Saturday, 28 January 2023 21:05

‘የጉልቤነት ዲያሌክቲካዊ ትራንስፎርሜሽን’

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

በነገራችን ለይ... መቼም ዘንድሮ መላ ቅጡ የጠፋ ነገር ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ከብሩና ብሩ ካለበት ቦታ ሳንወጣ አንዳንድ የባንክ ሠራተኞች የሚቀጠሩት፣ በድምርና በቅንስ ችሎታ ብቻ ነው እንዴ! አሀ...አንዳንድ ቦታዎች እኮ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ለደንበኛ የሚያሳዩት የሥነስርአት ጉድለት የሚገርም ነው፡፡--”


  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
አፍጣጭ በዛብን፡፡ ጉልቤ፣ ጉልቤ የሚያደርገው በዛብን:: የምር እኮ አስቸጋሪ ነው። ‘ከተሜነት’ ብርቅ የሆነባት ከተማ እየመሰለች ነው፡፡ ባህሪያችን ሁሉ፣ ነገረ ሥራችን ሁሉ፣ ምን እንደምንፈልግና ምን እንደማንፈልግ ግራ የገባበት ዘመን! በፊት ጊዜ እኮ...አለ አይደል... “የእንትን አካባቢ ልጆች ሀይለኞች ናቸው!” “የእንትን ሰፈር ልጆች ጉልቤዎች ናቸው!” ምናምን ይባል ነበር፡፡ ደግሞ እንዲህ አይነት ነገር፣ በዘንድሮ አነጋገር ‘ፌክ ኒውስ’ የሚባለው አይነት ሳይሆን፤ የሆነ አከባቢ ሰዎች “ጉልቤዎች ናቸው...” ከተባለ በቃ ጉልቤዎች ናቸው፡፡ የምር ስንትና ስንት የእነዛን ዘመኖች መልክ የሚያሳዩ ታሪኮች ነበሩ፡፡ “የእንትና የእንትን ሰፈር ልጆች አራት ኪሎ እየተከታከቱ ነው፣” ከተባለ ድፍን ፒያሳ እኮ ወላ ሱቅ የለ፣ ወላ መሥሪያ ቤት የለ ጥርቅም አልነበር እንዴ! እናላችሁ.... የጉልቤነት ‘ፕሬሚየር ሊግ’ እና ‘የጤና ቡድን’ ነገር አለው ለማለት ሳይሆን፤ የዘንድሮው መልኩን ልውጥውጥ አደርጎብን ለሜሞሪም ክራይቴሪያ የማያሟላ ሆነብን ለማለት ነው፡፡
እናላችሁ... ‘ኢንዴንጀርድ ስፒሽየስ’ ከሆኑ በቆዩትና የትናንቱን የሚያስታውሱ ተወካዮች አየተመናመኑባቸው መሆናቸው ‘አሳሰቢ’ ነው በሚባልላቸው የቀድሞ አራዶች ቋንቋ፤ የሀይለኞችና ጉልቤዎች ዋነኛው ባህሪይ፣ ያው በትንሽ ትልቁ ‘መፈሳፈስ’ ነው፡፡ እና “ከጀርባ ተልእኮ...” ምናምን አይነት የ‘መርሲነሪ’ አይነት ነገር አልነበረም፡፡ ያው ሲፈሳፈስ ይውልና እንትና ሻይ ቤት ሳህን ድንች በትሪ አስሞልቶ ሲገምጡ መዋል ነው፡፡
የሚገርም እኮ ነው! ትናንት በጣም እንጠላቸው የነበሩ ነገሮችን፤ ትናንት ፊታችንን እናዞርባቸው የነበሩ ጉዳዮችን፣ ትናንት የትችት ናዳ እናወርድባቸው የነበሩ ነገሮችን መለስ ብለን አንደ “ጉድ ሜሞሪ” እያስታወስን ዘና የምንልበት ዘመን ይምጣ! እነ አንትና... “የሰፈራችን ልጅ ገርል ተነጠቀች” እያላችሁ እንደ ማጀላን ድፍን ከተማዋን ስትዞሩ የነበራችሁትን፣ “የተባረከ ዘመን”  የሚሉትን ስትሰሙ ምን ትላላችሁ! የምር ግን... ሀሳብ ያጠረበት ዘመን አይደል...የማትከፍሉበት ሀሳብ ለመስጠት ያህል እነኛን ነገሮች ወደ ተከታታይ ድራማ የማትለውጧቸውማ! አሀ... በፊልሞቻችን ስንት አይነት ነገር እያየን አይደል!
“አንተ ቅድም አብረሀት የነበረችው ልጅ ምንህ ነች?”
“አዲሷ ገርሌ ያልኩህ እኮ እሷ ነች፡፡”
“ምን! አንተ ሰውዬ አንደኛውን የሰፈሩን ሰው ልታስጨርሰው ነው እንዴ!”
