Saturday, 03 December 2022 12:11

የስፖርት ውድድር፤… ክብሩና ተወዳጅነቱ፤ ውበቱና አሪፍነቱ ምኑ ላይ ነው?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

የሰውን ብቃት የማክበር፣ እያንዳንዱን ሰው እንደየተግባሩ የማድነቅ ብሩህ የቅንነት መንፈስ አለው- የስፖርት ውድድር።
ነገር ግን የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ ማቀጣጠያ፣ የዘረኝነትና የጭፍን እምነት ማራገቢያ፣ የጥላቻ መሳሪያም ያደርጉታል- ቀሽምና ክፉ ሰዎች።
የስፖርት ውድድር፣ ላይ ላዩን ሲያዩት ከስፖርት ጋር የሚዛመድ ይመስላል። በመሰረታዊ ባሕርይና በዓላማ ግን፣ ከስፖርት አጠገብ አናገኘውም። ወደ ጥያቄና መልስ ውድድር ይቀርባል። ከልብ ወለድ ድርሰት በተለይ ከትያትር ጋርደግሞ በጣም ይቀራረባል።
በአንድ በኩል፣ ሳይንስ መማርና ማስተማር አለ። በሌላ በኩል፣ “ሳይንስ ቀመስ ልብወለድ ድርሰት” መጻፍና ማንበብ አለ።
የወንጀል ምርመራ ላይ ያተኮረ ልብወለድ ድርሰት ማሳተም ወይም ገዝቶ ማንበብ፣ የሼርሎክ ሆልምስ  ፊልም መስራትና መመልከት አንድ ነገር ነው። በእውኑ ዓለም ውስጥ የፌደራል ፖሊስ የወንጀል መርማሪ ወይም ተመርማሪ መሆን ደግሞ ሌላ ነው።
የስፖርት ውድድርም የዚህን ያህል ከስፖርት ይለያል። ስፖርት የሳይንስና የእለታዊ ኑሮ ጉዳይ ነው። ስፖርት መስራት፣ እግረ መንገድ ከሰው ጋር ለመተዋወቅና ቀልብ ለመሳብ ሊያገለግል፣ አልያም ሰውን ለማስፈራራትና ለመደባበደብ ሊውል ይችላል። ዋነኛ አላማው ወይም ፋይዳው ግን፣ ለጤና፣ ለአካል ብቃትና ለንቃት የሚስገኘው ጥቅም ነው።
የስፖርት ውድድር ግን፣ እንደ ፊልምና እንደ ትያትር፣… ለትዕይንት የሚፈለግ መንፈሳዊና አዝናኝ መስተንግዶ ነው። የውድድሩ አዘጋጆችና ተወዳዳሪ ስፖርተኞች፣ እንደ ትያትር አዘጋጆችና እንደ ተዋናዮች ናቸው። ስራቸው እንጀራቸው ነው። የሙያ ጥበባቸው የኑሮ መተዳደሪያቸው ነው። ለተመልካች ደግሞ መዝናኛ ወይም መንፈስ አዳሽ ድግስ።
በእርግጥ፣ የስፖርት ውድድርና የኪነጥበብ ቅርርብ ይህ ብቻ አይደለም።
ለሙያተኞቹና ለጥበበኞቹ መተዳደሪያ ስራ መሆኑ፣ ለተመልካችና ለአንባቢ  ደግሞ መንፈሳዊ ድግስ ወይም የመዝናኛ ዝግጅት መሆኑ፣ በአጋጣሚ የተፈጠረ ምስስሎሽ አይደለም።
የስፖርት ወድድርና የኪነጥበብ ድርሰት፣… ሁለቱም ምናባዊ የፈጠራ ውጤቶች ናቸው። ምናባዊ ዓለምን ነው የሚያሳዩን። ተወዳጆቹ የሃሪ ፓተር ልብወለዶች ወይም ቴሪ ጉድ ካይንድ የጻፋቸው ድንቅ ድርሰቶችን አንብቡ። ሕይወት ሰጪ ዕንቁ፣ እና የሐቅ ሰይፍ እያሉ ይተረኩልናል።
