Print this page
Saturday, 26 November 2022 00:00

ኪነ-ጥበብ ኢትዮጵያን ትመስላለች?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 ተዓምራዊ ስራዎችና መዓተኛ ጥፋቶች የተተረኩባት አገር ናት። “ለማመን የሚከብዱ” ናቸው ታሪኮቿ። ግን ደግሞ ለበርካታ ሺ ዓመታት ገዝፎ የሚታይ ህልውናዋንና ታሪኳን፤ እንደ ዘላለማዊ የተፈጥሮ ሕግ፣ አምነው የሚቀበሉት እንጂ የሚጠራጠሩት አይደለም።
አለቀላት፣ ጠወለገች። አፈር ሆነች፣ ጠፋች… የሚያስብሉ መዓቶች ይደራረቡባታል። ከውጭ በኩል ተዘምቶባታል። ከውስጥ በኩል፣ ተጠፋፉ፣ ተላለቁ ተብሏል- በጦርነት ብዛት። ለዚያውም የሚያሳዝኑና የሚዘገንኑ። እንዲያም ሆኖ፣ አፈር በልታም፣… እንደ ቡቃያ ቀና ትላለች። “ለማመን ቢከብድም”፣ እውነት ነው።
ተነሳች፣ ታደሰች፣ ገሰገሰች፣… ሰላም አወረደች፣ ለጎረቤቶችም ተረፈች። ከቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ፣ ከጦርነት እንዲወጡ አገዘች። የሆነ ዘመን ላይ በኢኮኖሚ አንሰራራች። በሆነ ዘመን በስልጣኔ ተራመደች ይባልላታል። ለማመን ቢከብድም እውነት ነው። መጣች፣ መጠቀች እንዳልተባለች፤… እንደገና መቀመቅ የሚያወርድ መዓት ታመጣለች - “በማይታመን ፍጥነት”። ግን እውነት ነው። ለዚያውም ከተራ ገጠመኝ የላቀ እውነት!
ስኬቷና ክብሯ እንደ “ተዓምር” የሚያስደንቅ፣ ውድቀቷና ውርደቷ እንደ “መዓት” የሚያስደነግጥ ነው። ግን ሳይዘሩት የበቀለ፣ ሳይወረውሩት የወረደ አይደለም። ያለ ጥፋት የመጣ፣ ያለ ጥረት የተገኘ አለመሆኑን አስተውለው ሲያዩት፣… “ድሮስ ምን ሊሆን ኖሯል?” የሚያስብል፣ ያለ ጥርጥር የሚያሳምን ታሪክ ነው - ተዓምራዊና መዓተኛ ቢመስልም።
በጦርነት የመንደድና በሰላም የመተንፈስ ያህል፣ አስደናቂና አስደንጋጭ ለውጦችን፣… የመዓትና የተዓምር ትረካዎችንን፣ ከፅኑ ተዓማኒነት ጋር ማዋሐድ የኪነጥበብ ባህርይ ነው። ታዲያ፣ ኪነጥበብ፣ ኢትዮጵያን አትመስልም? ግን ተረትም ትመስላለች።
         
     አላዋቂ ነው፣ አዋቂ የሚሆነው። በሁለት በሦስት ቃላት የጀመረም፣ ሊቀ ሊቃውንት ይሆናል። ለዳዴ የሚቸገር ህጻን ነው ሯጭ የሚሆነው። ከዚያም አልፎ፣ የመኪና የአውሮፕላን ሰሪ፣… ከፍጥነትም ባሻገር ክንፍ አውጥቶ በራሪ ይሆናል - የቴክኖሎጂ ፈጣሪ።
ባዶ እጁን ተወልዶ፣ ሃብት ፈጣሪ ባለፀጋ ይሆናል።
