Saturday, 31 December 2022 12:19

የወንድ መሀንነት፡፡

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በአለምአቀፍ ደረጃ 48 ሚሊዮን ጥንዶች እንዲሁም 186 ሚሊዮን ሰዎች ልጅ ያለመውለድ ችግር (መሀንነት) አለባቸው። ችግሩ 50% በወንዶች እንዲሁም 50% በሴቶች ላይ ባሉ ተፈጥሯዊ ወይም ከጊዜ በኋላ በመጡ እክሎች አማካኝነት የሚከሰት ነው። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የመሀንነት እና የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ “ልጅ ያለመውለድ ችግር[መሀንነት] መከሰቱን በህክምና ማረጋገጥ(መመርመር) የሚያስፈልገው ጥንዶች ለ1 አመት ያህል የግብረ ስጋ ግንኙነት እየፈጸሙ እርግዝና ካልተፈጠረ ነው” ብለዋል። የመሀንነት ችግር ካልተከሰተ 85 % በሚሆኑት ጥንዶች ላይ በ1 አመት ውስጥ እርግዝና ይፈጠራል። ነገር ግን የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት የሴቷ እድሜ ከ35 አመት በላይ ከሆነ፣ የወር አበባ መዛባት ካለ እና ከዚህ ቀደም ለመሀንነት የሚያጋልጥ ሁኔታ ከነበረ ጥንዶች በተጋቡ በ6 ወር ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም ቢሄዱ ይመከራል።
በ1 አመት ውስጥ ከ10 እስከ 15% የሚሆኑ ጥንዶች ልጅ ላለመውለድ ችግር ይጋለጣሉ። 85% የችግሩ መንስኤ በህክምና ይታወቃል። እንዲሁም 15% የተፈጠረው የመሀንነት ችግር ምክንያት (መንስኤ) በህክምና ምርመራ እንደማይታወቅ የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።
የመሀንነት ችግር (ልጅ አለመውለድ) ለድብርት እና ለጭንቀት በመዳረግ ለስነልቦና መታወክ ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በሚኖር ግንኙነት ላይ ተፅእኖ በማሳደር የአይምሮ ሰላም ያናጋል። ስለሆነም የህክምና ባለሙያው “መሀንነት በሽታ ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል።
መሀንነት ሁለት አይነት ሲሆን ይህም የመጀመሪያ መሀንነት (primary infertility) እና ሁለተኛ መሀንነት (secondary infertility) ተብሎ ይከፈላል።
1, የመጀመሪያ መሀንነት (primary infertility); ሙሉበሙሉ ልጅ ለመውለድ ያልቻሉ ማለትም በተለያየ ምክንያት 1 ልጅ ለመውለድ የተቸገሩ ሰዎች በዚህ ምድብ ይካተታሉ።
2, ሁለተኛ መሀንነት (secondary infertility); በዚህ ውስጥ የሚመደቡት አንድ እና ከአንድ በላይ ልጅ ወልደው በቀጣይ ልጅ ለመውለድ የተቸገሩ ሰዎች ናቸው። እንዲሁም ልጅ ባይወለድም ከማህጸን ውጪ እርግዝና ተፈጥሮ ወይም በሌላ ምክንያት ፅንስ በመሀል ከተቋረጠ እዚህ ውስጥ ይካተታል። ስለሆነም እርግዝና ከተከሰተ በኋላ ‘መሀን መሆን’ በመባል ይጠራል። ሁለቱም የመሀንነት አይነት ተመሳሳይ በሆነ መንስኤ[ምክንያት] ሊፈጠር ይችላል።   
