Saturday, 11 February 2023 21:11

የቱጋ ነን? ወዴትስ ነን?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(2 votes)

ሊሻሻሉ የሚችሉ ብዙ ናቸው። መነካት የሌለባቸው ነባር መሠረቶች ደግሞ አሉ።
             
       “አነሳስና አወዳደቅ” እየተባለ የበርካታ ከተሞችና የብዙ መንግስታት ታሪክ ተጽፏል።
የአጋድ ግን ይለያል።
ከምንም ተነስታ፣ ከሁሉም በላይ የገነነች፣ ከዚያም የአለም መዲና ተብላ የተወደሰች፣… ብዙም ሳትቆይ ድርሿ የጠፋች ከተማ ናት።
አንድ ስንዝር የማትሞላ፣ ከቁጥር የማትገባ ደቃቃ መንደር ነበረች። ድንገት ገነነችና ትልልቆቹን አንጋፋ ከተሞች ጥላ፣ መናገሻ ሆነች።
“ከታችኛው ባህር እስከ ሌላኛው ባሕር የመላው ዓለም መዲና” የሚል ስያሜም ተሰጣት- አጋድ።
በጣም የተጋነነ ሊመስል ይችላል። ግን አልተጋነነም።
ጊዜው ከ4300 ዓመት በፊት እንደሆነ አስቡት።
የአንድ መስራችና ጌታ፣ ከተማይቱ የምልዓተ ዓለሙ መዲና መስላዋለች። እሱም የምድር ሁሉ ገዢ ነኝ ብሏል። አንድናላግጥበት ራሱን ያመቻቸ ይመስላል። ነገር ግን የዘመኑን ርቀት አትርሱ። በዚያ ላይ፣ በዚያ ዘመን፣ አቻ የለሽ የዓለማችን “ልዕለ ኃያል” መንግሥት ነበር። ግዛቱም ቀላል አይደለም። እውነትም ከባሕር እስከ ባሕር ነው።
ከወዲያ በኩል በተራሮች የታጠረ ነው። በወዲህ በኩልም እስከ ጥግ ተጉዟል። ሕይወት አልባ በረሃ ነው። ሰውና አራዊት፣ ረዣዥም ዛፍና የፍራፍሬ ተክል ይቅርና፣ ለእሾህና ለጊንጥ እንኳ የማይሆን እልም ያለ ደረቅ በረሃ፣ አሸዋና አቧራ ነው።
ይህን አይቷል የአጋድ መስራች መሪ።
ከታች በኩልም፣ ሁለቱን “የዓለማችን ትልልቅ ወንዞች” ተከትሎ እስከ መጨረሻው ሄዷል። እስከ ባሕር ዳርቻ ደርሷል።
“የታችኛው ባሕር” እየተባለ ሲነገርለት ሰምቷል። ሄዶም በአይኑ አይቷል።
ወደላይም ብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዟል።
“የላይኛውን ባሕር” ተመልክቷል።
ምን ቀረው?
