Saturday, 31 December 2022 12:01

ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ሃሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እያዘጋጁ ሲሸጡ የነበሩ 3 ግለሰቦች  በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ መታወቂያዎቹን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ማህተሞችና  ወረቀቶችም በብርበራ መያዛቸው ተጠቁሟል፡፡  
 ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶብስ ተራ አካባቢ ነው። ተጠርጣሪዎቹ ለዚሁ ህገ-ወጥ ተግባር ማስፈፀሚያ የሚውሉ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 አስተዳደር ጽ/ቤት እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የቀበሌ 01 አስተዳደር ጽ/ቤት የሚሉ ሃሰተኛ ክብ ማህተሞችን እንዲሁም የግለሰብ የስም ቲተር በማስቀረፅና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርማ ያረፈበትን የመታወቂያ ወረቀት አመሳስለው በማሳተም ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር በምርመራ ተረጋግጧል፡፡
ማህተሞቹንና ወረቀቶቹን በአንድ የሸቀጣሸቀጥ መሸጫ ሱቅ ውስጥ ደብቀው በማስቀመጥ የነዋሪነት መታወቂያ ለሚፈልጉ ሰዎች ሃሰተኛ መታወቂያዎችን እያዘጋጁ እንደሚሸጡ ከህብረተሰቡ በተገኘ ጥቆማና ፖሊስ ባደረገው ክትትል 3 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራ ሲሆን፤ ሃሰተኛ መታወቂያውን ለማዘጋጀት የሚጠቀሙባቸው ወረቀቶችና ማህተሞችም ከተደበቁበት በብርበራ እንደተገኙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

Read 4493 times