በተለምዶ ሰዎች መሀን ናቸው ተብሎ የሚታሰበው አንድ ልጅ ካልወለዱ ነው። ባለሙያው እንደተናገሩት ይህ አስተሳሰብ በብዛት የሚስተዋለው ከዚህ ቀደም ልጅ ያላቸው ወንዶች (አባቶች) ላይ ነው። ከዚህ ቀደም ልጅ የወለደ አንድ አባት ልጅ የመውለድ ችግር እንደሌለበት ያስባል። የትዳር አጋሩ (ሚስቱ) በተመሳሳይ መልኩ ችግሩ የእሱ ሳይሆን የእሷ እንደሆነ ታምናለች። “ህክምና ስንሰጥ በጣም የምንቸገረው ወንዶች ‘እኔ ወልጃለው እኔ ጋር ችግር የለም’ በማለታቸው ነው። በተመሳስይ ሴቶቹ ‘እኔ ጋር ነው ችግር ያለው’ ይላሉ። ነገር ግን እንደዚህ ብለን መደምደም አንችልም” ብለዋል ዶ/ር አቤል ተሾመ። ይህ አስተሳሰብ የሚንፀባረቀው ባል አስቀድሞ ልጅ ስለወለደ ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድ የመሀንነት ችግር የሴቶች ችግር እንደሆነ ስለሚታሰብ ነው። ነገር ግን ሁለቱም የመሀንነት ችግር አይነት በሁለቱም ጾታዎች ይከሰታል።
በአለም አቀፍ ደረጃ እስከ 15 በመቶ ጥንዶች የመሀንነት ችግር ያለባቸው ሲሆን ከዚህም ውስጥ 7 በመቶ የሚሆኑ ወንዶች ለመሀንነት እንዳተጋለጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። አንድ ወንድ በተፈጥሮ (ሲወለድ) ከ15 ሚሊዮን በላይ የዘርፈሳሽ (የዘር ፍሬ) ይዞ ይወለዳል። ልጅ ለመውለድ ይህ የዘር ፍሬ መኖር አለበት። እንዲሁም የዘር ፍሬው ከ40% በላይ ተንቀሳቃሽ እና መጠኑ 1.5 ሚሊሊትር በላይ መሆን አለበት። በተጨማሪም ቅርፁ ጤነኛ መሆን እናዳለበት የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል። እነዚህ መሟላት ያለባቸው ነገሮች ሲጎድሉ መሀንነት ይከሰታል። ይህ መጓደል በሁለት መንገድ ሊያጋጥም ይችላል። በተፈጥሯዊ እና ከጊዜ በኋላ የተከሰተ በማለት ይከፈላል።
1, በተፈጥሮ የሚያጋጥም ሙሉ በሙሉ የዘር ፍሬ አለመኖር ወይም የዘር ፍሬ የማምረት ችግር  
2, ከአንጎል(አይምሮ) ተመርተው የዘር ፍሬን የሚያነቃቁ ሆርሞኖች (pituitary hormones, hypothalamus hormones, testosterone) በአፈጣጠር ችግር ምክንያት አለመመንጨት
3, የዘር ፍሬ የሚያልፍበት መንገድ(መስመር) ችግር
4, የዘር ፍሬ በተፈጥሮ ሆድ ውስጥ ይመረታል። በሂደት የተመረተው የዘር ፍሬ ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት ይገባል። ነገር ግን ሆድ ውስጥ ከቀረ የመሀንነት ችግር ያስከትላል።
በተፈጥሮ የሚያጋጥም የመሀንነት ችግር መቶበመቶ በሚባል መልኩ ልጅ ላለመውለድ [መሀንነት] ችግር ይዳርጋል።
ከጊዜ በኋላ ለሚከሰት ልጅ ያለመውለድ ችግር የሚያጋለጡ ምክንያቶች;
1, የጭንቅላት እጢ እና ኢንፌክሽን
2,ኢንፌሽን; ለምሳሌ በልጅነት የሚከሰት የማጅራት ገትር እና ጆሮ ደግፍ በሽታ
