Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 October 2012 09:47

የኦባማና የሮምኒ የምርጫ ውጤት በከፊል ይታወቃል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ለኛ ምናችን ነው? ለኢትዮጵያ ይቅርና ለአፍሪካ ጊዜ ያላቸው አይመስሉም
የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ገና ሁለት ሳምንት የሚቀረው ቢሆንም፤ ከወዲሁ ተጋምሷል ማለት ይቻላል። ከግማሽ በላይ የሚሆነው ውጤት ገና ካሁኑ ይታወቃላ። ይህ የሚሆነው፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሁለት ልዩ ባህርያት ስለያዘ ነው።
አንደኛው ባህርይ ያን ያህልም ውስብስብ አይደለም። ዜጎች፤ ከምርጫው እለት በፊት፤ ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ። ለምሳሌ በአዮዋ ግዛት ድምፃቸውን ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት ከሚሊዮን በላይ መራጮች መካከል፣ ግማሽ ያህሉ የድምፅ መስጫ ወረቀት ወስደዋል። ብዙዎቹም፤ ለሚፈልጉት እጩ ድምፅ በመስጠት የምርጫ ወረቀታቸውን እንዳስረከቡ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። ከአዮዋ ግዛት መራጮች መካከል ሲሶ ያህሉ ከወዲሁ ድምፅ ሰጥተዋል።

ሌሎቹ ግዛቶችም መራጮችን ማስተናገድ ጀምረዋል። ለምርጫ ዘመቻ ሲዋከቡና ሲሯሯጡ የሰነበቱት ባራክ ኦባማ በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ቺካጎ ያመሩት፣ ድምፅ ለመስጠት ነው። በዚህም ምክንያት ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ከወዲሁ እየተካሄደ ነው ማለት ይቻላል። እንግዲህ የምርጫው አንዱ ልዩ ባህርይ ይሄ ነው - አስቀድሞ የመምረጥ አሰራር።
በእርግጥ፤ ከምርጫው እለት በፊት ድምፅ የመስጠት አሰራር በሁሉም ግዛቶች ይፈቀዳል ማለት አይደለም። ለምሳሌ በፔንሲልቫኒያ፤ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው ለሚጓዙ ሰዎች ካልሆነ በቀር ከምርጫ እለት በፊት ድምፅ መስጠት አይፈቀድም። በአዮዋና በሌሎች በርካታ ግዛቶች ግን፤ ማንኛውም ሰው አስቀድሞ ድምፅ መስጠት ይችላል። እስካሁን ድምፅ ከሰጡ 350ሺ ገደማ የአዮዋ ነዋሪዎች መካከል ብዙዎቹ ባራክ ኦባማን እንደመረጡ አሶሼት ፕሬስ የዘገበ ሲሆን፤ ኦባማ ግዛቲቱ ውስጥ ማሸነፋቸው እንደማይቀር ይጠቁማል ተብሏል። ኦባማ በአዮዋ ካሸነፉ፤ “6 ድምፅ” ይመዘገብላቸዋል። በምርጫው ለማሸነፍና ፕሬዚዳንት ለመሆን፣ በአጠቃላይ “270 ድምፆችን” ማሰባሰብ ያስፈልጋል። በፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ላይ የምናገኘው ሁለተኛውና ዋነኛው ልዩ ባሕርይ ይሄ ነው።
ዋሺንግተን ዲሲን ጨምሮ 51ዱ የአሜሪካ ግዛቶች፤ ከሞላ ጎደል የህዝብ ብዛታቸውን በተከተለ መንገድ፤ የየራሳቸው የድምፅ ኮታ አላቸው። ለምሳሌ የአዮዋ 6 ነው። የካሊፎርኒያ 55፣ የቴክሳስ 38፣ የፍሎሪዳ 29፣ የኦሃዮ 18፣ የኒውዮርክ 29 ወዘተ። ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚያሸንፍ ተፎካካሪ፣ 55 ድምፅ ይመዘገብለታል። ቴክሳስ ውስጥ የሚያሸንፍ ደግሞ 38 ድምፅ ይመዘገብለታል። የሁሉም ግዛቶች ድምር 538 ስለሆነ፤ አንድ ተወዳዳሪ በምርጫው አሸንፎ ፕሬዚዳንት ለመሆን፤ ቢያንስ 270 ድምፅ ማስመዝገብ ይኖርበታል። የሁለቱ ተፎካካሪዎች የባራክ ኦባማና የሚት ሮምኒ ፍልሚያም፤ እዚህ ቁጥር ላይ ለመድረስ ነው። እስካሁን ድረስም፣ እያንዳንዳቸው ከ200 በላይ ድምፅ አስመዝግበዋል። እንዴት? ገና የምርጫው እለት ሳይደርስ?