“እኔ ገርልፍሬንድ ስለያዝኩ ነው እንዴ የሰፈሩ ሰው የሚያልቀው?”
“የማን ገርልፍሬንድ እንደሆነች አታውቅም እንዴ!”
“የእኔ ነች እያልኩህ ነው እኮ!”
“ስማ፣ የእንትን ሰፈር ልጆች መጥተው ሰፈሩን ድምጥማጡን እንዳያወጡት!”
“ለምን ብለው...?”
“የእንትና ገርል ፍሬንድ ነች እኮ!”
“ምን! እና...ዝም ብላችሁ ታዩኛለችሁ!”
“ግዴለም፣ እስካሁን አላወቀ ይሆናል፡፡”
“እሱ አወቀ አላወቀ፤ እኔ አገር ቤት ወደ ዘመዶቼ ነው የምመርሸው!”
ከዛ በኋላማ...አለ አይደል...አይደለም ሶቶ ምናምን ነገር ይዞ ከአንድ ባቅላባ ግብዣ በኋላ በሲኒማ ኢትዮጵያ ፎቅ ጥግ ሊወሸቅ ቀርቶ ገና ከሩቅ ሲያያት አራት በአራቱን ማስነካት ነው፣ አገር ቤት እስኪመርሽ ድረስ ማለት ነው። እናላችሁ፣ ምን ለማለት ነው... ያኔ ‘ጉልቤነት’ በምክንያት ነበር፡፡ (ቂ...ቂ...ቂ...) “የእነ እንትና ዘመድ ነው...” “አጎቱ እኮ ባለስልጣን ነው...” “የሰዎቹ አገር ሰው ነው...” “አጎቱ በገንዘቡ ድፍን ሀገርን መግዛት የሚችል ነጋዴ ነው፣” ብሎ ‘ቴረር’ አልነበረም፡፡ በቃ ጉልቤነቱ  ራሱ የሚመለከተው  ሰው ላይ ነው እንጂ ባለሥልጣንና የነጋዴ መደገፊያ ግንብ፣ ግድግዳ ብሎ ነገር የለማ!
እናላችሁ...ዘንድሮ እኮ አብዛኛው ነገር ‘አፕሳይድ ዳውን’ ሆነና ግራ ገባን ለማለት ነው፡፡ ‘ጉልቤው’ መብዛቱ! ትርፍ ሰው ለመጫን “ጠጋ በልልኝ” ሲባል ለመጠጋት ፈቃደኛ ባልሆነና መብቱን ለማስከበር በሚሞክር ተሳፋሪ ላይ የሚያፈጥና ብሎም የስድብ ናዳውን የሚያወርድ ‘ጉልቤ’ ረዳት ሞልቶላችኋል፡፡
“ብራዘር እሱ ጋ ጠጋ በል...” ትብበር ሳይሆን ትእዛዝ ነው፡፡ እሱዬው አይጠጋም። “ታክሲውን የገዛኸው መሰለህ እንዴ! ምን...” ከዚህ በኋላ ተከትለው ከሚመጡት ቃላት “ይሰውራችሁ” እንጂ ሌላ ምንም ማለት አይቻልም፡፡ ደግሞላችሁ... ጉልቤነቱ ረዳቱ ላይ አይቆምም፡፡ ሾፌሩ “ምን በጠቅላላ ምቀኛ ብቻ!” ይልና በተሳፋሪና በረዳት መሀል ያለውን የግለሰቦች ጭቅጭቅ... አለ አይደል... ‘ዓለም አቀፋዊ’ ያደርገዋል! 
