Saturday, 10 December 2022 13:32

የሰላም ሥምምነቱ ህይወት ተከፍሎበታል!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(1 Vote)

   - ኢትዮጵያ ሁሌም የምታተርፈው ከዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ነው
     - የተመድ ዋና ኃላፊ ጉቴሬዝ በአዲስ አበባ ከጠቅላዩ ጋር መክረዋል
     - አሜሪካ ለመልሶ ግንባታው የ10 ቢ. ዶላር ድጋፍ ቃል ገብታለች
     - ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ህብረት ሞገስ ማግኘት አስተዋፅኦ አድርጋለች
          
       የዘንድሮ የፅዮን ማርያም ክብረ በዓል በርዕሰ አድባራትወ ገዳማት አክሱም ፅዮን በድምቀት ተከብሯል - ባለፈው ህዳር 21 ቀን 2015 ዓ.ም። ከብረ በዓሉ በድምቀት የተከበረው ከሁለት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡ በአገሪቱ በነበረው ጦርነት ምክንያት ያለፉት የፅዮን ክብረ በዓላት እንደ ከዚህ ቀደሙ ህዝበ ክርስቲያኑ ተገኝቶ ባያከብረውም፤ አሁን ላይ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አዲስ ተስፋና ደስታን የፈጠረ መሆኑን የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል፡፡
“በሚቀጥለው ዓመት ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት በሚሳተፉ የበዓሉ አክባሪዎች እንዲሁም በውጭ ቱሪስቶች ታጅቦ ይከበራል” ሲሉም የበዓሉ ታዳሚዎች ተስፋቸውን ለኢቲቪ ገልፀዋል፡፡
ላለፉት ሁለት ዓመታት ግን በተለይ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍሎች ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትን ተሰባስቦ በድምቀት ማክበር  እንደ ቅንጦት የሚቆጠር ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ እየሄዱ ለፈጣሪ ፀሎት ማድረስም የማይታሰብ ነበር፡፡
ለ2 ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሽ ጦርነት፤ የብዙ መቶ ሺዎችን ህይወት ከመቅጠፉም ባሻገር ሚሊዮኖችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ ዜጎች በምግብ እርዳታ እጥረት ለረሃብና ለህልፈት ተዳርገዋል፡፡ በመድሃኒትና የህክምና አገልግሎት አለመኖር ሳቢያም ብዙዎች በቀላሉ ሊድኑ በሚችሉ በሽታዎች ጭምር ህይወታቸው ማለፉን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ የሰሜኑ አስከፊ  የእርስ በርስ ጦርነት በህዝባችን ላይ ያደረሰው እልቂትና መከራ በአጭር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ ባጠቃላይ የዜጎችን  ህይወት ሲኦል አድርጎት ነበር ማለት ይቻላል፡፡
የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መግባታችንን አይተው ድንበራችንን የደፈሩ  ጎረቤት አገራትም አልጠፉም - የደረሱልን ያሉትን ያህል፡፡ ዓለም ባልጠበቅነው ሁኔታ ፊቱን አዙሮብን ነበር - በጦርነቱ ወቅት፡፡ ፊት ማዞር ብቻ ቢሆን ደግ ነበር፡፡ እጅ ጥምዘዛው፤ ጫናው፤ ተፅዕኖው፤ ማዕቀቡ፤ ስም ማጠልሸቱ፤ ማስፈራሪያው ወዘተ እንደ ጉድ ተፈራርቆብናል፡፡ ነገርዬው ማንም ከሚያስበውና ከሚገምተው በላይ ነበር፡፡ እጅግ ፈታኝና እልህ አስጨራሽ!!