በአጠቃላይ፣ በፍጥረተ ዓለም የተተረከላትን መሬት፣… ማለትም ከትልቅ ውቅያኖስ ውስጥ ተገልጣ የወጣችውን “የብስ”፣… በባህር የተከበበችውን ምድር ከጫፍ እስከ ጫፍ ተመላልሶባታል።
ለሽርሽር አይደለም። “የምድር ሁሉ፣ በአራቱ አቅጣጫዎች የአራቱ ክፍለ ዓለማትና ማዕዘናት ጠቅላይ ገዢ” ብሎ ራሱን የሰየመው፣ አንድ ቦታ ላይ ተቀምጦ አይደለም።
በወዳጅትም በጠላትነትም፣ ለጦርነትም፣ ለሰላምታም፣ ግራና ቀኝ፣ ታች ላይ ዘምቷል።
ሳርጎን ይባላል።
ሳሩኪን፣ ሳሩቂን ተብሎም ተጽፏል። የአባቱ ስም ግን አይታወቅም።
በእርግጥ፣ “አባቱ የዝነኛዋ ከተማ የኡር ነዋሪ ነበር” ብለው ያኔ ከበርካታ ሺ ዓመታት በፊት የተረኩ የጥንት ጸሐፊዎች አሉ።
የሳርጎን አባት፣ የኡር ቤተመንግስት አትክልተኛ እንደነበር፣ ከዚያም ተወዳጅትንና ተዓማኒነትን በማትረፍ የቤተመንግስት ቤተኛ፣ የንጉሱ ታማኝ አማካሪና ዋና ባለስልጣን ለመሆን እንደበቃ የያኔ ፀሐፊዎች ይጠቅሳሉ- የሳርጎን አባት ማለታቸው ነው።
በሌላ አነጋገር፣…
ሳርጎን፣ ለንግስና የሚያደርስ የትውልድ ሐረግ መምዘዝ አይችልም። አባቱ አትክልተኛ ከነበረ።
ግን ደግሞ፣  ሳርጎን፣ ለቤተመንግስትና ለንጉስ፣ ለሕግና ለሥርዓት፣ ለስልጣንና ለታሪክ፣ “ባይተዋር” አይደለም። የቤተመንግስት ባለሟል፣ ለዚያውም የንጉሡ ታማኝ ባለሰልጣን ከነበረ አባቱ።
ሳርጎን፣ በአንድ በኩል “የቤተመንግሥት ሰው ነው”። በሌላ በኩል ግን፣ የገዢዎች ወገን “አይደለም”።
እነዚህን ሁለት ነገሮች ለማስታረቅ መሞከር፣ የሁሉም መንግስታት ራስ ምታት ነው።
የነባር የወራሽነትን እንዲሁም የለውጥ አርበኛነትን ይፈልጋሉ አዳዲስ ንጉሦችና ባለሥልጣናት።
ሳርጎን በራሱ ትዕዛዝ በሐልውት ያስቀረፀው ጽሁፍ ላይም ይህን የንጉሦች ምኞትና ፈተናቸውን ማየት እንችላለን።
አባቴን አላውቀውም ይላል ጽሁፉ። የሩቁ የተራራማው ጠረፍ የገጠር ሰው ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል- ስለ አባቱ ሲናገር። ከዚህ ውጭ ምንም አያውቅም። የአባቱ ስም ማን እንደሆነ እንኳ አያውቅም። በሌላ በኩል ግን  እናቴ ልዕልት ነበረች ይላሉ።
 በአንድ በኩል “የነባሩ ስርዓት ወራሽ ነኝ። የቤተመንግስት ቤተኛ ነኝ” ይላል። እናቱ ልዕልት ናትና። ለዚያውም እጅግ የተከበረች ናት፡፡ የንጉሦችን ሥልጣን የማጽደቅና የመሻር ስልጣን ነበራት።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከነባሩ ስርዓት ጋር ያልተነካካሁ፣  ነባሩን ድል አድርጌ፣ ብልሽቱንና በደሉን ያስወገድኩ የለውጥ አርበኛ ነኝ ይላል። ችግራችሁን የማወቅ እንደናንተው ተራ ሰው ነኝ ይላል- የጉዲፈቻ ልጅ እንደሆነና አሳዳጊ አባቱ አትክልተኛ እንደነበረ በመግለጽ።