የዓለም ዋንጫ ላይ ደግሞ፣ ማጥቃት ላይ ባተኮረ አሰላለፍ በርካታ ግቦች እንደተቆጠሩ ይዘግቡልናል። የጥቃት  ዘመቻው ግን ለጨዋታ ያህል ምናባዊ ጥቃት እንጂ የምር አይደለም። የሐቅ ሰይፍና ሕይወት ሰጪ፣… እንቁ ምናባዊ ናቸው። ነገር ግን፣ እንመሰጥባቸዋለን። “ይሄ ሁሉ፣ ከእውኑ ዓለምና ከዘወትሩ የሰው ሕይወት ጋር አይመሳሰልም” ብለን አንከራከራቸውም።
ዳቦ አይሆንም። ግን ሰው በዳቦ ብቻ አይኖርም።
በመስመር በተከበበ ቦታ ውስጥ፣ አንዷን ኳስ በእግር እየተቀባበሉና እየተነጣጠቁ፣ እያንከባለሉና እየተከተሉ፣ እየተሻሙና እየለጉ መሯሯጥ፣… ከሕይወት ጋር ምን ግንኙነት አለው?
ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ወዴት ሄደ? እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ኳስ ይዞ የመምጣትና ራሱን የመቻል ሃላፊነት የለበትም? በገዛ ንብረቱ ላይ የማዘዝ መብቱስ ወዴት ሄደ? መበዳደርና መገበያየት እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። እንደ ጋራ ንብረት ቆርሶ መካፈል ይሻላል የሚሉስ አይኖሩም?
ለነገሩ፣ ኳስ ከነነፍሷም ሆነ ቁራሽ ኳስ ምን ያደርጋል? አይበላ፣ አይጠጣ፣ አይለበስ ነገር! ስለ እውነተኛው ዓለምና ስለ ሰው ኑሮ እንነጋገር ከተባለ፣ እንደ አመቺነቱ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ፣ በእጅም በእግርም አማርጦና አስተባብሮ መስራት ነው የሚያዋጣው።
የአገር ድንበር፣ የግቢ አጥር፣ የቤተመንግስት በር ከኋላው ሳይኖር፣ በ7.3ሜትር ስፋት በ2.4 ሜትር ቁመት፣ ቋሚና አግዳሚ ብረቶችን ሰርቶ “በር መጠበቅ”፣ ምን ትርጉም አለው? ኳሱ ቢገባ ባይገባ ምን ችግር አለው? እንዲያውም ዋጋ የሚያወጣ ከሆነ፣ ኳስ እየደጋገመ ቢመጣና “የግብ መረብ” ላይ ቢጠራቀም አይሻልም?
ወደ ተፎካካሪ ሜዳ በስልትመሮጥ፣ በፍጥነትና በብልሃት ማጥቃት፣ ተከላካዮቹን አልፎ የግብ ክልሉን ጥሶ፣ ኳስን ወደ ግብ ማስገባት፣… ምንድነው ይሄ? የመሬት ይገባኛል ጥያቄ ነው? ድንበር የማስፋት ዘመቻ ነው? ተከላካዮቹን ጥሶ፣ በረኛውን አልፎ የገባ ኳስ፣… ልዩ የንግስና ዘውድ ነው? የጠላት አገር ቤተመንግስት ውስጥ ገብቶ ዘውድ የጫነ ይመስል እንዲያ መፈንጠዝና መቦረቅስ ምን ይባላል?