አንዳንዴ ሲያስቡት ለማመን የሚቸግር ብርቅ ድንቅ ነው - የእውነት የሕይወት ነገር። ያስደንቃል። ወይም ያስደነግጣል።
ግን ደግሞ፣ “ድሮስ?!” ያስብላል። ከዚህ ውጭስ ምን እንዲሆን ይጠበቃል? ከእውነትና ከሕይወት የበለጠ የሚታመን ምን ይኖራል? የዘወትር ገጠመኛችን፣ የእለት ተእለት ኑሯችን እንዲህ ነው። እንዲያም ሆኖ፣ ብርቅ ድንቅ ገፅታውንም መካድ አይቻልም። እንደ ተዓምር ነው- የሚያስደንቅ አልያም የሚያስደነግጥ።
መቼም፣ ዘላለማዊ የመሰለ የተረጋጋ ሕይወት፣ በመብረቅ ፍጥነት ድንገት ዱብዳ ወርዶበት ሲናወጥ፣… ያስደነግጣል። ሕይወት ይናጋል፤ ወይም ክው ብሎ ይደነዝዛል።
በሸክም ብዛት እየተንገዳገደና እየተንገላታ ሲያዘግም የነበረ የችግር ኑሮ፣… “መቼ ይሆን የሚያልፍለት?” ያሰኛል። “ከዚህ በላይ ምን ይመጣል?” ያስብላል።  ለሃሳብ ለምናብ ያስቸግራል።
ጭራሽ፣ ይባስ ብሎ፣ አበሳው ሲበዛና እጥፍ ድርብ ሲጭንበት፣ መከራው ከወዲህና ከወዲያ ሲያጎሳቁለው፣ እያላጋ ሲያጣድፈውና ሲያላትመው፣ የቆመበት መሬት የከዳው ያህል፣ ሸክም የታከተው እግሩ ሲለመጥና የቀለጠ ሲመስል፣ ቁልቁለቱ ሲጨልምበት፣… ያልጠበቅነው ፍዳ ይሆንብናል። ያስደነግጠናል።
ግን፣ የሕይወት እውነታ እንደሆነም አያጠራጥርም። ድክመት እንደገና ያደክማል። የተራበ መስራት እያቃተው የሚበላውን ያጣል። ውሸት፣ መልሶ መላልሶ ያስዋሻል። ይሄ ዘላለማዊ እውነት ነው። ነገር ግን፣ እንደተዓምር ያስደነግጠናል።
ደግ ደጉን ስናስብ፣ በሜዳው ልምላሜና በፏፏቴው ግልቢያ መንፈሳችን ሲዝናና፣ ሌላውን ሁሉ ብንረሳው አይፈረድብንም። ክንፎቿን የዘረጋች እርግብ፣ ሽቅብ መጥቆ ቁልቁል የሚምዘገዘግ ንስር፣ የተራራው ከፍታ፣ የዋርካው ባለ ግርማ ሞገስ ጥላ፣… የፈካና የደመቀ ዓለም ይታየናል። ቢያንስ ቢያንስ፣ አጓጊ ወገግታና በተስፋ የበራ ፈገግታ ማየታችን አይቀርም።
እንዲህ፣ መልካምና ቀናውን ስናስብ፣… ሌላ ሌላውን ሁሉ ቸል ለማለት፣ ለመዘንጋት ወይም ላለማየት ይገፋፋናል። ይጋርደናል።
የጊዜውን ጭርታና እርጋታ እንጂ የከርሞውን ካላየን፣ የደጀ ሰላሙን አለት እንጂ ከጓሮ በኩል አፋፍ ላይ መድረሱን ዞረን ካልተመለከትን፣ አዝመራውንም አደጋውንም ከወዲሁ አናስተውልም። ለዚህም ነው ዱብዳ የሚሆንብን። ሲፈነዳ ወይም ከዚያ በኋላ ነው ነገሩን የምናየው።
