Saturday, 11 February 2023 20:44

መዶሻ ያለው ሰው፤ እያንዳንዱ ችግር፣ ሚስማር ይመስለዋል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ እናት ቢምቢ ትንኝና ልጅ ቢንቢ ትንኝ ነበሩ፡፡ ልጅዬዋ ቢምቢ፤ በአገሩ እየተዘዋወረች ዙሪያ ገባው ውስጥ ነዋሪ - የሆኑትን እንስሳት፣ አዕዋፍና ነብሳት ልትጠይቃቸው ጎራ ልትል አሰበች፡፡ ይህንን ያወቀችው እናት፤
“መሄዱንስ ሂጂ፡፡ ዘመድ ማግኘትና መጠየቅ በጣም ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ወዳጅና ጠላትሽን መለየት ይኖርብሻል፡፡ ጠላት የመሰለሽ ወዳጅ ሆኖ ይገኛል፡፡ ወዳጅ ያልሺው ደግሞ፣ ጠላት ሆኖ ተለውጦ ታገኚዋለሽ። ለማንኛውም ማጣራትን የመሰለ ነገር የለም፡፡”
ልጅዬዋ ቢምቢም፤
“እሺ እማማ፣ ቀስ ብዬ እያጣራሁ ለማየት እሞክራለሁ” ብላ አካባቢዋን ልታጠና መንገድ ቀጠለች፡፡
መጀመሪያ ቢራቢሮን አገኘች፡፡ “ቢራቢሮ እንደምነሽ?”
ቢራቢሮ፤
“ደህና ነኝ” አለች፡፡
“በአካባቢው ያሉ ነብሳት ተስማምተውሽ ይኖራሉ?”
“አዎን፡፡ ግን ክረምትም በጋም ሳልቸገር ለመኖር በመቻሌ፣ ወረተኛ ነሽ እያሉ ይወቅሱኛል”
“እነሱ ምን ፈልገው ነው?”
“ወይ የበጋ ሁኚ ወይ የክረምት ሁኚ ነው የሚሉኝ”
“ቆይ፤ ስለዚህ ጉዳይ እናቴን ጠይቄ ምን እንደምትል እነግርሻለሁ” ብላት ቢምቢ ሄደች፡፡
ቀጥላ ጦጣን አገኘቻት፡፡
“ጦጢት እንደምንድነሽ?”
“ደህና ነኝ”
“ከእንስሳቱ ጋር ስትኖሪ ምን ችግር ገጥሞሽ ያውቃል?”
“ምንም ችግር አልገጠመኝም፡፡ ግን ሁሉም በአንድነት በእኔ ላይ ፈርደው ብልጣ - ብልጥ ብትሆኚ ምን አለበት ታዲያ?”
“ታታልይኛለሽ፡፡ ታሞኚኛለሽ እያሉ ነው፡፡”
“የራሳቸው ጅልነት ነው ተያቸው” ብላ ቢምቢ መንገድ ትቀጥላለች፡፡
ብዙም ሳትሄድ አንበሳን አገኘችው፡፡
ቢምቢ፤
“ደህና ዋልክ አያ አንበሶ?”
“ደህና ነኝ፤ ቢምቢ”
“እንስሳት አብረውህ ሲኖሩ ምን ይሉሃል?”
“ጉልበተኛ ነህ፡፡ አምባገነን ነህ፤ ነው የሚሉኝ” አለ እየተጎማለለ፡፡
“አቅም ስላነሳቸው ነው እነሱ፡፡ ተዋቸው፡፡” ብላው መንገዷን ቀጠለች፡፡
በመጨረሻ የተሰበሰቡ ሰዎች አግኝታ፣ እነሱን አዳመጠችና፣ እየመሸ ስለመጣ ወደ እናቷ ተመለሰች፡፡
የሆነችውን ሁሉ ነገረቻት፡፡
“ሰዎችስ ምን አሉሽ?” አለቻት እናት ቢምቢ፡፡
ልጅየዋ ቢምቢም፤
“ይገርምሻል፤ ሰዎችማ ሲያጨበጭቡልኝ ዋሉ” አለቻት፡፡
እናት ቢምቢም፤
“ልጄ ሁለተኛ እንዳትሳሳቺ! እንደ፣ሰዎች ክፉ የለም፡፡ ያጨበጨቡልሽ የመሰለሽም በመዳፍና መዳፋቸው ጨፍልቀው ሊገድሉሽ ሲሞክሩ ነው፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ እንዳትታለይላቸው!” አለችና መከረቻት፡- “ማጨብጨብ የሰው ልጆች ኃይለኛ መሳሪያ ነው፤ ተጠንቀቂ!”
***
አክራሪ መሆን መጥፎ የመሆኑን ያህል አድር - ባይና ወላዋይ መሆንም ያንኑ ያህል አስቸጋሪ ጠባይ ነው! ብልጣ ብልጥ መሆን የራሱ ችግር እንዳለው ሁሉ፣ ሞኛ - ሞኝ መሆንም ለማንም ብልጥ - ነኝ - ባይ የማታለል ተግባር ሰለባ ስለሚያደርግ፤ መጠንቀቅ ተገቢ ነው! አምባገነንነት ሁልጊዜ አያበላም፡፡ በእርግጥም የተገፉ፣ የተበደሉ፣ ፍትሕ - ያጡ፣ የተመረሩ ህዝቦች በተነሱ ጊዜ ማናቸውም ፈላጭ - ቆራጭ አገዛዝ አሳሩን ያያል፡፡ በዓለም ላይ ስንት አምባገነኖች ተሰባብረው እንደወደቁ ማሰላሰል ነው! የደገፉ መስለው ጧት ማታ ሲያጨበጭቡልን ጤነኛ መስለውን፤ “አሁን ነው ራስን ማሳየት” ብሎ ብቅ ማለት አደጋ አለው! ለመውረድ ብዙ ሽቅብ መውጣትም ክፉ ባህሪ ነው፡፡ ሁሉን፣ ሁልጊዜ አገኛለሁ ማለትም ግብዝነት ነው፡፡ እያጨበጨቡ ጎል ከሚከቱን ይሰውረን!
