Saturday, 28 January 2023 21:13

ልጅ ለመውለድ ሀያዎች የእድሜ ክልል ተመራጭ ናቸው፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ወንድ ልጅ በተፈጥሮው ሙሉውን ጊዜ የዘር ፍሬ እያመረተ ይኖራል፡፡
ሴት ልጅ ስትወለድ የተወሰነ ቁጥር ያለው እንቁላል ይዛ ነው የምትወለደው፡፡
የወር አበባ ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ምንድነው? የማህጸንስ መስተንግዶ ምን ይመስላል? የሚለውን እና ከወር አበባ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች ለጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስቱ ዶ/ር እዮብ አስናቀ አንስተን ባለፈው እትም አንብባችሁዋል። አሁን ደግሞ በወር አበባ  ምክንያት ስለሚከሰቱ ህመሞች.. የወር አበባ በደንብ አለመፍሰስ.. እንዲሁም የወር አበባ የሚቋረጥባቸውን ምክንያቶች እና ተያያዥነት ያላቸውን ከተለያዩ መረጃዎች ያገኘነውን ጭምር ለዚህ እትም ብለናል፡፡
ዶ/ር እዮብ አስናቀ በአበበች ጎበና የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
በወር አበባ ጊዜ ህመም ሊኖር ይችላል። ለዚህም ምክንያት አለው፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት (estrogen) የሚባለው ሆርሞን ያዘጋጀው የማህጸን ግድግዳ በፕሮጄስተሮን (progesterone) ይደገፋል፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ እንደ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) አይነት የታለያዩ ቅመሞች ማህጸን ወስጥ ይዘጋጃሉ፡፡ እንዲሁም እርግዝና ካልተካሄደ ወደ ወሩ መጨረሻ ላይ ፕሮጄስተሮን (progesterone) እና ኤስትሮጂን (estrogen) የሚባሉ ቅመሞች ዝቅ ይላሉ፡፡ በዚህን ጊዜ አዲስ የተሰራው የማህጸን ግድግዳ ላይ ውስጡ ያለው የደም ዝውውር ያንሳል፡፡የደም ዝውውር አነሰ ማለት ውስጡ ያለው ነገር እየሞተ ነው ማለት ነው። የማህጸን የውስጥ ግድግዳው የሞተ እና እየሞተ ያለ ከሆነ ህመም ሊሰማ ይችላል፡፡ ሁለተኛው እና ዋናው የህመም መፈጠር ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) የሚባለው ቅመም ማህጸን ውስጥ ያለውን ስፓይራል (spiral) የሚባለውን የደም ስር እንዲኮማተር በማድረጉ ለኤስኪሚክ (ischemic) ወይም ለምግብ እጥረት በማጋለጥ  ህመም እንዲሰማ ያደርጋል፡፡    
ሶስተኛው የህመም ምክንያት ደግሞ ፕሮስታግላንዲን (prostaglandin) የሚባለው ንጥረ ነገር የማህጸን ግድግዳ እንዲኮማተር በማድረጉ ነው፡፡ እንዲኮማተር የሚያደርግበት አንደኛው ምክንያት የደም ዝውውሩ እንዲቀንስ እና ሴቲቱ  ብዙ እንዳትደማ ለማድረግ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምግብ እጥረት የተነሳ ከውስጥ የሞተው ክፍል ከማህጸን ውስጥ እንዲወጣ የግድ ማህጸን መጭመቅ ስላለበት የመጭመቅ ሂደቱ ህመም እንዲሰማ በማድረጉ ነው፡፡ ስለዚህ ባጠቃላይ በወር አበባ ጊዜ ሶስት መሰረታዊ ህመሞች አሉ ማለት ነው፡፡ በምግብ እጥረት ፣አየር (oxygen) እጥረት እና ሶስተኛው ደግሞ ማህጸኑ እራሱ ስለሚኮማተር በእነዚህ ምክንያቶች ህመም ይከስታል፡፡
ጥያቄ፦ የወር አበባ ጊዜውን አለመጠበቁ ወይንም በደንብ አለመፍሰሱ የሚያስከትው ጉዳት ምንድነው?
