Tuesday, 15 November 2022 00:00

ከአመፅና ከትርምስ የሚያድን መፍትሔ ከየት ይምጣ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

ነባሩን አኗኗርና ያደጉበትን ባሕል ሸሽተው፣ ከነባሩ ሕግና ሥርዓት አምልጠው ከግብፅ ወጥተዋል - ሙሴና ተከታዮቹ። “ለውጥ” እያልን እንደዘበትና በዘፈቀደ ብዙ ጊዜ እናወራ የለ! ካወራን አይቀር፣ ክፉና ደጉን ለማገናዘብ፣ የሙሴ ትረካ ሳይጠቅመን አይቀርም።
በእርግጥ፣ “ለውጥ” ማለት፣ የጠላነውን መቃወምና ማስወገድ ማለት ብቻ ይመስለናል-አብዛኞቻችን። ያስቀየመንን ነባር ሥርዓት የማጥላላትና የማፍረስ ዘመቻ ብቻ ነው የሚታየን። ጠማማ መስሎ የታየንን ዛፍ ስለቆረጥን፣ የተቃና ዛፍ በራሱ ጊዜ የሚከሰት ይመስለናል። ለዚያውምኮ፣ የተቃና ነገር ከተመኘን ነው። የባሰ መከራ በመናፈቅ ነባሩን ለማፍረስ የሚቸኩሉ አብዮተኞችን አይተናልና።
ታዲያ፣ በየዋህነትና በአላዋቂነት፣ በስህተትና በክፉት ሳቢያ ከሚከሰቱ “የለውጥ ችግሮች” ለመዳን፣ ከሙሴ ትረካ ጠቃሚ ትምህርቶችን ብናገኝ ይከፋናል? ደግሞም፣ “ለምዕተ ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ፣ እጅግ ትልቅ ታሪካዊ የለውጥ ትረካ ነው” ማለት ይቻላል።
ነባሩን ጠማማ ዛፍ የመገንደስ ለውጥ፣… አዲስ የተቃና ዛፍ ከማልማት ጋር ካልተጣመረ፣… ትርፉ ምድረበዳ አይሆንም? እንደሚሆን ያስተምራል-ትረካው።
ነባሩን ጠልቶ የማምለጥ ለውጥ፣… ወደተሻለ አዲስ ሕይወት ከመድረስ ጋር ካላዋደዱትና ካላዋሃዱት፣… በየበረሃው እየተንከራተቱ እድሜን ከመጨረስ ያለፈ ትርፍ የለውም። ትክክለኛ አላማ ይዘው የነፃነት ጉዞ የጀመሩና መድረሻቸውን ያወቁ የሙሴ ተከታዮች እንኳ አበሳቸውን አይተዋል። በፈርዖን አገዛዝ የተሰቃዩ መከረኞች፣ በምሬት ቢያመልጡም እንኳ፣ በረሃብና በውሃ ጥም ተሰቃይተዋል። ለበርካታ አመታት ተንከራትተዋል።
በሌላ አነጋገር፣… መልካም የለውጥ ጉዞ፣… ገና ከመነሻው በአካል፣ በአእምሮና በመንፈስ ካልተዘጋጁበት፣… ከቀድሞ ወደከፋ መከራ ሊያስገባ እንደሚችል ከትረካው አይተናል።
ከዚያስ? ፈርዖን ላይ ሲያማርሩ የነበሩ መከረኛ ስደተኞች፣ አሁን ሙሴ ላይ ያጉረመርማሉ። በሞቀ ቤታችን ውስጥ ብንሞት ይሻል ነበር ብለው ይነቅፉታል። በረሃብ ልትፈጀን ነው ከግብፅ ያስወጣኸን ብለው ይወነጅሉታል። ለአድማ ይቧደኑበታል። በውሃ ጥም ከነልጆቻችን ልትፈጀን ነው ብለው ሊያምፁበት እንደተነሳሱ ለመግለፅም፣ “ሊገድሉኝ ተቃርበዋል” በማለት ሙሴ ስጋቱን እስከመናገር ደርሷል። ከአመጽና ከትርምስ የሚያድን ሁነኛ መፍትሄ አላገኘም።  ለጊዜው፣ በዚህም ብሎ በዚያ፣ በአንዳች ተዓምረኛ መፍትሄ ከአጣዳፊው አደጋ ያድናቸዋል። ግን እስከ መቼ?