በእርግጥም፣ የምርጫው ቀን ተቃረበ እንጂ ገና አልደረሰም። ባለፈው ሰኞ እለት ሶስተኛውን የቴሌቪዥን ክርክር ያጠናቀቁት ባራክ ኦባማና ሚት ሮምኒ፤ ለምርጫው እለት 10 ቀን ይቀራቸዋል። ከአመት በላይ የዘለቀውንና እንደማራቶን የረዘመውን የምርጫ ዘመቻ በቀሩት ቀናት ውስጥ በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ ዙሩን አክርረውታል። ማክረር ሲባል እንዴት? ፉክክሩ ከ8 በማይበልጡ የአሜሪካ ግዛቶች ላይ ብቻ ያጠነጠነ ሆኗል። ለምን በ8 ግዛቶች ብቻ?
ያው፤ የሌሎቹ ግዛቶች የምርጫ ፉክክር ከሞላ ጎደል ያለቀለት ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ፣ በካሊፎርኒያ፣ በኒውዮርክ ወይም በዋሺንግተን ዲሲ ማን እንደሚያሸንፍ ከወዲሁ ይታወቃል። በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ ባራክ ኦባማ ከፍተኛ ተቀባይነት ስላገኙ፤ ሚት ሮምኒን በሰፊ ልዩነት ለመምራት ችለዋል። ሮምኒ ካሊፎርኒያ ውስጥ ሌት ተቀን በምርጫ ዘመቻ ልፎካከር ቢሉ እንኳ፣ ሰፊውን ልዩነት ለማጥበብ ይችሉ እንደሆነ እንጂ መሸነፋቸው አይቀርም። ታዲያ ምን አደከማቸው? በሰፊ ልዩነትም ሆነ በጠባብ ልዩነት መሸነፍ ለውጥ አያመጣም። ካሊፎርኒያ ውስጥ የሚያሸንፍ ተፎካካሪ፤ 55 ድምፅ ይመዘገብለታል፤ የሚሸነፈው ተፎካካሪ ደግሞ ዜሮ። ለዚህም ነው፤ ሚት ሮምኒ ካሊፎርኒያና ዋሺንግተን ዲሲ መሳሰሉ አካባቢዎች ብዙም እንቅስቃሴ የማያደርጉት። እንደሚሸነፉ ያውቁታላ።
በተመሳሳይ ሁኔታ፤ ባራክ ኦባማም እንደቴክሳስና አላባማ፣ ሚዙሪና ሚሲሲፒ በመሳሰሉ ግዛቶች ውስጥ ሚት ሮምኒን ለመፎካከር ብለው ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን አያባክኑም። በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ አብዛኛው መራጭ ሚት ሮምኒን እንደሚደግፍ በግልፅ ይታወቃል። በአንድ ግዛት ውስጥ እንደማታሸንፍ እርግጠኛ ከሆነክ፤ ለምርጫ ዘመቻና ለማስታወቂያ ብዙ ጊዜና ገንዘብ የምታባክንበት ምክንያት አይኖርም። ለዚህም ነው፤ ሰሞኑን በኖርዝ ካሮላይና የኦባማ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ የጀመረው - ሮምኒ እንደሚያሸንፉ ግልፅ እየሆነ ስለመጣ። ሮምኒ ደግሞ፣ ከሚቺጋንና ከፔንሲልቫንያ እያፈገፈጉ እንደሆነ ብሉምበርግ ዘግቧል።
በአጭሩ፤ እስካሁን በ43 የአሜሪካ ግዛቶች፤ ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ምን አይነት ውጤት እንደሚኖረው ከሞላ ጎደል ይታወቃል። በቀሪዎቹ 8 ግዛቶች ግን፤ ኦባማና ሮምኒ በመራጮች ዘንድ ያላቸው ድጋፍ ተቀራራቢ ነው። የምርጫው ጠቅላላ ውጤት ወዴየትኛው ተፎካካሪ እንደሚያጋድል የሚለይለትም በእነዚህ የመፎካከሪያ ግዛቶች ውስጥ ነው።
