Print this page
Saturday, 26 November 2022 00:00

የጉራጌ ዞን በኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተወሰነ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(0 votes)

  ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በተነሳው ተቃውሞ ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
                 
           በደቡብ ክልል ጉራጌ ዞን ውስጥ ከክልል አደረጃጀት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተቀሰቀሰ አመፅና ተቃውሞ ሳቢያ ዞኑ ከትናንት ህዳር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር መወሰኑ ተገለፀ፡፡ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም እስከ አሁን ከ70 በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር  እንዲውሉ መደረጉም ታውቋል፡፡
የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ በውዲ ከትናንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ በአካባቢው የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር በመደበኛ አሰራር ለማስተዳደር ባለመቻሉ ምክንያት ዞኑ በተደራጀ ኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ተወስኗል፡፡
የፌደራል ፖሊስና የክልሉ ልዩ ሃይል የኦፕሬሽኑን ስራ በቅንጅት እንደሚመሩት ያስታወቁት ሃላፊው፤ ሁለቱ አካላት የፀጥታ ሃይሎችን ይዘው በተደራጀ መንገድ የአካባቢውን የፀጥታ ሁኔታ እንደሚቆጣጠሩና እየተፈጠረ ያለውን የፀጥታ ችግር ለመቅረፍ እንደሚሰሩ ገልፀው፤ በደቡብ ክልል በማዕከል ደረጃ ይህንን የሚያስተባብር አካል መቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡
እስከ አሁን በአካባቢው በተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው፣ የጥፋቱን ይዘት የመሩ ያስተባበሩ፤ ያቀዱና እንዲተገበር ድጋፍ ያደረጉ ሁሉ በአግባቡ እየተጣራ እንዲለዩና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ የተደረጉ ሲሆን በቀጣይም በድርጊቱ ውስጥ ተሳትፎ የነበራቸው በሙሉ በቁጥጥር ስር ይውላሉ ብለዋል፡፡
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ነሐሴ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ፣ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳን በማካለል የሚመሰረተው አዲስ ክልላዊ መንግስት አካል እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ በአብላጫ ድምፅ ውድቅ ማድረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ውሳኔውን ተከትሎ የዞኑ አስተዳዳሪን ጨምሮ በርካታ አመራሮች ከሀላፊነታቸው ሲነሱ፣ ከፊሎቹ ደግሞ ለእስር መዳረጋቸው አይዘነጋም፡፡  


Read 8385 times