በማማረርና በቅሬታ ብቻ መፍትሔ የሚጠብቁ ሆነዋል - አብዛኞቹ የሙሴ ተከታዮች። “ምን ይሻላል?” ብለው ለማሰብና መፍትሔ ለመፍጠር አይሞክሩም። ያለ በቂ ስንቅ ለጉዞ የተነሱት ስደተኞች፣ የሃሳብና የመንፈስ ስንቅም አልነበራቸውም።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ሙሴና አሮን፣ ገና ከመነሻው በሃሳብና በተግባር የተሟላ የነፃነት ዝግጅት አድርገዋል ማለት አይደለም። የሃሳብ፣ የተግባርና የመንፈስ ስንቅ አሟልተዋል ወይም ለነፃነት ጉዞ በብቃት ተዘጋጅተዋል ማለት አይደለም። በጭራሽ።
ደግነቱ፣ ጥበበኛው ዮቶር መጣ።
ጥሩነቱ፣ ሙሴም ጥበበኛ ነውና ዮቶርን ያከብረዋል። ያማክረዋል። “ዮቶር” ሲመጣ፣ ለሙሴ ምን ዓይነት የመፍትሔ ሀሳቦችን እንደሚያቀርብ ለመመልከት እንሞክር።
የተጓዦቹ ችግር፣… የእህልና የውሃ እጦት ብቻ አይደለም። ጥምና ረሃባቸው ብዙ ነው። የሥነምግባርና የፍትሕ መርሆችን አሰናድተዋል? በጭራሽ። ሕግና ሥርዓትን እንዴት እንደሚያዋቅሩ አውቀው መላ አዘጋጅተዋል? በጭራሽ አላሰቡበትም።
ያለ ምግብና ያለ ውሃ በሕይወት መቆየት እንደማይቻል ግልፅ ነው። ነገር ግን፣ በቂ ስንቅ የላቸውም።
ያለ ሥነምግባርና ያለ ፍትሕ መርሆችስ፣ ለምን ያህል ጊዜ በሰላም ይቆያሉ? ብዙ አይቆዩም። የሥነምግባር መርህ በቅጡ ካልታወቀና ለልጆቻቸው በጥዋቱ ካላስተማሩ፣ ጥሩና መጥፎ ይምታታሉ። ሐላልና ሐራም ይደበላለቃሉ። ሕይወታቸውን እንዴት መምራት ይችላሉ? በጭፍን ስሜትና በጩኸት፣ እንደ አውሬ በጉልበትና በመንጋ ጋጋታ፣… የሰው ሕይወት ይጠወልጋል እንጂ አይለመልምም።
ያለ ሕግና ያለ ሥርዓትም፣ በደህና መሰንበት አይቻልም።
ልክ እንደዚያው፣ የመንፈስ ስንቅ ካልገነቡ፣ ከሌሎች እንስሳት የባሰ እንጂ የተሻለ እጣ አይኖራቸውም። መልካም የግል ማንነትን ለመገንባት ከሚያገለግሉ የሥነምግባር መርሆች ጎን ለጎን፣ የመልካምነትን ልዕልና በድምቀት አጉልተው የሚያሳዩ የጀግንነት ታሪኮችና የኪነጥበብ ትረካዎች ያስፈልጋሉ። መንፈስን የሚያድሱ ትዕይንቶችና ክብረ በዓላትም እንዲሁ። የእያንዳንዱን ሰው ሕልውና ከግል ሃላፊነት ጋር ያጣመረ፣… ራስንና ሰውን የማክበር፣ ብቃትን የመገንባትና የሰው ልህቀትን የማድነቅ ባሕል ያስፈልጋል። የመንፈስ ብቃቶችና መንፈሳዊ ስንቆች ልንላቸው እንችላለን።
አለበለዚያ፣ የሰዎች ሕልውና በመንፈሳዊ ረሃብ ይራቆታል። ይዋረዳል። ታዲያ መልካም የባሕል ችግኞችን ለማብቀል፣ መንፈስን አድሰው የሚያነቃቁ የኪነጥበብ ትረካዎችና ክብረ በዓላትን ለመገንባት፣ ከመነሻው አስበውበታል?
