Saturday, 03 December 2022 11:56

ሄርቬ ሚልሐድ፤ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በሥራ አመራር መስክ የካበተ ልምድ እንዳላቸው የተነገረላቸው  የ60 ዓመቱ ፈረንሳዊ  ሚስተር ሄርቬ ሚልሐድ፤ ከጥቅምት  2015 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው በካስቴል ግሩፕ መሾማቸው ተገለጸ፡፡
ሚስተር ሚልሐድ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ አህጉሮች በሚገኙ በርካታ አገራት  ከሚሠሩ ዳኖኔ ግሩፕን ከመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ያዳበሩ ሲሆን፤ በዳኖን ግሩፕ ብቻ ለሃያ ዓመታት የኦፕሬሽንስ  ም/ፕሬዚዳንት (WW VP Operations) እንዲሁም  ለአልጀሪያ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው መሥራታቸው ታውቋል፡፡   
በመቀጠልም የl’Européenne d’Embouteillage ዋና ሥራ አስፈፃሚ፣ እንዲሁም የጃፓን መጠጦችና አልኮል ኩባንያ የሳንቶሪ (Suntory Group) አካል የሆነው የኦራጂና ሳንቶሪ ፈራንስ (Orangina Suntory France (OSF) የኦፕሬሽንስ ም/ፕሬዚዳንት (VP Operations) በመሆን  650 ሠራተኞችን ያቀፉ አራት ፋብሪካዎችን እንደመሩ፤  ኩባንያው ለአዲስ አድማስ የላከው መግለጫ ያመለክታል።
ሚስተር  ሚልሐድ የረዥም ጊዜ ዕቅዶችን እንደ አዲስ ነድፈው የተገበሩ፣ ለስኬታማ ሥራ አፈፃፀም፣ የደንበኞች አገልግሎትና ወጪ ተገቢ ትኩረት የሚሰጡ፣ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂዎችን በመተግበር ድርጅቶች የሥራ ቅልጥፍናን ከሠራተኞች ደህንነት  ጋር ባጣጣመ መልኩ አሠራራቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የቻሉ የሥራ መሪ መሆናቸውም ተጠቁሟል፡፡
በሚያዝያ 2010 ዓ.ም ካስቴል ግሩፕን ከተቀላቀሉ በኋላም፣ ሶዲብራን (ኮትዲቯር)፣ ኤስኤቢሲን (ካሜሩን) እና የመካከለኛ አፍሪካውን (Centrafrique) MOCAF በሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ ቆይተዋል ተብሏል፡፡
በቅርቡ ሚስተር ሚልሃድ የካስቴል ማላዊ ሊሚትድ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በመሆን ላለፉት አራት አመታት ያገለገሉ ሲሆን ለድርጅቱ ባከናወኑት ታላቅ ሥራ “ድርጅቱን ከመዘጋት ያዳነ ሥራ አስኪያጅ” የሚል ስያሜ መቀዳጀታቸው ታውቋል፡፡   
በተለያዩ ባህሎች ውስጥ አልፈው ካካበቱት ልምድና ለሠራተኞች ደህንነት እንዲሁም ለማኀበራዊ ኃላፊነት ሥራ ከሚሰጡት ትኩረት አንፃር፣ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፣ የቆየውን የቢጂአይ ኢትዮጵያ ስኬታማ የንግድ ሥራ ጉዞ፣ የኢንዱስትሪ ሰላምና የማህበረሰብ ድጋፍን ባህል አጠናክረው ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
“አዲሱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቢጂአይን የተቀላቀሉበት የአሁኑ ወቅት በንጽጽር እጅግ ምቹ ሊባል የሚችል ነው፤ ከምክንያቶቹም መካከል ዋነኛው በሰሜን ኢትዮጵያ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማብቃቱን ተከተሎ፣ በአገር ደረጃ የሰላም ተስፋ ማንሰራራቱ ሲሆን እንደ ድርጅትም ለዓመታት ሥራ ፈትቶ የቆየው የራያ ቢራ ፋብሪካ ሥራ የሚጀምርበት ዕድል መገኘቱ፤ እንዲሁም  ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ ቢራ ፋብሪካን መግዛቱ፣ ተጠቃሽ ናቸው።” ብሏል ኩባንያው በመግለጫው፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሚስተር ሚልሃድን “እንኳን ደህና መጡ”  በማለት በደስታ መቀበሉን የጠቆመው መግለጫው፤ በዓለም አቀፍ መጠጥ ንግድ ካካበቱት  የረዥም ጊዜ  ዘርፈ-ብዙ ልምድ ለመጠቀም መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ላለፉት 25 አመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ የቆየ ደርጅት ሲሆን መቶ ዓመት ያስቆጠረው የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ ብቁና የተገባ ወራሽ መሆኑ ይታወቃል።

Read 11819 times