Monday, 28 November 2022 16:50

«ነፋስ ነው ወዳጄ»

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(0 votes)

 ይሄ በስጋ ሳይሆን በነፍስ ስለተሰቀለች፣ በደስታ ሳይሆን በመከራ ስለተፈተነች፣ በሳቅ ሳይሆን በእንባ ስለታጠበች እንስት ነው። ፉካውን ከፍታ አመታትን አንድ ሰው ስላማተረች፣ በሯን ከፍታ “ይመጣል” ን  ለአመታት ስለወጠነች ... ፍቅሯን ዓለም ላይ ዘርታ አመድ ስለአፈሰች... ስለዚያች እኔ ... ስለዚያች የፅልመት ገላ ነው። ስለዚያች ስለ ደረቀች አበባ... ስለዚያች ... ዓለም ስለረሳት... ዓለምንም ስለረሳች ነፍስ ነው።
ስለዚያች የሴትነት እድሜዋን በተስፋ ስለቀየረች፣ ሻማዋን ተማምና የህይወቷን  ፀሃይ  ስላጨለመች.... ማተቧን በጥሳ .እግዜር ላይ ቂም ስለቋጠረች ስለዚያች እኔ...
“በፍቅር የምለመልም በጥላቻ የምደርቅ የህይወት አበባ ነኝ” ስለምትል...
ግንባሬ ላይ ተሸብሽበው የቀሩ ቆዳዎቼ ገድሌን በስውር የከተቡ የህይወቴ ድርሳን ናቸው። እውነተኛ ገድል ግንባር ላይ እንጂ ቅጠል ላይ አይፃፍም...  የሰው ልጅ ጀብዱ ጦርሜዳ ሳይሆን ግንባር እና ልብ ላይ ነው ያለው። ....
ዓለምን መርሳት፣ ተድላን መሰረዝ...ህይወትን መደለል  እችል ይሆናል። ለሞተው ሳቄ እዝን ተቀምጬ አላውቅ...ግድም አልሰጠኝ ይሆናል። ላለፈው ሴትነቴ... አፈር ለለበሰው ፍቅሬ ዝም እንጂ ምን እላለሁ?  የማልረሳው፣ የማልዘነጋው... ከህይወቴ የተጣባ ክስተት በዚያን ዕለት ተመለከትኩ።  ዘላለም የተፀነሰው በዚያች ዕለት ማህፀን ውስጥ ነው።  
እደነግጣለሁ። እፈራለሁ።
 ይሄ ስለ ትላንት ፣ ስለ ትዝታ፣ ስለ አላፊው...ዓይነ እርግባችንን ስለገለጠው እውነት ነው።  ስለተገፈፈ ክንብንባችን፣ ስለጋረድነው ስቃያችን... በቁማችን ስለተበላው እዝናችን ነው። ይሄ ብቻችንን ስለ አነባነው እንባ ነው።
ይሄ ስለ ሞተው ፍቅራችን የወረደ ሙሾ ነው።
ይሄ እድሜዬን ሙሉ ስለ ደረብኩት የህመም በርኖስ ነው።
ይሄ ተበድዬ ስላልጠየኩት ፍትህ ነው።
ተገፍቻለሁ... እረክሻለሁ...በክህደት ዘገር ጎኔ ተወግቷል... “አባቴ አባቴ ለምን ተውከኝ” ከማለት ውጪ ግን ምላሴ ቃል አይናገርም።
ይሄ ህሊና ብቻ ስለሚዳኘው ፍርድ ነው።
...