የስልጣኔ ባህል ለመገንባት ይቅርና አጣዳፊ ችግሮችን ለመዳኘት የሚያገለግል ሕግና ሥርዓትን እንኳ በቅጡ ለማበጀት አልጣሩም።
የሙሴ የዳኝነት ውሎና የዮቶር ትዝብት።
በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች መሃል፣ በእለት ተእለት ኑሮ ላይ፣ ብዙ አለመግባባቶች እንደሚፈጠሩ መገመት ያቅታቸዋል?
ውዝግብ ይፈጠራል። በዳይና ተበዳይ ይኖራል። ወንጀለኞች የሚፈፅሙት ግፍና በንፁሃን ላይ የሚደርስ ጉዳት፣… የእለት ተእለት ክስተት ነው።
ዋናው ነገር፣ አለመግባባትን ለማስቀረትና ወንጀልን ለመከላከል የሚችል የሥነምግባር መርህ መኖር አለመኖሩ ነው።
ዋናው ነጥብ፣… አለመግባባትን ለመፍታትና ወንጀለኞችን ለመቅጣት የሚችል ሕግና ሥርዓት መኖር አለመኖሩ ነው።
የሥነምግባር መርሆችን አጥርተው እያወቁ የማስተማር፣ ሕግና ስርዓትን በቅጡ እየገነቡ ፍትሕን የማስፈን ጉዞ ካልጀመሩ፣… መጨረሻቸው አያምርም።
ሥነምግባርን የማያውቅ፣ ህግ የሌለው ስርዓት አልበኝነትና የሥልጣኔ እጦት፣… መዘዛቸው፣ ከረሃብና ከጥም አይተናነስም።
ለዚህም ይመስላል፣ የረሃብና የጥም ትረካዎችን ተከትለው የመጡት ሁለት ክስተቶች፣ በሥነምግባርና በፍትሕ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
ትረካው እንዲህ ነው። ተለይተውት የቆዩ የሙሴ ቤተሰቦች ተመልሰው እንደመጡ በመግለፅ ይጀምራል - የምዕራፍ 18 ትረካ።
“ዮቶር” መጣ - ታሪክን የሚቀይር ምክር ይዞ።
የሙሴ ባለቤት፣ ሁለት ልጆቿን ይዛ፣ አባቷ ጋ ተጠልላ እንደከረመች ትረካው ይነግረናል። የምድያም ካህን ዮቶር ነው አባቷ። (ራጉኤል ተብሎም ተጠቅሷል) አሁን ወደ ሙሴ ሊያደርሳቸው መጥቷል። መልካም አቀባበልም ተደረጎለታል።
በማግስቱ ግን፣ የሙሴን ውሎ ሲታዘብ፣ ቅር የሚያሰኝ ነገር አየ። ቅሬታውንም ተናገረ። ታዲያ የዮቶሮ ቅሬታ ከሌሎቹ ይለያል። ሙሴን ይወቅሰዋል። ነገር ግን የመፍትሔ ሃሳቦችንም ጭምር ነው ለሙሴ የሚያቀርብለት። ታሪክ የሚቀይር ምክር ይሰጠዋል።
የሥነምግባርና የፍትህ መርሆች፣ ህግና ስርዓት፣ ታቦትና ፅላት፣ ባሕልና ክብረ በዓል፤… መልክ እየያዙ የሚመጡት ከዮቶር ምክር በኋላ ነው።
ለካ፤ ሙሴም ለነፃነት ጉዞው በቂ የሃሳብና የመንፈስ ስንቅ አላዘጋጀም ነበር። ብዙዎቹ ስደተኛ ተከታዮቹ ደግሞ፤ ሁሉንም ነገር በሙሴ ትከሻ ላይ ጥለውታል። ሙሴ ሁሉንም ነገር እንዲያሟላ ይጠብቃሉ። እሱም ግን፤ ሁሉንም ሃላፊነት መሸከምና ሁሉንም ነገር ማሟላት የሚችል ወይም ማሟላት የሚገባው ይመስለዋል።
ግን እንዴት ብሎ ይችለዋል?