ነባሩን ያስወገደ ድል አድራጊ አዲስ ንጉስ እንደሆነ፤ ግን ደግሞ ነባሩን አክብሮ የሚጠብቅ አለኝታ ወራሽ እንደሆነ ለመግለጽና ለማሳመን ነው ጥረቱ።
አዎ፣ ብልጣብልጥነትና ሾላካነት ይመስላል። ሊሆንም ይችላል።
ግን ደግሞ፣ ነባሩን የማክበርና አዲስ የተሻለ ነገር የመመኘት ስሜቶች፣ ተፈጥሯዊ ስሜቶች ናቸው።
በነባር ችግሮች ላይ ቅር እየተሰኘ አንዳች ለውጥን መናፈቅ፣…
ነባሩን የሚያሳጣ የባሰ ለውጥ እንዳይፈነዳ መስጋት፣… ከሰው ተፈጥሮ የሚመነጩ ዘላለማዊ የሕይወት ገጽታዎች፣ የዘወትር የእለት ተእለት የኑሮ ጥያቄዎች ናቸው።
ለዚያውም ፈታኝ ገጽታዎች፣ ከባድ ጥያቄዎች ናቸው።
በእርግጥ፣ ቀላል የኑሮ ዜቤዎች እንደሆኑም አንርሳ።
ትክክለኛና መልካም የሆኑ ነባር ሃሳቦችና ባህሎችን አክብረው  መጠበቅ፣
ነባር ስህተቶችንና የጥፋት መንገዶችን  ደግሞ ማስተካከልና ማስወገድ፣ መግታትና ማቃናት ይቻላል።
አዳዲስ የመሻሻል ለውጦችን በትክክለኛ መንገድ እውን ለማድረግ መትጋት፣…
በተሳሳተ ሃሳብ ከነባሩ የባሱና ጠንካራ መሠረቶችን እያፈረሱ የሚያበላሹ የጥፋት ለውጦች እንዳይፈጠሩ መጠንቀቅ፣ አስጊ አደጋዎችን መከላከልም ይቻላል።
እናም፣ እነዚህ ሁለት ነጥቦች፣ ያን ያህልም ውስብስብና ከባድ ነጥቦች አይደሉም ማለት ይቻላል።
ከነባርም ከአዲስም ጥሩ ጥሩውን መደገፍ፣…
ከነባርም ከአዲስም መጥፎ መጥፎውን መገሰጽ እንደማለት ነው።
በትክክል እንዲህ የተጣመሩ የውሕደት ሃሳቦች፣ ለግንዛቤ ያስቸግራሉ? አያስቸግሩም።
ችግሩ ምንድነው? መፈክር ለማስጮህ፣ ተቀናቃኝን ለማውገዝ፣ ስሜት ለማጋጋል አይመቹም። መስመሩን አጣርቶ ሚዛኑን አስተካክሎ ነገሮችን መገንዘብና መዳኘት ይኖርብናል። ለዚህም ትክክኛ የውሕደት “አስተሳሰብ” ያስፈልጋል ብሎ መናገር አንድ ቁም ነገር ነው። ትክክለኛ የአስተሳሰብ ቅኝትን ከራስ ጋር ማዋሃድና የዘወትር ባሕርይ እንዲሆን ማድረግ ደግሞ ሌላ ነገር ነው።
ከዚህ ይልቅ፣ በጭፍን መደገፍና መቃወም፣ በጭፍን ሆይሆይታ ማሞገስና በኡኡታ ማውገዝ፣ በጣም ቀላል ይሆኑልናል።
በነባሩ ላይ የተማረረና ቅሬታው የገነፈለ ሰው፣ ማንኛውም አይነት ለውጥ የገነት መንገድ መስሎ ይታየዋል። ተስፋና ናፍቆት እንጂ ስጋትና አደጋ እንዲወራ አይፈቅድም። ማሰብ አይፈልግም።
ከነባሩ የባሰ አደገኛ ለውጥ እንዳይመጣ የሚያሰጉ ሰዎች ደግሞ፣ ነባሩን በጭፍን የሚያጥላሉና  ለማፈራረስ የሚቀሰቅሱ የለውጥ ዘማቾች እጅግ ገንነው ይታይዋቸዋል። የባሰ ከሚመጣ ነባሩን መጠበቅ ይሻላል የሚል ስሜት ይበረታባቸዋል።
በዚህ መሃል፣ የነባሩን ጥሩና መጥፎ ገጽታዎች፣ የለውጥ አጥፊና አልሚ ገፅታዎችን ለመተንተን የሚሞክር ሰው ይኖራል?
ቢኖርስ ማን ይሰማዋል?
