Saturday, 10 December 2022 13:21

የመልካምና የክፉ ፉክክር አይደለም - የስፖርት ውድድር ፍፃሜ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

• የልብወለድ ድንቅ ውበትም፣ የሰናይና እኩይ፣ የቅዱስና የከይሲ ፍልሚያ አይደለም - የጀግኖች እንጂ።
 • ድንቅ ብቃት ያላቸው ተፎካካሪዎች፣… በየእርከኑ እየከበደ የሚሄድ ፈተና ውስጥ፣ በብርቱና በልሕቀት ሲወዳደሩ ለማየትና ለማሳየት የተቀረጸና        የተቀናበረ ነው - ምርጥ የስፖርት ውድድር፣ ምርጥ የልብወለድ ታሪክ።
 • ከደካማ፣ ከቀሽምና ከልግመኛ ተቀናቃኝ ጋር የሚደረግ ፍክክር በጣም አስልቺ እንጂ አዝናኝ አይሆንም፡፡ የአሸናፊው ክብር የሚደምቀው፣           በተቀናቃኙ ብቃትና ትጋት ልክ ነው፡፡
 • ምርጥ የልብ ወለድ ድርሰት፣ ትያትርና ፊልሞችንም ተመልከቱ፡፡ ዋናዎቹ ባለታሪክ ፣ አላማቸውን ለማሳካት፣ ጥቃትን ለመግታትና ለማስወገድ፣        ከሞት ለማምለጥና ሕይወትን ለማጣጣም ፈታኝ የአቀበት የቁልቁለት ጉዞ ይጠብቃቸዋል፡፡
 • አጥፊ ሰዎችን መመከት፣ የክፉዎችን ጥቃት ማስቆምና መቅጣት እንደ ዋዛ ቀላል አይደለም፡፡
 • ፈተናቸው ግን ከዚህም ይከብዳል። የጀግናው ባለታሪክ፣ ዋና ተቀናቃኝ እሱን የሚመጥን ሌላ ጀግና ሲሆን ነው የኪነ ጥበብ ውበት የሚደምቀው፡፡

         ከታች ከሰፈርና ከትምህርት ቤት ጀምሮ፣ ከዝቅተኛ ክለቦች እስከ አገራዊና አለማቀፋዊ የሻምፒዮና ውድድሮች ድረስ፣… የድል ጉዞው ወደ ባሰ ፈተና ነው። ወደ ላቀ ብቃትም። በእያንዳንዱ እርከን ወደ አዲስ ብቃት በእመርታ እየተመነደጉ ክብርን መቀዳጀት፣ በብርቱ ጥረት ፈተናዎችን እያሸነፉ በስኬታማ ውጤት ደስታን መጎናፀፍ ይችላሉ - ትጉሃን።
ነገር ግን፣ ፈተናዎችን አሸንፈው በድል የሚደሰቱት፣ ወደ ተጨማሪና ወደ ባሰ ከባድ ፈተና በመሸጋገራቸው ነው። ለዚያውም፣ የእስካሁኑ ብቃትና ጥረት በቂ አይሆንላቸውም። ከመጀመሪያው እርከን አልፎ የተሻገረና ማጣሪያውን ያለፈ ጀግና፣ ከቀድሞው የበለጠ ኃያል ተቀናቃኝ ይጠብቀዋል፡፡ ተጨማሪ ብርታትንና ፅናትን፣ እንዲሁም የብቃት ልሕቀትን የሚጠይቅ ነው - የቀጣዩ እርከን ፈተና።
ከምልመላ ጀምሮ እስከ ስልጠና ድረስ፣… ከቅድመ ማጣሪያና ከመጀመሪያ ዙር ውድድር ጀምሮ፣ በጥሎ ማለፍ ፉክክፎች ተጣርቶ እስከ ፍጻሜው ወደ ዋንጫ ግጥሚያ የሚጓዘው፣ በደስታም በመከራም ነው፡፡ ከጉብታው ወደ ጋራው፣ ከኮረብታው ወደ ተራራው የሚያመሩ  የአቀበት መንገዶች፣ በውጣ ውረድና በወጣ ገባ የተከበቡ ባለ ብዙ ቀንድ ባለ ብዙ ጭራ አስቸጋሪ መንገዶች ናቸው፡፡
