Saturday, 27 October 2012 10:50

“የአመጻ ብድራት”ን እንዳነበብኩት

Written by  ደሳለኝ ሥዩም
Rate this item
(1 Vote)

የመጽሐፉ ርእስ…የአመጻ ብድራት
ደራሲ…ጌቱ ሶሬሳ
ዓይነት…ረዥም ልብወለድ
የሽፋን ዋጋ…38 ብር
የገጽ ብዛት…274
የታተመበት ዘመን ….2004 ዓ.ም
ከኢትዮጵያ ሰዓሊያን እና ቀራጺያን ማኅበር ሰዎች ጋር ሻይ ቡና እያልን ነበር፡፡ በየጨዋታው መሃል ስለዘመናችን የኪነጥበብ ሥራዎች እናነሳለን፡፡ ከሰዓሊያኑ አንዱ እንደዘበት ተናገረ፡፡ ስለ ፊልም ፖስተሮች እና ስለመጻሕፍት ሽፋን ሥራዎች፡፡ የፊልም ፖስተሮች ይቆዩን፡፡
ሰዓሊው ወደ ኋለኛው ዘመን ተመልሶ የመጻሕፍት ሽፋን በሠዓሊያን የሚሠራበትን ዘመን አስታውሶ አወጋ፡፡ በዚህ ዘመን የመጻሕፍት ሽፋን ሥራዎች ከውጭ ፊልሞች አሊያም ኮምፒዩተር ላይ ከሚገኙ ምስሎች እየመነተፉ መስራቱ ኢ - ስነ ምግባራዊ መሆኑን ነገረን፡፡ ይህን ብቻ አይደለም፡፡