አስገራሚው ነገር፣ በምናባዊው ዓለም ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ከመመሰጣችን የተነሳ ይሄን ሁሉ ጥያቄ ከመጤፍ አንቆጥረውም። ጨርሶ አይመጣልንም። እንዲያውም፣ ዋና ጉዳያችን፣… በትክክል ጎል መግባቱ አለመግባቱ፣ አስደናቂነቱና አስደንጋጭነቱ፣ አስደሳችነቱ ወይም አሳዛኝነቱ ነው የሚታየን።
ጭራሽ፣… ኳስ ከመስመር ወጥቷል፣ በእጅ ተነክቷል፣ “ኦፍ-ሳይድ ገብቷል”፣ “ፋውል ሰርቷል” በማለት የምናባዊውን ዓለም ሕጎች እንተነትናለን፤ በየፊናችን ዳኝነት እንሰጣለን።
ኳስ ከመስመር ቢወጣ ይፈነዳል? ፍንጥርጣሪው ሰውን ይጎዳል? በእጅ ቢነኩት ሰውነትን ይመርዛል? ተላላፊ በሽታዎችን ያዛምታል?
በእውኑ ዓለምና በዘወትሩ ሕይወት ውስጥ፣… “ከተፈጥሮ ሕጎች” በተጨማሪ፣ የሥነምግባር መርሆችና የፍትሕ ሕጎች የሕልውና ጉዳይ ናቸው።
 በመሳጭ ምናባዊ ዓለም ውስጥም፣ የቦታ መስመሮችና የጊዜ ወሰኖች፣ የእንቅስቃሴ ሕጎችና ደንቦች  ለውድድር ጨዋታው የሕልውና ጉዳይ ናቸው። በልብወለድ ድርሰት ምናባዊ ዓለም ውስጥም ነገሩ ተመሳሳይ ነው።
ጊዜውንና ቦታውን በ1980ዎቹ በአዲስ አበባ ያደረገ የልብወለድ ድርሰት ውስጥ፣ ሞባይል ስልክና ኢንተርኔት ህልውና አይኖራቸውም። ምናባዊውን የልብወለድ ዓለም ይረብሹታል። 50 ዓመት የኋሊት፣ 50 ዓመት ወደፊት መጓዝ የሚችል የጊዜ መንኮራኩር በምናባዊው የልብወለድ ዓለም ውስጥ ከተካተተ ግን፣… የቀድሞው፣ የዛሬው፣ ወይም ወደፊት ሊፈጠር የሚችል የቴክኖሎጂ ውጤት በትረካው ውስጥ ቢገባ፣… ምናባዊውን ዓለም የሚገነባና የሚያስውብ ሊሆን ይችላል። መሳጭነቱን ያጨምርለታል።
ማሰብና መናገር የሚችሉ እንስሳት የሞሉበት ነው፤ የብዙዎቹ ተረቶች ምናባዊ ዓለም። ዋናው ነገር፣… ምናባዊው ዓለም፣ ቅጡን የተከተለና ለጥበባዊ አላማው የሚፈይድ መሆኑ ላይ ነው።
የስፖርት ውድድር ምናባዊ ዓለምም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። የብቃት ልሕቀትን አጉልቶ የማሳየትና የሰውን መንፈስ የማደስ አላማውን በሚያሳካ መንገድ የተዋቀረ ከሆነ፣ የቦታና የጊዜ መስመሩ፣ የግቡ ዓይነትና መጠኑ፣ የእንቅስቃሴ ሕጎቹና ደንቦቹ፣… እንደ ተፈጥሮ ሕግ፣ እንደ ሥነምግባር መርህና እንደ ፍትሕ ሕጎች መታየት ይኖርባቸዋል - በምናባዊው ዓለም፣ በውድድሩ ሜዳ።
ቅጥ ባለው ዓለም፣ ግብ ያለው፣… “ብቃትን፣ ጥበብን፣ ብርቱ ትጋትን” አጉልቶ የሚያሳይ ፈጠራ ነው- የስፖርት ውድድር።
የስፖርት ውድድር መሰረታዊ ባህርይ፤… ሕግና ሥርዓቱ ላይ ነው የሚሉ አሉ። አንድ ሁለት ዋና ህጎችን ብትቀይሩ፤… የተጫዎቾቹ ቁጥር ከ12 ወደ ሁለት ቢቀነስ፤ ወይም ወደ ሁለት መቶ ቢጨመር፤… የእግር ኳስ የዓለም ዋንጫ ምን ይሆን ነበር?
