Saturday, 12 November 2022 13:20

የማን ያለህ ነው የሚባለው?

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

     የመጋቢት 2010 ዓ.ም ለውጥ እንደባተ ሰሞን ነው፡፡ የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ ለዓመታት የዘለቁ የፖለቲካ ድርጅቶች መሳሪያቸውን አስቀምጠውና ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ተስማምተው ወደ አገር ቤት የሚመለሱበት ጊዜ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳና በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ወደ አስመራ በመጓዝ፣ መቀመጫውን አስመራ አድርጎ ከነበረው በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ተገናኙ። ከዚህ ግንኙነት በኋላ የኦነግ አመራርና ሰራዊት ወደ አገር ቤት ገቡ። የኦነግ ሰራዊት የገባው ግን ከሌሎች ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ከፈለጉትና በፈቃደኝነት መሳሪያቸውን ካወረዱት በተለየ ሁኔታ ከእነ ትጥቁ ነበር፡፡ ታጥቆ መግባቱ ብቻ አይደለም በጊዜው አነጋጋሪ የነበረው። በአንድ ማቆያ ስፍራ እንዲሰበሰብና ተሐድሶ እንዲወስድ፣ በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው ሁሉ ወደ  ኢትዮጵያ መደበኛ ሰራዊት የሚቀላቀልበት መንገድም አለመዘጋጀቱና ሲደረግ አለመታየቱም እንጂ። የኦነግን ሰራዊት ከእነ ትጥቁ መቀበል ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄ በሕዝብ ውስጥ በመመላለሱ አቶ ዳውድ ኢብሳን ማነጋገር አስፈላጊ አጀንዳ ሆኖ ተገኘ። አቶ ዳውድም መግለጫ ሰጡበት፤ “ማን ትጥቅ ፈቺ፣ ማንስ አስፈቺ ይሆናል!?” በማለት፡፡
ይህ ምላሻቸው ዛሬ ኦነግ ሸኔ እየተባለ ለሚጠራው ታጣቂ ቡድን “በያዝከው ግፋበት” የሚል አብሪ ምልክት ሆኖ ተገኘ። ምዕራብ ወለጋን መዳረሻው አድርጎ ብቅ ጥልቅ እያለ፣ ምን አልባትም ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከአስራ ስምንት በላይ ባንኮችን እንዲዘርፍና እራሱን በገንዘብ አቅም እንዲያደነድን እድል ሰጠው። ከባንክ በዘረፈው ገንዘብ የሰው ሃይሉን ለማብዛት፣ በየአካባቢው ህዋሱን ለመዘርጋት እንደተጠቀመበት መረዳት አያዳግትም።
በባንክ ዘረፋ ጉልበቱን ማሳየት የጀመረው ኦነግ ሸኔ፤በምስራቅ ኦሮሚያ እንደ አንገርጉቱ ባሉ አካባቢዎች በሰፈሩ አማሮች ላይ ክንዱን አነሳ። እዚያ አካባቢ ከትግራይም ከሌሎችም የኢትዮጵያ አካባቢዎች መጥተው የሰፈሩ ብዙ ሰዎች ቢኖሩም በዘሩ እየተመረጠ የሚገደለው አማራ ሆነ። ዛሬም በአማራ ላይ የሚደረገው ግድያ ከምስራቅ ኦሮሚያ ወደ ምዕራብ፣ ወደ ኢሉባቡር ዞን፣ ወደ ምእራብ ሸዋ ወዘተ ተዛምቶ ይገኛል።
ከሁለት ዓመት በፊት በአባ ገዳዎች የተሸመገለው ኦነግ፤ዛሬ ሽማግሌ የሚሰማበት ጆሮ ያለው አይመስልም። ሰዎችን አግቶ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ  ይቀበላል። በፈለገ ጊዜ ተነስቶ በአንድ አካባቢ የሚገኙ ሰዎችን ተሰብሰቡ ብሎ አዳራሽ አስገብቶ ይረሽናል። አንድ ከተማ ውስጥ ገብቶ መንደር ለመንደር እያሯሯጠ ሰዎችን ይገድላል። ይህን ሥራውንም በማህበራዊ ሚዲያ ያሰራጫል፡፡ ጉዳቱ ለጊዜው ያልደረሰበት ክፍል ነገ የእኔ እጣ ነው ብሎ ሲሸበርና ሲበረግግ ያድራል።
የመንግስት የመገናኛ ብዙኃን የተናገሩት ነገር ባይኖርም ሰሞኑን ነቀምቴ ከተማ በኦነግ ሸኔ እጅ ውስጥ መውደቋ በማህበራዊ ሚዲያ ተዘግቧል። በዚህ ወረራው በከተማው የሚገኙ ባንኮችና መንግስታዊ ተቋሞች መዘረፋቸው ተገልጿል። ከአንድ የመሳሪያ ማከማቻ ግምጃ ቤትም መጠኑ ያልታወቀ መሳሪያ መዝረፉ ተነግሯል። የአንድ ዞን ዋና ከተማ እንዴት እንዲህ ለመደፈር በቃ ብሎ መጠየቅ ይገባል፤ ያስፈልጋልም።
ጀኔራል ከማል ገልቹ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር እየሰሩ በነበሩበት ጊዜ “ኦነግ ሸኔን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማጥፋት ይቻላል። ችግሩ ያለው የክልሉ መንግስት ውስጥ ነው።” የሚል መንፈስ ያለውን ሃሳብ መግለጻቸውን አስታውሳለሁ።
የተከበሩ ብርጋዴር ጄነራል ኃይሉ ጉንፉ (የምክር ቤት አባል ናቸው) ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የደህንነት አማካሪ ሆነው መሾማቸው ሰሞኑን ተዘግቧል። አዲሱ የሥራ ሃላፊነታቸው ከየት እስከ የት ሊያስኬዳቸውና ሊያደክማቸው እንደሚችል የጠረጠሩት ብርጋዴር ጄኔራል ኃይሉ፤ “ጫካ ካለው ኦነግ ሸኔ ይልቅ ለመንግስት የሚያሰጋው በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ የተሰገሰገው ሸኔ ነው” ማለታቸው የሰሞኑን የፖለቲካ አየር ሸፍኖት ሰንብቷል።
እነ እንቶኔ ተብለው በስም ሊጠቀሱ በማይችሉ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ውስጥ ባሉ አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት የሚደገፈው ኦነግ ሸኔ፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አካባቢዎችም የስጋት ምክንያት እየሆነ እንደሚገኝ እየተነገረ ነው።
በክልሉ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ ያሉትን ሸኔዎች ማነው ለማጽዳት የሚነሳው?
“በቆረጡት ዱላ ቢመቱ፤ በጠሩት ምስክር ቢረቱ ምን ይባላል” ይላሉ አበው። አሁን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ላይ አደጋው ጎልቶ እየመጣ ነው። እየመጣ ያለውን አደጋ ለማስወገድ የማን ያለህ ነው የሚባለው። ፈጣን መፍትሄ ይሻል፡፡

Read 6734 times