እንዲህ ነበር የሆነው።
የሱቢ ፀሃይ በበራችን መቃን በኩል አጮልቃ ታየናለች። አጠገቤ ተኝቷል።  “ምን ሆንኩ” እያለ ሲያንባርቅ ልቤ ልትወጣ ደረሰች። በቅፅበት አካሉ በድን ሆኗል። መንቀሳቀስ አይችልም። ምላሱ ብቻ ነች የምትሰራው።
ደነገጥኩ። ጮህኩኝ። ጎረቤት ተሰበሰበ። ተጋግዘን ሀኪም ቤት ወሰድነው።
ሀኪሞች ውስብስብ ነገር አወሩ። ፓራላይዝ እንደሆነ፣ ህክምና እንደሚደረገለት ለፈፉ። አልጋ መያዝ ቢገባውም በአልጋ እጦት ምክንያት እንድዳልተቻለ ተናገሩ። የጨለመ ፊቱ በተስፋ ፀዳል ሲፈካ ተመለከትኩ። ቤት አምጥተን አልጋው ላይ አስተኛነው። በዚህ ጊዜ ባርያ ልሆንለት፣ ቆሻሻውን ልጠርግ... አንዴም ፊቴን ላላዞርበት ለእራሴ ቃል ገባሁ።
ቃል የእምነት እዳ ነው ይላል ባለቅኔው!
ነገር ግን ጤናው ለውጣ ሳያመጣ አመታት አለፉ። ደከምኩ፣ ጎበጥኩ...
ቢሆንም ቢሆንም...  ቃል የእምነት እዳ ነው።
የሽንቱንና የሰገራውን ጠረን ችዬ አጠገቡ ቆምኩ። መስቀሉን ተሸከምኩ። ወላጆቹ ግን “ምን ተስፋ አለው” በሚል አይነት አይተውት ጠፉ። እላዩ ላይ ሲፀዳዳ... (መቆጣጠር አይችልም ነበር) እህቱ “እፍፍ” ብላ ተነስታ ስትወጣ አይቶ አንሶላ ተከናንቦ ሲያነባ ሰማሁ።
ደረቴ ላይ ጭንቅላቱን አስተኝቼ እንዲህ አልኩት:-
“ታመህ አይደለም ብትሞት እንኳ መቃብርህ ውስጥ እገኛለሁ”
“እንኳን የተፀዳዳህበት መጥፎ ጠረን፣ ለአመታት የቆየ የሬሳህ ጠረን ለእኔ ናትራን ነው።”
አምርሮ ማልቀስ ጀመረ!
“የአይጥ መርዝ ምግብ ውስጥ አድርገሽ ስጪኝና ተገላገይ” አለኝ።
“ግን መርዝ እንዳደረግሽበት እንዳትነግሪኝ። ምክንያቱም ሞትን እፈራለሁ”
“የኔ ጌታ” አቅፌው ተንሰቅስቄ አነባሁ...
እለት እለት ... እሱን ማገላበጥ አድካሚ ነበር። ለሚወዱት፣ ላፈቀሩት ግን ይህቺ ድርጊት ኢምንት ነች። ፍቅር የማይችለው መከራ፣ የማይታገሰው ስቃይ አልነበረም። ህይወቴን ለሰጠሁት ባሌ ይሄ ምንድነው?
ሁሉም ሰዎች ሲሸሹን አየሁ። ሃዘን ጡንቻ እያወጣ፣ እየበረታ እየደለበ መጣ።
ስንተኛ መፅሃፍ አነብለታለሁ። እንቅልፍ ሲወስደው ግን ስለ ህመሙ፣ ስለ ስቃዩ ሳነባ አድራለሁ። የዓይኔን መቅላት ሲጠይቀኝ እንቅልፍ በማጣት እንደሆነ ነግሬ አሳምነው ነበር።
በዚህ መሃል ውጪ ሄዶ መታከም እንዳለበት ከሀኪሞች ሰማን። የጠየቁን ብዙ ብር ነበር። በእኔ ስም ያለውን ቤት ሸጥኩ። ገጠር አባቴ ያወረሰኝን  መሬት ሸጥኩ። ወርቆቼን... ያለኝን ሁሉ ሸጥኩ። ጀርባ የሰጠዃቸውን  የዘመዶቼን ደጅ ጠናሁ። ለመንኩ... ክብሬን ሳልል... ገንዘብ ፈለጋ ባዘንኩ... ይሄን ሁሉ ሳደርግ ቤተሰቦቹ...”ተስፋ አለው ብለሽ ነው ሰርኬ” ከሚል ነገር ውጪ አልረዱኝም።
ተሳክቶ አብሮት የሚሄድ አስታማሚ ሲጠየቅ፣ በህመሙ  የተፀየፈችው እህቱ እኔ ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለሁ አለች። መዳኑን ተስፋ አድርጌ ሸኘሁት። በዚህ ጊዜ ያለች ሰርክአዲስ አሁን ካለችው ሰርክአዲስ ፍፁም ትለያለች። ያቺኛዋ ተስፋ የሞላት፣ ተድላ የናፈቃት መከራዋን በነገ ህልም የምትቋቋም ነበረች። ግን...
