Saturday, 27 October 2012 10:00

ጠ/ሚኒስትሩ ከ “ልማታዊ ተቃዋሚዎች” ጋር ቢወያዩስ?

Written by  - ኤልያስ -
Rate this item
(12 votes)

ጋዜጠኞች ለኢትዮጵያ ህዳሴ አያስፈልጉም እንዴ?
አባት ተርብ የሆኑ ነጋዴ ናቸው፡፡ ሴት ልጃቸው ደግሞ ሰቃይ ተማሪ ናት - በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ፡፡ በነገራችን ላይ ሁለቱም አሜሪካውያን ሲሆኑ የሚኖሩትም እዚያው አሜሪካ ነው፡፡ አባት ባለሃብቶች ላይ ከፍተኛ ግብር የሚጥለውን የዲሞክራት ፓርቲ አይደግፉም፡፡
የሪፐብሊካኖች ቀንደኛ ደጋፊ ናቸው፡፡ ልጅት ደግሞ ዲሞክራት ናት፡፡ የኮሌጅ ፕሮፌሰሯም እንዲሁ፡፡
እናም ሁሌ ይወያያሉ - የአሜሪካን ሃብት ጠቅልለው ስለያዙት 1በመቶ ባለሃብት አሜሪካውያንና 99 በመቶ ምስኪኖች፡፡ “እነዚህ ስግብግቦች እኮ ናቸው …” እያሉ ያማሉ፤ ይተቻሉ፡፡

