Saturday, 17 December 2022 13:17

አዲስ አበባ፤ “ኧረ የሰው ያለህ” ማለት ያለባት አሁን ነው

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  አገሮች የተመሰረቱት ከአንድ አካባቢ የተነሳ ኃይል ሌላውን በጉልበት በመውረርና በማስገበር ወይም በስምምነት እንዲገብር በማድረግ ነው።
ጀርመን የተመሰረተችው ከ1863 እስከ 1910 ዓ.ም ድረስ በተካሄደ ጦርነት ነው። የጦርነቱ ቀስቃሽና አስገባሪ ኸሩሽያ ነበረች።
13ቱ የአሜሪካ ግዛቶች በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ላይ አምጸው በ1768 ነጻነታቸውን አወጁ። ከእንግሊዝ ጋር የሰላም ስምምነት ባደረጉ ጊዜ ከፑልቹን ተራራ እስከ ሚስስፒ ወንዝ፤ ከካናዳ እስከ እስፓኒሽ ፍሎሪዳ ድረስ ያለውን አገር እንግሊዝ ሰጠቻቸው። የባርነት ስርዓት እንደነበረው እንዲቀጥል የሚፈልጉት ደቡቦች ከህብረቱ ተገነጠሉ። ከ1854 እስከ 1857 ዓ.ም ባለው ጊዜ አሜሪካኖች የእርስ በእርስ  ጦርነት አድርገው ጦርነቱ በኅብረቱ አሸናፊነት ተጠናቀቀ። ድል አድራጊዋ የተባበረችው አሜሪካ፤ የካሊፎርኒያን፣ የኢቫዳንን፣ የዋሽንግተንን፣ የኦሪጋንን ወዘተ ግዛቶች በኃይል የአሜሪካ አካል አደረገች። ፍሎሪዳን ከእስፔን፣ አላስካን ከሩሲያ ወዘተ ብዙ ሚሊዮን ዶላር በማውጣት በግዥ የግዛታቸው አካል አድርገዋል። በ15 ሚሊዮን ዶላር ኒውኦርሊንስንና ሉዚያናን ለአሜሪካኖች የሸጠላቸው እውቁ የጦር መሪ ናፖሊዮን እንደሆነ መጥቀስም ያስልጋል። እንዲህም ነው አሜሪካኖች አሜሪካን ትልቅና ኃያል ሀገር አድርገው የገነቧት።
ሊሰመርበት የሚገባው በጉልበትም ሆነ በግዥ የአሜሪካ አካል ከተደረጉት ግዛቶች ውስጥ አንዱም በጉልበት ነው የተያዝኩት እና የቅኝ ግዛት የተደረኩት፤ እንደ እቃ ተሽጬ የተባበሩት የአሜሪካ ግዛት አባል የሆንኩት ብሎ የነጻነት ጥያቄ ሲያነሳ አመጽ ሲቀሰቅስ ተሰምቶ አይታወቅም። የጆሴፍ ስታሊን የብሔረሰብ ጥያቄ መጽሐፍ ከእኛ በፊት ቀድሞ እነሱ አገር የደረሰ ቢሆንም፣ ከማንም ዘንድ የተከፈተ ጀሮና ልብ አግኝቶ አለማወቁም የታመነ ጉዳይ ነው።
ወደ እኛ ሀገር እንግባ። ደጃዝማች ካሣ፣ ደጃዝማች ውቤን አሸንፈው ዳግማዊ ቴዎድሮስ ተብለው ነገሱ። በዘመነ መሳፍንትና ከዚያም ቀደም ብሎ  የተበታተነውን የኢትዮጵያን ግዛቶች በአንድ ማዕከላዊ መንግሥት ስር የማምጣት ዘመቻቸውን ጀመሩ። አፄ ዮሐንስ ግዛት የማስፋፋት እድል ስላልነበራቸው አልገፉበትም። ዳግማዊ ዐጼ ምኒልክ ግን የዐፄ ቴዎድሮስን ሀሳብ ይዘው ጥንት የኢትዮጵያ ግዛት የነበሩትን አካባቢዎች ወደ አንድ ኢትዮጵያ የማምጣቱን ስራ ቀጠሉ።
እንደ ጅማው አባጃፋር ካሉት ጋር ተደራድረው፣ እንደ ወላይታው ደጃዝማች ጦና  ካሉት ጋር ደግሞ ተዋግተው የዛሬዋን ኢትዮጵያን መሰረቱ።
በጦርነትና በድርድር አገር ሆኖ በመመሥረት ኢትዮጵያ ከዓለም የተለየች አገር ባትሆንም፣ የአገረ መንግስቱን ምስረታ መቀበል ባለመቻልና ባለመፈለግ፣ አገሪቱ በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ ኖራለች። እየታመሰችም ትገኛለች።
እንደ ሌሎች አገሮች ሁሉ የአገረ መንግሥቱን አመሠራረት በመቀበልና በመጠበቅ፣ ተጓድሏል ተበላሽቷል የተባለውን ስርዓት በማረምና በማስተካከል አገርን በፖለቲካ ባህል፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳይ አሳድጎ ጠንካራና የተከበረች አገር ከማድረግ ይልቅ ስራዬ ተብሎ የተያዘው አገርና መንግስትን በማዳከም በውዝግብ ውስጥ እንድትቀጥል ማድረግ ነው። ሰሞኑን በአዲስ አበባ የሚታየው ሁኔታ የዚህ ችግር (በሽታ) ቅጥያ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ጽ/ቤት መቀመጫ ናት። የህብረቱን ህልውና የሚያናጋ ክብሩን ዝቅ የሚያደርግ ሥራ በነዋሪዎቹ እንዲፈጸም የኢትዮጵያ መንግሥት አይፈቅድም፤ ሊፈቅድም አይችልም። ይህን አለማድረጉ ደግሞ ጽ/ቤቱ በኢትዮጵያ እንዲቆይ ምንጊዜም ያስችለዋል። እጋፋለሁ ቢል መገፋቱ አይቀርም።