ሲብላላ ሲንተከተክ፣ ሲንሸራተት ሲንከባለል እንደነበረ የሚገባን፣ ውሎ ካደረ በኋላ ነው። የፈካና የተዋበ ገጽታ ላይ ተመስጠን፣ ከጎን በኩል ልብ ያላልነው አደጋ፣ መብረቅ ይሆንብናል።
ድንገተኛ ከመሆኑ ደግሞ፣ የልዩነቱ ርቀት! ሰማይና መቀመቅ እንደ ማለት ነው። የተራራና የገደል ያህል… ነገሮች በድንገት በእናታቸው የተገለጡ ያህል ነው።
እንዲህ አይነት ክስተቶች የስነ-ጽሁፍ ፈጠራ ባህርይ ናቸው። “reversal” ብሎ ይጠራቸዋል  ፈላስፋው። ሰማይ ምድሩ ሲዟዟርብን… ያልጠበቅነውን ያህል ያስደንቀናል። ግን እውነት ነው። የተፈጥሮ ሕግ ያህል ደግሞ እውነታነቱ በአጥንት በስጋችን ስር ይሰማናል።
በአንድ በኩል ያላሰብነው ያልገመትነውን ያህል ያስደነግጠናል።
ግን ደግሞ አይቀሬ ክስተት መስሎ ይታየናል። እንዴት ዘነጋሁት እንዴት ተጋረደብን ያስብለናል።
ኪነጥበብ፣ እነዚህ ሁለት ተቃራኒ የሚመስሉ መንፈሶችን በውበት የሚያዋሕድ ድንቅ ፈጠራ ነው።
የተዓምር ያህል የሚያስደንቁ ክስተቶችንና ለውጦችን ሲተርክልን፣ ተፈጥሯዊውን እውነታና ዘላለማዊ የሕይወት ምስጢራትን ማሳየቱ ነው። ድንቅ የተዓምር መንፈስንና ተዓማኒ የሕይወት እውነታን ካላዋሃደ፣… አንድም የማይታመን የማይጨበጥ አስደናቂ አስደንጋጭ ቅዠት፣ አንድም በተጨባጭ የሚታይ የቅራቅንቦ  ክምር ይሆናል።
እጅግ የተዋበ ኪነጥበብ ግን፣ የምናብ ፈጠራ የመሆኑ ያህል በተጨባጭ እውነትንና ሕይወትን አግዝፎ ያሳያል።
ሰፈር ውስጥ የምናውቃቸው ጎልማሶች፣ ከሃያ ዓመት በኋላም ጎልማሳ፣… በለጋ እድሜ ያየናቸው ሕጻናት ከአስር ዓመት በኋላ ከልጅነት መልካቸው ጋር የምናገናቸው ይመስለናል? ጎልማሳው ሸምግሎ፣ ህጻኗ ሐኪም ሆና ወይም ልጅ ወልዳ ስታስከትብ ስንመለከት ይደንቀናል። በጭራሽ ያልጠበቅነው ያልገመትነው ይሆንና ለማመን ይከብደናል።
ግን ከዚህ የሚበልጥ አሳማኝ እውነታስ ከየት ይገኛል? ለዚያውም የዘወትር፣ የትላንቱ የዘላለሙም እውነታ ነው።
በአንድ በኩል፣ አስደናቂና አስደናጋጭ፣ ያልተጠበቀና ለማመን የሚከብድ ሆኖ ይሰማናል። በሌላ በኩል ግን፣ “ድሮስ!” ያሰኛል። እንደ ኃያል ፍቅር፣ እንደ ጓደኛ ክህደት፣ እንደ ሰላምና ጦርነት ነው።
የሞቀ ቤት፣ የተደላደለ ኑሮ እንዴት በአንዲት ቅጽበት ይናጋል? ለማመን ይከብዳል።
በእርግጥ እንደሚናጋ ከልብ በማመን በየእለቱ እንጠነቀቃለን።
ነገር ግን፣ የዘወትሩ ጥንቃቄ፣ ለምን የታሰበ እንደሆነ እንረሳዋለን።