(ኢህአዴግ ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብት እንደሚለው) አንድ ቀን ልጅትና አባት ቁጭ ብለው ሲያወጉ የተለመደው አከራካሪው ጉዳይ ተነሳ፡፡ “መንግስት የጣለብህን ግብር እየከፈልክ እኮ አይደለም …ህዝብ እየበዘበዝክ ነው… በጣም ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ነው” ስትል ልጅ አባቷን ትወቅሳለች፡፡ አባት ከመናደድ ይልቅ መላ አመጡ፡፡ “ግን ትምህርት እንዴት ነው የእኔ ልጅ? ውጤትስ?” ይሏታል 
“እኔስ ቀንቶኛል … 4A እና 3B አግኝቻለሁ … ጓደኛዬ ግን ጠቅላላ C ነው ያመጣችው”
“ታዲያ ካንቺ 4Aዎች አታካፍያትም?” ጠየቁ አባት (ለብልሃታቸው)
“እንዴ … ለፍቼ እኮ ነው ያገኘሁት”
አባት ፈገግ ብለው “እኔም ለፍቼ ያመጣሁትን እኮ ነው ስጥ የምትይኝ… ገባሽ?” አሏት፡፡ (የገባት ግን አይመስለኝም)
እኔ የምለው የአሜሪካን ምርጫ እየተከታተላችሁ ነው? እኔማ ቀናሁባቸው! በነገራችሁ ላይ ኢቴቪ የኦባማ (ዲሞክራቶች) ደጋፊ ነው እንዴ? (ጥያቄ ነው!) የሰሞኑን የአሜሪካ ምርጫ ዘገባዎች በኢቴቪ ካስተዋላችሁ እኮ የአሜሪካ ዲሞክራት ፓርቲ ደጋፊ ነው የሚመስላችሁ፡፡
ኢቴቪ ዲሞክራቶችን ደገፈ ማለት ደሞ ኢህአዴግም የዲሞክራት ደጋፊ ነው ማለት ነው፡፡ (ኢቴቪ የኢህአዴግ አፈቀላጤ ነው አልወጣኝም!) ኢህአዴግም ሆነ ኢቴቪ ኦባማን የሚደግፉት እኮ (ከደገፉት ማለቴ ነው) ጥቁር ስለሆኑ አሊያም “የአፍሪካ ልጅ” በሚል ጠባብነት እንዳይመስላችሁ (ኢህአዴግ ጠባብነት አይነካካውም!) ይልቁንም መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ እጁን ማስገባት አለበት የሚል ሃሳብ ስለሚያቀነቅኑ ነው - ኦባማ፡፡ ሪፐብሊካኖች ግን መንግስት የ“ዘበኝነት” ሚና ሊኖረው ነው የሚገባው ወደ ማለት ያዘነብላሉ፡፡
በሌላ አነጋገር ሥራው ወይም ሚናው አገር ማስተዳደር እንጂ ሌላ ሌላው አያገባውም ባይ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የቢዝነስ ነገር! ለዚህ ይመስለኛል ኢህአዴግ ኦባማን የመደገፍ ዳር ዳርታ የሚታይበት (መንግስት እንጂ ዘበኛ መሆን አይፈልግማ!)
አንድ የኢህአዴግ ካድሬ ወዳጄ ምን አለኝ መሰላችሁ?
“ኦባማ እኮ እንደኛ ናቸው”
“እንደኛ ስትል?” አልኩት
“ልማታዊ መንግስት!” አለኝ በኩራት - ካድሬው ወዳጄ (“የዋህ” አልኩት በልቤ)“ኦባማ ልማታዊ መንግስት? ለመሆኑ ልማታዊ መንግስት ምን ዓይነት ነው?” ግራ ቢገባኝ ነዋ የጠየቅሁት፡፡
“እንደኛ ፓርቲ! ለኪራይ ሰብሳቢዎች ቦታ የለውም … ኪራይ ሰብሳቢነትንና ኒዮሊበራሎችን ይታገላል” (የኪራይ ሰብሳቢነት መገለጫዎች ይፋ ይሁኑልን!)
“እና የኦባማ መንግስት እንደናንተ ፓርቲ ነው?” (አስቆኛል ነገሩ!) “አልታገለም እንጂ እንደኛ ነው! ስግብግብ ነጋዴዎችን በታክስ ልክ ሊያስገቧቸው እኮ ነው!” አለ - በእልህ፡፡
(“ነው ብለህ ነው?” አልኩ በልቤ) ይሄ ወዳጄ አንድ ነገር ከያዘ ሙጫ ነው - አይለቅም፡፡ (ኢህአዴግ ስለሆነ ግን አይመስለኝም) በቃ ከራሱ ውጭ የሰው ሃሳብ አይሰማም፡፡ ይተናነቀዋል፡፡
ሃሳቡን የተቃወመ ወይም የተለየ ሃሳብ ያቀረበ ጠላቱ ነው - (የእናቱ ልጅም ቢሆን) ስለዚህ በዘዴ ጨዋታ አስቀየርኩት፡፡ ከደህና ወዳጄ መቀያየም አልፈልግማ! ከካድሬ ወዳጄ ከተለየሁ በኋላ ግን ኢህአዴግንና የኦባማን ፓርቲ (ዲሞክራት) በምን ተዓምር እንዳገናኛቸው እያሰብኩ መገረሜ አልቀረም፡፡ ለካስ ኢህአዴግን የማናወቀው እኛ ብቻ አይደለንም፡፡ አንዳንድ ካድሬዎቹም አያውቁትም፡፡
በነገራችሁ ላይ … አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ከ “ልማታዊ ባለሃብቶች” ጋር ውይይት ማድረጋቸው አስደስቶኛል፡፡