የመፎካከሪያዎቹ ግዛቶች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ፤ የተፎካካሪዎቹን እንቅስቃሴ ማየት ብቻ ይበቃል። ባራክ ኦባማ ሮቡዕ እለት በጀመሩት የ48 ሰዓት ያላቋረጠ የምርጫ ዘመቻ ስድስት ግዛቶችን አካልለዋል ... አዮዋ፣ ኔቫዳ፣ ኮሎራዶ፣ ፍሎሪዳ፣ ቨርጂኒያና ኦሃዮ። ሌሎቹ ሁለት የመፎካከሪያ ግዛቶች፣ ኒው ሃምፕሻዬርና ዊስኮንሲን ናቸው። ለነገሩ ፔንሲልቫንያም የመፎካከሪያ ግዛት እንደሆነች ትታሰብ ነበር። ነገር ግን፤ ግዛቲቱ ውስጥ ከመራጮች የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ሚት ሮምኒን በ5 ነጥብ እየመሩ የሚገኙት ባራክ ኦባማ ማሸነፋቸው እንደማይቀር ተገምቷል። በሰፊ ልዩነትም ሆነ በጠባብ ልዩነት ማሸነፍ ልዩነት የለውም። በፔንሲልቫንያ ያሸነፈ ተወዳዳሪ 20 ድምፅ ያገኛል። በተቃራኒው፣ በኖርዝ ካሮላይና የሚት ሮምኒ ብልጫ ከቀን ወደ ቀን እየሰፋ ወደ ስድስት ነጥብ እየተጠጋ ስለሆነ፤ በግዛቲቱ ውስጥ አሸናፊነት እንደሚያገኙ ይጠበቃል። ካሸነፉም 15 ድምፅ ያገኛሉ።
እንግዲህ እስካሁን በ43 ግዛቶች ማን እንደሚያሸንፍ ስለሚታወቅ፤ ለእያንዳንዱ ግዛት የተመደበውን የድምፅ ኮታ በመደመር ኦባማና ሮምኒ ምን ያህል ድምፅ እንደሚያገኙ ማወቅ ይቻላል ማለት ነው። ካሊፎርኒያና ማሳቹሴትስ፣ ኤሎኖይና ኒውዮርክ በመሳሰሉ 20 ግዛቶች ከፍተኛ ተቀባይነት የያዙት ኦባማ፣ የግዛቶቹን ሙሉ ድምፅ ይወስዳሉ። በድምር ኦባማ የሚያስመዘግቡት ድምፅ 243 ይደርሳል። በሌሎች 23 ግዛቶች ደግሞ ሚት ሮምኒ ከፍተኛ ተቀባይነት ይዘዋል። ሮምኒ በእነዚህ ግዛቶች ማሸነፋቸው ስለማይቀር፤ ከእነዚህ ግዛቶች የሚያገኙት ድምፅ ሲደመር 206 ይሆናል። በኮሎራዶና በፍሎሪዳ የተወሰነ ያህል ብልጫ እያሳዩ ስለሆነ፤ በሁለቱ ግዛቶችም ሚት ሮምኒ ያሸንፋሉ ብለን ብናስብ፤ የሚያስመዘግቡት ድምፅ 244 ይሆናል። ባራክ ኦባማ 243 ድምፅ፣ ሚት ሮምኒ 244 ድምፅ ሆነ ማለት ነው።
ምርጫው የዚህን ያህል ተቀራራቢ ነው። አንገት ለአንገት ተያይዘዋል የሚባለውም በዚህ ምክንያት ነው። በአሸናፊነት ለመውጣት 26 ወይም 27 ተጨማሪ ድምፅ ያስፈልጋቸዋል። ቀሪዎቹ ወሳኝ ድምፆች የሚገኙት ከአራት ግዛቶች ይሆናል - የኦሃዮ 18፣ የቨርጂኒያ 13፣ የዊስኮንሲን 10፣ የአዮዋ 6 ድምፅ። ኦሃዮን ያሸነፈ ተፎካካሪ ምን ያህል ፕሬዚዳንት የመሆን እድሉ ምን ያህል እንደሚጨምር አስቡት። በኦሃዮ ደግሞ ባራክ ኦባማ በጣም ጠባብ በሆነ ልዩነት እየመሩ ነው - ከግዛቲቱ ነዋሪዎች የተሰበሰቡ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱት። የቀጣዮቹ ቀናት የተፎካካሪዎቹ ፍልሚያ በእነዚህ ግዛቶች ላይ ያተኮረ ይሆናል።

የሆነስ ሆነና፣ ለኛ ምናችን ነው?