እንደ ፈሪ አድርባይ፣ እንደ ጀብደኛ ልወደድ ባይ፣ እንደ ወላዋይ ሲብስም እንደ ከሃዲ ይቆጠራል እንጂ።
ለዚህም ነው፤ የነባሩ ቅርስና ሸክም፣ የለውጥ ተስፋና አደጋ፣ በጣም አስቸጋሪ ጥያቄዎች የሚሆኑት።
ለዚህም ነው፣ “የነባሩ ወራሽና የነባሩ አስወጋጅ ነኝ” ብለው የሚያውጁ ንጉሦች በብዛት በታሪክ የታዩት።
በአንድ በኩል፣ ቅሬታ የበረታባቸውን ዜጎች ለመማረክ፣…
በሌላ ደግሞ በስጋት የተጨነቁትን ለማረጋጋት… ምን ማድረግ ይቻላል?
“ነባሩን የሚያስወግድ የነባሩ ጠበቃ ነኝ። አደራ ተቀባይና የለውጥ አርበኛ ነኝ።” ይላል ብልጣብልጥ።
ግን ደግሞ፣ ከቅን ልቦናና ከእውቀት የመነጨ ንፁሕ የጥበብ አባባልም ሊሆን ይችላል። ለነባሮቹ ጥሩ መሰረቶች የሚቆረቆር ጠበቃ፣… መጥፎ ነባር ስህተቶችን ደግሞ በአዲስ የተሻለ ለውጥ የሚያስወግድ፣…
በአንድ ጊዜ የነባሩ አወዳሽና ወቃሽ፣ በአንድ ጊዜ ጥሩ የለውጥ ፊታውራሪና የመጥፎ ለውጥ ተፃራሪ ቢሆን ስህተት ነው?
እንዲህ ሲታይ የብልጣብልጥነት ጉዳይ አይደለም። ግን ይመስላል።
አንዳንዴም ከመምሰል አልፎ፣ እጅግ እየተምታታ ግራ የሚያጋባ ቅዠት ይሆናል።
የኦዲፕሰን ትረካ ከዚህ አይነት ቅዠት ጋር አያይዘን ልናየው እንችላለን።
በአንድ በኩል፣ ከሌላ አገር የመጣና ነባሩን በደለኛ ንጉሥ አሸንፎ ዙፋን ላይ የተቀመጠ፣ ድል አድራጊ የለውጥ ጀግና ይመስላል- ኦዲፐስ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የንጉሥ ልጅና ሕጋዊ አልጋ ወራሽ እንደሆነ የሚገልጽ ነው ትረካው።
የኦዲፐስ የወራሽና የአስወጋጅ ሁለት ትረካዎች፣ በጠማማ መንገድ ተጠላልፈው ሲወሳሰቡ፣ የኦዲፐስ አይነት ቅዠት ይፈጠራል።
 አባቱን ገድሎ እናቱን የሚወርስ አዲስ ንጉሥ ይሆናል።
በምሳሌያዊ ዘይቤ ሲተረጉሙት፣…
ከፋም ለማም፣ አረረም መረረም፣ አማረም ጣፈጠም፣… ነባሩ መንግስት፣ አገርንና ድንበርን፣ ሕግንና ስርዓትን ጠብቆ ያቆየ የአባቶች ዘመን መንግሥት ነው።…
በአመፅና በጦርነት፣ ወይም በሽኩቻና በሴራ የሚመጣ አዲስ የልጆች መንግስት፣ የቀድሞውን የአባቶች መንግሥት በጭካኔ አስወግዶም አልያም በቀስታ ገፋ አድርጎ፣ የሥልጣን ዙፋኑን ይነጥቃል ወይም ይወርሳል። አዲስ የልጆች ንጉሥ፣ ጥሶ ወይም አስከፍቶ ይገባል። ነባሩን ቤተመንግሥት ነባሯን እናት አገር ጠልፎ ይወስዳል ወይም ይረከባል።
አባባ ጃንሆይን ገድሎ እማማ አገርን ይወርሳል።
ኃጥያቱን ሲያበዙት ደግሞ፣… አባቱን ገድሎ እናቱን አገባ ይሉታል ወቃሾቹና ተቀናቃኞቹ።
አዲሱ ንጉሥም ዝም አይልም። አፉ አያርፍም።
