Saturday, 10 December 2022 12:52

የባንዲራ ፖለቲካ የቀሰቀሰው ረብሻና ግጭት!

Written by  ጽዮን ከልደታ
Rate this item
(2 votes)

    ብልጽግና ፓርቲ አሁንም ራሱን በቅጡ ይፈትሽ
                 

        ሰሞኑን ከኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር ጋር በተያያዘ በመዲናዋ የተለያዩ ት/ቤቶች የተቀሰቀሰው ረብሻና ግጭት በእጅጉ አሳዛኝና አሳፋሪ ነው። በተለይ በዚህ ሰዓት ፈጽሞ መነሳት ያልነበረበት ነው - አጀንዳው። የሰሜኑ ግጭት ጋብ ብሎ በአገሪቱ የሰላም አየር መንፈስ ከጀመረ ገና አንድ ወር እንኳን ሳይሞላው፣ በመዲናዋ ት/ቤቶች ግጭት ቀስቃሽ ድርጊት መፈጸም አንድም የለየለት እብደት ነው፤ንድም ደግሞ  የፖለቲካ ጀብደኝነት ነው።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አበቤ ሰሞኑን በጉዳዩ ላይ እንደተናገሩት፤ የሰላም ስምምነቱን የማይፈልጉ ወገኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ መንግስት በሙሰኞች ላይ የጀመረው ጥብቅ  ቁጥጥርና እርምጃ መፈናፈኛ ያሳጣቸው ሌቦችና ወንጀለኞች፣ አዲስ የግጭት አጀንዳ በመፍጠር የመንግስትን ትኩረትን ለማስቀየር አስበው ያደረጉትም ሊሆን ይችላል። ሙሰኞች እኮ እንዳሻቸው የሚሰርቁትና የሚዘርፉት አገር በጦርነትና በቀውስ ስትናጥ ነው፡፡
እስከዚህ ድረስ ከከንቲባዋ ጋር እስማማለሁ። በአንጻሩ ብልጽግና ፓርቲ ራሱን በቅጡ እንዲፈትሽ እመክረዋለሁ፡፡  (ፓርቲው የመላዕክቶች ስብስብ አይደለምና!)
እንግዲህ በአዲስ አበባ በሚገኙ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ በግድ አውለብልቡና የኦሮሚያ መዝሙር በግድ ዘምሩ ብሎ በማስገደድ፣ ተማሪዎችን ለረብሻና ግጭት የቀሰቀሱት የትምህርት ቤቶቹ ሃላፊዎችና መምህራን እንደሆኑ ታውቋል።  ግን ለምን? እንዴትስ በዚህ ወቅት? ወይስ እንደሚባለውም፣ የሌላ ቡድን አጀንዳ ነው እያስፈጸሙ ያሉት? ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች  ናቸው፡፡
ምንም ሆነ ምንም ግን ከተጠያቂነት አያመልጡም፡፡ በነገራችን ላይ ድርጊቱ በአንደኛው ት/ቤት ረብሻና ግጭት መፍጠሩን እያወቁ፣ ለምንድን ነው በተከታታይ ቀናት፣ በሌሎች ት/ቤቶች ያንኑ ድርጊት በመፈጸም ረብሻውንና ግጭቱን ያስፋፉት? ውጤታማ አለመሆናቸውን ተገንዝበው ለምን አላቆሙትም? (ጉዳዩ ባንዲራ ከማሰቀልና መዝሙር ከማዘመር የሚልቅ አጀንዳ ይመስላል፡፡)   
ለመሆኑ በአዲስ አበባ ት/ቤቶች ተማሪዎች ስለሚዘምሩት ብሔራዊ መዝሙርና ስለሚሰቅሉት ሰንደቅ ዓላማ ህጉና መመሪያው ምን ይላል? በቅርቡ ይህን አስመልክቶ የተለወጠ ወይም የተሻሻለ ህግና መመሪያ አለ? ወይስ በማን አለብኝነት የራስን የፖለቲካ ፍላጎት ለማስፈጸም የተደረገ ተግባር  ነው? ነገርዬው ጥልቅ ምርመራና ፍተሻን የሚፈልግ ነው፡፡
ከሁሉም የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ ህጻናት ተማሪዎች፣ ገና በለጋ አዕምሯቸው የጥላቻ ፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ መገደዳቸው ነው። የኦሮሚያ ሰንደቅ ዓላማ መሰቀልና የኦሮሚያ መዝሙር መዘመር አለበት የሚሉትም ሆነ የተቃወሙት ተማሪዎች (ሁለቱም ወገኖች) በአደባባይ ሲያሰሟቸው የነበሩ መፈክሮች፣ የመረረ ጥላቻና ቅራኔን የሚፈጥሩ መሆናቸው ሲታይ ደግሞ እጅግ የሚያስደነግጥና የሚያስፈራ ነው። ባለፉት ዓመታት በየዩኒቨርስቲውና ኮሌጆቹ የታዘብናቸውን ዘር-ተኮር መቆራቆስና  ግጭቶችን፣ ወደ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ወደንና ፈቅደን ለማምጣት እየታተርን ያለ ነው የሚመስለው፡፡ በእጅጉ ያስፈራል!  
ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅምና ጀብደኝነት ሲባል ኢትዮጵያውያን ታዳጊ ተማሪዎች ገና ካሁኑ  እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩና ቂምና በቀል እንዲቋጥሩ የሚያደርግ ግጭትና ክፍፍል  ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ከሁሉም የከፋ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡
የልጆች ትምህርትና ዕውቀት ላይ ከማተኮር ይልቅ የራሳቸውን ጽንፈኛ የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ የተንቀሳቀሱት ወገኖች ከባድ  ጥፋት ነው የፈጸሙት፡፡ በተማሪዎች ላይ ክፉ ጥላቻን ነው የነዙት፡፡  መጠላላትንና መገፋፋትን ነው ያስተማሩት፡፡
በሚያሳዝን ሁኔታ በመዲናዋ ት/ቤቶች ከሰሞኑ  በተቀሰቀሰው ግጭት፣በርካታ ተማሪዎችና መምህራን ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸው ተሰምቷል፡፡ ለዚህ ተጠያቂው ማነው? ነገስ ግጭቱ እንዳያገረሽ ምን መፍትሄ ታስቧል? በጉዳዩ ላይ እውነተኛና ግልጽ መረጃ የሚሰጠን ማነው? እስከዛው ግን  በማስተዋል ብንራመድ ነው የሚበጀን እላለሁ፡፡  

Read 12039 times