ቢሆንም ግን፣… እንደ ልብወለድ ታሪክ ሁሉንም ቅርንጫፎች አቅፎ የሚሰበስብ፣ ሁሉንም አቅጣጫዎች የሚያገናኝ ትልም አለው- ምርጥ የስፖርት ውድድር።
ትጋትንና ብርታትን፣ የሙያ ፍቅርንና የአላማ ፅናትን፣ ብቃትንና ጥበብን እየገነቡ፣ ልሕቀትን እየመረጡ እንዲያሳልፉ የተዘረጉና የተከፈቱ ናቸው- ቦዮቹና ጎዳናዎቹ፡፡
እናም፣ መንገዶች ሁሉ ወደ ትልቁ ተራራ ወደ ከፍታው ጫፍ፣ ጅረቶች ሁሉ ወደ አውራው ግዙፍ ወንዝ ወደ አስደናቂው ኃያል ፏፏቴ የሚያመሩ ይሆናሉ። በዚህ ስሌት ከምር እየታሰበባቸው የተቀረፁ፣ በተግባር እየተፈተሹ የተቃኙ ከሆኑ ነው ተወዳጅነትን የሚያገኙት - ድንቅ የስፖርት ውድድሮችና ዝግጅቶች።
ያለ ብቃትና ያለ ጥረት፣ አንዱን እርከን በአንዳች አጋጣሚ የሚሻገር አንድ ቀሽም ተወዳዳሪ ቢኖር እንኳ፣ ብዙም አይራመድም።
ምርጥ የስፖርት ውድድር፣ “የብቃት፣ የብርታ፣ የልሕቀት አምባ” ስለሆነ፣ ፈተናው እየቀለለ ሳይሆን እየከበደ ስለሚቀጥል፣ ለቀሽምና ለደካማ ቦታ አይሰጥም፡፡
 በአጋጣሚ ቢገባና ቦታ ቢያገኝ፣ በድንገተኛ ዕድል ውሎ ቢያድር እንኳ፣ ቀሽምና ደካማ፣ በልሕቀት አደባባይ አይሰነብትም። ከማጣሪያው ዙር በአንዳች አጋጣሚ ሾልኮ የማለፍ እድል ቢገጥመው፣ በቀጣዩ የውድድር እርከን ከመንገዋለልና ከመሰናበት አያመልጥም።
መሳጭ ድንቅ የልብወለድ ትረካም፣ ተመሳሳይ ባህርይ አለው፡፡ አንዱን ፈተና ሲሻገሩ ወደ ባሰ ከባድ ፈተና ያስገባል፡፡  በአስቸጋሪ ጥረት ከአደጋ ሲያመልጡና ድል ሲያደርጉ፣ ወደ ባሰ አደጋ፣ ትዕግስትን ወደሚያስጨርስ ብርቱ ጥረት የሚወስድ ነው- ምርጥ የልብወለድ ድርሰት፡፡
ለአፍታ ያህል ትንሽ እረፍት ወደሚናፍቁበት፣ ወደ ፋታ የለሽ ውጥረት፣ ማምለጫ ወደ ሌለው የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው የምርጥ ልብወለድ ጉዞ።… ያለ የሌለ አቅምን፣ የመጨረሻ የጽናትና የብቃት ሃይልን እስከ ጥግ ድረስ ተጠቅመው ቢጣጣሩም እንኳ፣ የሰውን ሁለመና እጥፍ ወደ ሚፈትን አደጋ ነው መንገዱ።
በሙሉ ሃሳብ፣ በሙሉ ሃይል፣ በሙሉ መንፈስ፣… እንደሚባለው ነው።ሃሳብና ንግግር፣ አላማና ስነምግባር፣ ማንነትና ተግባር፣… ሰምረው አምረው በባለታሪኩ ስብዕና ውስጥ የሚዋሃዱት፣… የተጣርሰው ተጣልተው ተበጣጥሰውና ወዳድቀው ፤ረክሰውና ተዋርደው የማይቀሩበት ደረጃ ላይ የሚደርሱት በዚህ የጀግንነት ፈታኝ ጉዞ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ፣ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ የፍፃሜውን ይፋለማል። ወይ በክብር ድል ማድረግ ነው፤ ወይ ድልን ባያጣጥም እንኳ ክብርን ሳይጥል ውጤቱን መቀበል ነው።