ኳሷ እንደ ብይ ያነሰች፤ወይም እንደ በርሜል የገዘፈች ብትሆን፤… የሜዳው ስፋት አምስት ሜትር ወይም አምስት መቶ ሜትር ቢሆን… የጎሉ ቁመትና ወርድ አንድ ስንዝር ወይም 50 ሜትር ቢሆን፤… ተጫዋቾች የሚመረጡት ከተመልካቾች በእጣ ቢሆን፤ወይም አሸናፊው ቡድን የሚታወቀው ከጨዋታው በፊት በእጣ ቢሆን፤ ወይም በወረፋ፤ በተራ በተራ፤ በኮታ ቢሆን ኖሮ ሜዳ ላይ ምን አይነት ጨዋታ እንደምናይ አስቡት።
ከጨዋታ በኋላ በኮሚቴ አሸናፊው የሚሰየም፤ በሕዝብ ፍላጎት፤ በሆታና በጭብጨባ ድምቀት፤… በሞባይል የፅሁፍ መልዕክት 2022 ላይ በመላክ ቢሆንስ?
ዋንጫውን በጨረታ ወይም በተጫዋቾች የትምህርት ደረጃ፤… የሚገኝ ቢሆንስ? ወይም ባለፈው አመት ባስቆጠሩት ግብ፤ ወይም በፆታ ተዋፅኦ፤… ወይም ለእርዳታ በለገሱት የገንዘብ መጠን፤ ወይም በፆም በፀሎት፤…
ለተፎካካሪ ቡድን ባሳዩት ሃዘኔታስ? “እኔን!... እኔ ልደፋ” ብሎ ተፎካካሪውን ለማፅናናት በራሱ ግብ ላይ እያስቆጠረ በከፈለው መስዋዕትነት፤ አሸናፊ ቡድን የሚመረጥ ቢሆንስ።
ከተቀናቃኝ ቡድን ስንቶቹን ጠልፎ እንደጣለ፤ በክርን ጎናቸውን እንደነረተ፤ በግንባሩ እየተላተመ የስንቱን አፍንጫ ሰብሮ ምን ያህል ጥርስ እንዳረገፈ፤ የተሰበረ እጅና እግር፤ ክንድና ቅልጥም እየተቆጠረ ሻምፒዮን የሚመረጥ ቢሆንስ?
ብዙ የተሰበረ፤ ክፉኛ የወላለቀ ቡድን ነው አሸናፊ? ወይስ የሰበረና ያወለቀ? በየዓመቱ ይለያያል። በጎዶሎ ዓመት ከሆነ፤… የተሰበረ ቡድን ዋንጫ ይወስዳል። ዘንድሮ ግን 2022 ነው… ሙሉ ቁጥር ነው። የሰበረ ያሸንፋል ማለት ነው። በእርግጥ፤ ይሄ ዳኝነት ትክክል አይደለም። ፍርደ ገምድል ነው። ከባህላችን ጋር አይስማማም። በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ዘንድሮ፤ ሙሉ ቁጥር አይደለም።
ከአገራችን ባሕል ጋር አይሄድም? ባሕል፤ ልማድና ወግ ከስፖርት ውድድር ጋር ምን አገናኘው?
ውድድርን ውድድር የሚያደርገው ሕግና ሥርዓት ነው የሚለውን የመጀመሪያ ሃሳብ አይተናል። አንድ ሁለት ዋና ዋና ህጎችን ወይም ሥርዓቶችን መቀየር፤ የውድድሩን ባህርይ ጨርሶ ሊለወጠውና ከውድድር ተራ ሊያስወጣው እንደሚችልም ተመልክተናል።
ግን፤ አንዱ የውድድር ዓይነት ከሌላው የላቀ ተወዳጅና ተመራጭ እየሆነ ለምን ያገንናል?
