Saturday, 10 December 2022 13:16

“የቁርጡ ቀን ሁሉም የክት አለው!”

Written by 
Rate this item
(5 votes)

   ከረዥም ጊዜ በፊት በተካሄደ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈው ወደ መንደራቸው የተመለሱ ተዋጊዎች ስለ ጦርነቱ ሂደት ይወያያሉ።
አንደኛው፤
“ጠላት ባይቆርጠን ኖሮ አንሸነፍም ነበር!”
ሁለተኛው፤
“የለም፤ ትልቁ ችግር የደጀን ጦር በሰዓቱ ስላልደረሰልን ነው። የፊት አውራሪው ጦር በጣም ፈጠነ። አዛዣችን “ቅደሙ! ቅደሙ!” ባይል ኖሮ ጦሩ በአንድ ፍጥነትና ረድፍ ይገሰግስ ነበር።”
ሦስተኛው፤
“እኔ ደሞ የሚታየኝ ጦራችን ውስጥ ሰርገው የገቡ የጠላት ወገን ሰዎች መኖራቸው ነው! ተሸርሽረናል!”
አንደኛው፤
“አሁን ከመካከላችን ገብቶ ያኔ ያተራመሰን አንድ ሰው እንደዚያ ሊያምሰን የቻለው ለምንድን ነው?”
 በመጨረሻ አንድ አዛውንት ጣልቃ ገቡ፡-
“ልጆቼ፤ በእኔ ጊዜ አባቶቼ ያጫወቱኝ አንድ ጨዋታ ትዝ ብሎኝ ነው። እንዲህ እንደኛ ጦርነቱን ይገመግሙ ነበር አሉ።”
“አንድ ጦርነት ላይ ሽንፈት የሚመጣው አንድም ከዝግጅት ማነስ፣ አንድም ከሃይል እጥረት፣ አለበለዚያ ከአመራሩ ብቃት ማነስ ነው ይባላል። ጀግናው ግን “በምን ምክንያት ተሸነፋችሁ? የጠላት ወታደሮች ብዙ ነበሩ እንዴ?” ተብሎ ሲጠየቅ፤
“ብዙማ ቢሆኑ አንድ ለአንድ እንይዛቸው ነበር። አንድ ብቻውን ሆኖ ውር ውር እያለ፣ እኛኑ እርስ በርስ እያጋጨ፣ እያተረማመሰ ጉድ አደረገን እንጂ!” ብሎ መለሰ አሉ።
***
አቶ መንግስቱ ለማ የተባሉት የሀገራችን ጸሐፌ ተውኔትና ገጣሚ በ”ባለ ካባና ባለ ዳባ” ቴአትራቸው ውስጥ፡-
“ቀማኛን መቀማት፣ ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ፣ የድሆችን ጭንቅ፤
በኔ ቤት ጽድቅ ነው፤ አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው፣ ኪኖር በምጽዋት” ይሉናል። ዞሮ ዞሮ የአንድ ሰው ዲክታተርነት ለማንኛችንም አይበጀንም ለማለት ነው! አገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ አምባገነን መሪ ወይም መሪዎች አጥታ አታውቅም። መሪዎች በተለዋወጡ መጠን የቅርጽ እንጂ የይዘት ለውጥ አለማየታችን፣ የሁልጊዜና ያፈጠጠ ዕውነት ነው! በአንድ ጀንበር ለውጥ ለማምጣት አቅሙ የለንም። ፍቃደኝነቱንም ለማዳበር ዝግጁነቱ የለንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ወጣቱ ትውልድ ላይ ብዙ አልሰራንም! ያለነዚህ ቁልፍ አጀንዳዎች ወደፊት እንጓዝ ማለት… “ሒማሊያ ተራራን በሁለት ቆራጣ እግር መውጣት” የሚባለውን የህንዶች ተረት ሥራ ላይ እናውለው፤ የማለት ያህል ነው። ለውጥ አዳጊ እንጂ በአንድ ጊዜ የሚፈጠር ጉዳይ አይደለም።
በለውጥ ውስጥ የምሁራን ሚና የላቀ ነው። ለውጥ የብዙኃንን ተሳትፎ የማታ የማታ ይጠይቅ እንጂ በጥቂት ግንባር- ቀደም የፖለቲካ ሰዎች መነሳሳቱ ያለ፣ የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው። ጥቂቶቹ አብሪዎች፣ ህሩያን ሕዳጣን ይሁኑ እንጂ ብዙኃኑን ይታደጋሉ። “ፀሐይ የሚያሞቀው የፒራሚዱን አናት ነው” ይባላል። The tip of the ice-berg melts first እንደሚሉት መሆኑ ነው!
ሌላው ዋንኛ የለውጥ አንኳር የኢኮኖሚው ክፍል (Sector) ነው። አብዛኛውን ጊዜ ፖለቲካው የኢኮኖሚው የተከማቸ ነጸብራቅ መሆኑን እንረሳለን። ሆኖም ኢኮኖሚ የአንድ ሀገር ሐብለ-ሠረሠር ነው። የኢኮኖሚውን ችግር የማይነካ (የማያንጸባርቅ) ፖለቲካ የይስሙላ ነው! ሥሩ ሳይኖር ዛፉ የለምና! ስለዚህ ለኢኮኖሚያችን  ብርቱ ትኩረት እንስጥ!
ፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን ካነሳን ዘንድ የሚቀረን የማህበራዊ ኑሮ ማሠሪያ የሆነው ባህላችን ነው። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የብዙ ብሔር ብሔረሰብ አገራት፣ ባህልና ታሪክ እጅግ ከባድና ቁልፍ ሚና አላቸው። ስለዚህም ጥልቅ ጥናት ምርምርና ስርዓትን ይሻሉ። ከትውልድ ትውልድ የሚደረገው ቅብብሎሽም በትምህርትና በዕውቀት መሳሪያነት አገርን የማሳደግና የመለወጥ ሥር-ነቀል ሽግግርን ሊያስከትል የሚችለው በዚህ ጥበብ ነው። ለዚህ ደግሞ የኪነ-ጥበብ አስተዋጽኦ እጅግ ሰፊ ሥፍራ አለው። ንቃተ ህሊናን የማትባትን ተግባር ሥራዬ ብሎ በያዘ  መንግስት ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው ሊሆን ይገባል።
የመንግስት ራሱን ማጽዳት (Purging oneself) የሁልጊዜ እንቅስቃሴ መሆን አለበት። መዛግን፣ መሸርሸርን፣ ንትበትን፣ መበስበስን መከላከል የሚቻለው ሳያቋርጡ ተሐድሶን በማድረግ ነው። ይህን ካላደረግን ንቅዘት ይከተላል። ይህንን ንቅዘት ለመቆጣጠርና በጊዜ ለማሸነፍ ተብሎ እንጂ “ለቁርጡ ቀንማ ሁሉም የክት አለው!” ለማለት አያቅትም።
እንደተለመደው “ትምህርታችንን ይግለጥልን” ብለን እናሳርግ!

Read 11917 times