Saturday, 04 February 2023 18:29

“ኢትዮጵያ ውስጥ ከሕግ ውጪ ከፍተኛና አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈጸማሉ”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ኢትዮጵያ ውስጥ በዜጎች ላይ ከሕግ አሠራር  ውጪ  በሆነ መንገድ እጅግ  ከፍተኛና አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታውቋል። ማዕከሉ በአገሪቱ  የሰብዓዊ መብት ጥበቃው በጣም  የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱንም   ገልጿል።
በዋናነት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን መብት ለመጠበቅ ከሁለት ዓመታት በፊት የተቋቋመው ይኸው  ተቋም፤   የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሥራቸውን በመሥራታቸው ብቻ ለእሥር እንደሚጋለጡና  ትንኮሳና ዛቻዎች እንደሚደርስባቸው ገልጾ፤ በአሁኑ ወቅት  በአገሪቱ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሁኔታ “በጣም የከፋ” ደረጃ ላይ ደርሷል ብሏል።  
 የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቆርቃሪዎች ለእሥር እየተዳረጉና   ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው ቢሆንም  ተቋሙ    የታሠሩት እንዲለቀቁ በመጠየቅ ፣ ጠበቃ በማቆም፣ ለቤተሰቦቻቸው የገንዘብ ድጋፍ በማድረግና ለችግር ሲጋለጡ ቤተሰቦቻቸውን በገንዘብ በመደገፍ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።  
 አብዛኛውን ጊዜ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች  በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ  እንደሚሠሩ የገለጸው ተቋሙ፤  ብዙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሥራቸው ምክንያት ብቻ እንደሚታሠሩ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸውና  ለከፋ እንግልት እንደሚዳረጉ አስታውቋል።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ አሁን እጅግ  የከፋ ሁኔታ ውስጥ መሆኑን ያመለከተው ማዕከሉ፤ ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ቢያበቃም እንደ ኦሮሚያ ባሉ  ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በየቀኑ የሰብዓዊ መብት በገፍ ይጣሳል፤ በዜጎች ላይ አሰቃቂ በደል ይፈጸማል ብሏል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ባለፉት ዓመታት በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መካከል ጠንካራ ጥምረት በመመስረት. የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችንና የሌሎችንም አቅም በማጠናከር ደህንነቱ የተጠበቀ የሥራ አካባቢ በመፍጠር ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደህንነትና መብቶች መከበር ሲሰራ  መቆየቱም ተገልጿል።

Read 1891 times