Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 October 2012 10:05

በየዓመቱ ሚሊዮኖችን የሚቀጥፍ ገዳይ በሽታ Featured

Written by 
Rate this item
(13 votes)

HIV በደም የመተላለፍ ዕድሉ 0.3% ሲሆን ሔፓታይተስ ቢ ግን 30% ይደርሳል፡፡
በሆስፒታሎች የሚሰጥ ደም በሽታው በጤና ተቋማት ውስጥ ለሚገኙ የህክምና ባለሙያዎች ሥጋት ሆኗል
በአንዳንድ ሆስፒታሎች የህክምና ባለሙያዎች ክትባቱን መውሰድ ጀምረዋል፡፡
በሽታውን ሊያስተላልፍ ይችላል
በህይወት ለመኖራችን እጅግ ወሳኝ ከሆኑትና በሰውነታችን ውስጥ በርካታ ተግባራትን ከሚያከናውኑት የሰውነት ክፍሎቻችን አንዱ ጉበት ነው፡፡ ጉበት በሰውነታችን ውስጥ ከሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሰውነት መከላከያ ኃይል የሆነውን ንጥረ ነገርና ፕሮቲን ማምረት፣ ለሰውነታችን አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ማከማቸትና አላስፈላጊዎቹን በአግባቡ እንዲወገቡ ማድረግ፣ ለደም መርጋትም ይሁን አለመርጋት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን ማምረትና ቀይ የደም ሴሎቻችን በሰውነታችን ውስጥ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ፈጽመው በሚሞቱበት ወቅት እንዲወገዱ የማድረግ ተግባራት የሚከናወኑት በጉበታችን ነው፡፡


