Saturday, 04 February 2023 20:42

የእንቧይ ካብ

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(5 votes)

 ሮበርት ጆንሰን እባላለሁ፡፡ ሠዓሊ ነኝ። እነሆ ለንደን እምብርት ከሚገኘዉ ዘ ሀይደን የተሰኘ ታዋቂ ሆቴል ዉስጥ ተጎልቻለሁ፡፡ ወደ እዚህ ሆቴል ከመጣሁ ሰዓታት አልፈዋል። ይህ ሆቴል ከቀድሞ ፍቅረኛዬ ሄራን አበበ ጋር ሳንለያይ በፊት እናዘወትረዉ የነበረ ሆቴል ነዉ። ዛሬ፣ ከእሷ ጋር ከተለያየሁ ከረዥም ጊዜ በኋላ ነዉ ዳግም ሆቴሉን የረገጥኩት፤ ከእሷ ጋር እዚሁ ሥፍራ ያሳለፍኩት ታሪክ ጎትቶኝ። እዚህ ከመምጣቴ በፊት በንግስት ቪክቶሪያ ጎዳና ብቻዬን ስመላለስ ነዉ የዋልኩት፤ ሄራን የተመላለሰችበትን የእግር ማህተም የማስስ ይመስል፡፡ ሰዉ የአንድ ሥፍራ ቁራኛ የሚሆነዉ በተለየ ምክንያት ነዉ፡፡ ይህ ባይሆን፣ የቀትር ሐሩር፣ የሌሊት አመዳይ ሳይበግረኝ ከእሷ ጋር እጅ ለእጅ ተቆላልፈን በተንሸራሸርንባቸዉ የለንደን ጎዳናዎች ላይ ብቻዬን እንከራተት ነበር? ይህ ባይሆን ጠረኗን ኀሰሳ አብረን የዋልንባቸዉን ሥፍራዎች ዞሬ ሳካልል እዉል ነበር?
ሄራን ኢትዮጵያ ተወልዳ ያደገች ጠይም መልአክ ናት፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነዉ አፖሎ ቴአትር ነዉ፣ የሸክስፒርን ሐምሌት ለመመልከት ሄጄ፣ ከሁለት ዓመታት በፊት፡፡ በወቅቱ ቴአትሩን ለመታደም የመጣዉ ህዝብ ብዙ ስለነበር ቴአትሩ በራፍ ረዥም ሰልፍ ተሰልፌአለሁ፡፡ ዘ ግሬፕስ ኦፍ ራዝ የተሰኘ መጽሐፍ በግራ እጄ ይዣለሁ፡፡ ዐይኖቼን ጎዳናዉ ላይ ተክዬ መኪናዉንና አላፊ አግዳሚዉን በቸልታ እየተመለከትኩ ሳለ።
“ወንድም” የሚል የሴት ጥሪ ከሐሳቤ አናጥቦኝ በፍጥነት ወደ ኋላዬ ዞርኩ፡፡ የጠራችኝ ሴት የቀይ ዳማ ናት፡፡
“ይቅርታ፣ መጽሐፉን ላየዉ እችላለሁ?” ድምጿ ለስላሳ ነዉ፣ ልክ እንደ አርጋኖን በጆሮ ዉስጥ የሚፈስ፡፡   
“ይቻላል፡፡” መጽሐፉን ሰጥቻት መልሼ ዞርኩ፡፡
አእምሮዬ መዝግቦ የያዘዉን የእዚች ሴት ገፅታ በመጎልጎል ተጠምዷል፡፡ በአእምሮዬ የታተመዉ የሴቷ መልክ ይህን ይመስል ነበር፡ ዐይኖቿ የብር አሎሎ ናቸዉ፣ አፍንጫዋ ረዥም ሆኖ ከወደ ጫፉ ቀልበስ ይላል፣ ልክ እንደ ንስር አፍንጫ፡፡ ደረቷ ላይ በትእቢት ጉች ያሉትን ክብ ጡቶቿን በጥቁር ቢትልስ ጋርዳቸዋለች፡፡ ካላይ ቀይ ኮት ደርባለች፡፡ አእምሮዬ መዝግቦ የያዘዉን የሴቷን ተጨማሪ የመልክ ዝርዝሮች ከሰሌዳዉ ላይ እያገላበጠ ሳለ።
“ርእሰ ጉዳዩ ምንድን ነዉ?” አለች አንዴ እኔን አንዴ ደግሞ የሰጠኋትን መጽሐፍ እያፈራረቀች እያየች፡፡
“ልብወለድ ነዉ፡፡”
“እንዴት ነዉ ታዲያ? ጥሩ መጽሐፍ ነዉ?”  