ዛሬ የትምህርት ጊዜ ነውና ትምህርታችንን ይግለጥልን፡፡ እንደ እስያ፤ “ዕውቀት እያለ የሚማር ጠፋብን” የሚል ትራጀዲ ውስጥ እንዳንገባ አምላክ ይጠብቀን!
“ምዕራቡ ዓለም ሲያስነጥስ ሌላው ክፍለ ዓለም ኒሞኒያ ይይዘዋል” የሚለውን በማሰብ፤ እንዳይምታታብን ራሳችንን እንቻል! የራስን የመሰለ ምንም ነገር የለም፡፡
የመጨረሻው እንግሊዛዊ የህንድ ገዢ ሎርድ ሉዊ፣ ለማህታማ ጋንዲ እንዲህ አለው “እኛ ከወጣን በህንድ አገር ቀውስ ይፈጠራል!”
ይሄኔ ማህታማ ጋንዲ፤
“አዎን ቀውስ ይፈጠራል - ቀውሱ ግን የራሳችን ነው!” አለና፤ ኩም አደረገው፡፡
“የራሳችንን ቀውስ ‘ራሳችን እንፈታዋለን!”
አንድ ፀሐፊ ካነበብናቸው በርካታ መጣጥፎች አንዱ ላይ፤ “የአዕምሯችን ማዕከል፣ እና ደጃፉም ሆነ ግንባሩ በጣም ሩቅ ለሩቅ ናቸው! ግን ተቀናጅተው ሥራ ይሰራሉ” ይላል፡፡ የእኛም ተግባር እንደዚሁ የተቀናጀ መሆን ይኖርበታል! ከተሳሰብንና ከተናበብን የስሌት ስህተት አንሰራም፡፡ የፍርድ ማዛባት ስህተት አንሰራም፡፡ የመረዳዳት ማቃት ስህተት አንሰራም፡፡
ዛሬ “ነፃ ኢኮኖሚ”፣ “ዲሞክራሲ”፣ “መልካም አስተዳደር” አስፈላጊ ነው ብለን ተፈጥመናል፡፡ ያም ሆኖ የፌደራሊዝምን ስርዓት፣ በተለይ የብሔር ብሔረሰብን ፌደራሊዝም ጨርሶ ካላደገው ካፒታሊዝማችን ጋር አብረን ለማስኬድ ብዙ እንቅፋት ሲፈጠርብን ይታያል፡፡ ኦሊቨር ጎልድስሚዝ የተባለው ገጣሚ፤ “ሀብት ይከማቻል ሰው ይበሰብሳል” ወደ ውስጥ እያየን፣ ራሳችንን እንፈትሽ፡፡ ነፃ ኢኮኖሚ ስንል በምን የዕድገት ደረጃ ላይ ላለ ኢኮኖሚ ነው ያጨነው? ብለን እንጠይቅ፡፡ ዲሞክራሲ ስንል በምን ደረጃ ላለ አገር ነው ያስቀደድነውና ስፌቱን የምንመርጠው? እንበል፡፡ ከፊውዶ ቡርዥዋ ሥርዓት ገና ሙሉ ለሙሉ ባልተላቀቀ ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ላይ መልካም አስተዳደርን መጋለብ ቀርቶ መፈናጠጥስ ይቻላል ወይ? ብለን እንጠይቅ! ታላቅ ኃይል ያዘለውን ካፒታሊዝም፤ ከማህበረሰባዊ ኮንሰርቫቲዝም ጋር ማጋባትስ አማራጭ ይሆናል ወይ? (ምናልባት የቻይናን፣ የህንድን ስነልቦና ቢሰጠን) ብለን እንመርምር፡፡
የንድፈ-ሀሳብ መንገዳችን ከረኮንች ነው፡፡ እንኳንስ አስፋልት ኮብል-ስቶኑም ገና እያንገዳገደን ነው፡፡ ቆም ብሎ የሚያስብ አስተዋይ አዕምሮ አሁንም ያስፈልገናል! ከዕለታት አንድ ቀን የያዝነው ቲዎሪ ስህተት ሆኖ ቢሆንስ? ብለን መጠያየቅ አይከፋም፡፡ ለሁሉም ህመም አንድ መድኃኒት በመስጠት (ፓናሲያ እንዲሉ) ፈውስ እናገኛለን ብሎ ማሰብ ቀቢፀ- ተስፋ ነው፡፡ ማርክ ትዌይን፤ “መዶሻ ያለው ሰው፣ እያንዳንዱ ችግር ሚሥማር ይመስለዋል!” የሚለው በእኛ ዓይነቱ ላይ ሲሳለቅ ነው፡፡ ከዚህም ይሰውረን፡፡
 

Read 1552 times