ጥበብ በጥበብ ልትጐለምስ እንደሚገባ ተናገረ፡፡ ደራሲው ተጨንቆ የፈጠረውን ታሪክ ሰዓሊው ተጨንቆ በቀለም እና በንድፍ ሊገልፀው ይገባል አለ፡፡ አገላለጹ ተወዳጅም አሳማኝም ነበር፡፡ 
ይህ ውይይት ተጽእኖ ፈጠረብኝ መሠለኝ የመጻሕፍትን ሽፋን በትኩረት መመልከት ጀመርኩ፡፡ የዘመናችን መጻሕፍት እንደመብዛታቸው በእጅ/በቅብ/ የተሠሩ የመጻሕፍት ሽፋኖች ብዙም አይደሉም፡፡ በዚህ መሃል ነው ሰዓሊው እንደተመኘው ዓይነት ሽፋን የተሰራለትን “የአመጻ ብድራት”ን ያገኘሁት፡፡ መጽሐፉ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ይታተም እንጅ እጄ ሲገባ ዘግይቶ ነበር፡፡
አንድ ቀን ቡና እየጠጣሁ መጽሐፉ ጠረጴዛዬ ላይ ተቀምጧል፡፡ ቡና ከሚያጣጡኝ አንዷ የመጽሐፉን ሽፋን ተመልክታ “ጥሩ መጽሐፍ ነው?” አለችኝ፡፡ ስለጠቅላላ መጽሐፉ ለማውራት ሲቃጣኝ ዓይኗን ካተኮረችበት ሳትነቅል “ያለጥፋቱ የታሰረ ባለታሪክ አለ?” አለችኝ፡፡ እውነት ነበር፡፡
ዛሬ የመጽሐፉን ሽፋን ብቻ አይደለም መዳሰስ የፈለግሁት፡፡ ውስጡንም ነው፡፡ ደራሲው የህግ ባለሙያ እንደሆነ ከመጽሐፉ ጀርባ ተጠቅሷል፡፡ “የአመጻ ብድራት” ማጠንጠኛ ፍትህና የፍትህ ሥርዓቱ መሆኑ ትኩረቴን ሳይስበው አልቀረም፡፡
በተደጋጋሚ በየጽሑፉ እንደማነሳው ስነ ጽሑፋችን ወይም የስነ ጽሑፍ ሰዎቻችን ከበፊት ጀምሮ ሲደጋገሙ በኖሩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ መጻፋቸው ብዙ የሚያኩራራ አይደለም፡፡ በእውነት ላይ የተመሰረቱ ወይም ነባራዊውን ዓለም ለመግለጽ ጭልጥ ብለው ወደ ልብ ወለድ ዓለም የማይገቡ ሥራዎች ተመራጭ ይሆኑልኛል፡፡
“የአመጻ ብድራት” ብዙ ደራስያን ልብ ያላሉት የመሰለኝን የፍትህ ሥርዓት መሠረታዊ ማጠንጠኛ አድርጐታል፡፡ አዲስ አበባን እና ሐዋሳን ዋነኛ የታሪኩ ቦታዎች በማድረግ ነው የተጻፈው፡፡
በሐሰት ተወንጅሎ በእስር ላይ የሚገኝ የአንድ ሰው ጉዳይ መነሻ በማድረግ የፍትህ ሰዎች ማለትም ፖሊስ፣ አቃቢ ህግ፣ ዳኞች ብሎም ጠበቆች በታሪኩ ውስጥ እየተፈራረቁ እኩይ እና ሰናይ ተግባራትን ሲያከናውኑ እያሳየን ይዘልቃል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የህግ ሰዎች ቢሆኑ ብለው የሚመኟቸው እንግዳ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ የተከሳሹን ጉዳይ የሚከታተለው “ዓለምዬ የህግ አማካሪ እና የግል መርማሪ” በሚል የሚታወቅ ድርጅት የታሪኩ አካል ሆኖ መቅረጹ፣ ለሀገሪቱ ፍትህ ስርዓት መሻሻልና መቀልጠፍ የግል ምርመራ አገልግሎት አንድ አማራጭ መሆኑን ለመጠቆም ይመስላል፡፡
ደራሲው ሐገሩን በሚያገለግልበት ሙያው ውስጥ ያለውን በጐ እና ደካማ ጐን በስነ ጽሑፍ ለማስቃኘት መሞከሩ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ የእኛ ተግባር ደግሞ ይህ ድርሰት ተሳክቶለታል ወይ የሚለውን መቃኘት ነው፡፡
በአስራ ስድስት ክፍሎች እና ብዙ ንኡሳን ክፍሎች የተከፈለው ልብወለዱ ነባራዊ ድክመቶችን በመተቸት፣ ደካሞችን ሸንቆጥ በማድረግ በኩል እንደተሳካለት መመስከር ይቻላል፡፡ “ሰኞ ሜክሲኮ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በር ላይ የገጠመኝ የበር ዘብ ምግባረ ብልሹ ሆኖብኛል፡፡
ኮሚሽኑ የሚመጥነውን ህንጻ አስገንብቷል፡፡ ሌላው ቢቀር የፖሊስ አባል ነበርኩና በዚህ ደስ ይለኛል፡፡ የዘቡን ነገር አስቤ ግን ዋናው ቁም ነገር የድንጋይ ቤትን ሳይሆን ሰውን ማነጽ ነው፡፡ በማለት መተረቤ አልቀረም፡፡” (28)
በዚህ የባለታሪኩ ትረካ ላይ የምናስተውለው ጥሩውን በግልጽ ማድነቅ እና ሊስተካከል የሚገባውን ጠቆም አድርጐ ማለፉን ነው፡፡ ይህ በጐ ልማድ በስነ ጽሑፋችን እንዲዛመት ብንመኝም ደረቅ እውነታን እንዳለ ማስቀመጥ ግን ስነ ውበታዊ ጉድለት ሆኖ ሊታይ እንደሚችል ያግባባናል፡፡
ጌቱ ሶሬሳ በዚህ ልብወለድ ስህተቶችን እየጠቆመ፣ ጥንካሬዎችን እያደነቀ የመጻፍ ልማድ አንዳንዴ ወደ ደረቅ ሪፖርትነት እንዳያደላ ያሰጋናል፡፡ ለዚህ ምሳሌ ማየት ይቻላል፡፡