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ዋና ከተማ  የሆነችው አዲስ አበባ፤ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ ተደርጋለች። እኔ እስከምረዳው ድረስ አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማነቷ ለቢሮ መቀመጫነት እንጂ፣ እንደ ሌላው የከተማ አስተዳደር አዲስ አበባን የመያዝና የመምራት መብት አለው ማለት አይደለም። ለዚህ ስራና ኃላፊነት ማለትም ከተማውን ለማስተዳደር በህግ  የቆመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው።
የኦሮሚያ ክልል በጀት  የሚያስተዳራቸው ት/ቤቶች በአዲስ አበባ ካሉ፣ እነሱም በአዲስ አበባ የሚገኙ የኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ስለሚሆኑ የኦሮሚያን ክልላዊ መንግስት መዝሙር ቢዘምሩ መብታቸው ነው፤ ሊከለከል አይገባም። የአዲስ አበባ አስተዳደር በጀት መድቦ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የሚያስተዳድራቸው ትምህርት ቤቶች ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር ትምህርት ቤቶች ናቸው። ስለዚህም የኦሮሚያ መዝሙር የመዘመር ግዴታ ሊጫንባቸው አይገባም። እንዲፈጽሙ የሚያስገድዳቸውም ምክንያት የለም።
ከንቲባ አዳነች አበቤ፤ “በአዲስ አበባ የኦሮምኛ ቋንቋን እያስተማርን ነው። የምንጠቀመው የኦሮሚያ ክልልን የትምህርት ካሪኩለም ነው።  ካሪኩለሙ የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት መዝሙር ማዘመርን ግድ ያደርጋል እና የምናዘምረው በዚህ ምክንያት ነው” ሲሉ የሰጡት መግለጫም፣ ችግር ከተፈጠረ በኋላ የግድ ምክንያት ለማግኘት የተደረገ ሙከራ ነው። “ከእውነት የመሸሻ ምክንያት” ማለት ቢባል ነገሩን ይበልጥ ይገልጠዋል ብዬ አምናለሁ። የአዲስ አበባ  አስተዳደር ኦሮምኛን ማስተማር ከፈለገና አስቦ የያዘው አጀንዳ ከሆነ ለምን የራሱን ማስተማሪያ አስቀድሞ አላዘጋጀም ብሎ ከንቲባዋን መጠየቅም ያስፈልጋል።
ከንቲባዋ በግልጽ መናገር ያለባቸው የከተማ መስተዳደሩ፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ት/ቤቶችን እያስተዳደረ መሆን አለመሆኑን ነው። እያስተዳደረ ከሆነ ደግሞ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ተጽዕኖ ወይም ጣልቃ ገብነት “እዚያው በጸበልህ” ሊባል ይገባል።
አዲስ አበባ እንደ ፌደራል ዋና ከተማ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ድረስ ያሏትን ት/ቤቶች እንደ አዲስ አበባ ንብረት ለመረዳት አለመፈለግ በፈጠረው ችግር፣ ተጠያቂ የአዲስ አበባ አስተዳደር መሆኑ መታወቅ አለበት።
ስለዚህም የአዲስ አበባ አስተዳር የጉልበት እርምጃውን አቁሞ ትምህርት ቤቶች ሰላም እንዲያገኙ ያደርግ ዘንድ አጥብቄ አሳስባለሁ። ከንቲባ አዳነችና ካቢኔያቸው፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤትና ልዩ ልዩ ቢሮዎች ወደ ሕዝብ የሚያወርዷቸውን ጉዳዮች ከቢሯቸው ከማውጣታቸው በፊት አጥብቀው ሊያስቡባቸው እንደሚገባ መጠቆም እወዳለሁ።
በኢትዮጵያ መሬት በየትኛውም አካባቢ የሚፈጠር ችግር የአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ችግር ነው። የአዲስ አበባ ችግርም ተመልሶ የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ነው። የአዲስ አበባ ምክር ቤት ይህንን የማይረዳ ከሆነ እግዚኦ ያሰኛል።
አዲስ አበባ፤ “ኧረ የሰው ያለህ” ማለት ያለባት አሁን ነው።

Read 2991 times