Print this page
Saturday, 11 February 2023 21:14

ጥር - በኢትዮጵያ ስለእናቶች ደህንት የሚወሳበት ወር

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ጥር - በኢትዮጵያ ስለእናቶች ደህንት የሚወሳበት ወር


       ኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት በተመለከተ ባለፉት አስርት አመታት ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝ ገቡዋ አለም የተነጋገረበት ነው፡፡ እንደውጭው አቆጣጠር በ2000 አመተ ምህረት የነበረው የእናቶች ሞት ከ100,000 በህይወት ከሚወልዱ ወደ 871 የሚሆኑ እናቶች ይሞቱ ነበረ ይህ ቁጥር ተሻሽሏል። እንደውጭው አቆጣጠር በ2017፣ ከ100,000 በሕይወት ከሚወልዱ እናቶች መካከል 401 ያህሉ እናቶች ለህልፈት እንደሚዳረጉ ተገልጦአል፡፡
መረጃው በጊዜ ሲሰላ በየአመቱ 12‚000 እናቶች እንደሚሞቱ ያሳያል፡፡ በቀጥታ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው ሞት ወደ 85% የሚሆነውን የእናቶች ሞት ድርሻ ይይዛል- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ2021 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው፡፡ ሴቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር ባልተያያዘ መንገድ ቢሞቱ የእናቶች ሞት ተብሎ አይመዘገብም፡፡ የእናቶች ሞት የሚባለው ሴቶች ከእርግ ዝናና ወሊድ ጋር በተያያዘ ለሞት ሲዳረጉ ነው፡፡ ከዚህ ውጭም የእናቶች ደህንነት የሚቃወስ ባቸው የጤና ጉድለቶች፣ ለምሳሌም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ምክንያት የአካል ጉዳተኝነት ፣የፊ ስቱላ ህመም፤ የማህጸን ከቦታው መልቀቅ፤ አደገኛ የሆነ የወገብ ሕመም፤ ድብርት እና ከበድ ያለ ድካም ሊከተትባቸው ይችላል፡፡
በኢትዮጵያ፣ ፊስቱላ በተለይም በተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ባሉ ሴቶች ላይ የተለመደ በእናቶች ላይ የሚደርስ የጤና ጉዳት ነው፡፡ የፊስቱላ  ምክንያት ደግሞ የታዳጊዎች ወይንም የወ ጣት ሴቶች ካለ እድሜአቸው ለእርግዝና እንዲጋለጡ ማድረግና ምጣቸው በሚመጣበት ወቅት አፋጣኝ የሆነ እርምጃ አለመወሰዱ ወይንም ችላ መባሉ ነው፡፡
ወጣቶቹ ምጥ በሚመጣባቸው ወቅት በአፋጣኝ ወደ ጤና ተቋም ካልተወሰዱ እና በሰለጠነ ባለሙያ እንዲታዩ ካልተደረጉ በመ ወለድ ላይ ያለውንም ህጻን ከማጣት በተጨማሪ፣ በተራዘመ ምጥ ምክንያት በማህጸን ዙሪያ ባሉ የሰውነት ክፍሎች ላይ የመቀደድ  ጉዳይ ይፈጠራል።
የመጸዳጃ አካሎቻቸው እንዲሁም ማህጸናቸው ከጥቅም ውጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ ይስተዋላል፡፡       
ከፍተኛ የሆነው የእናቶች ሞት ገና በተወለዱ ህጻናት ከሚከሰተው የጨቅላዎች ሞት ጋርም ይገናኛል፡፡ ለዚህም ከ1000 በህይወት ከሚወለዱ ጨቅላዎች ወደ 29 የሚሆኑት ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው እናትየው በምትወልድበት ጊዜ የነበራትን አስቸጋሪ ሁኔታ ነው፡፡ በአብዛኛው ጨቅላዎች የሚሞቱት ጊዜያቸው ሳይደርስ መወለዳቸውና ኢንፌክሽን(መመረዝ) በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው፡፡  
እናቶች ይሞታሉ ሲባል፣ ከቀጥተኛ ምክንያቶች መካከል ጽንስን ማቋረጥ የሚገኝበት መሆኑን ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡ ነገር ግን በሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች እና የእናቶቹም አረ ዳድ ተጨምሮበት፣ በህገወጥ መንገድ ጽንስን የማቋረጥ ድርጊት ቀርቷል ባይባልም እንኩዋን በጣም በመ ቀነሱ ምክንያት ዛሬ ዛሬ ጽንስን ማቋረጥ ለእናቶች ሞት ምክንያት መሆኑ ቀንሶአል፡፡ በሌላ በኩል ግን ህጻናቱ በሚሞቱበት ጊዜም ይሁን ከሞቱ በሁዋላ በሚኖረው የደም መፍሰስ ምክ ንያት ሞቶች መከሰታቸው አልቀረም፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ የእናቶች ሞት እንዲቀንስ ያስቻለው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች እና በትብብር ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር ተናቦና አብሮ በመስራቱ እንዲሁም የህብረተሰቡ እና ስራቸውን ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር አቀናጅተው ትኩረት ሰጥተው በሚሰሩ ኃይሎች እገዛ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያምናል፡፡