የምንበላውንና ምንጠጣውን፣ የምንለብሰውን የምንነካውን፣ የምንረግጠውን የምንተኛበትን ሁሉ አስበንበት ነው። በዘፈቀደ ያጋጠመንን ነገር አንነካም። የምንሳሳለት ተሰባሪ ጌጥ፣ የምንጠነቀቅለት የኤሌክትሪክ ገመድና የምድጃ ጋን፣…
እንዳይቆሽሽ የምንሸፍነው፣ እንዳይበከል የምንከድነው፣…
እንዳይነካን የምንርቀው፣ ለእይታ እንኳ የሚያስጠላን፣…
የቤት መሰረትና ግድግዳ፣ አጥርና ጣሪያ፣… በርና መስኮት፣… መቼ ከፍተን መቼ መዝጋት እንዳለብን፣ ከመኝታ በፊት ቆልፈን አረጋግጠን…
እነዚህን ብቻ ሳይሆን ሌሎች እልፍ ነገሮችን የምናስበውና የምናደርገው፣… የተደለደለ ቤትን የሚያናጉና ኑሮን  የሚያተራምሱ ነገሮች ስላሉ ነው።
አደጋዎች እንደሚከሰቱ እርግጠኛ በመሆናችን ነው መጠንቀቃችን። እንዲያም ሆኖ በየሴኮንዱ እንጨነቅባቸዋለን ማለት አይደለም።
በር መቆለፋችን፣ እንደ ልማድ እንቆጥረዋለን። ከአደጋ የማምለጥ ጥረት ሆና አይሰማንም። ሰላማዊና የተደላደለ ኑሮ ላይ ነው ሃሳባችን።
አንዳንዴም ጥንቃቄውን እንዘነጋዋለን። ደግሞም፣ አንድ ሁለት ቀን ስለተዘናጋን ወደያውኑ ጉዳት አይመጣብንም። ነገር ግን፣ አለመጠንቀቅ መዘዝ እንደሚያመጣ ምን ይጠየቃል? ያልተዘጋ በር፣ ዛሬ ባይሆን ነገ፣ አካልንና ኑሮን፣ ህይወትና ንብረትን ለአደጋ ያጋልጣል። የተቆለፈውን ሰብሮ፣ አጥርና ግንቡን ጥሶ ወይም ሰርስሮ የሚመጣም ይኖራል እንጂ።
እንደሚኖር እርግጠኛ ስለሆንን ነው፣ ለግንብና ለአጥር፣ ለመዝጊያና ለቁልፍ ማሰባችን።
ቢሆንም ግን፣ ጆሯችንን ግድግዳ ላይ ለጥፈን፣ ዓይናችንን በሩ ላይ ተክለን፣ እንቅልፍ አጥተን እናድራለን ማለት አይደለም። በሩ እንደተዘጋና እንደተቆለፈ ለማረጋገጥ ዘጠና ጊዜ አንለፋም።
የምንችለው የምናውቀውን ያህል መጠንቀቅ የላላውን ማጥበቅ የግድ ነው። ይህን ማከናወን፣… ከዚያ  ግን ኑሮን የማደላደልና የማጣጣም፣ በሰላም ሰርቶ በሰላም እረፍት የማግኘት ዑደት ላይ እናተኩራለን።
ሕይወትን እንኖራለን፣ ቀን ከሌት ከሴኮንድ ሴኮንድ ስለሞት አናስብም። ስለማይከሰት አይደለም። እንደሚከሰትማ ማን ይጠፋዋል? የጥንት የዘላለምም እውነታ ነው። ቢታወቅም ግን፣ ከማዶ ብቅ ሲል፣ ክው እንላለን። እየቀረበ እየተጠጋ አፍጥጦ ሲመጣም፣ እንደ ዱብዳ እንደነግጣለን።
እለት በእለት የምናያቸው እውነታዎችና የዘወትር ዑደቶች ላይ ስናተኩር፣ ተመልሰው የማይመጡ የዓመታት ሂደቶች ምን ያህል ለውጥ እንደሚያስከትሉ አንዘነጋቸዋለን።