የአንድ ነጥብ አምስት ኪሎግራም ክብደት ያለው ጉበታችን በተለያዩ ምክንያቶች ጤናው ሊታወክ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ የተለመደ ተግባሩን ማከናወን ይሳነዋል፡፡ በዚህ ጊዜም በሰውነታችን ሥርዓቶች ውስጥ ከፍተኛ የጤና መታወክ በመፍጠር እስከ ሞት ሊደርስ የሚችል አደጋ ያስከትላል፡፡
ጉበት በተለያዩ ምክንያቶች በኢንፌክሽን ሊጠቃ ይችላል፡፡ ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል ዋንኞቹ የተለያዩ መድሃኒቶችን (ኪኒኖችን) በመውሰድ፣ የተበከለ ምግብና መጠጥ በመጠቀም፣ የአልኮል መጠናቸው ከፍተኛ የሆነ መጠጦችን በብዛትና በተከታታይ መውሰድ፣ የጉበት ደም መተላለፊያ ቱቦ መዘጋትና የጉበት ሲል የውሃ መቋጠርና በቫይረስ የሚከሰት የጉበት ኢንፌክሽኖች ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል በቫይረስ አማካኝነት በሚከሰት ኢንፌክሽንየ የሚፈጠረው የጉበት በሽታ ሰፊ ሥፍራ ይይዛል፡፡
ከጤናጥበቃ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት የጉበት በሽታ ሰባት የተለያዩ ዓይነቶች አሉት እነዚህም ሔፓታይተስ ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ፣ ኢ፣ ጄ እና ሔፓይተስ ቲ የተባሉት ናቸው፡፡
በተከበለ ውሃና በተበከሉ ምግቦች የሚተላለፈው የሔፓይተስ አይነት ሔፓታይተስ ኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ይህም በአብዛኛው ህፃናትና እድሜያቸው በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ያጠቃል፡፡ በዚህ ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው የጉበት በሽታ በአብዛኛው ለሞት የሚዳርግ አይደለም፡፡ በሽታውንም የምግብና የመጠጥ ውሃን ንጽህና በመጠበቅ መከላከል ይቻላል፡፡
ዛሬ በዚህ ጽሑፍ የምናተኩረው እጅግ በርካቶችን ለህልፈተ ህይወት በማብቃቱና በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በመሆኑ የሚታወቁት ሔፓታይተስ “ቢ” እና ሔፓይታይተስ “ሲ” የተባሉ የጉበት በሽታ ( በአገራችን በተለምዶ የወፍ በሽታ እየተባለ በሚጠራው) አይነቶች ናቸው፡፡
ይህ ኢንፌክሽን ለጉበት ካንሰር በሽታ ዋንኛ መንስኤ በመሆንም ይታወቃል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በዓለም ላይ በሔፓታይተስ ቢ እና ሲ በሽታዎች የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 550 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ጉበት ካንሰርነት ተቀይረዋል፡፡
ሔፓታይተስ ቢ ቫይረስ በተለያዩ መንገዶች ከህመምተኛው ሰው ወደ ጤነኛው ሰው ይተላለፋሉ የበሽታው የመተላለፊያ መንገዶች ከ ኤችአይቪ ቫይረስ የመተላለፊያ መንገዶች ጋር በአብዛኛው ተመሳሳይነት አላቸው፡፡ በሔፓታይተስ ቢ በሽታ ከተያዘ ሰው ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ፣ በደም ንኪኪ ማለትም በሽታው ያለበት ሰው በተወጋበት መርፌና ስለታም ነገር መጠቀም (አደንዛዥ እፆችን በአንድ መርፌ በጋራ መውሰድ)ና በመፀዳጃ ቤት በጋራ መጠቀም ዋንኞቹ የተመላለፊያ መንገዶች ሲሆኑ በሽታው ያለባት ነፍሰ ጡር እናት ለጽንሱ በሽታውን ታስተላልፋለች፡፡ በሽታው በአብዛኛው የሚታየው የወጣትነት ዕድሜን ባለፉ ሰዎች ላይ ሲሆን በሽታው ፆታን አይመርጥም፡፡
የሔፓታይተስ ቢ በሽታ መኖሩ ከተረጋገጠ ከህመምተኛው ጋር የደም ንኪኪ ከማድረግ መቆጠብ አስፈላጊ ሲሆን የተለያዩ ንኪኪዎችን ከህመምተኛው ጋር የሚደረጉ ሰዎች ክትባቱን መውሰድ ይኖርባቸዋል፡፡
በተለይም ነፍሰጡር ሴቶች ቫይረሱ እንዳለባቸው ካወቁ ክትባት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በሽታ የመተላለፍ እድሉ ከሌሎች በሽታዎች ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ኤችአይቪ ቫይረስ በደም የመተላለፍ እድሉ 0.3 %ሲሆን የሔፓታይተስ ቢ 30% ይደርሳል፡፡ ይህም እጅግ በጣም ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ በሽታ እንደሆነ አመላካች ነው፡፡ የሔፓታይተስ ቢ በሽታ የመከላከያ ክትባት የለው መሆኑ በበሽታው የመያዝ ሥጋቱን በመጠኑ ይቀንሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ክትባቱ እንደልብ በየትኛውም ያጤና ተቋማት ውስጥ የሚገኝ አለመሆኑና ክትባቱን ለማግኘት የሚከፈለው ክፍያም በአብዛኛው ሰው በቀላሉ የሚቻል አለመሆኑ የብዙዎች ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡
የሔፓታይተስ ቢ በሽታ በወቅቱ ታውቆ ሕክምና ካልተደረገለት የጉበትና የስኳር በሽታዎችን የሚያስከትል ሲሆን ወደ ካንሰር የመቀየር እድሉም ከፍተኛ ነው፡፡ በሔፓታይተስ “ቢ” በሽታ የተያዘ ሰው የምግብ ፍላጐት አይኖረውም፡፡
ሰውነቱን ድካም ድካም ይለዋል፣ የዐይኑ ውስጣዊ ክፍል ወደ ቢጫነት ያደላል፣ የሽንት ቀለሙ ይደፈረሳል፡፡ በቀኝ ጐኑ በኩል የህመም ስሜት ይኖረዋል፡፡
የጥፍርና የቆዳ ቀለሙም ቢጫ ይሆናል፡፡ እነዚህን ምልክቶች ያሳየ ህመምተኛ በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋማት መሄድና ተገቢውን ምርመራና ሕክምና ማድረግ ይኖርበታል፡፡ በወቅቱ ታውቆ ምርመራና ህክምና የተደረገለት በሽተኛ የመዳን እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡
ሔፓታይተስ “ሲ” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የጉበት በሽታ ደግሞ በአብዛኛው የሚላለፈው በቀጥታ የደም ለደም ንኪኪ በማድረግ ሲሆን ይህ በሽታ በሆስፒታሎች ለህሙማን በሚሰጥና ጤናማነቱ ባልተመረመረ ደም አማካኝነት ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በአነስተኛ ደረጃ በግብረሥጋ ግንኙነት ወቅትም ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ይህ በሽታ ወደ ጉበት ካንሰር በሽታ የመቀየር እድሉ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ከሰባቱ የሔፓታይተስ በሽታ አይነቶች መካከል እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት እያደረሱ የሚገኙት እነዚህ ሁለቱ ሔፓታይተስ ቢ እና ሲ የተባሉ ኢንፌክሽኖች ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንፌክሽኖች በአንድ ሰው ላይ በተናጠል ወይንም በጋራ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
ሁለቱ የኢንፌክሽንአ ይነቶች በጋራ የተከሰቱበት ሰው እጅግ ከፍተኛ ለሆነ ስቃይ የሚጋለጥ ከመሆኑም በላይ በሽታው ወደ ክሮኒክ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡
በሽታው በተለይም በርካታ ሰዎች ተሰባስበው በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፣ በሆስፒታሎችና ጤና ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ ሰዎች በጋራ በሚኖሩባቸው ዶርሞች፣ ካምፖች፣ ውስጥ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ ሥጋቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህንን ሥጋት ለመቀነስም አሁን አሁን ክትባት መውሰድ እየተለመደ መጥቷል፡፡
በሆስፒታሎችና የጤና ተቋማት ውስጥ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን መውሰድ ጀምረዋል፡፡ ከዓመታት በፊት ለህፃናት በሚሰጡ ፀረ ስድስት ክትባቶች ውስጥ እንዲካተት የተደረገውን ይህንኑ የሒፓታይተስ “ቢ” ክትባት ዛሬ ዛሬ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሰዎች እየወሰዱ ነው፡፡
የሔፓታይተስ በሽታ በተለያዩ መንገዶች ሕክምና መስጠት የሚቻል ሲሆን ለህክምናው የሚጠይቀው ክፍያ ግን ከበድ ያለ ነው፡፡
እስከ አንድ አመት ለሚደርስ ጊዜ ለሚሰጠው ለዚህ ህክምና ከ100ሺህ ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ሲሆን ህክምናውም ሆነ ክትባቱ በአገራችን በመሰጠት ላይ ነው፡፡
የበሽታውን ስርጭት ለመግታትና በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥርን ለመቀነስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልግ ሲሆን ጥንዶቹ ጋብቻቸውን ከመፈፀማቸውም በፊት ምርመራ ማድረግ እንደሚገባቸው የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል፡፡

Read 15585 times Last modified on Saturday, 27 October 2012 10:11