ከሄደ አንዴ ደውሎ መድረሱን ነገረኝ። ከዚያ ድምፁ ጠፋ። ቤተሰቦቹን ጠየኩ... ምንም መልስ የለም።
ቀናት ቀናትን  እየወለዱ ሄዱ። አመት ሊደፍን ኩርማኗ ጷግሜ ብቻ ቀረች። ፉካዬን እከፍታለሁ... እሱን አማትራለሁ...መልኩን አልማለሁ፣ ቆሞ መሄዱን ተስፋ አደርጋለሁ...በሩን እከፍታለሁ... በጭለማ ውስጥ ጥላውን አያለሁ፣ ኮቴው ይሰማኛል። ደርሷል እላለሁ። ... እንባዬ ይቆማል... ሌሊት ሊንቀዠቀዠቅ መዓልት ይቆማል።
ብቻ ተስፋ እህል ሆኖ አኖረኝ...
ሁለተኛ ዓመት ሊያልቅ ክረምት ብቻ ቀረ።
አሁንም ፉካዬን እከፍታለሁ። እሱን አማትራለሁ... ሲሄድ ያስቀረሁትን የሸሚዙን ጠረን ሌሊቱን ሙሉ እምጋለሁ... አነባለሁ...እግዜርን እጨቀጭቃለሁ። ልየው እላለሁ። ሳቁ ትዝ ይለኛል።
በጭለማ ውስጥ ጥላውን አያለሁ። ድምፁ ይሰማኛል። “ደርሻለሁ” የሚል አስገምጋሚ ድምፁ ይሰማኛል። ይሄኔ በሩን እከፍታለሁ። ሳይንኳኳ ማን ነው እላለሁ። የማልክለትን ደብዳቤ እፅፋለሁ፤
“እንዳልሞትብህ ቶሎ ና...እንዳልጠፋብህ ቶሎ ና...እባክህ መጥተህ እንባዬ ይቁም...ስቃዬ ይብቃ እስኪ...”
መደምደሚያ ቃላቴ ናቸው።
አራተኛ አመት ...
አምስተኛ አመት...
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ነፍሴም፣ መልኬም እየከሰመ መጣ። መስታወት ፊት ቆሜ እራሴን አየሁ። ቅላቴ ወዴት አገር ሸሸ? ሳቄን ማን ገደለው? ቆዳዬ እንዴት እንደ ባልቴት ተሸበሸበ? ገና ሰላሳ መጀመርያ ነኝ እኮ...ላብ ላብ እስክሸት እንዴት እራሴን ጣልኩ? ለምን እረዥም ቀሚስ ለበስኩ? ለምንስ ነው ዓይኖቼ ደም የለበሱት? ምን  አጋጥሞኝ ነው እንዲህ የሆንኩት... ተስፋ ነው ያቆመኝ... ፈጣሪስ ምነው እረሳኝ...,
ሴት ነኝ እኮ...
እግሬን ሳልታጠብ እስከ ቆሻሻዬ አልጋ ላይ የመውጣት ግድ የለሽነት ....
ጣር የበዛባቸው አመታት
ተስፋ ከቀቢጸ ተስፋ ጋር ተቀይጦ... የሚላገድበት ዘመን
ብቸኝነት እንደ አውሬ ሊበላኝ አፉን የከፈተበት ዘመን
ፍቅሬን የመናፈቅ ሰቀቀን...
አመታት...ዘመን...
በዚህ መሃል አንደኛው አበዳሪዬ መጣ። አብሯ አደጌ ነበር በእርግጥ። ሲያየኝ ደነገጠ። ተቀምጦ አፍታ እንደ ቆየ:-
“ሰርኬ...ያበደርኩሽን ገንዘብ ፈልጌ ነበር” እያለ ተቅለሰለሰ...