ነባሩን መንግስት አፍርሶ፣ ነባሩን ንጉስ ገድሎ ሲያበቃ፣ እውነተኛ የመንግሥት ሥልጣን ተረካቢ ነኝ፣ እውነተኛ የንጉሥ ልጅ ህጋዊ አልጋወራሽ ነኝ ይላል። አስተማማኝ የአገር አለኝታ ነኝ፣ ንግሥቲቱን በክብር እጠብቃሁ። በይሁንታም ንግስቲቱ እጃቸውን ዘርግተው ተቀብለውኛል ይላል።
ተቀናቃኞቹም ንግግሩን ተቀብለው፣… አዎ፣ አዎ፣ ንጉሡን የገደልክ የንጉሥ ልጅ ነህ። አዎ፣ ንግስቲቱን ያገባህ የንግስት ልጅ ነህ ይሉታል።
እሱ ሲምታታበት ወይም ለማምታታት ይሟሟታል። ተቀናቃኞቹም ከግራና ከቀኝ በተቃራኒ አቅጣጫዎች ያዋክቡታል።
ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አይጣፍጥም፤ አንተም ያው የነባሩ ስርዓት ወራሽ ነህ ብለው የለውጥ አርበኝነቱን ያጣጥሉበታል- ገሚሦቹ።
ሌሎች ተቀናቃኞች ደግሞ፣ “የበላበትን ጉልቻ ሰበረ፣ ያጎረሰውን እጅ ነከሰ፣ ስርዓት አልበኛ “አፄ በጉልበቱ” ሆነ።” ከማለት ያወግዙታል። ወራሽነቱ ህገ-ወጥ የውሸት ወሬ ነው ብለው ይወነጅሉታል።
በአንድ በኩል፣ “ንጉሥ ሄደ፤ ንጉሥ መጣ። ታዲያ ምኑ ተለወጠ!” ብለው ያብጠለጥሉታል። ስሙ ብቻ ተቀየረ ይሉታል።
በሌላ በኩል፣ “ንጉሥ ሞተ፣ ወንበዴ ነገሠ። ታሪክ ተበላሸ። ሥርዓት ፈረሰ” ብለው ያወግዙታል። አገር መጫወቻው ሆነ ይሉታል።
አዲሱስ ንጉስ መች ዝም ይላል። ሁለቱንም ተቀናቃኞች ለማስተባበል ወይም ለማሳደድ ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱንም ተቃራኒዎች ለማሳመንና ለማግባባት ወይም ለመሸንገልና ለማምታታት መከራውን ያያል።
ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ በአግባቡ ሥልጣኑን የተረከበ ህጋዊ ወራሽ እንደሆነ ይናገራል- ሥርዓት አልበኛ ወንበዴ አለመሆኑን፣ ለሽፍትነት ዋሻ፣ ወደ ቤተመንግስት የገባ አፄ በጉልበቱ እንዳልሆነ ያስረዳል። ወራሽ ነኝ፣ የስርዓቱ ልጅ ነኝ ይላል።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ነባሩን ሥርዓት የገረሰሰ ሥር-ነቀል የለውጥ አርበኛ እንደሆነ ይገልፃል- ከነባሩ ነጥቄ፣ ገሚሱን  ገድዬ፣ ገሚሱን አስሬ፣ ቀሪውን አባርሬ… እያለ ይዘረዝራል።
ገርሳሸና ወራሽ፣… ነጣቂና ጠባቂ እንደሆነ ለማሳመን ይጥራል። እንዳልሆነ ለማስረዳትና ለማስተባበልም ጠብ እርግፍ ይላል።
ወራሽም ገርሳሽም?
የንጉሡና የንግሥቲቱ ልጅ?
ገዳይም ተወላጅም ነህ?
እንግዲያውስ ንጉሡን ገድሎ ንግሥቲቱን እንደሚማርክ ሽፍታ ሆነሃል የሚል ነው የኦዲፐስ ትረካ አተረጓጎም።
ታዲያ፣ በሼክስፔር የተፃፈው ሃምሌት የተሰኘው ትያትርም፣ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ትረካ ይዟል።






Read 1285 times