የአንደኛው ውድድር ሕግና ሥርዓት ከሌላኛው ይበልጣል? የሕጉ ብዛት፤ የስርዓቱ ዓይነት ነው ልዩነቱ? የሕጉ ጥራትና የሚያስከትለው ቅጣት ነው ብልጫው?
ደግሞስ፤ በአሜሪካ ወይም በእንግሊዝ አገር ተወዳጅ የሆኑ የውድድር አይነቶች፤ ለምን በመላው ዓለም ተመራጭ አልሆኑም? ሕንድና ቻይና፤ ፓኪስታንና ኢንዶኖዢያ፤ ከዓለም ጠቅላላ ሕዝብ ግማሽ ያህሉን የያዙ አገራት ቢሆኑም፤ በዓለማቀፍ የእግር ኳስ መድረክ ድምፃቸው አይሰማም። ሕግና ሥርዓቱ አልጣማቸውም? ተቃውሞ እና ድምፅ አቅርቦ ነው?
ዋናው ነገር ባሕልና ልማድ እንጂ፣ ህግና ሥርዓቱ እንዳልሆነ ለማሳመን እነዚህን ምሳሌዎች ይጠቅሳሉ።
አንዳንዴ የውድድር ሜዳ የብቃት መቅደስ መሆኑ ይቀርና የስድብና የድብድብ ጉራንጉር ይሆናል። የባሕልና የልማድ ነገር!
ትልቁ ቁም ነገር፤ የስፖርት ውድድሮች ፋይዳና ክብር፣ ከታሪክና ከባሕል ጋር መዛመዳቸው፤ ወግና ልማድ መሆናቸው ላይ ነው ይላሉ።
ከአገር አገር፤ ከዘመን ዘመን ብቻ ሳይሆን “ፆታ” ላይም ልዩነት አለ።
በእርግጥም፤ በየአገሩና በየዘመኑ የተለያዩ የስፖርት ውድድሮች መግነናቸውን ስናይ፤…
በሌላ አገር ውስጥ ሰማይ ምድሩን የሚያናውጥ የሚያስፈነድቅ የውድድር ዓይነት ለ5 ደቂቃ የማንታገሰው አሰልቺ ሲሆንብን፤ አንዳች ጣዕም ሰናጣበት፤… የባሕልና የልማድ ጉዳይ ቢሆን ነው ያስብለናል።
የስፖርት ውድድር- የፖለቲካ ማገዶና ጅራፍ።
የስፖርት ውድድር ፋይዳና ተወዳጅነት፤… አገራዊና ፖለቲካዊ አገልግሎቱ ነው ብለው የሚተነትኑና የሚያብራሩ ምሁራን አልጠፉም።
ዛሬ ዛሬማ ብዙ ናቸው። ለነገሩ አዲስ ዲስኩር አይደለም። የስፖርት ውድድርና ስፖርትን የሚያምታቱ በርካታ አባባሎችን መጥቀስ ይቻላል።
“ስፖርት ለወዳጅነት”፤ “ስፖርት ለሰላም”፤ “ስፖርት ለጤና”፤ “አገር ተረካቢ ትውልድን ለመገንባት”፤… ብዙ ተብሏል። ለወንድማማችነት በሚለው ላይ፤ “ለእህትማማችነት” ብለን አለመጨመራችን ቅሬታ ይፈጥር እንደሆነ እንጂ፤ አዲስ አይሆንብንም።
ስፖርት ለአገር ብልፅግና፤ ብቁ ሰራተኛ ኃይል ለማፍራት፤ ለአገር ፍቅርና ለብሔራዊ ኩራት ብለው የሚያስቡም ይኖራሉ።… የቀድሞ ኮሚኒስቶች ደግሞ፤ “ለመደባዊ ንቃተ ህሊና”፤ “ለተደራጀ አብዮታዊ ንቅናቄ፤ ለሕዝባዊ ተሳትፎ” እያሉ መፎክራቸውን ከታሪክ ማንበብ እንችላለን።