“የወደፊት ተስፋችን የተንጠለጠለው በናንተ ነው” ብለዋል (ተመስገን!) “ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶችስ?” የሚሉ ወገኖች አይጠፉም ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ ግን ከኪራይ ሰብሳቢዎች ጋር አይደራደርም! (አራት ነጥብ!)
እኔ የምለው ግን … ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚዎችንም ቢያወያዩ ጥሩ አይመስላችሁም? (በነካ እጃቸው ብዬ እኮ ነው!) “ግን ልማታዊ ተቃዋሚዎች”ን ማለቴ ነው! “በፖለቲካ እንቅስቃሴው መሳተፍ እንጂ ጣት መቀሰር ፋይዳ የለውም” ብለው የለ! አንድ መጥራት ያለበት ጉዳይ ግን ያለ ይመስለኛል፡፡
ለመሆኑ በአገራችን ምን ያህል ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች እንዳሉ ይታወቃል እንዴ? (በፐርሰንት ይነገረን!) እኔ በበኩሌ ምን ያህል ልማታዊና ኪራይ ሰብሳቢ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉ ጥናት ለማካሄድ ፈቃደኛ ነኝ - ስፖንሰር ከተገኘ! (ብቻ ስፖንሰርም ኪራይ ሰብሳቢነት ነው እንዳይባልና እንዳይገርመኝ) ራሱ ኢህአዴግ ስፖንሰር ይደረጋል እኮ!
አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ የኢህአዴግ ደጋፊ ባለሃብቶች ፎረም ምነው ድምፁ ጠፋ? ለኢህአዴግ ምን እንደምፈራለት ታውቃላችሁ … ፎረሙ በኪራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶች እንዳይሞላ!
እኔ የምለው … “የተቃዋሚ ደጋፊ ባለሃብቶች ፎረም” ለምንድነው የማይቋቋመው? በሰላማዊ መንገድ እስከተንቀሳቀሰ ድረስ እኮ ችግር የለም (ዕድሜ ለህገመንግስቱ!)
ጠ/ሚኒስትሩን ሥራ እንዳላበዛባቸው ብዬ እንጂ ጋዜጠኞችንም (እኔን ጨምሮ) ቢያወያዩ ጠቃሚ ይመስለኛል (“በሬ ወለደ” ማለታቸውን አልተውም እንዴ?)
መቼም እንደ ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች (“ልማታዊ ጋዜጠኞች”ን ማለቴ ነው) ትዕግስተኛ የለም፡፡ ከምሬ እኮ ነው! እስከ ዛሬ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር የመወያየት ዕድል ያላገኙት እነሱ ብቻ ናቸው፡፡ (መድልዎና መገለል ይብቃ!) ይኸውላችሁ 21 ዓመት ሙሉ መንግስት ከዳያስፖራ፣ ከወጣቶች፣ ከምሁራን፣ ከአርሶ አደሮች፣ ከሴቶች … ከአርቲስቶች ወዘተ … ማን ያላወያየው አለ? ጋዜጠኞች ግን ይሄን ዕድል ተነፍገዋል፡፡
(ለኢትዮጵያ ህዳሴ አናስፈልግም እንዴ?) ግን እኮ … ጋዜጠኞችም እንደ ምሁራን ቤት መስሪያ መሬት ይፈልጋሉ … ከታክስ ነፃ መኪና ማስገባት ቢፈቀድላቸውም አይጠሉም፡፡
ኧረ ብዙ የመብት ጥያቄዎች አሉን (ፖለቲካዊ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ!) የሙያ መብት ጥያቄም እኮ ነበረን፤ ግን ይሄኛው ይቀድማል ብዬ ነው፡፡ እናም አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ያወያዩን!! (ጋዜጣዊ መግለጫ ሳይሆን ውይይት!)
በነገራችሁ ላይ የግል ፕሬሱ ከመንግስት ጋዜጠኞች ጋር የመወያየት ፍላጐት እንደሌለው ልገልፅ እወዳለሁ (ጦር ይዘው እንደማይመጡ እኮ እናውቃለን) ግን በቃ አይመቹንም፡፡
(መድረክ ኢዴፓ እንደማይመቸው ማለት ነው!) ጠ/ሚኒስትሩ የራሳቸውን ሚኒስትሮች ማወያየቱንም እንዳይዘነጉት አደራ እላለሁ፡፡ እነሱን ካላወያዩ እኮ ሌላው ሁሉ ዋጋ የለውም!!

Read 2811 times