ድል አለማድረግ፣ ጀግንነቱን አይቀንሰውም። ታሪኩ የሚያስቆጭ የሚያሳዝን (tragic) ውድቀት ይሆናል። ግን የከበረ ታሪክ ነው - የድንቅ ሰው ታሪክ።  ጀግናዋ አንቲገን ተቀናቃኝ የሆነባት ሃያል ንጉሥን የተገዳደረችበት ታሪክን መጥቀስ ይቻላል።
ምንዱባን ተብሎ የተተረጎመው የቪክቶር ሁጎ ድርሰት ውስጥም የዋናዎቹ ባላንጦች ታሪክ፣ የዣቬርና የዣን ቫልዣ መጨረሻ አሳዛኝ ነው። ታላቁ የኪነጥበብ ሰው ሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር”  በሚል ርዕስ የተፃፉት የአገራችን ምርጥ የልብወለድ ድርሰትም ከእነዚህ ጋር ይመደባል - በአሳዛኝ ፍፃሜው።  
እነዚህ ድንቅ የኪነ ጥበብ ስራዎች ላይ ከምናስተውላቸው ተመሳሳይ ባህርያት መካከል፣ የተቀናቃኞቹ ጥንካሬ አንዱ ነው። ዋና ባለታሪኮች ዋና ተቀናቃኞች፣ ክፉ ሰዎች አይደሉም። ዓይነቱ ቢለያይም፣ የየራሳቸውን ጥንካሬ የገነቡ ናቸው። ፍጻሜቸውም አሳዛኝ ነው- እንደ ጀግኖቹ ባለታሪኮች።
የጀግንነት ታሪክ፣… ለውጣ ውረዱና ለፈተናው፣ ለብቃቱና ለጽኑ ጥረቱ በሚመጥን በአስደሳች ድል ሊጠናቀቅም ይችላል። ዊልበስሚዝ የተወነበት The pursuit of happiness የተሰኘውን ፊልም መጥቀስ ይቻላል።
አብዛኛው የጀግንነት ታሪክ ግን በድል ቢጠናቀቅም እንኳ… ብዙ ስቃይ ያሳለፉበት፣ ንፁሐን ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበትና መራራ ሃዘን ተደራረበበት ከመሆኑ የተነሳ፣ የድል ፍጻሜው፣ ሃዘን ያልራቀው ግማሽ ደስታ፣ ግማሽ እፎይታ ይሆናል። ከጥንታዊው የሆሜር ልብወለድ Iliad ጀምሮ፣ እፎይታ በሚል ርዕስ የተተረጎመው “ካውንት ኦፍ ሞንቶክሪስቶ”፣ እንዲሁም፣ ሃሪሰን ፎርድ የተወነበት The fugitive፣… ወይም አዲሱ The Black Adam የተሰኘውን ፊልም መጥቀስ ይቻላል።
በእርግጥ፣ አብዛኞቹ የወንጀል ምርመራ ድርሰቶችና ፊልሞች፣… ወንጀለኛው የእጁን ሲያገኝ የሚያሳዩና በድል የሚጠናቀቁ ናቸው። የብዙ ሰዎች ህይወት ከአደጋ ይድናል፤ ወንጀልም በፍትህ እልባት ያገኛል። እፎይታ ነው። ነገር ግን ከመነሻው በወንጀል የጠፋውን ሕይወት መመለስ ስለማይቻል፣ የድሉ ደስታ ከሃዘን ያመለጠ አይሆንም።