ለነገሩ፤ ቀድሞውኑ በቂ ስንቅ አለመዘጋጀቱ ብቻ ሳይሆን የእለት ተእለት ችግሮችን ከስር ከስር ለመፍታት የማሰቢያ ጊዜ አጥቷል። አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ደግነቱ የዮቶርን ምክር ሰማ። አመነበት። በተግባር ተጠቀመበት። ከብዙ የመከራ ሸክም ለመዳንም ትልቅ ታሪክ ለመስራትም ቻለ። ትረካው እንዲህ ይላል።
“በማግስቱ፣… ሙሴ በሕዝቡ ዘንድ ሊፈርድ ተቀመጠ። ሕዝቡም በሙሴ ፊት ከጠዋት እስከ ማታ ቆመው ነበር”…
የሙሴ አማት ዮቶር፤ በዚህ የሙሴን የዳኝነት ውሎ አየ። ታዘበ። በዚህም ደስተኛ አልሆነም። ደግነቱ፤ ዮቶር ጥበበኛ ነው። እንደ ብዙዎቹ ሰዎች አይደለም። ስህተትን መንቀፍ እንደሚያስፈልግ ያውቃል። ነገር ግን ነቀፋ ብቻውን መፍትሄ እንደማይወልድ ገብቶታል። በቦታውና በልኩ ትችት ማቅረብ ተገቢ ነው። ሙሴ እንኳ ይሳሳታል። ያጎድላል። ቅሬታና ትችት በጭፍን ጥላቻ እስካልተመረዘ ድረስይ ጠቅማል።
ነገር ግን፣ ከትችትና ከቅሬታ ባሻገር መፍትሔ መሻትና መላ መፍጠር የሰዎች ሁሉ ሃላፊነትና ድርሻ ነው። ዮቶር ይህን ሁሉ ያውቃል። እናም ከሙሴ ጋር ተነጋገረ።
“ይህ የምታደርገው ነገር ምንድነው? ሕዝቡ ሁሉ ከጥዋት እስከ ማታ በዙሪያህ ቆመው፤ አንተ ብቻህን ለምን ትቀመጣለህ?” ብሎ ጠየቀ ዮቶር። በቅሬታ መንፈስ የቀረበ ትችትን ያዘለ ጥያቄ እንደሆነ ሙሴ አይጠፋውም። ነገር ግን ለማቃናት እንጂ ለማጥላላት አይደለም።
“ሕዝቡ እግዚሄርን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ። ነገር ቢኖራቸውም ወደ እኔ ይመጣሉ። በዚህና በዚያ ሰው መካከልም እፈርዳለሁ። የእግዚሄርንም ሥርዓትና ሕግ አስታውቃቸዋለሁ” ብሎ መለሰ ሙሴ።
“አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም” ብሎ ተናገረ ዮቶር። ምክንያቱንም ገለፀ።
ሙሴ ከጠዋት እስከ ማታ የሁሉንም ሰው አቤቱታና ክስ እየሰማ ዳኝነት ለመስጠት የቱንም ያህል ቢተጋ፤… ችግሮችን ማቃለል አይችልም።
ዮቶርም ነገረው።
ይሄ ነገር አያዛልቅህም። አትችለውም። ትደክማለህ። ለሌላ ስራ ምንም ጊዜ አታገኝም፤ በቂ አቅም አይኖርህም አለው። ይህም ብቻ አይደለም።
ከሳሽና ተከሳሽ ሁሉ ተራ እስኪደርሳቸው በየእለቱ ቆመው በከንቱ ይደክማሉ። ቅሬታ ይበረክታል። ለአምባጓሮና ለፀብ፣ ለጥላቻና ለአመጽ ሰበብና ማመካኛ በብዛት ይፈለፈላል። ጉዞው የተረበሸ፣ ከመድረሻ አላማው የተንሻፈፈ፣ መፃኢ ሕይወቱም በትርምስ የተበጠበጠና እርካታ የራቀው፣ ኑሮውም ሰላም የጠፋበት ይሆናል። ነገሮች ስርዓት ካልያዙ መድረሻ ያጣሉና ነው።