 በዶላር የፈረጠሙ ኃያላን መንግስታትና ዓለማቀፍ ተቋማት እንዴት ደካማ አገራትን እንዳፈረሱና በቁጥጥራቸው ሥር እንዳስገቡ በተግባር የተማርንበትም አጋጣሚ ነበር፡፡  ከጦርነቱ ባልተናነሰ ድህነታችንና የልመና ስንዴ ጠባቂ መሆናችን የቱን ያህል ጥገኛ እንዳደረገን ያስተዋልንበት መልካም አጋጣሚም ነው - ከተማርንበት፡፡
ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው ህወሓት ቢሆንም፤ በኋላ ላይ ግን በርካታ  አገራትና መንግስታት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሰበብ አገራችንን ለማፍረስ ተደጋጋሚ ሙከራ  ሲያደርጉ አስተውለናል - በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፡፡ ሆኖም በፈጣሪ ተዓምርና በመከላከያ ሠራዊታችን የሕይወት መስዋዕትነት ከተጠመደልን ወጥመድ ተርፈናል፡፡ ኢትዮጵያ ከመፍረስ ድናለች፡፡
 ለዛሬው የሰላም ብሩህ ተስፋ የደረስነው ግን በማንም መልካም ፈቃድና ፍላጎት አይደለም። በቆራጥነትና በመስዋዕትነት ነው፡፡ የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት የትዕግስታችን፣ የፅናታችንና የቁርጠኝነታችን ፍሬም ነው፡፡ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሃቅን የሙጥኝ ማለታችን፣ በሃላፊነትና በተጠያቂነት መንቀሳቀሳችን፣ ሃሰተኛ መረጃና ፕሮፓጋንዳ አለማሰራጨታችን፤ ለምዕራባውያን ፍላጎት አለማደራችን---ለጊዜው ጎድቶን ይሆናል፤ የማታ ማታ ግን ከፍሎናል፤ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ታድጎልናል፡፡
በደቡብ አፍሪካዋ መዲና ፕሪቶርያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ለፍሬ እየበቃ ነው፡፡ አንድ ወር ባልሞላ  ጊዜ ውስጥ የጦርነቱ ተጠቂ በነበሩ አካባቢዎች ተዓምራዊ ለውጥ እየታየ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ህዝቡ የጥይት ድምፅ ሳይሰማ ማደሩ ትልቅ ድል ነው፡፡ በበርካታ አካባቢዎች የስልክና መብራት አገልግሎቶች በማይታመን ፍጥነት ዳግም አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን እየሰማን ነው፡፡ መቀሌን ጀምሮ በርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡  የምግብና የመድሃኒት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል ያለ ገደብ እንደ ልብ  እየገባ ነው - በምድርም በየብስም!! ከዚሁ ጎን ለጎን የህውሓት ሃይሎችን ትጥቅ የማስፈታት እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን ለመከላከያ የማስረከብ ሂደት መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ በቀጣዮቹ ቀናት መከላከያ መቀሌ እንደሚገባም ታውቋል፡፡
እኒህ ሁሉ ደግሞ  የሰላም ስምምነቱ ትሩፋቶች  ናቸው፡፡ በእርግጥም በሰላም ስምምነቱ ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለምን ቢሉ? ኢትዮጵያ ሁሌም የምታተርፈው ከሰላም እንጂ ከጦርነት አይደለም፡፡  
የሰላም ስምምነቱ በተፈረመ ማግስት፣ ለአማፂው ቡድን ህወሓት  በመወገን  የሚታማው የአውሮፓ ህብረት፣ ለኢትዮጵያ መልሶ ግንባታ የ30 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ አድርጓል - በጦርነቱ ለፈራረሱ ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት ግንባታ የሚውል፡፡ በገንዘብ ድጋፉ እንደሚቀጥልበትም ነው ህብረቱ ያስታወቀው። የአሜሪካ መንግስትም ለትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች የመልሶ ግንባታ ስራ የሚውል የ10 ቢ. ዶላር ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብቷል፡፡ በጦርነቱ ወቅት እጁን ሰብስቦ የቆየው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) እንዲሁ የ10 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተሰምቷል፤ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች፡፡  እኒህ ክንደ ፈርጣማ መንግስታትና ተቋማት፣ ይህን ሁሉ ድጋፍ እያደረጉ ያሉት ኢትዮጵያ በማሸነፏ እንደሆነ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሁሌም የምታሸንፈው ደግሞ በግዛቷ ሰላምን ስታሰፍንና ከእርስ በርስ ጦርነት ራሷን ስታቅብ  ለመሆኑ  ይሄ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግስታት ትልቁ ሰውዬ (አድራጊ ፈጣሪው) በሸገር ድንገት  ተከስተው ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መክረዋል። አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያቸው ነው። እስከ ዛሬ ሰውየው ስለ ኢትዮጵያ ደጉንም ክፉውንም ሲናገሩ የቆዩት ከተቀመጡበት አገር ሆነው ነበር፡፡ የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን ተከትሎ ግን  አዲስ አበባ ድረስ መጥተዋል፡፡ ለምን ቢሉ? ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናታ!!
በሌላ በኩል፤ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ፣ የጋራ ብልጽግና እና ልማት ጉዳዮች ጸሐፊ የሆኑትን ሚኒስትር ጀምስ ክሌቨርሊን በሐዋሳ ከተማ አነጋግረዋል። ውይይቱ ከወቅታዊ ጉዳዮች በተጨማሪ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጓል ተብሏል። እንዴት ቢባል? ኢትዮጵያ አሸንፋለቻ!
