Saturday, 26 November 2022 00:00

በኦሮሚያ ክልል በሚፈጸሙ ጥቃቶች ኦፌኮ እና አብን እየተካሰሱ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  - አብን በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ጠይቋል
    - ኦፌኮ ለችግሮቹ መባባስ “አብን”ን ተጠያቂ አድርጓል
     
        በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችና በንፁሃን ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች ላይ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)እርስ በርስ እየተካሰሱ ነው፡፡
አብን  በክልሉ በአማራ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም መንግስት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ጠይቋል። ኦፌኮ በበኩሉ፤ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ችሮች መባባስ ተጠያቂው አብን ነው ብሏል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ላለው ጥቃት ኦፌኮ እና ኦነግን ተጠያቂ ያደረገው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፤ በንፁሃን ላይ እየደረሰ ያለውን መጠነ ሰፊ ጥቃት ለማስቆም መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅና የመከላከያ ሠራዊቱን በስፍራው እንዲያሰማራ ጠይቋል።
በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ፣የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ ጭምር በጥቃቱ ይሳተፋሉ ያለው አብን፤ መንግስት ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል ብሏል።
በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ በንፁሃን የአማራ ተወላጆች ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉንና ለዚህም የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን የአብን ሥራ አስፈጻሚ አባልና የብሔራዊ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ዶ/ር ቴዎድሮስ ተክለማሪያምን ጠቅሶ ዶቼቬሌ ዘግቧል።
 ውንጀላውን የሚቃወመው ኦፌኮ በበኩሉ፤ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እያጋጠሙ ላሉት የፀጥታ ችግሮች አብንን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ “በአገሪቱ ውስጥ ሁልጊዜ ግጭት እንዲፈጠር የሚቀሰቅሱት የአብን አባላቶች ናቸው፤ ኦፌኮ ጦርነትን አይፈልግም።” ብሏል ፓርቲው በመግለጫው፡፡
“ኦፌኮ የሰሜኑን ጦርነት ባወገዘበት ወቅት አብኖች በጦርነቱ ተካፍለዋል፤ ህገ-መንግስቱ እንዲፈርስም ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ግጭቱ እንዲባባስና እንዲቀጥል ያላቸውን ፍላጎት የሚያመላክት ነው” ሲልም አክሏል፤ ፓርቲው፡፡
አሁን በአካባቢው የተፈጠረውን ቀውስ ለማስቆም የኦሮሚያና የአማራ ክልል መንግስታትና ሁሉም በኦሮሞና በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሃላፊነት አለባቸው ያሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ፤ ችግሩን በዘላቂነት ለማስቆም በትጋት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
ኦፌኮ በበኩሉ፤ በዚህ ዘመን ጠመንጃ ይዞ መገዳደል ተገቢ ባለመሆኑ ችግሮቻችን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይኖርብናል ሲል አሳስቧል።
በሌላ በኩል፤ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ቃለምልልስ ያደረገው  ታዋቂው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ፣ ሸኔ ሕዝብን እየገደለና እየዘረፈ የራሱን ምቾት ለመጠበቅ የሚንቀሳቀስ የዘራፊ ስብስብ ነው ሲል  ተናገረ።
“ሸኔ እንደ ሀገር በህዝብ ላይ ያደረሰው ተጽእኖ ከባድ ቢሆንም፤ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ በተለይ በኦሮሞ አርሶ አደር ላይ የሚፈጽመው ዘግናኝ ግፍ ደግሞ ለመናገር እንኳ የሚከብድ ነው።” ብሏል፤አትሌቱ፡፡
የሕዝቡ ሰቆቃ እንዲያበቃ የሸኔ ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ እንዲያገኝ በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባም  አትሌቱ ጠቁሟል።
ቀደም ሲል የቡድኑ እንቅስቃሴና ግፉ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ ነበር ያለው አትሌት ፈይሳ፤ አሁን ላይ ግን ግፉም እንቅስቃሴውም በጣም ስለሰፋ ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት ካልተሰጠ መዘዙ ከአሁኑ የከፋ ይሆናል ብሏል።
በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አመለካከቶች ሸኔን መስመር ለማስያዝ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ውስብስብ እንደሚያደርጉት የጠቆመው አትሌቱ፤ ሸኔን ለመዋጋት ባለው ጠንካራ አቋም ምክንያት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ባሉ አንዳንድ አካላት ጫና እንደሚደርስበትም አልሸሸገም።

Read 7996 times