መልሰ፦ ዶ/ር እዮብ በሰጡት መልስ የወር አበባ ጊዜውን አለመጠበቁና መብዛቁ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ከማጸን እጢ ጋር ተያይዞ ሊመጣ ይችላል ብለዋል፡፡ የማህጸን ግድግዳ ካንሰር ሊኖር ይችላል፡፡ ከውፍረትና ከሆርሞን ችግሮች ጋር ተያያዥ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ሴቶች በጣም ወፍራምና ቡጉር ያላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች የወር አበባ መዛባት ሊገጥማቸው ይችላል። በየወሩ የወር አበባ ጊዜውን ጠብቆ አይመጣም፡፡ ሲመጣም በጣም ብዙ ፍሰት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይህ ሕመም በሳይንሳዊ አጠራሩ polycystic ovarian syndrome ይባላል፡፡ ይህ ችግር ከወር አበባ መዛባትም ባለፈ ለተለያዩ ህመሞች ለምሳሌም እንደስኳር፤ የማህጸን ግድግዳ ካንሰር ተጋላጭነት ለመሳሰሉት የሚያጋልጥ ሲሆን በእርግጥ ይህ ክስተት በሁሉም ሴቶች ላያ የሚከሰት አይደለም፡፡ በተጨማሪም የወር አበባ በጣም በብዛት ይፈሳል ከተባለ ይህችን ሴት ለደም ማነስ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ድካምን እና የተለያዩ ሕመሞችን ሊያስከትል ስለሚችል ስራዋን ለመስራት፤ ትምህርትዋን ለመማር ትደገራለች፡፡ የወር አበባ መዘግየትና በዝቶ መምጣት ከእንቁላል አለመመረት ጋር ሊገናኝ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የመካንትን ችግር ሊያመጣ ይችላል፡፡  እንደዚህ ያለ ችግር ለባቸው ሴቶች ወደህክምና ተቋም መሄድ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ጥያቄ፦ የወር አበባ ከመፍሰሱ በፊት የሚያጋጥመው ህመም ከምን የተነሳ ነው?
መልስ፦ የወር አበባ ከመፍሰሱ በፊት በጣም የሆርሞኖች መዋዠቆች ይኖራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመጣ የህመም ስሜት ይኖራል። በሆርሞን መዘበራረቅ ምክንያት የስሜት መቀያየሮች….መደበር፤የሆድ መነፋት፤የጡት ሕመም የመሳሰሉት ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ይህ ስሜት ምናልባት ከ20-30%የሚጠጉ ሴቶች ላይ ይኖራል፡፡ በጣም ባስ ያለው ሕመም ደግሞ ከ3-5% የሚደርሱ ሴቶች ላይ የሚደርስ ሕመም ነው፡፡ ስለዚህ እንደዚህ ያለ ችግር ያለባቸው ሴቶች ህመሙ የራሱ ሕክምና ስላለው ወደ ሐኪም ጋ ቀርበው መታየት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሴቶች እንደዚህ ያለውን ሕመም የሚያስታግሱበት መንገድ ይኖቸዋል፡፡ ለምሳሌ ካፊን ያለባቸው መጠጦችን …እንደ ቡና …ኮካ ያሉትን መቀነስ…ፈሳሽ በደንብ መውሰድ፤በተወሰነ መልኩ እንቅስቃሴ ማድረግ ይንን ስሜት የማስታገስ እድል አለው፡፡ ከዛ ባስ ባለ ሁኔታ የእለት እለት እንቅስቃሴአቸውን፤ ትምህርታቸውን በሚጎዳ መልኩ ህመሙ የሚያጋጥም ከሆነ የግድ ወደሐኪም ጋ ቀርቦ መፍትሔ ማግኘት ያሻል፡፡
ጥያቄ፦ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰትን ህመም ለመቀነስ ጋብቻ መፍትሄ ነውን?