“ቆይ እስቲ ይምጣና ሰርተን እንከፍላለን። እኔ እንኳን በቤተሰቦቼ እርዳታ ነው የምኖረው” አልኩት...
“አዝናለሁ በጣም...”
“ለምኑ?”
“ድኖ መምጣቱን አታውቂም እንዴ? እንዳገባስ?”
ምንድነው የምሰማው? ብዥ አለብኝ... ቢጫና ሃምራዊ ቀለም አይኔ ላይ ቡጊ  ደነሱ...ደስታና ሃዘን... ፍቅርና ክህደት... ምላሳቸውን እያወጡ አላገጡ... ሲኦል ገነት አጠገብ የተሰራች ዳስ መሆኗ ታየኝ ደግሞ.... ልነሳ ፈለኩ ግን አልቻልኩም። ህልም ላይ ሆኜ እንድቀሰቀስ ተመኘሁ። አልቻልንም እንጂ ስንት በህልም የምንለውጣቸው እውነቶች ነበሩን። አቃተን እንጂ የጨው አምድ ሆነው  እንዲቀሩ የምንሻቸው ትላንቶች አሉን።
አላለቀስኩም...በረታሁ...
“የት እንደሚኖር  ታውቃለህ?” የሞት  ጣር ያሰማው ድምፅ ነበር።
አድራሻውን ፅፎ ሰጠኝና ሄደ።
በሩ ላይ ሲደርስ፣ ቆሞ እንዲህ አለኝ:- “ከተዘረጋው ሰማይ በላይ ሃዘንሽ ከብዶ ታየኝ”
ይሄን ሰዓት እኔ ደስታ ከክህደት ህመም ጋር ተቀላቅሎ ሊያስጮኸኝ ደርሷል።
ልሂድ ልቅር? ልየው ወይስ... ምን...ምን ፍለጋ ነው የምሄደው? አይፈልገኝም እኮ... ታድያ የችግር ጊዜ ወዳጅ ታሞ ሲድን አቅፎ እንኳን ለዚህ አበቃ አይባልም እንዴ? የመገፋት ህመሜን ብደብቅ ከአመታት በኋላ የመጣ ደስታዬን እንኳን ልኑረው እንጂ!
ፍቅሩ በውለታ እስር ቤት እንዳይገኝ ፈልጓል። ውለታዬን ብሎ ከሚመጣ... ግን ይሄ የሚገ’ባኝ ሴት ነኝ? አልወቅሰውም። ላሳለፍኳቸው የስቃይ አመታት፣ ለኖርኳቸው የእንባ ዘመናት... የተሰማኝ ብርታት እንጂ ቁጭት አይደለም።
መዳኑን ብቻ አሳይቶኝ ቢርቀኝ እኮ ህመም ይቀንሳል? ፉካዉን ከፍቼ እሱን የማተርኩባቸው አመታት ዘበት ብቻ ናቸው?  ጥላውን ያየሁበት... ድምፁን የሰማሁበት... አመታት በቅዠት የተባዙ እብደት ብቻ ነበሩ? ስለ እሱ የመከራን መስቀል መሸከሜ ጅልነት ብቻ ነው? ማቆሚያ የሌላቸው እነዚያ ሁሉ እንባዎችስ ያለ ምክንያት ፈሰሱ? ስለምን የፍቅር ሾተላይነት ተጣባኝ? ስለሌላ አይደለ። ስለመዳኑ!  የመከራዬ መስቀል በእጥፍ ስለመቅለሉ ነው!  ስለ ሌላ አይደለም። የምሄደው ስለመዳኑ ብቻ  ነው።
እንባዬ ገንፍሎ ሲወርድ ጉንጬን ለበለበኝ። የሴት ልጅ እንባ እሳት ነው ለካ።
* * *
ይኖርበታል የተባለው ቤት ደረስኩ። አንኳኳሁ። ጠይም ልጅ ከፈተች። እሱን ጠየኳት። ልትጠራልኝ  ወደ ውስጥ ገባች።
ፈራሁ! ለዓመታት ያቀፍኩትን ባሌን ለማየት ለምን እፈራለሁ? ሳጥናኤል እሳት ይዞ እንኳን ቢመጣ አልሸሽም።
መጣ። ዓይኖቹ በድንጋጤ ፈጠጡ።  አየሁት፣  አምሮበታል...  ቀልቷል... ወፍሯል። ተጠምጥሜ አቀፍኩት።
እያመናጨቀ ገፋኝ። በዚህች ቅፅበት በግዴታ ከወደዱት ገላ የመላቀቅ ህመም ተሰማኝ። ለሁለተኛ ጊዜ ላቅፈው ተጠጋሁት።
“ያምሻል እንዴ” እያለ ሸሸ...