የእቶች ሞት ይህን ያህል የመቀነሱ ድል የተገኛው የሰለጠነ የማዋለድ አገልግሎት ሰፋ ባለ መንገድ በመላ ሀገሪቱ እንደውጭው አቆጣጠር በ2000 ዓ/ም ከነበረው ከ8% በ2016 49% እንዲደርስ በመደረጉ ነው፡፡
ዘመናዊ የሆነው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ያልተፈለገ እርግዝናን ለማስወገድ ምክንያት መሆኑ፤
በእርዝና ክትትልና ወሊድ ጊዜ እንዲሁም ከወሊድ በሁዋላ የሰለጠነ የሰው ኃይልን እና የጤና ተቋማትን እንዲጠቀሙ በማድረግ፤
በየትኛውም አካባቢ እናቶች በምጥ በሚቸገሩበት ቦታ ሁሉ አፋጣኝ የሆነ የማዋለድ አገልግ ሎትን እና የጨቅላ ህጻናትን ጤና መጠበቅን አገልግሎት ባሉበት የሚሰጥ የህክምና ባለሙያ እና አገልግሎቱን እንዲያገኙ በመደረጉ…ወዘተ
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከወሊድ በፊትም ይሁን ከወሊድ በሁዋላ አስፈላጊ የሆኑት የክትትልና የማዋለድ አገልግሎቶችን በሀገር ደረጃ በአንድ አይነት አሰራር አስፈላጊ የሆነው ሁሉ እንዲሰራ በማድረጉ እና ሌሎችም ከማህጸንና ጽንስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የስራ መመሪያዎችን በመዘርጋቱ ውጤቱ እየተሻሻለ መምጣቱ ግልጽ ነው፡፡ እናቶች ከወለዱ በሁዋላ የሚሰጠው ክትትልና ጽንስን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ ማስወገድ የሚቻልበት አሰራር በመዘርጋቱ የእናቶች ሞት በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አስችሎአል፡፡ በእርግጥ አሁንም የእ ናቶች ሞት ካለበት ቁጥር ዝቅ እንዲል ስለሚያስፈልግ ገና ብዙ መሰራት ያለበት መሆኑንም ሁሉም ይስማማል፡፡
በኢትዮጵያ ጥር ወር በየአመቱ የእናቶች ደህንነት የሚወሳበት፤የተለያዩ መግለጫዎች የሚ ሰጡበት፤የእናቶችን ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የተለያዩ ውይይቶች የሚካሄዱበት እየሆነ ሲውል እነሆ አመታት እየተቆጠሩ ነው፡፡  
የእናቶች ጤንነት ፕሮግራም ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው መረጃ እንደሚከተለው ተዘርዝሮአል፡፡
ጥራት ያለውና በእኩል ደረጃ የእርግዝና ክትትል ከ1ኛ-4ኛ ደረጃ ድረስ አገልግቱን መስጠት፤
በጥራትና መረጃን መሰረት ባደረገ መልኩ የምጥ እና የማዋለድ አገልግሎት መስጠት፤
ከወሊድ በሁዋላ ለሀያ አራት ሰአት በወለዱበት የጤና ተቋም በሰለጠነ የሰው ኃይል ክትትል እየተደረገላቸው እንዲቆዩ ማድረግ፤
በየትኛውም ስፍራ አፋጣኝ የሆነ የማዋለድ አገልግሎትና የጨቅላ ህጻናት ክትትል ማድረግ፤
የእናቶችና የወሊድ ሞት ክትትል ማድረግ እና ምላሽ የመስጠት ስርአት ዘርጋት፤
የማህጸንና ጽንስ ችግሮች ሪፈራል እና የአውታረ መረብ (ኔትወርክ) ስርአት መኖር፤
በፊስቱላ ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ የማህጸንና ጽንስ እንዲሁም የወገብ አካባቢ ጉዳቶች እንዳይደርሱ መከላከልና አስቀድሞውኑ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ፤
በተለይም ከእርቀት ቦታ እየተመላለሱ የእርግዝና ክትትላቸውን ለሚያደርጉ መቆያ የሚሆኑ የእናቶች መቆያን በህብረተሰብ ጤና አገልግሎቶች እንዲዘጋጁ ማድረግ ፤
የሚሉ ነጥቦች ይገኙበታል፡፡
የእናቶችን ጤንት ለመጠበቅ የተደረጉ ተነሳሽነቶች ምንድናቸው በሚልም የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚከተለውን ዝርዝር ባለፈው አመት በ2021/ አውጥቶ ነበር፡፡

የእርግዝና ክትትል ጥራት ባለው ደረጃ በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚፈልጉት ሁሉ ማመቻቸት፤
በጤና ተቋማት የሰለጠነ የወሊድ አገልግሎትን ማጠናከር፤
የተሻሻለ የድህረ ወሊድ እንክብካቤን ማድረግ፤
የተሻሻለ በቀዶ ሕክምና ማዋለድ C/S አገልግሎት ሽፋን መስጠት፤
በተለያዩ ምክንያቶች እየሞቱ የሚወለዱ ህጻናትን ቁጥር መቀነስ፤
ወላዶች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች እየተገኙ ስላሉበት የጤና ሁኔታ ክትትል ማድረግ፤
የእናቶችን ጤንነት ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ግብአቶችን እና የደም መስጠት አገልግሎትን በማጠናከር የእናቶችን ሞት መቀነስ፤
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማስወጣት አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉ፤
ለፊስቱላ እና ለማህጸን መውጣት የሚሰጠው አገልግሎት መጨመር፤
የመሳሰሉት አገልግሎቶች በመተግበር ላይ በመሆናቸው የእናቶች ሞት እንዲቀንስ በምክንያትት ከሚጠቀሱት መካከል ናቸው፡፡

Read 729 times