“እጅግ በጣም! ንባብ ወዳጅ ከሆንሽ እንድታነቢዉ እጠቁምሻለሁ፡፡”
“እዉነትህን ነዉ?”
“አዎ፡፡”
“መልካም ገዝቼ አነበዋለሁ፡፡” አለችና ለሁለተኛ ጊዜ የመጽሐፉን ፊትና ጀርባ አገላብጣ አይታ መለሰችልኝ፡፡ “ሄራን እባላለሁ፣ ኢትዮጵያዊት ነኝ፡፡”  
“ሮበርት፡፡” የዘረጋችዉን እጇን ጨበጥኩ፡፡
በመጽሐፍ የተጀመረዉ የእኔ እና የሄራን ወግ ደርቶ ብዙ ቁም ነገሮችን አንስተን ተራችን እስኪደርስ ድረስ  አወጋን፡፡ ረዥሙ ሰልፍ ተጋምሶ ወደ ዉስጥ ለመዝለቅ ተራችን ሲደርስ ትዉዉቃችንን ለማጠንከር በማሰብ ቀድሜ የሁለት ሰዉ መግቢያ ትኬቶች ገዛሁ፡፡  
ከሄራን ጋር ወደ ቴአትር አዳራሹ ከዘለቅን በኋላ በእኔ መሪነት ሁለተኛዉ ረድፍ ላይ ቦታ መርጠን ጎን ለጎን ተቀመጥን፣ እኔ በቀኝ እሷ በግራ፡፡ ከፊሉ ቴአትር ታዳሚ ጎኑ ከተቀመጠ ሰዉ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ ወግ በመሰለቅ ላይ ነዉ፡፡ ይኸን ሁካታ ኪንግስተን ሆኖ፣ ኖቲነግ ሂል ሆኖ፣ ሆላንድ ፓርክ ሆኖ፣ ቸልሲ ሆኖ፣ ፉል ሀም ሆኖ መስማት ይቻላል፡፡ የቀረዉ ታዳሚ ደግሞ በዝምታ የቴአትሩን መጀመር በቋፍ የሚጠብቅ ነዉ፡፡ ሄራን ለብሳዉ የነበረዉን ኮት አዉልቃ ጭኗ ላይ አኖረችዉ፡፡ እኔ አካባቢዬን ቸል ያልኩ መስዬ ተጎልቻለሁ፣ ዐይኖቼ ግን አንዴ እሷን በስላቺ በመሰለል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ የግል ስልኬን እያፈራረቁ በማየት ተጠምደዋል፡፡
“ታዲያ መቼ ነዉ ስቱዲዮህን የምታስጎበኘኝ?” ስለ ሥራ ሕይወት ስንጫወት ሠዓሊ መሆኔን ነግሬአት ነበር፡፡   
“ሁሌም በሬ ክፍት ነዉ፡፡ ሥነ-ጥበብ ወዳጅ ነሽ?”   
“አዎ በጣም!” ከቦርሳዋ ዉስጥ ባወጣችዉ ቀይ የከንፈር ቀለም ከንፈሮቿን አስዋበች፡፡
“የትኛዉን የአሣሣል መንገድ ነዉ የምትከተለዉ? ማለቴ፣ ሪያሊስት ነህ ወይስ አብስትራክት ሠዓሊ?”
“ብዙዎቹ ሥራዎቼ አብስትራክት ናቸዉ፡፡”
“አብስትራክት ሠዓሊ ነሃ?”  
“አዎ፡፡”
“ሸጋ ነዉ፡፡ የአብስትራክት የሥዕል ሥራ አድናቂ ነኝ፡፡ ሸራ ላይ መገለፅ ያለበት ፍልስፍና መሆን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡”
“ግሩም ሐሳብ ነዉ፡፡ የሪያሊዝም የሥዕል ሥራን በተመለከተ ምን አይነት አተያይ አለሽ?”
