Saturday, 10 December 2022 12:51

ከውጭ አገር በኔትወርክ ትስስር ብቻ ከኢትዮጵያ ቤት ለመግዛት የሚያስችል አሠራር ተጀመረ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

     በውጭ አገር እያሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ሳያስፈልጋቸው፣ በኢንተርኔት አጋዥነት፣ በኔትወርክ ትስስር ብቻ ቤቶችን  ለመግዛት የሚያስችል አሠራር ተጀመረ።
“በዳዳ ገመቹ የድለላ ባለሙያዎች” ድርጅት  ይፋ ባደረገው በዚሁ  አለም አቀፍ የቤት ግብይት፤ ከኢትዮጵያ ውጪ ሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ ቤት ለመግዛት የሚፈልጉ ደንበኞች ስለቤቶቹ ሙሉ መረጃ ማለትም:- የቤቶቹን ስፋትና የተሰሩበትን ማቴሪያል፤ አድራሻቸውንም ጭምር በኢንተርኔት በማየትና በኢንተርኔት የክፍያ ስርዓት በመፈጸም  ቤት ገዝተው፣ የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን አመቺ አሰራር  ይዞ መምጣቱን አስታውቋል።
“በዳዳ ገመቹ የድለላ ባለሙያዎች” ሥራ ድርጅት ከ26 ዓመታት ቆይታ በኋላ ሃገር ውስጥ የከፈተውን “ኢትዮ ሌግዠሪ ሆምስ” ቢሮ፣ በኔትወርክ  አሜሪካን ሃገር አስቀድሞ ከከፈተው “ኢትዮ ሌግዤሪ ሆምስ” ቢሮው ጋር የገበያ ትስስር ማስጀመሩንም ጠቁሟል፡፡  
በአሜሪካ አሌክሳንድሪያ ከተማ  “Ethio-Luxury Homes” በሚል ሥራ የጀመረው ድርጅታቸው፤በዚህ አገልግሎቱ ኑሯቸውን ባህርማዶ ያደረጉ ወገኖች  በሀገራቸው የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው እድልና አጋጣሚ  የሚፈጥር መሆኑን አቶ በዳዳ ገመቹ ተናግረዋል።
ድርጅቱ ከቤት ግብይቱ በተጨማሪ ዳያስፖራው ማህበረሰብ ከባንኮች ጋር መስራት የሚችልባቸውን  ሁኔታዎች ያመቻቻል። ገዢዎች ከባንኮች ጋር  መስራት ስለሚችሉባቸው ሁኔታዎችም  ያማክራል። ከዚህ በተጨማሪም  ቤቶች ግንባታቸው ሳይጠናቀቅ የግብይት ስርዓት እንዲኖራቸው ማድረግ፤ የቤት ዋጋዎችን ግልጽ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ማዋቀር፤ ድርጅቱ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ። “ኢትዮ ሌግዤሪ ሆምስ”፤ ሕንጻና የተለያዩ ንብረቶችንም  ያስተዳድራል፡፡


Read 11815 times