አንዳንድ ታሪኮችማ ለዚህም ያስቸግራሉ። በወንጀለኞች ጥቃት እልፍ ሰዎች ሞተው፣… በከባድ ጥፋትና ነውጥ የመቶ ሺ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶ፣ ቢሊዮኖችና ከዚያም በላይ ሕዝብ ያለቀበት አደገኛ ፍልሚያ በድል ሲጠናቀቅ፣ ምን ዓይነት ደስታ ሊሰጥ ይችላል? ተጨማሪ እልቂትን መከላከልና እፎይታ ማግኘት ነው መቋጫው።
የምርጥ ልብወለድ ፍጻሜ በድል የሚጠናቀቅ መሆኑ ወይ አለመሆኑ፣ አስደሳችም ይሁን አሳዛኝ፣… አልያም ደስታና ሃዘን በተቀላቀለበት የእፎይታ ስሜት የሚያበቃ ቢሆን፣… የድርሰቱን፣ የትያትሩን የፊልሙን ድንቅ ጥበብ አይቀንሰው።
የዋናዎቹን ባለታሪኮች ክብር አያሳንሰውም። ታሪካቸው፣ የጀግንነትና የዓላማ ጽናት ነው። ማንነታቸው፣ የብቃትና የመርህ ጽናት ነው።
ከትክክለኛ ሃሳባቸው ጎን ለጎን አንዳንድ ጥቃቅን ስህተቶች፣…
በተቃናው የመርህ መንገዳቸው መሃል አባጣ ጎርባጣና ከመስመር ያፈነገጡ ቅያሶች፣…
በጠንካራ ብቃትና በአስተማማኝ የሰብዕና ምሰሶ ላይ ትናንሽ ጉድለቶችና ተለጣፊ ብናኞች፣ ተቀጥላ ስንጥሮች ይኖራሉ፡፡
ሊቀሊቃውንት ሆኖ የተወለደ የለም፡፡
እናም ጀግና ባለታሪክ ገና ከመነሻው ፍጹምና ንፁህ፣ እንከን የለሽ ብፁዕ ቅዱስ፣… አይሆንም።  ስህተቶቹና ጉድለቶቹ ተቀጥላና ጊዜያዊ እንከኖች ቢሆኑም እንኳ፣ ለትልቅ ጉዳትና ለውድቀት ይዳርጉት ይሆናል።
እንዲያም ሆኖ፣ እየገነነና እየገዘፈ የሚመጣባቸው ፈተና ሳይበግራቸው ወደ አላማቸው ከሚያደርጉት ጉዞ ጎን ለጎን የገነቡት ጠንካራ የጀግንነት ብቃትና ሰብዕና ጎልቶ ደምቆ ይታያል። ደረሱበት የሰብዕና ከፍታ አስደናቂ ነው፡፡ በጥረታቸው ከብረዋል።
እናም፣ ይከበራሉ፤ በአርአያነት ይጠቀሳሉ።
እንደ ሰብእናቸው ጥንካሬ፣ እንደ አላማቸው ትልቅነት፣ እንደ ብቃታቸው ልህቀትና እንደ ጥረታቸው ጽናት፣… ፈተናቸውና መከራቸው እጅግ የበዛና ከበደ ቢሆንም፣…
መጎሳቆላቸውን መጎዳታቸውን ተቋቁመው፣ ወድቀው ተነስተው፣ ቆስለው አገግመው ወደ አላማቸው በጽናት መገስገሳቸውና ወደ ለተሟላ ድል መድረሳቸው፣ ቢያንሳቸው እንጂ አይበዛባቸውም። እንዲያውም አብዛኛው መከራ፣ ጥቃትና ጉዳት የደረሰባቸው አለጥፋታቸው ነውና ያስቆጫል።
ያሳዝናል፡፡ ቢሆንም አላማቸውን አሳክተዋልና ያስደስታል።
 ከጉብታው ወደ ጋራው፤ ከዚያም ወደ ኮረብታው ከወጡ በኋላ ወደ ትልቁ ተራራ ለመድረስ ባይሳካላቸው፣…ወይም ከብዙ የብቃት ጀብድ በኋላ ቁልቁል ወርደው ቢፈጠፈጡ፣ በቁጭት ከማሳረር አልፎ በሁለመና የሚሰርጽ የሚቆረቁር የመንፈስ ጉዳት ይሆናል- አሳዛኝነቱ።