“ሪያሊስቲክ የሆነ የሥዕል ሥራ ልክ እንደ አጥር ነዉ፣ የምናባችንን ወሰን የሚጋርድ፡፡”
“እንዴት ማለት?”           
“እንዲህ አይነቱ የጥበብ ሥራ ፊትህ የሚያቀርብልህ በገሀድ የምታየዉን የዓለምን መልክ ነዉ፡፡”
ቴአትሩ መጀመሩን የሚያበስረዉ ቀዩ መጋረጃ በመከፈቱ የአዳራሹ ታዳሚያን ሁካታቸዉን ገተዉ በዝና የሚያዉቋቸዉ ተዋንያን መድረክ ላይ ግጭት ፈጥረዉ ሲራኮቱ ለመመልከት አሰፈሰፉ፡፡ የመጀመሪያዬ አይደለም ከሴት ጋር ጎን ለጎን ተቀምጬ ቴአትር ስመለከት፣ የእዛ ቀኑ ግን የተለየ ድባብ ነበረዉ፡፡
የተዋናዮቹ ትወና ድንቅ ነዉ፣ በተለይ የመሪዉ ገጸባሕሪ አተዋወን፡፡ ሄራን፣ እጆቿን ጭኖቿ ሲነባበሩ የፈጠሩት ስንጥቅ ዉስጥ ወሽቃ ቴአትሩ ላይ አተኩራለች፡፡ ቀሚሷ ስሪቱ አጭር በመሆኑ ጠይም ጠብደል ጭኖቿን ከዐይን መጋረድ አልቻለም፡፡ ነፋሱ ስቦ አምጥቶ የሚያዉደኝ ከገላዋና ከልብሷ የሚነሳዉ ምዑዝ ጠረኗ የፅጌ አፀድ ዉስጥ የተገኘሁ ያህል እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ ዐይኖቼን ከሄራን ሰዉነት ላይ አሽሽቼ ቴአትሩን በትኩረት መመልከት ጀመርኩ፡፡ አእምሮዬ ተዉኔቱ ሐሳብ አጭሮበት መዳከር ጀምሯል፡፡ ብዙ ሰዎች ለምን ራሳቸዉን በጭንብል ጋርደዉ ይኖራሉ? ለምንስ ነዉ የተከናነቡበትን ግምጃ ገፈን እዉነተኛ ማንነታቸዉን ማወቅ የሚያዳግተን? ለዚህ ይሆን እጅግ ባመንናቸዉ የምንታለለዉ? እጅግ ባከበርናቸዉ የምንዋረደዉ? አእምሮዬ ዉስጥ የሚርመሰመሱትን ሐሳቦች ቸል ብዬ የሄራንን ገፅ ለማየት ወደ ቀኝ ስዞር፣ እሷም እኔን ለማየት ወደ እኔ ስትዞር አንድ ሆነ፡፡ እንደ ፀሐይ የደመቀ ፈገግታዋን ለግሳኝ ኮከብ ዐይኖቿን መድረኩ ላይ ተከለች፡፡ የፈገግታዋን ገፀ በረከት ዘግኜ እንደገና ዐይኖቼን ወደ መድረኩ ትእይንት መለስኩ፡፡
አእምሮዬ በተዉኔቱ ቀስቃሽነት ሐሳብ እያነሳ እየጣለ መብሰክሰኩን ቀጥሏል፡፡ መሪ ገጸባሕሪዉ የተናገረዉ ቁም ነገር በልብ ሰሌዳ ላይ እድሜ ልክ ተከትቦ የሚዘልቅ ነዉ። ጊዜዉ ይዘገይ አልያም ይፈጥን ይሆናል እንጂ ሰዉ የዘራዉን ማጨዱ አይቀሬ ነዉ። በእብሪት ተነፍቶ ግፍ የሠራ የማታ ማታ የሀፍረትን ማቅ መልበሱ አይቀርም፡፡ ማን ነዉ ግን ይኸ ሕግ እንዲፀና የደነገገዉ? መፍታት የተሳነኝ ታላቁ ምስጢርም ይኸዉ ጉዳይ ነዉ። ዓለሙ ላይ ፍትሕ አንዲሰፍን ይሆን ይኸ ስርአት የተዘረጋዉ? ኃያሉ ፍጥረት ደከማዉን እንዳይጨቁነዉ አቅዶ ይሆን ተፈጥሮ ይኸን ስርአት ያረቀቀዉ? የሚያብሰከስከኝን ሐሳብ ሸሽቼ ቀልቤን ወደ ተዉኔቱ መለስኩ፡፡
