Saturday, 03 December 2022 12:50

የጡዘት መጋረጃ ሲቀደድ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(4 votes)

 ፊይዶር ደስቶቭስኪ በየትም አገር የገነነ ራሺያዊ ደራሲ ነው፡፡ ደስቶቭስኪ ከሚታወቅባቸው ስራዎች መካከል  “white Nights” አንዱ ነው፡፡ በዚህ መጽሃፉ በፒተርስበርግ ከተማ ባይተዋር ስለሆነ፣ ከስጋው ወደ ነፍሱ ስለሚያይ በምሽቱ የሚደነቅ አንድ ገጸ፟ ባህሪ አለ፡፡ ዶስቶቭስኪ እንዲህ ጽፏል፡-
“My history!” I cried in alarm. “My history! But who has told you I have a history? I have no history....”
“Then how have you lived, if you have no history?” she interrupted, laughing.
“Absolutely without any history! I have lived, as they say, keeping myself to myself, that is, utterly alone—alone, entirely alone.[White Night ገጽ-16]
ሰውን ‘ሚያህል ብርሃን ታሪኩ ሲያጨልመው ታሪክን ‘ሚያህል ታላቅ ነገር ሰው ሳይሰራው ሲቀር ከዚህ የበለጠ ‘ሚለበልብ ምን ጸጸት አለ? ገጣሚና ጋዜጠኛ ፋሲል ተካልኝ ይህንን ጉዳይ አብሰልስሎታል።
“…ሰፊ ሆኖ ተገኝቶ እንደ ጨርቅ ታሪኬ
ተንዘልዝሎ ቀረ አልሆን አለ ልኬ።
ከልደት እስከ ሞት ሲተረክ ሰማሁት
የሕይወት ታሪኬ ላይ ታሪኬን አጣሁት።”
©ፋሲል ተካልኝ
[ጡዘት ገጽ-30]
በሕይወት ታሪካችን፣ ታሪካችን ከሌለ እኛ ምንድን ነን? ማነን? የፍልስፍናው አባት ሶቅራጠስ እንዳለው ነው፤ “unexamined life is not worth living” (ያልተመረመረ ሕይወት ሊኖር አይገባም!)  ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ “ለራስ ወቀሳ” የሚል ግጥም አላቸው፤ ከራስ ፀበሉ የተጣላን አንድ ‘ራስ የሚወቅሱበት፤ ከእድሜ እድሜ ምንም ቀለም፣ ታሪክ ቢያጡበት እንዲህ ወቀሱት፡-
ለራስ ነፍስ ወቀሳ፣
ላጠራቅም ዕድሜ፣
በራፌን ከርችሜ፣
መስኮቴ ላይ ቆሜ፣
አልድን ወይ አላድን፣
በድን!
[የራስ ምስል ገጽ-44]
ግጥም ሲሰምር እንደዚህ ያሉ ውስብስቦችን ይገልጻል፡፡ ዕውቁ ገጣሚ ቻርለስ ብኮቮስኪ፤ “Poetry is what happens when nothing else can.” ይላል። “ግጥም ምንም መሆን ሳይችል ሲቀር ‘እሚሆን (‘ሚገለጥ) ነው” እንደማለት ነው።
ገጣሚው ጉደኛ ነው፤ ሐሳብ ምልከታ አይነጥፍበትም፡፡ መቼም ይች ዓለም እንቅብ ሙሉ ሐዘን ነው የደፋችብን፡፡ ይህም ሐዘን ለማረጋገጫ - nihilism - Absurdism- የሚባሉ ‘ርዕዮቶች ፈጥሯል። ፈረንሳዊው ደራሲ አልቤር ከሙ በካሊጉላ መንፈስ “ሰዎች ያለቅሳሉ ምክንያቱም ይህች ዓለም ፍትሃዊ ዐይደለችም” ይላል፡፡ ፋሲል ደግሞ “ሰበብ” ሲል ተመስጦበታል።
የመጀመሪያ መጨረሻ
እየታወቀው ለሰው እየታየው ለሰው
ሞቱ እየታወሰው
ገና ሲወለድ ነው ቀድሞ ‘ሚያለቅሰው።
©ፋሲል ተካልኝ
[ጡዘት ገጽ-68]
ለምን? የክፍለ ዘመናችን ታዋቂው ደራሲ Anthony T. Hincks እንዳለው ነው። “Sometimes, I cry other people’s tears”.(“አንዳንዴ የሌሎችን ዕንባ አለቅሳለሁ።”) የዓለሙ ፍጽምና ማነስ ሲያስቃስተው እንከተለዋለን።
ገለልተኛ ተመልካች ሳይሆን፥ ተቆርቋሪ ነው፤
በንጽረተ-ዓለሙ አፈጣጠር ምልዓተ ፍጽምና መጉደልና በሰው ኅላዌ የሚንፀባረቀው ሰቆቃ ያብሰለስለዋል? ዕንባን ተማምኖ ወደ ዓለም  መጥቶ ማቃሰት ግጥሙ የተሸከመውን ህመም አከረረው።
ገጣሚው ስለ እግዜርና ሰይጣን በጻፈው ግጥም ለመመራመር ይጥራል።[ገጽ-45-46]
ለመኖር አምላክ ወይ ሰይጣን ‘ሚል ምርጫ ያስቀምጣል። ያለነዚህ ዓለም ሁሌም ባዶ ነው።
ለገጣሚው ከምናቡና ከንጽጽሩ በዘለል ሐሳቦቹ የግጥሞቹ አጧዥ ናቸው።
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በጀርባ አስተያየት  እንዲህ  ይላሉ፤ “ግጥምን የተዋጣ ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል ‘ሐሳብ’ የቃላት አመራረጥና አደራደር በመጨረሻም ‘ምናባዊነት’ እና ‘ንጽጽር’ ናቸው። የፋሲል የግጥም ስብስቦች፣ ስለ ባህል፣ ታሪክ፣ ስለ ፖለቲካ በጠቅላላው የሰው ልጅ የሚገኝበት ሁኔታ በተዋቡ ስንኞች ቀርበዋል።”  እውነትም!!

Read 4485 times