የአሜሪካ ምርጫ ለኛ ምናችን ነው የሚለው ጥያቄ ዘንድሮም መነሳቱ አልቀረም። በእርግጥም፤ በቀጥታ ከታየ ብዙም ለውጥ የሚያመጣልን አይደለም። የዛሬ አራት አመት ኦባማ የተመረጡ ጊዜ፣ “አፍሪካ አለፈላት” እያሉ አፋቸውን ሞልተው የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። እንዲያውም፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያ ላይም ለውጥ ያመጣሉ ሲባል እንደነበር ታስታውሱ ይሆናል።
በተለይ አሜሪካ ውስጥ የሚገኙና ኢህአዴግን የሚቃወሙ ፓርቲዎች በኦባማ ላይ ትልቅ ተስፋ ነበራቸው። ኦባማ ስልጣን በያዙ ማግስት፤ ሳይውሉ ሳያድሩ ኢህአዴግን ወጥረው እንደሚይዙ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነትና መብት እንዲከበር ተፅእኖ እንደሚያሳድሩ ሲነገር ሰምተናል። በቃ፣ “ኢህአዴግ ጉዱ ፈላ” ተብሎ ነበር። በተግባር ግን በአራቱም አመታት፣ ኢህአዴግን የሚያስደነግጥ አንድም የኦባማ ኮሽታ አልሰማንም።
ለነገሩ፤ ኦባማ ከኢህአዴግ ጋር እንደማይጣሉ፣ ከነጭራሹም ወቀሳና ትችት እንደማይሰነዝሩ ከመነሻው መገመት ይቻል ነበር። ከፖለቲካ ነፃነትና መብት በፊት፤ በቅድሚያ የኢኮኖሚ ጉዳይ ትኩረት ማግኘት አለበት የሚል አዝማሚያ የያዙት ኦባማ፤ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ ድሃ አገራት ላይ፣ “የፖለቲካ ነፃነትና መብት ይከበር” ብሎ ጫና ማሳደርም ሆነ ትችት መዘንዘር ውጤት ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም። እንዲያውም፤ በነፃነትና በመብት ጉዳይ ዙሪያ፤ እንደ ኦባማ ከመሳሰሉት የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ይልቅ፤ እንደ ሮምኒ የመሳሰሉ የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ጠንካራ አቋም ይታይባቸዋል።
እንዲያም ሆኖ፤ ሚት ሮምኒ ቢመረጡ አፍሪካ ውስጥ ወይም ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ነፃነትና መብት እንዲከበር ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገታሉ ማለት አይደለም። ምክንያቱም ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ትኩረት የሚሰጡበት በቂ ጊዜም ሆነ መፈናፈኛ የላቸው። አብዛኞቹ የአሜሪካ ፖለቲከኞች፤ በአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ ላይ ተጠምደዋል። የአገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ እንቅልፍ ነስቷቸዋል። 16 ትሪሊዮን የደረሰው የመንግስት እዳ ራስ ምታት ሆኖባቸዋል። እናም፤ ቢጨነቁ ቢጨነቁ፤ ስለ ቻይናና ራሺያ፤ ስለ ኢራንና ሊቢያ፤ ስለ ብራዚልና ኮሎምቢያ፤ ስለ አውሮፓና ጃፓን እንጂ፤ ስለ ኢትዮጵያ የሚያስቡበትና የሚጨነቁበት ጊዜ የላቸውም።