“ስለሌላ አይደለም። ስለመዳንህ እኮ ነው።”
እጄን እየጎተተ  በአቅራቢያው የነበረ አንድ ግሮሰሪ ይዞኝ ገባ።
“ከራበሽ ብይ” እያለ ሲጮህ ደነገጥኩ።
“ይሄ ስለ ምግብ አይደለም። ስለ መዳንህ ነው።” ግብታዊ ንግግሬ ውስጥ እውነት ነበር። ደጋገምኩት እንዴ? አልታወቀኝም።
ምግብ አጥቼ ሳይሆን በእሱ ናፍቆት እህል አልወርድልሽ ብሎኝ አመታትን  እንዳሳለፍኩ ልንገረው? ድምፁን እንደምሰማ፣  እቅፉ እንደራበኝ፣ ፍቅሩን እንደተጠማሁ ላውጋው እንዴ? ምን ልበለው?
“ሌላ ህይወት ውስጥ ነኝና እኔን መበጥበጥ አቁሚ”
“ይሄ ስለ ፍቅር አይደለም -  ስለ መዳንህ ነው። ደስ ብሎኛል።”
“ገንዘብ ከፈለግሽ እልክልሻለሁ። እዚህ እንዳትደርሺ። ምንድነው የመሰልሽው? ላብ ላብ እየሸተትሽ እንዴት ሰው ላይ ትጠመጠምያለሽ?"
ይሄ ላብ በእሱ ህመም የተቀመመ የተስፋ ግድ የለሽነት እንደሆነ አያውቅም። ለእሱ ቆሞ መራመድ እንደወደቅኩ፣ ለእሱ ጤና እንደታመምኩ፣ ለእሱ ፀዳል ህይወት እንደሸተትኩ አያውቅም። እድሜዬን ለፍቅሩ ጣዖት እንደገበርኩ፣ ለናፍቆቱ እንባዬን እንዳፈሰስኩ፣ ለህልሙ በቁም እንደቃዠሁ አያውቅም። ለሳቁ ሳቄን እንደገደልኩ፣ ለተድላው ድሎቴን እንደሰዋው አያውቅም። በሰገራ ሽታ የታወደ ገላውን አቅፌ ላደርኩ ሴት የላብ ጠረን ቁም ነገሩ ሆነ? ስለ እሱ እራሴን ብጥል፣ ስለ እሱ ጠቁሬ ብከሳ ለምን የሚለኝ ማን ነው?
ሲፀየፈኝ፣ “እወድሃለሁ” ብዬው ተነሳሁ።
እየተራመድኩ እግረኛ መንገድ ላይ እንደ እብድ በቂጤ ቁጭ አልኩ።
ለምን ግን  ፍቅር ሲያልቅ ክህደትና ጥላቻ ወደ ተባሉ ፀሊም  አገሮች ይሸሻል?
ማንም ሰው ሊያነሳኝ አልሞከረም። በተደጋጋሚ እንዲህ እላለሁ፡ “ይሄ ስለ ፍቅር አይደለም። ይሄ  ስለመዳንህ ነው”
ከዚህ በላይ  መቀጠል አልችልም።  ከዚህ በኋላ የቀረው ዝምታ ብቻ ነው። ...
ከዚህ በኋላ የተራመድኩት እያንዳንዱ የህይወት ጉዞዬ ከመኖር በላይ ለሞት ቅርብ ነበር። አንድ ብቸኛ ወዳጅ አገኘሁ። ይሄም ወዳጄ “ነፋስ” ይባል ነበር።


Read 1009 times