በአመዛኙ፤ የቡድን ስፖርቶችን እንጂ፤ የግል ውድድሮችን አይወዱም። የግል ማንነትንና ብቃትን የሚያጣጥል ማናቸውንም ሰበብ ሲያገኙ ይፈነድቃሉ።
የሩጫ ውድድር ላይ ሳይቀር፤ የግል ብቃት ቦታ ባያገኝ ይመኛሉ። “የቡድን ስራ” እያሉ አልፋና ኦሜጋ ያደርጉታል። ያለ ግል ብቃት የቡድን ስራ የሚኖር ያስመስሉታል።
ያው፤ እንደምታውቁት ለብሄር ብሔረሰብ ፖለቲካ ማማሟቂያ ማገዶ እንዲሁም የዘረኝነት ሱስ ማርኪያ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉ ቀሽም ሰዎች ጥቂት አይደሉም።
በብሔረሰብ ወይም በጎሳ የተሰየመ ቡደን ከሌለ፤ “ማንነት” የጣፋባቸው ይመስላቸዋል።
ቡድን ከተሸነፈ፤ ማንነት የተዋረደ ሆኖ ይሰማቸዋል። ሁሉም ነገር፤ የሰው ሕይወት ጭምር ለፖለቲካ ጨዋታ የመገልገያ መሳሪያ የሚመስላቸው፣ የፖለቲካ ተቀናቃኝን ለማጥቃት የተዘጋጀ ጅራፍ ወይም ፖለቲካን የሚያሟሙቅ የመስዋዕት ማገዶ እንዲሆንላቸው ይሻሉ። የስፖርት ጨዋታን፣ የፖለቲካ ጨዋታ መገልገያ ያደርጉታል። እንዲሆን ይመኙታል።
ቀሽም ቢሆን ምርጥ ቢሆን፤ ብትንቁትም ብታከብሩትም፣ ስፖርት ለሆነ ሌላ አላማ የሚሰጠው አገልግሎት ነው ፋይዳው ይላሉ። እንደ መሳሪያ ነው።
ይህን አስተሳሰብ ሲያጦዙት፤… የስፖርት ውድድር ለኃያላን የአገዛዝ መሳሪያ፤ ለድኩማን የአመፅ መሳሪያ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ።
የስፖርት ውድድር የህግና የሥርዓት አስፈላጊነትን፤ ቋሚነትንና አስገዳጅነትን የሚያረጋግጥ መሳሪያ ይሆንላቸዋል ለገዢዎች።
ለጭቁኖች ደግሞ፤ እኩልነትን የሚያጣጥሙበት፤ ጌታ አሸከሩን አስከትሎ የሚራመድበት ሳይሆን፤ ፈጣን እግሮች ቀድመው የመገስገስ እድል የሚያገኙበት ዓለም ነው ይላሉ።
በሌላ አነጋገር፤ የፖለቲካ ድራማ የሚተወንበት መድረክ ነው- የስፖርት ሜዳው።
በአጭሩ፣ አንዳንድ ምሁራን፣ ከሕግና ሥርዓት ጋር ያቆራኙታል Formalism, structuralism በሚል ቅኝት። ከባሕልና ከልማድ ጋር ያቆላልፉታል Constructivism, conventionalism በማለት።
እንደ ፖለቲካዊ መሳሪያ የሚቆጥሩትም አሉ- Functionalism ቦይ ውስጥ አስገብተው።
 ላይ ላዩን ሲያዩዋቸው፤… እያንዳንዱ የአስተሳሰብ ቅኝት በየፊናቸው፤… አንዳች የእውነት ቅርንጫፍ፤ አንዳች የግንዛቤ ገፅታ የያዙ ይመስላሉ።