ደግሞላችሁ... አሁንም ከታክሲው ሳንወርድ፣ ብዙ ጊዜ ተቀዶ “የተለጣጠፈ ብር አንቀበልም፣” የሚሉ ረዳቶችና፣ “የተለጠፈ ብር መልስ አልቀበልም” በሚሉ ተሳፋሪዎች መሀል ያለው ጭቅጭቅ አሁን፣ አሁን ደጋግመን የምናየው ሆኗል! እኔ የምለው...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...በፊት የምናውቀው የተቀዳደና የተለጣጠፈ ብር ወደ ባንክ ከገባ በኋላ ብዙ ጊዜ ተመልሶ አይወጣም ይባል ነበር። እንደውም ሰዉ የተለጣጠፈ ብር ሲገጥመው የሆነ ባንክ ይዞ ወስዶ ማስለወጥ ሁሉ ይቻል ነበር፡፡ ዘንድሮ በተለይ እነኚህ ‘ታስረው’ የሚመጡ ብሮች ውስጥ የሚገኘው የተቀዳደና የተለጣጠፈ ብር መብዛቱ የተለየ ነገር አለው እንዴ የሚያሰኝ ነው! (“ተለጥፋም፣ አቅምም እየከዳት፣ ጭራሽ ልጥፍጥፍ!” የሚለው ሀረግ ያልገባው በ’ምክንያት’ ነው፡፡) እናላችሁ..ሰዋችን “እንዴት ነው እንዲህ ዱቄት ሊሆን አንድ ሐሙስ የቀረው ብር መልሰው ወደ ገበያ የሚያስገቡት!” ቢል አይገርምም፡፡  
ስሙኝማ... እግረ መንገድ የሆነች ነገር ትዝ ብላኝ ነው፡፡ በወዲያኛው ዘመን የሆነ ነው። አንድ የፈረንጅ አፍ ጋዜጣ ላይ የሚጽፍ ሰው እንዲሁ አይነት “የተቀዳደና የተለጣጠፈ ብር በዛ...” የሚል ጽሁፍ ይጽፍና ለኢደተሮቹ ያቀርባል፡፡ ምን ቢሆን ጥሩ ነው...ጸሁፉ ‘ሳንሱር’ ይወድቃል፡፡ የተሰጠው ምክንያት ምን መሰላችሁ... “የተቀዳደና የተለጣጠፈ ብር ማለት፣ ብሩ ዋጋ የለውም ማለት ነው፡፡” አሪፍ ትንታኔ አይደል! እና በፈረንጅ አፍ አሽሙር መኖሩን ከዛ ጊዜ ጀምሮ ሳናውቅ አልቀረንም ለማለት ነው፡፡
በነገራችን ለይ... መቼም ዘንድሮ መላ ቅጡ የጠፋ ነገር ብዙ ነው፡፡ ከዚህ ከብሩና ብሩ ካለበት ቦታ ሳንወጣ አንዳንድ የባንክ ሠራተኞች የሚቀጠሩት፣ በድምርና በቅንስ ችሎታ ብቻ ነው እንዴ! አሀ...አንዳንድ ቦታዎች እኮ ቁጥራቸው ብዙ ባይሆንም ለደንበኛ የሚያሳዩት የሥነስርአት ጉድለት የሚገርም ነው፡፡ (በነገራችን ላይ እንደ ባንክ ባሉ ተቋማት ‘ጥቂት፣’ ወይም ‘አንዳንድ’ የሚባል ነገር የለም። ሰው በገዛ ገንዘቡ ትክክለኛውን መስተንግዶ ሳያገኝ ሲቀር ‘አንድ’ ማለት አንድ መቶም አንድ ሺህም ነው። ልክ አይደለማ! ልክ ከኪሳቸው አውጥተው የሚሰጡ ሲያስመስሉ አሪፍ ነገር አይደለም፡፡ እናማ...የቅርብስ የሩቅስ አለቆቻቸው ምን ይሠራሉ? ካሜራዎቹ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ‘ኤዲት’ እያደረጉ ያስቀራሉ እንዴ!
በቂ ምክንያት እያላችሁ ወደ ውስጥ አላስገባም ብሎ የሚንጎማለል የጥበቃ ሠራተኛ በራሱ መንገድ እኮ ‘ጉልቤ’ ነው፡፡ በነገራችን ላይ... በየቦታው የሚገኙ የጥበቃ ሠራተኞችን ደንበኛ አቀባበል የሚከታታሉ አለቆች ነገሮች የሏቸውም እንዴ! አንዳንድ ቦታ እኮ ግልምጫቸውና ዱላ አያያዛቸው “ሥራ አስኪያጁ ራሱ የጥበቃ ልብስ ለብሶ ይሆን እንዴ!” ለማለት ምንም አይቀራችሁ፡፡ መግባት የምትፈልጉበትን ምክንያትና ቢሮ፣ በዕለቱ ቀጠሮ እንዳላችሁ እያስረዳችሁት...በቃ የዓይናችሁ ቀለም፣ ወይ የሆነ ነገራችሁ ደብሮት “አይቻልም!” ካለ አይቻልም ነው፡፡ እናማ... ‘ጉልቤዎች’ የጥበቃ ሠራተኞች ከተማችን ውስጥ ብዙ ቦታ ስናይ ግራ የማይገባንሳ፡፡
እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...”የስልጠና ማኑዋላቸው የተለየ ነው እንዴ!” ልንል ምንም አይቀረን፡፡ አለ አይደል... ስለ ደንበኛ አቀባበል ያሰለጠኗቸው ሳይሆን፣ “የእናንተ ሥራ እዚች ቁጭ ብላችሁ፣ ወይም ቆም ትሉና ይቺን ዱላ፣ ዱላም ከጠፋ የመጥረጊያ ስባሪ ይዛችሁ፣ ደስ ያላችሁን ማስገባት፣ ደስ ያላላችሁን መመለስ ነው፣” የተባሉ ነው የሚመስለው! እናላችሁ... እነኛ የዛኛው ዘመን ጢማሞቹ ሰዎች ትዝ የሚሉት ‘ቦተሊከኛ’ ርዕስ ስጥ ቢባል፣ ‘የጉልቤነት ዲያሌክቲካዊ ትራንስፎርሜሽን’ ምናምን ሊል እንደሚችል አትጠረጥሩም!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 2496 times