኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪኖች ሽሬ መግባታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደሩ በዚሁ የቲውተር መልዕክታቸው ላይ እንዳሰፈሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 70 በመቶውን የትግራይ ክልል መቆጣጠሩንና ለሰብአዊ እርዳታ የአውሮፕላን በረራዎች ዳግም መፈቀዳቸውን ገልጸዋል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ በበኩሉ፤ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ ነው ብሏል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የሰነበቱት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ሰሞኑን ለሪፖርተሮች በሰጡት ምግብና መድኃኒት ወደክልሉ እየገባ አይደለም ማለታቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ እንደተናገሩት፤ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ እንደሆነ አመልክተው በሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም፣ አዲሃጋላይ፣ አዲቃሮ፣ ሰለክላካና አዲነብሪ ከተሞች 108 ሺ ለሚሆኑ ወገኖች 16 ሺ 100 ኩንታል ስንዴና ከ65,000 ኩንታል በላይ አልሚ ምግቦች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል። በራያ አላማጣና ኮረም ከ43,200 በላይ ኩንታል ስንዴና ከ7,300 ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ 287 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ተዳርሷል ተብሏል።

Read 12541 times