Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 27 October 2012 11:01

ሉሲዎች በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለምም ለመግነን ያስባሉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድን ኢኳቶሪያል ጊኒ በምታዘጋጀው ስምንተኛው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንሺፕ ለመካፈል በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደ ማላቦ ተጓዘ፡፡ ሼህ መሐመድ አላሙዲ ለሉሲዎች በወኪላቸው በአቶ አብነት ገ/መስቀል በኩል አምስት ሚሊየን ብር እንደሸለሙ ሲታወቅ በሻምፒዮንሺፑ በሚያስመዘግቡት ውጤት ባለ ሁለት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ለእያንዳንዳቸው ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ ወደ ሞላቦ የሚጓዘው ቡድኑ ባለፈው ረቡእ የመጨረሻ ልምምዱን በአዲስ አበባ ስታዲየም አድርጓል፡፡
በእለቱ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት ለጋዜጠኞች በተሰጠው መግለጫ ከኬኒያ ጋር ያደረጉት ያቋም መለኪያ ጨዋታ ያሉባቸውን ክፍተቶች ለማየት እንደረዳቸው በመናገር ተጨዋቾቻቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በመግለፅ የምስራቅ አፍሪካ ጠንካራው ቡድን ሉሲዎች እንደሆኑ እና በሻምፒዮንሺፑ ኳስ ተቆጣጥረን በመጫወት ከተጋጣሚዎቻችን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

ዋና አሰልጣኝ አብርሃም ተክለሃይማኖት እርስ በእርሳቸው እንደቤተሰብ በመቀራረብና ከነበራቸው አቋም በይበልጥ የተዘጋጁት ሉሲዎች ለውጤታማነት የሚጫወቱ ብርቱ ስነልቦና ያላቸው ብለው በልበሙሉነት አድንቀዋቸዋል፡፡ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ስንጓዝ የካናዳን የዓለም ዋንጫን በማሰብ ነው ያለችው ደግሞ የሉሲዎች አምበል ብዙሃን እንዳለ ቡድናችን በሞት ምድብ ውስጥ ገብቷል መባሉ ስጋት እንዳልሆነ ገልፃለች፡፡
የቡድኑ መሪ የሆኑት ወ/ሮ ጥሩወርቅ ብርሃኑ በበኩላቸው የኛ መለያ ፍቅርና ባንዲራ ነው፡፡የሄድንበትን አላማ ለማሳካት እንጫወታለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ወደ ኢኳቶርያል ጊኒ ሲጓዝ 21 ተጨዋቾች አካቷል፡፡ ለቡድኑ ባላቸው ከ8 እስከ 10 ዓመት የሚዘልቅ ልምድ ከፍተኛ ጥቅም ይኖራቸዋል የተባሉ 8 ተጨዋቾች ሲያዙ ፤ አዲስ የተመረጡ 7 ተጨዋቾች እና ከ2 አመት ወዲህ ቡድኑን የተቀላቀሉ 5 ተጨዋቾች ይገኙበታል፡፡ በአጥቂ መስመር ሽታዩ ሲሳይ፤ ረሂማ ዘርጋው፤ ብርቱካን ገ/ክርስቶስ፤ ብዙነሽ ሲሳይና ሄለን ሰይፉ ፤ በአማካይ ስፍራ ኤደን ሽፈራው ፤ዙሊካ ጁሃድ፤ብሩክታዊት ግርማ፤ቱቱ በላይ፤አይናለም ወንድሙ፤ቅድስት ቦጋለ እና አክበረት ገ/ፃዲቅ፤ በተከላካይ መስመር ብዙሃን እንዳለ፤ ወይንሸት ፀጋዩ፤ ህይወት ዳንጊሶ፤ ጥሩአንቺ መንገሻ፤ አዳነች ጌታቸውና ቀለሟ ሙሉጌታ እንዲሁም በረኞች ሊያ ሽብሩ ፤ ዳግማዊት መኮንን፤ እስራኤል ከተማ ናቸው፡፡ የልዑካን ቡድኑ ተጨዋቾቹን በስነልቦና የሚያማክር ባለሙያ በልዑካኑ እንዳካተተም ታውቋል፡፡ ስምንተኛው የአፍሪካ ሴቶች ሻምፒዮንሺፕ ነገ ሲጀመር ማላቦ ላይ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከደቡብ አፍሪካ የመክፈቻውን ጨዋታውን ያደርጋሉ፡፡
ሌሎቹ የምድብ 1 ቡድኖች ሴኔጋልና ዲ.ኮንጎ በሁለተኛው ጨዋታ ይገናኛሉ፡፡ በምድብ 2 የሚደረጉት ፍልሚያዎች ሰኞ ሲቀጥሉ በመጀመሪያው ጨዋታ ናይጄሪያ ከካሜሮን ሲገናኙ ፤ኢትዮጵያ ከአይቮሪኮስት ትፋለማለች፡፡ ሉሲዎች በምድቡ ሁለተኛ ጨዋታዎች ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ፋልኮንስ ከተባሉት የናይጄርያ ሴት ብሄራዊ ቡድን ጋር የፊታችን ሐሙስ የሚፋጠጡ ሲሆን በምድቡ የመጨረሻ ጨዋታቸውን የዛሬ ሳምንት ከካሜሮን ጋር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡

Read 3215 times