ቴአትሩ አልቆ ከግዮን ጋር አፖሎ ቴአትርን ለቀን እንደወጣን ዌስትሚንስተር የሚወስዳትን ታክሲ አሳፍሬአት፣ አድራሻዋን ወስጄ፣ ዉስጤ በአንዳች እንግዳ ስሜት እየታመሰ ዋንስወርዝ ገባሁ፡፡
*   *   *
አለ አንዳንድ መንገድ፣ ካልተለምነዉ መዳረሻ የሚያደርሰን፡፡ አለ አንዳንድ ክስተት፣ ጠዋት የካብነዉን ርእዮት ጀምበር ሳትጠልቅ ተቻኩለን አፍርሰን አዲስ እንድንገነባ ተፅኖ የሚፈጥርብን፡፡ አለ አንዳንድ ጊዜ ህልምና ገሀድ የሚቀናበሩበት፣ ቴአትር ቤት በራፍ ላይ በልኬ የተሰፋችዉን ሴት ሄራን አበበን አገኘሁ፡፡
*   *   *
ታላቅ አወዳደቅ የወደቅኩት በተላላነቴ ምክንያት ነዉ፡፡ ሄራንን ገፍቼ፣ ማዲሰንን ተከትዬ የሄድኩት እጥፍ ድርብ ደስታን እዘግናለሁ የሚል ከንቱ ተስፋን ሰንቄ ነዉ። እናም፣ በማዲሰን ሥጋ ተጠፍንጌ ሽፍትነትን ተማርኩ፡፡ ማዲሰን፣ ድንገት ሄራን ተንሰራፍታ ወደ ተቀመጠችበት ልቤ ዘዉ ብላ ገብታ፣ ገብቼ ያልተንቦጫረቅኩበት ሌላ የደስታ ወንዝ እንዳለ አሳየችኝ፤ ስሰለቻት ትዝታዋን አስታቅፋኝ ባካበተችዉ ጥበብ ቀስ ብላ ልትሸሽኝ ነገር፡፡ እኔ ሞኙ፣ የያዝኩትን ጥዬ አጨብጭቤ ቀረሁ። የሚቆጨኝ ማዲሰን ስለገፋችኝ አይደለም፣ ሄራንን ስለከዳሁ ነዉ፡፡ የሚበጀንን የማናዉቅ ግልቦች ነን፤ የሚወድኑን እየገፋን የሚሸሹንን እንከተላለን፡፡ እንዲህ ዛሬ፣ ሽፍትነቴ ዉሎ አድሮ በፀፀት መጋዝ እንደሚገዘግዘኝ ባዉቅ ኖሮ ዕንቁዬን በወጉ እይዝ ነበር፡፡ ሄራን ዕንቁዬ ነበረች፡፡ ከቶ እሷን ማን ይመስላታል? የመልካምነት አብነቷን፡፡
ማዲሰን ዘወትር ጥቁር መልበስ የምታዘወትር ሴት ናት፣ የአፍረት ልብሷ ቀለም ሳይቀር  ጥቁር ነዉ፡፡ የገና በአል በተከበረ በሦስተኛዉ ቀን (ዕለቱ ዓርብ ነበር) ከማዲሰን ጋር ከሥራ ወጥተን በእኔ ግብዣ ስትራትስፎርድ ወደሚገኝ ዝነኛ የጣሊያን ሬስቶራንት ተያይዘን ሄድን፡፡ እዛ ሬስቶራንት፣ ከማዲሰን ጋር እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ወይን እየተጎነጨን ስናወጋ ከአመሸን በኋላ ተያይዘን ዋንስወርዝ ወደሚገኘዉ መኖሪያ ቤቴ ሄድን፡፡ አብረን አደርን፡፡ የማዲሰን ገላ ልዩ ነበር፤ ግን ማዲሰን እንደ ሄራን ፍቅርን መስጠት የምትችል ሴት አልነበረችም፡፡ የማዲሰን አፍ ሲላወስ የሚደመጠዉ ድምጽ ማራኪ ነበር፤ ግን እንደ ሄራን ድምጽ በጆሮ ዉስጥ የሚፈስ ጥዑም ሙዚቃ አይደለም፡፡ ከማዲሰን ጋር ከሥራ የዘለለ ግንኙነት አልነበረንም፤ አብረን እራት በበላንበት ምሽት ግን የወሰድነዉ መጠጥ ገፋፍቶን ወንድማዊነት እና እህታዊነት የሚሉትን የግንኙነት ኬላ ጣስን፡፡ ማዲሰን ዕፀ በለስ ነበረች፣ የገላዋ ዉበት ፈተነኝ፣ ብስል ወይን ከንፈሮቿ ረቱኝ፡፡
ቅዳሜ ረፋድ፣ ገና ከዋለ አራተኛዉ ቀን፡፡ ከማዲሰን ጋር መኝታ ቤት መርፌና ክር ሆነን ተኝተን ነበር፡፡ ድንገት ወደ ቤቴ የመጣ እንግዳ ጉበኔ ላይ ተገትሮ የሰደደዉ አብሳሪ ድምፅ ቤቴ ዉስጥ አስተጋባ፡፡ በደዉሉ ቀስቃሽነት በመመረር እያጉተመተምኩ ከሞቀዉ የማዲሰን እቅፍ ወጥቼ በስካር የዛለ ጅስሜን እየጎተትኩ ሄጄ በር ከፈትኩ፣ በዐይኔ ያየሁትን ሰዉ ማመን አልቻልኩም፡፡ የእኔዉ ሄራን የንጋትን ፀሐይ በሚቀናቀነዉ ፈገግታዋ ተሞልታ ፊቴ ተገትራለች፡፡ ‘‘ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም’’ ትል ነበር ይችዉ የእኔ ጠንበለል፣ የአገሯን አበዉ ተረትና ምሳሌ ተዉሳ፡፡ በድንጋጤ አፌ መላወስ አቃተዉ፣ የጨዉ አምድ ሆንኩ። የገጠመኝ ዱብዳ በካበተ የተዉኔት ክህሎት የሚሸፋፈን አይነት አልነበረም፡፡ ምድር ምሼ ራሴን መቅበር አልችልም፡፡ ማምለጫ የለም፡፡ ሁኔታዬን ከቁብ ያልቆጠረችዉ ሄራን።
“ታዲያስ አንተ ሽፍታ? ሰዉ አይናፍቅህም?” ብላ ከንፈሬን በከንፈሮቿ አትማ ወደ ዉስጥ ዘለቀች፡፡ የዉርደት ቀን ቀርቧል፡፡ በሕይወቴ እንደ እዛ ቀን ነፍሴ የተሰቀቀበት ገጠመኝ አልገጠመኝም፡፡ ሄራን ካፖርቷን በእጇ እንዳንጠለጠለች፣ አፏን በድንጋጤ ከፍታ ወለሉ ላይ እዚህ እና እዛ የወደቁ የማዲሰን አልባሳትና ጫማ ላይ ዐይኖቿን ማንከባለል ጀመረች፡፡ ሄ
ራን ፈፅሞ ትመጣለች ብዬ ባልጠበቅኩበት ቀን ነበር ቤቴ የመጣችዉ፡፡ ሀኪም ስለሆነች ሌላ ጊዜ ቅዳሜን እጅግ ባተሌ ሆና ነበር በሥራ የምታሳልፈዉ፡፡   
“ምንድን ነዉ የማየዉ ጉድ? ማን ነዉ ቤትህ ዉስጥ ያለዉ?” ዐይኖቿን ሳሎኑን በመፈተሽ ጠመደቻቸዉ፡፡ የእኔ ዐይኖች የጠረጴዛዉን ግማሽ ያለበሰዉ የማዲሰን ቀይ ካፖርት ላይ ተተክለዋል፡፡
