Saturday, 10 December 2022 13:10

በኦሮሚያ ክልል በ13 ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 36 ወረዳዎች በንፁሀን ላይ ጥቃት ተፈጽሟል

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(5 votes)

  • የምሥራቅ ወለጋ ዞን አካባቢዎች በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩ ተጠየቀ
     • በመንግስት የጸጥታ ሃይሎችና ራሳቸውን ለመከላከል በታጠቁ ወገኖች መካከል በተደረገ ውጊያ በርካቶች መሞታቸውን ኢሰመኮ አስታውቋል
     • ኦፌኮ፤ የሰሜኑን ክፍል ግጭት ለማስቆም የተሄደበት የሰላም መንገድ በኦሮሚያ ሊደገም ይገባል ብሏል
         
       የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ህዳር ወር 2015 ዓ.ም ድረስ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች አከናወንኩት ያለውን የጥናት ሪፖርት ይፋ አድርጓል። በሪፖርቱም በክልል በሚገኙ 13 ዞኖች ውስጥ ባሉ 36 ወረዳዎች ግጭቶችና ጥቃቶች መፈጸማቸውንና በዚህም ሳቢያ በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጿል።
ኮሚሽኑ ላለፉት አምስት ወራት አከናወንኩት ባለው ጥናት ተገኘ የተባለው ውጤት እንደሚያመለክተው፤ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ በምስራቅ ወለጋ ዞን፤ በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ በሰሜን ሸዋ፣ በቄለም ወለጋ ዞን፣ በኢሉባቡር ዞን፣ በቡኖ በደሌ ዞን፣ በምስራቅ ሸዋ፣ በምዕራብና ደቡብ ሸዋ በአርሲ ዞንና በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ውስጥ ግጭቶች መከሰታቸውን አመልክቷል። በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ቡድኖች በአይነታቸውና ቁጥራቸው መጨመርና የሚፈጽሙት ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ አስከፊ እየሆነ መምጣቱንም ጠቁሟል።
በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ቡድኖች ሙሉ ቀበሌዎችን ወይንም ወረዳዎችን ጭምር ተቆጣጥረው መቆየታቸው የሚፈጽሟቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲባባስ አድርጎታል ተብሏል።
በዚሁ የኢሰመኮ ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው፤ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች፣ ራሳቸውን ለመከላከል የታጠቁ የአካባቢው ሃይሎች (እንደ አካባቢው አጠራር የአማራ ታጣቂዎች) እና የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ሸኔ) በሚያደርጓቸው ውጊያዎች በርካታ ንጹሃን ዜጎች ለሞት፣ ለመፈናቀልና ለንብረት ውድመት መዳረጋቸው ተመልክቷል።
ይህንኑ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የሚፈጸሙትን ጥቃቶችና የንጹሃን ግድያዎች አስመልክቶ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ ጥናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፤ የፌደራል መንግስት የአጎራባች አገራት ሃይሎችን ጭምር በመጋበዝ ግጭቱን ወደ እርስ በእረስ ግጭት ለመቀየር እየሞከረ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ጉዳይ አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማስቆም የተሄደበት የሰላም መንገድ በኦሮሚያም ሊደገም ይገባል ያሉት ዶ/ር መረራ፤ የሰሜኑን በሰላም ፈትቶ እዚህ በጦርነት ለመፍታት የሚደረገው ጨዋታ ታሪካዊ ስህተት ነውም ብለዋል። መንግስት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሁሉንም አማራጮች ሊጠቀም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
ሰሞኑን በክልሉ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ ዞኖች በተፈጸሙ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸውና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩት ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው ይታወሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን በሚገኙት ኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና ሀሮ አካባቢዎች፤ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደሩና የመከላከያ ሰራዊት ስፍራዎቹን እንዲቆጣጠር ሶስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠየቁ። በአካባቢዎቹ በተፈጸሙ “የንጹሃን እልቂት ባለስልጣናት ጭምር ተሳትፈዋል” ሲሉ የወነጀሉት ፓርቲዎቹ፤ በድርጊቱ የተሳተፉ የትኛውም ኃይሎች “በአስቸኳይ ለህግ እንዲቀርቡ” ጠይቀዋል፡፡
 ከሰሞኑ እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረቡት ሦስቱ ፓርቲዎች፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና እናት ፓርቲ ሲሆኑ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት  መግለጫቸው፤ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ፣ ጊዳ አያና እና ሀሮ አካባቢዎች ከሰሞኑ “እጅግ የሚሰቀጥጡ ፍጅቶች” መፈጸማቸውን  ገልጸዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ “ዘግናኝ ጭፈጨፋ” ሲሉ በጠሩት በዚሁ ድርጊት፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን፣ ሺህዎች ከቤት ንብረት መፈናቀላቸውንና ከፍተኛ መጠን ያለው ንብረት መውደሙን ጠቅሰዋል። በምስራቅ ወለጋ፣ ጉትን በተሰኘችው ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግም፤ በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ “የክልል የጸጥታ ኃይል ልብስ የለበሱ ኃይሎች” በንጹሃን ላይ “ጭካኔ የተሞላው ተግባር” መፈጸማቸው “እጅጉን አሳዝኖናል” ብለዋል።
ላለፉት አራት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል፣ በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ግድያዎች፤ የድርጊቱ ቀጥታ ሰለባ “የአማራ ማህበረሰብ” መሆኑን ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው አመልክተዋል። ከእነርሱ በተጨማሪ “ጭፍጨፋውን የተቃወሙ፣ የኦሮሞ ተወላጆችም የእልቂቱ ሰለባ መሆናቸውን ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ አስታውቀዋል፡፡

Read 12211 times