Saturday, 19 November 2022 19:42

አፍሪካውያን ሥራ ፈላጊዎች የወንጀል ሰለባ እየሆኑ ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

- ወጣቶች ከአጭበርባሪ ኤጀንቶች ይጠንቀቁ ተባለ !


          “ሲትዝን” የተሰኘው” ታዋቂው የኬንያ ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ፤ ኬንያውያን ወጣቶች በኢንተርኔት ላይ በሚተዋወቁ የእስያ ሃሰተኛ የስራ ዕድሎች እየተታለሉ የወንጀል ሰለባ እየሆኑ ነው ብሏል፡፡
 በታይላንድ የሚገኘው የኬንያ ኤምባሲ፣ ዜጎች በኢንተርኔት ለሚተዋወቁ የታይላንድ ሃሰተኛ የሽያጭና የደንበኛ አገልግሎት ስራዎች እንዳያመለክቱ ሲያስጠነቅቅ መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል።
ኬንያውያን በኢንተርኔት ላይ የሚወጡ ሃሰተኛ የሥራ ዕድሎችን በተመለከተ የተሰጡ ማስጠንቀቂያዎችን ከቁብ አለመቁጠራቸውን የጠቀሰው የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በዚህም ሳቢያ  አንድ ኬንያዊ ወጣት ለሞት መዳረጉን አስታውቋል።
“ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙሃንና በኦንላይን መድረኮች ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጥም፣ ኬንያውያን  የተጭበረበሩ የሥራ ዕድሎች ሰለባ ሆነው መቀጠላቸው ኤምባሲውን በእጅጉ ያሳስበዋል።” ይላል ፤የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መግለጫ።
በፖሊስ የሚፈለጉ በርካታ ኤጀንቶች አሁንም ድረስ በታይላንድ እንደሚገኝ የሚገልጹትን የሽያጭና የደንበኛ አገልግሎት ሥራዎች እያስተዋወቁ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ በዚህ ሐሰተኛ የሥራ ዕድል ወጥመድ ውስጥ የወደቁ ዜጎች፤ የማታ ማታ ራሳቸውን ማይናማር ውስጥ ያገኙታል ይላል፡፡ በዚያም ሳሉ ድብደባና ሥቃይ ይደርስባቸዋል። የሳይበር ወንጀሎችን እንዲፈፅሙም ይደረጋሉ፡፡
“በግዳጅ የጉልበት ስራ ካምፕ ውስጥ የሚሰሩ ኬንያውያንና በርካታ ሌሎች አፍሪካውያን ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎቻቸውንና ህይወታቸውን የማጣት ትልቅ አደጋ ይጋፈጣሉ። አንድ ኬንያዊ ወጣት በማይናማር በቻይና በሚመሩ ፋብሪካዎች ውስጥ የሰውነት ክፍሉን (ምናልባት ኩላሊቱን) አውጥቶ ለመውሰድ የልምድ ሀኪሞች ባደረጉት ኦፕራስዮን ለሞት ተዳርጓል።” ይላል፤ መግለጫው።
“ሌሎች ከሞትና ስቃይ እንዲተርፉ የተደረጉ ስደተኞች፤ እጅና እግራቸው ተሰብሮ በክራንች ነው ወደ ሀገራቸው የገቡት፤ በፋብሪካዎቹ ውስጥ በሚሰሩ እስከ 20 በሚደርሱ የወንበዴ ቡድን አባላት ክፉኛ ተደብድበው በደረሰባቸው ጉዳት፡፡”
አስር ኡጋንዳውያንና አንድ ብሩንዲያዊን ጨምሮ 76 የስቃዩ ሰለባዎች ወደ አገራቸው በህይወት እንዲመለሱ መደረጉን የዘገበው “ሲትዝን”፤ የህይወት ማዳን ዘመቻው በማይንማር ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ መስተጓጎሉን ጠቁሟል።
 ዳጎስ ባለ ክፍያ በመማለል ማይናማር ውስጥ ለመቅረትና የሳይበር ወንጀሎችን እየፈፀሙ ለመቀጠል የመረጡ አንዳንድ ኬንያውያን ጉዳይ ኤምባሲውን እንደሚያሳስበው ገልጿል።
“እነዚህ ኬንያውያን ለኬንያ ብሔራዊ ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ደቅነዋል።” ብሏል ኤምባሲው።
“ሲቲዝን ቲቪ” ከሳምንት በፊት የታይላንድ የተጭበረበሩ የሥራ ዕድሎች ሰለባ በነበሩና ከስቃይ በተረፉ ዜጎች ላይ ያጠናቀረውን  የምርመራ ሥራ በፕሮግራሙ  ማቅረቡን አስታውሷል።
የሥራ ማስታወቂያው፣አመልካቾች በነፍስ ወከፍ 125ሺ ብር ገደማ (ተበድረው) ለኤጀንቶቻቸው ከከፈሉና አጭር ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ፤በወር እስከ 50ሺ ብር ክፍያ እንደሚያገኙ ይገልጻል። (ይሄ ግን ሃሰተኛ ማማለያ ወይም ማታለያ ነው!)
ዘገባው እንደሚለው፤ በታይላንድ ስደተኛ ሰራተኞች ድብደባ ይፈፀምባቸዋል፤ ጨለማ ክፍሎች ውስጥ ይቆለፍባቸዋል፤ ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎቻቸው (ምናልባትም ኩላሊት) ተሰርቀው ይወሰድባቸዋል። ከዚህም ባሻገር፤ በዝሙት አዳሪነትና በሳይበር ወንጀሎች እንዲሰማሩ ይደረጋሉ ተብሏል።
እኛም በዚህ አጋጣሚ የአገራችን ሥራ ፈላጊ ወጣቶች፣ ራሳቸውን ከመሰል አጭበርባሪ ኤጀንቶች ይጠብቁ ዘንድ ልናሳስብ እንወዳለን። ያለበቂ መረጃና ዋስትና የገዛ አገርን ለቆ ለሥራ ቅጥር ባዕድ አገር መሻገር አይመከርም፡፡ መቶ ሺ ብሮች ለደላሎች ከፍሎ ባህር ማዶ ከመጓዝ አንዳንዴ እዚሁ አገር ቤት ምን መሥራት እችላለሁ ብሎ ጥቂት ማስብ ክፉ አይደለም። ህይወታችንን በጥበብና በሃላፊነት ስሜት እንምራ፡፡


Read 14386 times