ደሜ በሰዉነቴ ዉስጥ ቢዘዋወርም፣ ሳንባዬ አየር በማስገባት በማስወጣት ቢጠመድም፣ ልቤ የሰርክ ተግባሩን ቢያቀላጥፍም ቀልቤ ግን አብሮኝ አልነበረም፡፡  
“መልስልኝ እንጂ!” አለች ሄራን በቁጣ፣ ጠይም ፊቷ ጉበት መስሏል፡፡ አንደበቴ መላወስ አልቻለም፡፡ መኝታ ቤት ዉስጥ የነበረችዉ ማዲሰን የሄራንን ድምፅ ሰምታ ኖሮ በር ከፍታ ብቅ አለች፡፡      
“ምንድን ነዉ እየተሠራ ያለዉ ድራማ? ማን ናት ይቺ ሴት!” እሳት የሚተፉ የመሰሉ ዐይኖቿ ዐይኖቼ ላይ አፍጥጠዋል፡፡ እንደተለጎምኩ ዐይኖቼን ከአስፈሪ ዐይኖቿ አሽሽቼ አቀረቀርኩ። ዐይንን ከጠሉት ነገር ላይ ማሸሽ እጅግ ቀላል ነዉ፣ አዳጋቹ ጉዳይ ሳይታሰብ ከሚገጥም ነፍስን ከሚያስጨንቅ ቀዉስ መሸሽ አለመቻል ነዉ፡፡ አቅም ቢኖረኝ እንደ ንስር አሞራ ይኸን ደባሪ ኩነት፣ ይኸን ቤት፣ ይኸን አካባቢ፣ ይኸን ከተማ፣ ይኸን አገር፣ መላዉ አዉሮፓን ለቅቄ እሰደድ ነበር፡፡
ሄራን ቃል ሳትተነፍስ፣ በመጣችበት እግሯ መሰስ ብላ ከቤቴ ወጣች፡፡ ማዲሰን መኝታ ቤቱ በር ላይ ተገትራ የሚካሄደዉን ድራማ በግርምት በመታዘብ ላይ ናት፡፡ ገጿ የተረበሸ ከተማ መስሏል፡፡ በደመነብስ ሄራንን ተከትዬ ወጣሁ፡፡
ሄራን ቅጥር ግቢዉን ጨርሳ ነጭ ፎርድ መኪናዋ ጋ ልትደርስ ጥቂት ርምጃ ሲቀራት ደረስኩባት፡፡ ዞራ በጥላቻ ድባብ አጉረጠረጠችብኝ፡፡ ዐይኖቿ ዕንባ አቅርረዋል። ከአንደበቴ የማወጣዉ ቃል ስላልነበር፣ በዐይኖቼ ይቅርታን ተማጠንኳት፡፡ ዐይኖቿ አርግዘዉት የነበረዉን ዕንባ  ዘረገፉት፡፡ የፀፀት አርጬሜ ኅሊናዬን አደማዉ፡፡ ሄራን መኪናዋ ዉስጥ ገብታ አስነስታ በተገተርኩበት ጥላኝ ከነፈች። የእኔ ንግስት፣ ኩሸት የማታዉቀዉ ርግብ የፈፀምኩባት ክህደት ልቧን ሰብሮት፣ ዳግም ደጄን ላትረግጥ ርቃ ተሰደደች፡፡
ሄራን አለት ነበር ልቧ፣ ከእዛ ቀን በኋላ ዳግም ዐይኔን አላየችም፡፡ እኔም ምልጃዋን መማፀን የሚያስችል ሞራል ስላልነበረኝ በቁጭት ረመጥ እየተንገበገብኩ ጭንጋፍ ህልሜን ታቅፌ ከሕይወቷ ገለል አልኩ፡፡ ሁሉ ነገር ተበለሻሽቶ ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ናፍቆቷ ያንሰፈስፈኛል፣ እንደ ወትሮዉ አቅፌአት የጀምበር ወጋገን ለብሰን በቴምስ ወንዝ ላይ በጀልባ መንሸራሸር እመኛለሁ፡፡ ግን ምኞቴ ከንቱ ነበር፣ ጉምን እንደመዝገን፡፡


Read 1070 times