ያስደንቁናል። ነገር ግን፣ ሊከሰቱ የማይችሉ፣ የዘፈቀደና የአጋጣሚ ጉዳዮች እንዳልሆኑም እናውቃለን።
የልብ ወለድ ድርሰት ውስጥ የምናገኛቸው አስደናቂ ወይም አስደንጋጭ እጥፋቶች (reversal ወይም twist) የዚህ አይነት መንታ ባሕርይ ሊኖራቸው ይገባል።
ለጥርጣሬ የማይቀርቡ አሳማኝ ክስተቶች መሆን አለባቸው።
ያልተጠበቁ አስደናቂ የለውጥ ክስተቶች የመሆናቸው ያህልም ተዓምረኛ መንፈስን የሚያሳድሩም መሆን ይገባቸዋል።
 እንደ ተፈጥሮ ሕግ አይቀሬ፣ እንደ ተዓምር ብርቅ ነው - የትረካ ጥበበኛ እጥፋት። ምርጥ የተረትና ምሳሌ አባባሎችን ማየት ትችላችሁ።
የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች ይባላል።… የተመኘችውን አለማግኘቷ ብቻ ሳይሆን የነበራትንም ማጣቷ ነው - ድንቅ ብርቅ ገጽታው።
የቆጡን ለማውረድ ተሳካላት ወይስ ጥረቷ ተሰናከለባት የሚል ጥያቄ ላይ እንድናተኩር ይገፋፋናል - አጀማመሩ። ባልጠበቅነው አቅጣጫ ታጥፎ ትኩረታችንን መንጭቆ ይወስዳል፡፤ ያልጠበቅነው ቢሆንም፣ ተዓማኒነቱ ግን አያጠራጥርም። ነባር ፍሬዎችን እየዘነጉ አዳዲስ ፍሬዎችን መመኘት የሰው ባህርይ ነው።
እጥፋት የሌላቸው ተረትና ምሳሌዎችስ የሉም? እስቲ መከረኛዋ ቀበሮ ላይ ካሸከምናቸው ተረቶች መካከል አንዱን እንመልከት። አስደናቂ እጥፋት የሌለው ይመስላል።
ባማረው ዛፍ ላይ የተንዠረገገው ፍሬ ያስጎመጃል፡፡ ግመጡኝ ግመጡኝ ይላል፡፡ ቀበሮ ሳይቀር ፍሬውን አይቶ ማለፍ አልቻለም። ፍሬውን ለማውረድ ተንጠራራ፡፡ ዘለለ፡፡ ተስፈነጠረ፡፡
ለትንሽ፤… ለትንሽ፤… ያማረው ፍሬ ይበልጥ እያስጎመጀው፤… እልህ እየያዘው ሞከረ፤ ተፍጨረጨረ፡፡ አልሆነለትም፡፡ ተስፋ ቆረጠ። እንባ ተናነቀው፡፡ በብስጭት ተንጨረጨረ፡፡
ሲንቆራጠጥ፤ ሲቀመጥ፤ ሲንጎራደድ ዋለ። ማራኪው ውብ ፍሬ መልኩ አልደበዘዘም። ግን ርቀቱም አልቀነሰም፡፡ ወርቃማ ሁሉ ወርቅ አይደለም ለማለት አስቦ ነበር። ይሄኛው ፍሬ ግን ሁለመናው ውብ ነው። አያጠራጥርም። ቀበሮው ምንም ሳይቀምስ፤ አይጥ ምናምን የማሳደድ ስራውን ረስቶ፤ መሸ፡፡ የዛፉ ፍሬ አሁን በደንብ አይታይም፡፡
ቀና ብሎ አየ፡፡ “ይሄኔ ያልበሰለ ቆምጣጣ ፍሬ ነው” ብሎ ወደ እለታዊው ወደ ዘወትሩ ኑሮው ሮጠ፡፡
የተፈጥሮውን አደን ትቶ፤ እንደለመደው አይጥ ለመያዝ ከማድባት ይልቅ፤ ለአይን በሚያምር በሚጣፍጥ ፍሬ ተማረከ፡፡ ከዚህም ከዚያም ሳይሆን ቀረ። ይሄ ነው ድራማው? ታዲያ እጥፋቱ የታለ?