ሰኞ እለት የተካሄደው፣ የሚት ሮምኒና የባራክ ኦባማ ሶስተኛ ዙር የቴሌቪዥን ክርክር ጥሩ ማሳያ ነው። ክርክሩ ሙሉ ለሙሉ በውጭ ጉዳይ (በአለማቀፍ ጉዳይ) ዙሪያ ያተኮረ ነው ቢባብልም፣ የአፍሪካ ጉዳይ በወጉ ይህል እንኳ አልተነሳም። በ90 ደቂቃው ክርክር ውስጥ፤ የአፍሪካ ስም የተጠቀሰው አንዴ ብቻ ነው - ለዚያውም እግረመንገድ። ከኤስያ፣ ከአውሮፓና ከአፍሪካ ጋር የምናካሂደው ወታደራዊ ትብብርና የመረጃ ልውውጥ ጠንካራ ነው በማለት ተናግረዋል ኦባማ። በቃ፤ ከዚህ ውጭ የአፍሪካ ጉዳይ አልተነሳም።
በሌሎች አገራት ስላለው የፖለቲካ መብትና ነፃነት በተመለከተም አንድ ጊዜ ብቻ በሚት ሮምኒ ተነስቷል። ለሰዎች ነፃነት መከበር ድጋፍ መስጠት አለብን ያሉት ሚት ሮምኒ፤ አሜሪካ በሌሎች አገራት ላይ ገናና አልሆነችም፤ እንዲያም ሌሎች አገራትን ከአምባገነኖች ነፃ አውጥታለች ብለዋል። በቃ፤ ከዚህ ውጭ ስለ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ ስላለው የነፃነት እጦትም አልተወሳም። ከዚህ የምንገነዘበው ግልፅ እውነት ቢኖር፤ ባራክ ኦባማ አልያም ሚት ሮምኒ ቢያሸንፉ፤ ዞሮ ዞሮ የአሜሪካ ምርጫ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ላይ የሚያመጣው ቀጥተኛ ለውጥ እንደማይኖር ነው። በቀጥታ ለውጥ አያመጣም ማለት ግን፤ በተዘዋዋሪ አንዳችም የሚያስከትለው ውጤት አይኖርም ማለት አይደለም። አንደኛ፤ የአሜሪካ ምርጫ እንዲሁ ሲታይ መንፈስን ያነቃቃል። ነፃነት የተስፋፋበት ስልጡን ፖለቲካ በተግባር እውን ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ቋሚ ምስክር ነው - በየአራት አመቱ የሚካሄደው የአሜሪካ ምርጫ።
“እኛ አገርስ ለምን እውን አይሆንም?” የሚል ጥያቄና ምኞት ሊያሳድርብን ይችላል፤ ከዚያም ያነሳሳን ይሆናል። ወደፊት በኛም አገር እውል የማይሆንበት ምክንያት የለም። ለምሳሌ ህገመንግስትን ተመልከቱ። በህገመንግስት የመተዳደር አሰራር የተጀመረው በአሜሪካ አይደል? ግን ለሌሎች አገሮችም አርአያ ለመሆን በቅቷል። ዛሬ ህገመንግስት የሌላቸው አገራት ጥቂት ናቸው። የአሜሪካ ነፃ የፖለቲካ ምርጫም እንዲሁ፤ አርአያ ሊሆነን ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ፤ “የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በማስፋፋት የአሜሪካን የኢኮኖሚ ቀውስ እፈታለሁ” የሚሉት ሚት ሮምኒ ካሸነፉ፤ ለኢትዮጵያም ሆነ ለሌሎች አገራት ተጨማሪ አርአያነት ይኖራቸዋል።

Read 2674 times