መልስ፦ በትዳር ውስጥ ያሉ ሴቶች ወይንም የግብረስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ህመሙ ያልታገሰላቸው ሴቶች አሉ፡፡ አንዲት ሴት አርግዛ በምጥ ከወለደች በተወሰነ ደረጃ ህመሙ የመቀነስ እድል አለው፡፡ የመጀመሪያው ወይም ደግሞ ምክንያቱ ለማይታወቅ ለወር አበባ ጊዜ ህመም መፍትሄ ተብሎ የሚታሰበው ማግባት ብቻም ሳይሆን መውለድም ጭምር ነው፡፡ የዚህ ምክንያትም  የህመሞቹ መንስኤ ከማህጸን መጥበብ ጋር ይያዛል ተብሎ ስለሚገመት አንዲት ሴት ልጅ ከወለደች በኋላ  እጅግ ታላቅ በሆነ መልኩ የህመሙ መጠን ይቀንሳል፡፡ የህመሙ መንስኤ የሚታወቅ ከሆነ  ለምሳሌ እንደ ኢንዶሜትሪዮሲስ (Endometriosis) ወይም ማዮማ የሚባሉ የማህጸን ዕጢ እና የመሳሰሉት ምክንያቶች  ከሆኑ ግን  ህመሙን ያመጣው ምክንያት እስካልተወገደ ድረስ ብታገባም ባታገባም ህመሙ ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ የወር አበባ ሕመምን ለመቀነስ ሲባል ጋብቻ መፈጸም ይገባል የሚል ምክርም አንለግስም ብለዋል ዶ/ር እዮብ አስናቀ ፡፡
ጥያቄ፦ የወር አበባ የሚቋረጥበት (Menopause) የሚከሰትበት ምክንያት ምንድን ነው?
መልስ፦ አንዲት ሴት በጽንስ ላይ እያለች ወደ ሶስት ሚሊዮን ፤ስትወለድ ደግሞ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚሆን እንቁላል ይዛ ትወለዳለች፡፡ ያቺ ሴት ወደ ጉርምስና እድሜ ስትገባ በየጊዜው እየጠፉ ወደ 300.000ሺ እንቁላሎች ይቀሩዋታል። እንደገናም እነዚህ 300.000 እንቁላሎች በየወሩ ቁጥራቸው እየቀነሰ ይመጣል፡፡ ይህ ሂደትም በየጊዜው እየጨመረ ስለመሄድ ወደ ከ40-45 አመት ገደማ ስትደርስ በጣም በመመናመን በሚያልቁበት ጊዜ ከእንቁላል ማምረቻ የሚመረቱ እንቁላሎችም መመረታቸውን ያቆማሉ ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ያቺ ሴት የወር አበባ ስለማታይ ያቺ ሴት (Menopause) አረጠች ይባላል፡፡ ወንድ ልጅ ያለውን ተፈጥሮ ስንመለከት በየጊዜው የዘር ፍሬውን እያመረተ ይሄዳል፡፡ ሴት ልጅ ግን ስትወለድ ውስን የሆኑ እንቁላሎችን ይዛ ነው የምትወለደው፡፡ በየወሩ አንዳንድ እንቁላል እንዲመረት ለማደረግ ብዙ እንቁላሎች እየጠፉ ይመጣሉ፡፡ ይህ ማለትም ለእርግዝና የተዘጋጁ አንድ ሁለት እንቁላሎች በሚለቀቁበት ጊዜ አብረው አስራ አምስት እስከ ሀያ ድረስ ሊለቀቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ መልክ ሂደቱ እስከተወሰነ እድሜ ይቀጥልና በስተመጨረሻው ያቺ ሴት ከማረጥ ደረጃ ትደርሳለች፡፡ በእርግጥ አንዳንዴ ካለእድሜ የእንቁላሎች የማለቅ ሁኔታ ያጋጥምና ካለእድሜ ማረጥ ይከሰታል፡፡
ጥያቄ፦ ልጅ ለመውለድ የሚመከር የእድሜ ክልል አለ?
መልስ፦ ልጅ ለመውለድ ሀያዎቹ እድሜዎች ትክክለኛ እና ጥሩ ጊዜ ነው፡፡ እድሜ ወደ ሰላሳ ከገባ በሁዋላ የመረገዝ እድሉም እየጠበበ ይሄዳል። በተለይም ወደ ሰላሳ አምስት አመት ሲደረስ የእንቁላሉም ጥራት እና ቁጥር ሊቀንስ ስለሚችል በቀላሉ አይረገዝም ፡፡ ቢረገዝም ሙሉ  ጤነኛ የሆነ ልጅ ላይወለድ ይችላል፡፡ የአእምሮ ዝግመት፤የልብ በሽታ ያለባቸው ልጆች ሊወለዱ ይችላሉ፡፡ስለዚህ ከሃያ አንድ እስከ ሰላሳ ዓመት እድሜ ጥሩ የመውለጃ ጊዜ ነው ተብሎ ይያዛል፡፡ዕድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ጽንሱ ላይ የሚከተል ችግር ስላለ ቆይቶ መውለዱ አይመከርም፡፡

Read 1086 times