ከዚህም ይበልጣል እንጂ ብትሉ አይገርመኝም፡፡ የተመኘውን ለማሳካት፤ በአካልና በብልሃት የአቅሙን ያህል በብርቱ ተግቷል፡፡ ግን ተጨማሪ ብቃት ያስፈልገዋል፡፡ ለዛሬ አልተሳካለትም፡፡ ለጊዜው ያሳዝናል፡፡ግን ዘወትር የሚያጋጥም ጉዳይ ነው፡፡
የተመኘነውንነገር ሁሉ፣ ወዲያውኑ ለመጨበጥ በቂ ዝግጅትና አቅም ዛሬውኑ ላይኖረን ይችላል። አይኖረንም ማለት ግን አይደለም። ነገ ሌላ ቀን ነው፡፡ ብልሃትና ብቃት ማሳደግ ይችላል። ግን ጊዜ ይጠይቃል። ቢያበሳጨውም፤ አንጀቱን ቢያሳርረውም፤… ነገሩ የዓለም ፍፃሜ የሕይወት መጨረሻ አይደለም። ተስፋ ለዘላለሙ የጨለመበት ማንነት የተዋረደበት ምፅዓት አይደለም ብሎ ራሱን ማፅናት፤ ደጋግሞም ራሱን ማጽናናት አይችልም? ይችል ነበር፡፡
ግን፤ ለእውነታ የታመነ፤ በአእምሮው የተማመነ ኩሩ ማንነቱን የሚበክልና የሚያዋርድ ማመካኛና ማዘናጊያ ሰበብን መረጠ፡፡
በአካል ፊት ለፊት ያየውን እውነታ መካድ፤ በትክክል ግንዛቤ መጨበጥ የሚችል አእምሮውን ማስካድ፤… ራሱን መዋሸትና መሸወድ፤… ይሄ ነው ትልቁ ኪሳራ፡፡ ቀሽም የሸወዳ መንገድ፤… ከእውነት ጋር መጣላትን ራስን አርክሶ ማጣጣልን ያመጣል፡፡
እንደዚያ የጎመዠለትና ተሟሟተለት ጣፋጭ ፍሬ፤ ከእጁ አልገባ ሲለው፣ ጣፋጩን ፍሬ መራራ ነው ብሎ ያጣጣለ ይመስላል። ግን፣ ራሱን እንደ ሕፃን የማታለል ቀሽም ሙከራው ፈገግ ያሰኛል።
በእርግጥ፣ ያልተሳኩ አላማዎችን የማናናቅና በውሸት ራስን የማጽናናት ሙከራ ብቻ አይደለም የብዙ ሰው ስህተት።
ለተሳኩ አላማዎችና ለተጨበጡ ፍሬዎች በቂ ክብር አለመስጠትና በጥንቃቄ አለመጠበቅም የተለመደ ስህተት ነው።
በእጅ ያለ ወርቅ ተብሎ የለ። “በእጅ ያለ ወርቅ”… ምን? ውድና ብርቅ መሆኑን ለመግለጽ ያሰበ ይመስላል አጀማመሩ።
ነገር ግን፣ በእጥፋት ሊያስቀይሰን ነው ተዘጋጀው። በእጅ ያለ ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል ይለናል።
 በእርግጥ፣ ባህሩን ሞልተው ከሚተራመሱ የአሳ መንጋዎች ይልቅ፣ አጥምደው የያዙት አንድ አሳ ይሻላል ብሎም ይነግረናል። በውቅያኖሱ ሚሊዮን አሳዎች ሲጎመዡ፣ በእጅዎ የገባው አሳ ቢያመልጣቸው፣ ጦም ማደር ነው።
ነገር ግን የያዝከውን ብቻ ይዘህ ባለህበት ቁም ማለት አይደለም። “እል - ልፍ” ሲሉ፤ “እልፍ”  ይገኛል ይለናል - ሌላኛው ብሒል፡፡
“ያልተገላበጠ ያርራል” የሚልም አለ፡፡ ግን ደግሞ፣
“ከወደቁ መንፈራገጥ፤ ለመላላጥ ነው” ብሎም ይጨምርልናል፡፡
“እዩኝ እዩኝ ማለት፤ሸሽጉኝ ደብቁኝ ያመጣል” ብሎ አርፈን እንድንቀመጥም ይነግረናል።
“ደፋርና ጭስ፤መውጪያ አያጣም”፤… ብሎ ደግሞ ከድንዛዜ ቀስቅሶ ያስነሳናል፡፡
ደፋርን ከጭስ ጋር አዛምዶ ሲያመጣ፣… ለበጎ ሳይሆን ለቤተሰቡ እንባ ነው ለማለት ያሰበ ሊመስል ይችላል። ያው፣ ባልተጠበቀ አቅጣጫ ታጥፎ ሄዷል። ግን፣… እውነትም አሰኝቶ ነው። መላ ፈልጉ ይለናል።

Read 7929 times