“ከ1956 ዓ.ም ጀምሮ በየጊዜው እየወጡ ያሉት እግረኛውንም አሽከርካሪውንም የሚገዙት እንደ ድሪቶ የተጣጣፉት ህጐች የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻሉም፡፡ አሁን አሁን እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች መልካም ቢሆኑም የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እና ህጉን የማስፈፀም እንቅስቃሴዎች በስፋት በቀጣይነት እና በተጠናከረ መልክ የማይዘልቁ በመሆኑ ሰላማዊ የትራፊክ ፍሰት ማግኘት አልተቻለም፡፡ ስለሆነም የትራፊክ አደጋ የእለት ከእለት አጋጣሚ መሆኑ ቀጥሏል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ኮልፌ አካባቢ ለበርካታ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት የሆነው አደጋ የዚህ ችግር ነፀብራቅ ነው፡፡” (31)
ይህ እውነት መሆኑ ያስማማናል፡፡ እንዲህ አይጻፍም የሚል ህግ አለመኖሩም እንዲሁ፡፡ ይሁንና በስነ ጽሑፍ ቋንቋ የተጻፈ ሊሆን ይገባ ነበር፡፡
እንዲህ ያለ ጽሑፍ ከአንድ የመንግስት አካል የቀረበ ሪፖርት ነው የሚመስለው፡፡ ሌላው የአንድ ሰሞን ገጠመኝ የሆነውን የኮልፌ አደጋ በቅርቡ ብሎ ለመጥቀስ መሞከር ለልብወለድ መጽሐፍ ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በሌላ አባባል ይህ በጋዜጣ ላይ ሊወጣ የሚችል ዘገባ ነው፡፡
እነዚህና መሰል ደረቅ እውነታዎች ስነ ጽሑፋዊ ማራኪነቱን ያደበዘዙት ይመስላል፡፡ መጽሐፉ ማዕከላዊ የማጠንጠኛ ሐሳቡን ያደረገው በፍትህ ላይ ነው፡፡ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥም እንደ አርበኛ የገዘፉና እንደባንዳ የኮሰሱ ባለሙያዎችን ስራ ያስቃኘናል፡፡
ያለምንም ተጨባጭ ማስረጃ በሰው ህይወት ላይ የሚፈርዱ ዳኞች፤ ዳኞችን የሚያሳሳት አቃቢ ህግ፤ አቃቢ ህግን የሚያሳስት ወንጀለኛ፤ ወንጀለኛን የሚያማልል የሞራል ልሽቀት፤ ሞራልን የሚያላሽቅ የነዋይ ፍቅር ከመጽሐፉ መነሻ እስከ መድረሻ በእኩያን ገፀ ባሕርያት አማካኝነት ልብ እየሰቀለ ይጓዛል፡፡
ከዚሁ ጐን አቀንቃኝ ሆነው የተሳሉ ገፀ ባህርያት ደግሞ የግል ጊዜና ገንዘብ ሳያሳሳቸው፣ ዛቻ ሽሙጥና ማስፈራሪያ አለፍም ሲል ተኩስና ግድያ ሳያስጨንቃቸው እውነትን እያቀነቀኑ እስከመጨረሻው ድረስ ሲጓዙ ይስተዋላል፡፡
በዚህ በኩልም መጽሐፉ ከመነሻ እስከመድረሻ ድረስ ምን ይፈጠር ይሆን በሚል እሳቤ ልብን ያንጠለጥላል፡፡
የታሪኩ አካሄድም ፈጽሞ ሊገመት በማይችል መልክ እየተወሳሰበ ይጓዛል፡፡ ይህ ይበል የሚያሰኝ የደራሲው ክህሎት ግን ችግር የለበትም ብሎ ለመደምደም የሚያስችል አይደለም፡፡ ቀጣዩ ድርጊት በአንባቢ ያልተገመተ እና ልብ እየሰቀለ እንዲሄድ ለማድረግ የተደረገው ጥረት አልፎ አልፎ ሲፈራርስ ማስተዋል ይቻላል፡፡ ገባ ወጣ የሚሉ ጥቃቅን /አስተኔ/ ገፀ ባህርያትን መጨረሻው አካባቢ ማከማቸቱ ከዚህ የተነሳ የገጠመው ፈተና ይመስላል፡፡
ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ዋነኛውን ባለታሪክ አለሜ፣ ከፈታኙ የክትትልና የጥብቅና ሥራው ጐን ለጐን እኩል ታስጨንቀው የነበረችው ሄለን፤ በመጽሐፉ ማጠቃለያ ላይ ይህ ነው የሚባል ማሰሪያ ያልተበጀላት መሆኑ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ፍቅር የታሪኩ ማሄጃ መንገድ ሆኖ ያለበቂ አመክንዮ ውል ሳይበጅለት ታሪኩ በዋል ፈሰስ መጠናቀቁ የፀሐፊውን ድክመት ይጠቁማል፡፡
የ “አመጻ ብድራት” ታስቦበት (ደራሲው የህግ ባለሙያ ከመሆኑ አንጻር) ከረዥም ጊዜ ልምድ በመነሳት የተሠራ እና ብዙ የተደከመ በመሆኑ ያስመሰግናል፡፡ መጽሐፉ አንዴ ብቻ ተነቦ የሚተው አይደለም፡፡ ተደጋግሞ የሚነበብ መጽሐፍ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የፊደል ግድፈቶች መኖራቸው እንደሚያደናቅፍ ሳንዘነጋ፡፡

Read 1666 times