ይሄ ጥሩ እንደማይሆን ከገለፀ በኋላ ምን እንደሚሻል ዮቶር ተናገረ።
“እመክርሃለሁና ቃሌን ስማ።…” አለ።
ሥርዓትንና ሕግን ለሕዝቡ አስተምር።
መንገዱና አሰራሩን አሳያቸው።
ጥበበኛና ፍትሐዊ ዳኞችን ምረጥ። ስራውን ተከፋፍለው እንደየብቃታቸውም በእርከን እየተቀባበሉ ይሰራሉ ብሎ መከረ ዮቶር።
ከሕዝቡ መሃል እግዚሄርን የሚፈሩ፤ የሰውን ንብረት የማይመኙ፤ አላግባብ የሚመጣ ጥቅምን የማይፈልጉ ታማኝ አዋቂዎችን ምረጥ። በእርከን በእርከን ፍርድ የሚሰጡ ዳኞች ይሁኑ። ከባድና አውራ ጉዳዮችን ወደ አንተ ያምጡ አለው።
ይሄ መሠረታዊ የዳኝነት ሥርዓት መዋቅር እንደማለት ነው።
ብዙ የወረዳ ዳኞች፣… በእኩል የሃላፊነት ደረጃ ሥራዎችን ይከፋፍላሉ። ከበድ ያሉ ወይም በይግባኝ የሚመጡ አቤቱታዎች ደግሞ በከፍተኛ የዳኝነት እርከን ይስተናገዳሉ። ሙሴ ይህን ምክር ተቀብሎ ወዲያውኑ ተግባራዊ አደረገ። ትንሽ የእፎይታ ጊዜ አገኘ። ተረጋግቶ ማሰብና የሚያዛልቁ መፍትሔዎች ማተኮር ይችላል የዳኝት መዋቅር ብቻ።   ግን በቂ አይደለም።
ዳኞች፣ ማገናዘቢያና ማመዛዘኛ ሲኖራቸው፣ የፍትህ መርሆችንና ዝርዝር ህጎችን በሥርዓት ሲያገኙ ነው ፍርዳቸው የሚቃናው። ህግ አክባሪ የስልጣኔ ባሕል ለማዳበርም ያለግላሉ። ለዚህም፣ የዳኝነት መስመሮችና ሚዛኖች ያስፈልጋሉ። ማለትም የፍትህ መርሆችና የጥፋተኝት መስመሮች፣… ከዚያም በተጨማሪ የጥፋትና የቅጣት መለኪያ ሚዛኖች መኖር አለባቸው።፡
ሥርዓትና ሕግ አስተምራቸው ተብሎ የለ።
እነዚህ ናቸው የዮቶር ምክሮች። ከዚህ ትረካ በኋላ ነው ወዲያውኑ የሲና ተራራ ትረካ የሚመጣው። ክስተቱ እጅግ ልዩ ከመሆኑ የተነሳ፣ ህዝቡ ሁሉ ታጥበው ጸድተው ለመቅረብ ለሦስት ቀናት ዝግጅት አካሂደዋል። አይበዛበትም። እንዲያውም ከሁሉም የላቀ ተዓምረኛ ክስተት እንደሆነ በሙሴ ትረካው ተነግሮለታል።
ታዲያ፣ ወደር የለሽ ተብሎ የተነገረለት ተዓምራዊ ክስተት፣… የጦርነትና የመዓት ውርጅብኝ አይደለም። የግብፅን ምድር በበሽታ ወረርሽኝና በክፉ ህመም ማሰቃየት አይደለም። ከየቤቱ፣… ከስስውና ከእንስሳት ሁሉ የበኩር ልጆችን በአንድ ሌሊት የሞቱበት አስፈሪና ዘግናኝ የእልቂት መዓት አይደለም- አቻ የለሽ ተዓምር።
ባሕርን በአንዳች ምትሃተኛ ነፍስ ለሁለት ሰንጥቆ፣ የባሕሩንም ወለል ለስደተኞች ጉዞ አመቻችቶ ከሚያሳድዳቸው ጦር እንዲመያልጡ ማድረግ፣… ለማመን የሚያስቸግር ተዓምረኛ ትረካ ቢሆንም፣ “ወደር የለሽ ተዓምር” አልተባለም።
ከሰማይ እለት ተእለት እንጀራ ማዝነብ ወይም ክው ባለ በርሃ ላይ ምድርን በዘንግ ነካክቶ የውሃ ምንጮችን መፍጠርስ? ለትንግርትም ይከብዳል። ግን፣ ትልቁ ተዓምር አልተባለም።