ከላይ እንዳልነው የደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት የማንም ችሮታ አይደለም - በህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የህይወት መስዋዕትነት ብቻ በቂ አልነበረም፡፡ ከምዕራቡ ዓለምና ከዓለማቀፍ ተቋማት ይደርስብን የነበረውን ዲፕሎማሲያዊ ጫናና ተጽዕኖ ለማሸነፍ የተለየ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ ትዕግስትና ጥበብ ይጠይቅ ነበር፡፡ እኒህ ባይኖሩን ኖሮ ዛሬ የደረስንበት ብሩህ የሰላም ተስፋ ላይ መድረስ እንደምንችል አጠራጣሪ ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት እነ አሜሪካና አውሮፓ ሲያደርሱብን የቆዩትን  እልህ አስጨራሽ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎችና ተፅዕኖዎች በጥበብ ባይመክተው  ኖሮ፣ የከፋ ሁኔታ ውስጥ ልንወድቅ እንችል ነበር፡፡ እንደ ጥንቱ የኢህአዴግ ባህል፣ ለእያንዳንዱ የእነ አሜሪካ ማስፈራሪያና እጅ ጥምዘዛ ምላሽ ለመስጠት ቢሞከር ኖሮ፣ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች ነው። ምናልባትም ለአፍሪካ ቀንድ ስጋት የሆነ “አደገኛ የአምባገነን አገዛዝ” የሚል ታፔላ በመለጠፍ፣ የሃይል እርምጃ ሊወስዱብን ሁሉ ይችሉ ነበር። ሆኖም የኢትዮጵያ መንግስት ትዕግስትን፣ ፅናትንና ቁርጠኝነትን መሳሪያው በማድረግ፣ እነዚያን ክፉ የወጀብ ጊዜያት በጥበብ አሳልፏል።
በሌላ በኩል፤ በመንግስትና ህወሓት መካከል በተደረገው የሰላም ድርድር ውስጥ እጃቸውን በቀጥታ ለማስገባት የጓጉ አያሌ የምዕራብ አገራት የነበሩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግስት “ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚል የፀና አቋሙ መንገዱን ሊዘጋባቸው ችሏል። በዚህም የአፍሪካ ህብረት በሙሉ ሃላፊነትና ተጠያቂነት የሰላም ድርድሩን በመምራት ለስኬት በቅቷል - በቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴንጎ ኦባሳንጆ ዋና አደራዳሪነት።
በነገራችን ላይ አፍሪካ ህብረት ግጭቶችን በመፍታትም ሆነ ተፋላሚዎችን በማደራደር ከዚህ ቀደም ያስመዘገበው ስኬት የለም በሚል ለአደራዳሪነት የአውሮፓና አሜሪካ ተቋማትን ወይም መንግስታትን የሚመርጡ አያሌ ናቸው። የአፍሪካ ፖለቲከኞችን ጨምሮ። ለምሳሌ ከጥቂት ወራት በፊት ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የኦፌኮ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና፤ አፍሪካ ህብረት፣ ህወሓትና መንግስትን የማደራደር  አቅምና ብቃት አለው ብለው እንደማያምኑ  ጠቁመው፤ ድርድሩ በሌሎች አቅምና ኃይል ባላቸው የአውሮፓ አገራት ወይም መንግስታት ቢደረግ እንደሚመርጡ ተናግረዋል። (ህወሓትም ቢሆን የግድ ሆኖበት እንጂ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት ለመደራደር ፈቃዱ አልነበረም፡፡)
የሚገርመው ነገር፣ ፕሮፌሰሩ፣ በአገር ውስጥ በገለልተኛነቱ እምነት የሚጣልበት  አደራዳሪ የለም ብለው ነው የሚያምኑት። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም ጭምር  አለ ብለው የሚያምኑ አይመስሉም። በቅኝ እንደተገዙት አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ለማናቸውም ችግሮችና መፍትሔዎች ወደ ነጮቹ ነው የሚያነጣጥሩት (ያሳዝናል!)፡፡
ከዚህ በተቃራኒው በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት በአፍሪካ ህብረት ላይ ፅኑ እምነት አለው፤ በግድቡ ጉዳይም ሆነ በድርድሩ “ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ ነው በቁርጠኝነት የሚያቀነቅነው፡፡ ይህ መርህ በተለይ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ከመቀንቀኑ የተነሳም የምዕራብ አገራትም ሆኑ ዓለማቀፍ ተቋማት መርኹን ለመቀበልና ለመደገፍ ተገደዋል፡፡ እናም ኢትዮጵያ የሙጥኝ ብላ የሰላም ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት እንዲካሄድ በማድረጓ፣ አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ለዓለም አረጋግጠዋል፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የአፍሪካ ህብረት፣ በዓለም መድረክ ሞገስ እንዲያገኝ ኢትዮጵያ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጋለች ማለት ይቻላል፡፡ ከእንግዲህ በአፍሪካ ውስጥ ግጭት በተነሳ ቁጥር ወደ አሜሪካና አውሮፓ ማንጋጠጥ የግድ አይሆንም፡፡
እናም ብዙዎች እንደሚስማሙበት፤ በደቡብ አፍሪካው የሰላም ስምምነት ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ለማጽናትና ለማዝለቅ ግን ከፊታችን ብዙ የቤት ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው ሐሙስ በአዋሳ በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ላይ እንዳሉት፤ ሰላም በሰሜን ፣ ሰላም በደቡብ፣ ሰላም በምዕራብ፣ ሰላም በምሥራቅ፣ ሰላም በመላው ኢትዮጵያ ማስፈን ይጠበቅብናል፡፡ ኦሮሚያን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዘር ተኮር ጥቃት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማክተም አለበት፡፡ ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው ሰርተው የመኖር መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል፡፡ በመጨረሻም ለሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የምትመች የበለጸገች ሀገር መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ያኔ ነው ኢትዮጵያ በዘላቂነት የምታሸንፈው፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!!   

Read 690 times