በጀግናው ባለታሪክ ላይ ተገቢ ያልሆነ መከራና ጉዳት ሲደርስበት ወይም ሲያደርሱበት፣…
ለብቃቱ፣ ለጽናቱና ለጥረቱ የሚመጥን ተገቢ ውጤቱንም ሲያጣ… ሲያሳጡት፣…
ከነጭራሹም ሕይወቱን ሲያጠፉ፣ ስሙንና ታሪኩን ሲያጎድፉ… የሚቆረቁር፣ የሚያስቆጭ ሃዘን ነው። የርህራሄ አዘኔታ አይደለም። የሚያንገበግብ የሚነግድ ሚያስቆጣ ሀዘን ነው- በመልካም ሰው ላይ የሚደርስ ግፍ፤ወይም ጀግና ሰውን የሚጠፋ መዓት።
በዚህም ተባለ በዚያ ግን፣ አስደሳችም ሆነ አሳዛኝ፣… የትውልድ ቦታቸውና ዘመናቸው ምንም ሆነ ምን፣ ከነባሩ ሁኔታ ተነስው፤ የተፈጥሮ አቅማቸውን ተጠቅመው፣ የተሻለ ብቃትንና መልካም ሰብዕናን እየገነቡ፣ ወደ ተሻለ የስኬት ከፍታ መጓዝ ይችላሉ።
እንቅፋትንና ፈተናን እየተሻገሩ በጽናት ወደላቀ ደረጃ ወደ አላማቸው መራመድ ይችላሉ። የሚደርሱበት የማንነት ክብር፣ የሚቀዳጁት ስኬት፣ የሃሳብና የተግባራቸው ፍሬ ነውና ይመጥናቸዋል፤ ይገባቸዋል።… ይህን እምነትና ይህን የፍትህ መርህ በውስጡ ያዘለ ከሆነ ነው የጀግኖች ስኬት የሚያስደስተን።…ጉዳትና ጥቃት ሲደርስባቸውም የሚቆቁረን የሚያሳዝነን።
ከጫፍ እስከ ጫፍ፣ ዓይንና ጆሮን፣ ሃሳብና ህሊናን፣ ስሜትንና መንፈስን አዋህዶ የሚማርክና የሚመስጥ ምርጥ የልብወለድ ጥበብ፣ ከጫፍ እስከ ጫፍ ድንቅና ውድ ጸጋ ቢሆንም፣ ከዳር እስከ ዳር አስደሳች ወይም አሳዛኝ ይሆናል ማለት አይደለም።
የፈተናው የመከራው ብዛት አይጣል ነው። በዚያ ላይ አንዱን የፈተና ዙር “አሸነፈ”ብለን እፎይ ከማለታችን ፣እንደገና የባሰ ብርቱ ፈተና ሲጠብቀው ይታየናል። አንዱ ጉብታ ላይ ተጣጥሮ ሲወጣ የምንደሰተው፤ ሌላ የባሰ ትልቅ አምባ ላይ ለመውጣት እንዲሟሟት በመመኘት ነው።
የጉዞው መንገድ፣ ሁሌም አቀበቱ እየከፋ፣ ሸክሙ እየከበደ ነው የሚመጣው። እንደ ብቃቱ ልክ ነው። የማንነት ክብሩም፣ የጥረቱ ፍሬና የትጋቱ ውጤትም፣ እንደዚያው ነው። እንደ ዓለም ዋንጫ ነው።
የእግር ኳስ ጥበበኞች እንደየ ብቃታቸውና እንደየ ጥረታቸወ ወደ ብቃት መነሃሪያ፣ ወደ ብቃት መቅደስ የመግባት አቅም ኖራቸዋል።
ነገር ግን፣ ወደ ዓለም ዋንጫ  መግባትና ተሳፋሪ መሆን ማለት ከከፍተኛ ፈተና ጋር መጋፈጥ ማለት ነው። ማሸነፍና መደሰት ማለት ለመዝናናት ብቻ አይደለም። ከባሰ ፈተና ጋር ለመጋፈጥ ነው- በጥሎ ማለፍ ግጥሚያ። ይንን አሸንፎ ማለፍ ለደስታ ነው፡፡ ግን እየከረረ እየበረታ ወደሚቀጥል ተጨማሪ ፈተና ነው ጉዞው- ወደ ዋንጫው፤ ወደ ላቀ ብቃት።

Read 11295 times