ወደር የለሽ እንደሆነ ተተረከለት ክስተት፣… ሃይል ግርማዊ ተግባር አይደለም። የእርግማና የምርቃት፣ የቅጣት መከራ ወይም ተትረፈረፈ ጸጋና ያለጥረት የተገኘ የፍሬ በረከት አይደለም። በሌላ አባባል፣ ሞግዚትነትና ምጽዋት አይደለም።
አቻ የለሽ ተዓምር የሚል ማዕረግ የተሰጠው ክስተት፣ በሲና (በሆረብ) ተራራ ላይ ያላተኮረው ትረካ ነው።
ትምህርት የተሰጠበት ክስተት ነው - ሌላ ሳይሆን።
በመርህና በሥርዓት፣… በሥነምግባርና በፍትህ ዙሪያ የቀረበ ሰፊ ትምህርት ነው።  ቢሆንም ግን፣ ጠቅለል ባለ አጭር ስያሜም ይታወቃል። አስርቱ ቃላት ብለው ይጠሩታል። በእርግጥ ቃላት ሲባል፣ ሃሳቦች ወይም መርሆ ለማለትም ነው- አስርቱ ትዕዛዛት እንዲሉ።
አትስረቅ፣ አትግደል፣ አታመንዝር የሚሉ ቃላትን ይጨምራል። በሐሰት አትመስክር። ባለንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚሉ ዓረፍተ ነገሮችንም ያካትታል።
ይህም ብቻ አይደለም። ዋና ዋናዎቹን መርሆች የሚዘረዝሩ በርካታ የምክርና የተግሳጽ አንቀጾች፣… ጥሩና መጥፎ፣ ተገቢ የሆኑና ያልሆኑ፣ ጠቃሚና ጎጂ፣ መልካና ክፉ ነገሮችን ለመለየት፣… እንዲሁም የትኛው ይሻላል? የትኛው ይልቃል? የትኛው ይብሳል ብሎ ለማመዛዘን ያገለግላሉ የሚላቸውን የሥነምግባር ደንቦችንና ብዙ የህግ ነጥቦችን ያጠቃልላል- ትምህርቱ።
በአጠቃላይ፣ የሲና ተራራ ትረካ፣… የሥነምግባርና የፍትህ ዋና ዋና መርሆችን መልክ አስይዞ የማቅረብ፣ በጽሁፍም ለትምህርት የማሰናዳት ትረካ ነው።
ህግና ስርዓትን ከላይ እስከታች፣ ከጥቅል እስከ ዝርዝር፣ የወንጀል ዓይነቶችና ክብደታቸው፣ የማስረጃና የተዓማኒነት፣ የዳኝነትና የፍርድ ጉዳዮችን፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው የሚገልጹትም ከዚህ በኋላ ነው።
የመልካምነት ምሳሌዎች፣ የክብር ምልክቶች፣ በዓላትና የአከባበር ስርዓቶች፣… ጽላትና ታቦትን ጨምሮ፣… ሰፊ የትረካ ቦታ የያዙትም ከዚህ የዮቶር ምክር በኋላ ነው።
የሥነምግባርና የፍትህ መርሆቹ፣ የሕግና ሥርዓት ዝርዝር አንቀጾች፣ የበዓላት አከባበር ስርዓቶች፣… እስከ አለባበስ ድረስ የተጻፈው ዝርዝር የመመሪያ ብዛትና ይዘት፣ አንድ በአንድ አይቶ ትክክል ናቸው ለማለት አይደለም።
ትክክለኛና መሠረታዊ መርሆችን ማካተቱ መልካም ነው። ነገር ግን፣ የትረካው ፋይዳ ይሄ ብቻ አይደለም። የስነ-ምግባርና የፍትህ መርህ፣ ሕግና ሥርዓት፣ መልካም የሰብዕና መንፈስና የስልጣን ባሕል ለዘለቄታው የሕልውና ዋስትና መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑ የትረካው ትልቁ ቁምነገር።
Read 5811 times