3, ፅኑ ህመም;  እንደ ኩላሊት እና መሰል በሽታዎች ከአንጎል የሚለቀቁትን ሆርሞኖች ሊያዛቡ ይችላሉ።
4, የተለያዩ መድሀኒቶች; ለአይምሮ ህመም የሚሰጡ (ለድብርት በሽታ) መድሀኒቶች፣ የፀረ ካንሰር መድሀኒት እና ለካንሰር የሚሰጥ ህክምና (ዳሌ አከባቢ ከሆነ)
5, የአባላዘር በሽታ፤
6, ሙቀት እና አለባበስ; የወንድ ልጅ የዘር ፍሬ ያለበት አካል በተፈጥሮ የተቀመጠው ለሙቀት እንዳይጋለጥ ተደርጎ ነው። ስለሆነም ሙቀታማ ቦታ ማዘውተር እና የሚያጣብቅ የውስጥ ሱሪ መልበስ ለመሀንነት ሊያጋልጥ ይችላል።
7, ከፋብሪካ የሚወጡ የተለያዩ ኬሚካሎች (ፔትሮሊየም፣ ቤንዚን) እና ብረታብረት [ሊድ] ነክ ነገሮች ላይ የሚሰሩ ሰዎች መሀንት ሊያጥማቸው ይችላል፡፡
8, የውበት መጠበቂያ የሆኑትን ስቲም እና ሳውና ባዝ አዘውትሮ መጠቀም፤
9, የሰውነት ጡንቻ ለማፈርጠም የሚወሰድ መድሀኒት (አናቦሊክ ስትሮይድ); በውስጡ የቴስቴስትሮን [testosterone) ንጥረነገር(ሆርሞን) ካለው በሰውነት ውስጥ ያለውን የሆርሞን ስርአት ያዛባል። ይህም የዘር ፍሬ በመቀነስ ወይም ሙበሙሉ በማጥፋት ለመሀንነት ሊያጋልጥ ይችላል።  
የመሀንነት ምልክቶች; በተፈጥሮ ልጅ ያለመውለድ (መሀንነት) ችግር ካለ የጉርምስና እድሜ ላይ የሚታዩ ፀጉር የመብቀል፣ ድምፅ መወፈር (መጎርነን) እና መሰል ምልክቶች ላይታዩ ይችላሉ። ሌላኛው በአፈጣጠር ችግር የዘር ፍሬ ሆድ ውስጥ መቅረት ሲሆን ይህንንም እስከ 2 አመት ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት ካልገባ ችግር እንዳለ ማወቅ ይቻላል። ስለሆነም በህክምና ባለሙያዎች አማካኝነት ወደ ዘር ፍሬ ከረጢት እንዲገባ ይደረጋል።
ህክምናውን በተመለከተም የግብረስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በተለያየ ምክንየት ፍላጎት የማጣት ችግር ሲኖር፤ የዘር ፍሬ ቁጥር ዝቅተኛ ከሆነ፤ የዘር ፈሳሽ ወደ ሴት ማህጸን ሳይሆን ወደ ሽንት ፊኛ የሚሄድ ከሆነ በህክምና መርዳት ይቻላል፡፡ በተጨማሪ አይ ቪ ፍኤ [IVF] የተባለ ህክምና የሚገኝ ሲሆን ይህም የወንድ ዘር እና የሴት እንቁላል በላብራቶሪ እንዲገናኝ [እንዲቀላቀል] ተደርጎ ወደ ሴቷ ማህጸን እንዲገባ እና ልጅ እንዲወለድ የሚያስችል የህክምና ዘዴ ስለሆነ የመህንነት ችግርን ለማቅለል ይረዳል፡፡
የወንዶች የመሀንነት ችግር መከላከያ መንገድ ነው ከሚባለው ውስጥ ሰፋ ያለ የውስጥ ሱሪ መልበስ፣ ስቲም እና ሳውና አለማዘውተር፣ ፋብሪካ እና ብረታብረት አከባቢ [የሚሰሩ ሰዎች[ የፊት ጭምብል በማድረግ አፍ እና አፍንጫን መሸፈን የመሳሰሉትን መጠቀም ይመከራል።  
ልጅ ያለመውለድ ችግር የሴት ወይም የወንድ ብቻ ባለመሆኑ ለጋራ ችግር በጋራ መመርመር እና ህክምና ማግኘት ያስፈልጋል። ስለሆነም ጥንዶች ወደ ህክምና ተቋም በጋራ እንዲመጡ በማለት የስነ ሆርሞን ህክምና ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር አቤል ተሾመ ጥሪ አስተላልፈዋል።



Read 4593 times