ግን ደግሞ፣ አንዳች የእውነት ምልክት ያልያዘ ውሸት የለም። አንዳች ትክክለኛ ግንዛቤ የሌለው ጠማማ አስተሳሰብ የለም።
 የእግር ኳስ የግብ ስፋት ወደ አንድ ሜትር ካጠበብነው፤ ምን ያህል እንደሚበላሽ አስቡት። ሕግና ሥርዓቱ የጨዋታውን ምንነት መገንባትና መናድ ይችላል። በእርግጥ የማይመለሱ ጥያቄዎች አሉ። የጨዋታ ጊዜ ወደ 80 ደቂቃ ዝቅ፤ ወደ 100 ደቂቃ ከፍ ቢደረግ፤ ለጨዋታው ሞትና ትንሳኤ አይሆንም። ከአንድ ጎል የተለጋ ኳስ ሌላ ተጫዋች ሳይነካው የተፎካካሪ ጎል ውስጥ ቢገባ፤ አይቆጠርለትም የሚል ህግ ቢወጣ፤ ብዙም ልዩነት አያመጣም።
ሁሉም ሕግና ሥርዓት፤ እኩል ድርሻ የለውም። አንቀፅ ከማብዛትና፤ ነገር ከማንዛዛት ያለፈ ጥሩም ሆነ መጥፎ ለውጥ የማያመጡ አሉ። በሌላ በኩል የወሬ ሰበብ ከመሆን ባሻገር፤ ጨዋታውን የሚደግፍ ወይም ጫና የሚያሳድርበት የህግ ለውጥ ይኖራል።
የጨዋታውን ምንነት የሚገነቡ ባህርይውን የሚቀርፁ መሰረታዊ ሕጎችና ሥርዓቶች ይኖራሉ። የሚያፈርሱና ባህርይውን የሚያጠፉም እንዲሁ።
“ሕግና ሥርዓት” ያለጥርጥር፤ የጨዋታው ሁለመና ውስጥ አለ። ነገር ግን፤ ይሄኛው ሕግ ለጨዋታው አይፈይድም፤… ያኛው ሕግ ጨዋታውን ይበርዛል፤ ይረብሻል፤ ያበላሻል። የወዲያኛው ሕግ፤ የጨዋታውን ጣዕም እያበለፀገ በቀለማት ህብር እያሳመረ፤ እያጣራ፤ እያደመቀ፤ እያሟሟቀ እያቀላጠፈ በቅጡ ያስውባል ብንል አስቡት።
ያደምቃል፤ ያደበዝዛል፤ ያበላሻል፤ ያስውባል የምንለው፤ ምኑን አይተን ምኑን ተገንዝበን ይሆን? አንዱ ሕግ ጠቃሚ ሌላኛው ጎጂ የሚሆነውስ እንዴት ይሆን? ሕግና ሥርዓቱ ነው ወሳኙ ነገር ብለን ብንናገር፤ ለጥያቄዎቹ በቂ መልስ አይሆንልንም።
የስፖርት ወድድር ክብር፣ ከባህልና ከልማድ ጋር የተዋሐደ፤ ከብዙ ሰዎች መንፈስ ውስጥ የሰረፀ መሆኑና አለመሆኑ ነው ቢባል አይገርምም። ከሰፈርና ከትምህርት ቤት እስከ ክለብና ፌደሬሽን፤… ከአገራዊ ምርጥ ቡድን እስከ አህጉርና አለማቀፍ ውድድር፤… ከኳስ እስከ ስታድዮም ግንባታ፤… አዋቂዎች ከሚሰጡት ጊዜ፣ እንዲሁም ከልጆች የዘወትር ተግባርና የወደፊት ምኞት ጋር ያለው ቁርኝት፤… ይሄ ሁሉ በአንድ ዓመት አይደለም በ10 ዓመታትም ተሰርቶ የሚጠናቀቅ አይደለም። የረዥም ጊዜ ውጤት ነው። ባሕልና መንፈስ፤ ልማድና ባህርይ ነው።
 በእርግጥ በእግር ኳስ ባሕል የምትታማ አይደለችም-ኳታር። ነገር ግን የውድድሩ ምንነት አልተለወጠም። ያው እግር ኳስ ነው። ለኳታር የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ከ200 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጓል። በሃሩር በበረሀ፤ የዓለም ዋንጫ አምሮበት እየተካሄደ ነው። ስታድዮሞች ሆቴሎች ተገንብተዋል። ገና ከባሕል ጋር ባይዋሃድም፤ የተመልካችና የአፍቃሪ ቁጥር ብዙ ነው። ስታዲዮም ገብቶ የመመልከት የገንዘብ አቅምም እንደዚያው ሞልቷል።
 ቢሆንም ግን፤ ብራዚል ወይም እንግሊዝ ውስጥ ከሚዘጋጅ የዓለም ዋንጫ ጋር አይስተካከልም። እንደ ትኩሳት እንደ ዓመት በዓል ገና ከወራት በፊት ሕፃን አዋቂውን የሚያንቀጠቅጥ የሚያቅበጠብጥ መንፈስ ያጥለቀልቃቸዋል።
ኳታር ሃያ እጥፍ ወጪ ብታጎርፍም የእንግሊዝና የአርጀንቲና መንፈስን አትፈጥርም። ከባህልና ከልማድ ጋር መስረፅ መዋሃዱ፤ የጨዋታውን ትርጉም ከፍና ዝቅ እንደሚያደርገው አይካድም።
ነገር ግን፤ ምን ሲሆን ነው ከባሕል ጋር የሚዋሃደው? ምን ዓይነት ጨዋታስ በሰፊው የመሰራጨትና የመስረፅ እድል ይኖረዋል?
የጨዋታው ምንነት በዚሁ ሂደት መልኩና ቅርፁ መለወጡ ባይቀርም፤ ከባሕል ጋር ከመዋሐዱ በፊትም፤ ጨዋታው በእውን የነበረ ነው። ስለ ጨዋታው ምንነት ለመናገር፤ የአገር ባሕል እስኪሆን ድረስ መጠበቅ የግድ አይደለም። ከተዋሐደ በኋላ አይደለም የጨዋታ ውድድር የሚሆነው። ህልውነ የሚያገኘው። በተለያየ ባሕል ውስጥም፤ የተለየ የጨዋታ ዓይነት አይሆንም። እግር ኳስ፤ በሁሉም አገር፤… ያው እግር ኳስ ነው።
“የፖለቲካ አገልግሎት” የሚሉት ነገር፤… ከትልልቁ እስከ ትንንሹ ተራ ጉዳይ፤ ከቁም ነገር ሃሳቦች እስከ ስካር ስሜቶች ድረስ፤ አልፍ አእላፍ ተለጣፊና ተቀጥላ ጉዳዮች ከስፖርት ውድድር ጋር መግተልተላቸው አይገርምም። የኳታር መንግስት የዓለም ዋንጫ ለማዘጋጀት ያ ሁሉ ሃብት ማፍሰሱ፤ የፖለቲካ ጨዋታነቱን አስጩኾ ይመሰክራል። ቢሆንም ግን፣…
የስፖርት ክብሩ፣ የሰውን አቅም ማክበር፣ እያዳንዱን ሰው እንደየብቃቱና እንደየተግባሩ የማድነቅ መንፈሳዊ ፋይዳው ነው። መሳጭነቱና መዝናኛነቱም እዚያው ላይ ነው።
ይህን መንፈሳዊ አገልግሎት የሚያደምቁና የሚቆነጁ ነገሮች በጎ ናቸው- ተቀጥላ ነገሮች ቢሆንም።
መንፈሳዊ አገልግሎቱን የሚያደበዝዙና የሚያበላሹ ተለጣፊ ነገሮች ደግሞ ክፉ ናቸው።

Read 10967 times