Saturday, 27 October 2012 11:03

ኢትዮጵያ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ…

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

በምድብ 3 ከሻምፒዮኗ ዛምቢያ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከናይጄርያ ጋር ተደልድላለች
‹‹23 ተጨዋቾች ወደ ደቡብ አፍሪካ መሄድ አለባቸው፤ ውጤት ካለ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድል አለ››
የቀድሞው የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራ
ደቡብ አፍሪካ በምታስተናግደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በታሪክ ለ10ኛ ግዜ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በምድብ 3 ከሻምፒዮኗ ዛምቢያ፤ ከቡርኪናፋሶ እና ከናይጄርያ ጋር ተደለደለ፡፡ በቀሪዎቹ ድልድሎች በምድብ 1 አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬፕቨርዴ፣ ሞሮኮና አንጎላ፤ በምድብ 2 ጋና፣ ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ኒጀርና ማሊ እንዲሁም በምድብ 4 ኮትዲቯር፣ ቶጎ ፣ አልጄርያና ቱኒዝያ ተገናኝተዋል፡፡ የምድብ ድልድሉ ባለፈው ረቡዕ በደርባን በተደረገ ልዩ ስነስርዓት የወጣ ሲሆን ከ200 በላይ ታዳሚዎች ደርባን ውስጥ በሚገኘው ዓለም አቀፍ ማእከል ነበሩ፡፡

የተሳታፊ አገራት እግር ኳስ ፌደሬሽኖች ሃላፊዎች፤ የካፍ ፕሬዝዳንት ኢሳ ሃያቱ፤ የኮንፌደሬሽኑ ከፍተኛ ባለስልጣናትና እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡
በሌላ በኩል የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራ ለስፖርት አድማስ ባደረሱት መልዕክት ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫው ውጤታማ እንዲሆን በሁሉም አቅጣጫ ትኩረት በማግኘት ሰፊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል፡፡ ለቢቢሲ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጠቃላይ ዝግጅት እና በተጨዋቾቹ ዙርያ በሰፊ ቃለምልልስ የተጋዘ ዘገባ ለመስራት እየተንቀሳቀሱ ያሉት አሰልጣኝ ኢፌም ኦኑራ፤ ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋቸውን ባወቁ ጊዜ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ለስፖርት አድማስ ሲናገሩ ተጨዋቾች እና ህዝቡ በተፈጠረላቸው ደስታ የተሰማቸውን እርካታ ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከመግባቱ በፊት ባለው የዝግጅት ጊዜ በቂ የወዳጅነት ጨዋታዎች ማድረግ እንዳለበት የመከሩት ኦኑራ፤ ብሄራዊ ቡድኑ በደቡብ አፍሪካ በተሟላ የመሰረተ ልማት አቅም የሚሰራበት ማረፊያውን በጥናት መወሰን እንዳለበት አስረድተው በውድደሩ ላይ በሚኖረው ተሳትፎ 23 ተጨዋቾች ያሉበትን ሙሉ ቡድን ይዞ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ በሚያሰለጥኑበት ወቅት ወደ ውጭ አገራት በሚያደርጉት ጉዞ በቡድናቸው ሙሉ የተጨዋች ስብስብ ይዞ ለማቅናት ችግር እንደነበር ያስታወሱት ኢፌም ኦኑራ እንደ አፍሪካ ዋንጫ አይነት ውድድር ብዙ እና ከባባድ ግጥሚያዎች የሚደረጉበት በመሆኑ በጉዳቶች እና በካርድ ቅጣቶች የሚፈጠሩ ክፍተቶችን ለመድፈን ሙሉ ቡድን ይዞ መጓዝ ተገቢ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
ሁልግዜም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጨዋቾች ብቃት እና ተሰጥኦ እምነት እንዳላቸው ለስፖርት አድማስ የገለፁት ኦኑራ፤ በእንግሊዝ እግር ኳስ ያለፉት 25 ዓመታት ልምዳቸው እንዲሁም በአሰልጣኝነት ያካበቱት የ10 አመታት ልምድ የኢትዮጵያ ኳስ ተጨዋቾች ለፕሪሚዬር ሊግ የሚመጡንበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ለመመስከር እንደሚያስደፍራቸው ገልፀዋል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ከአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች እና ከመላው አለም አሰልጣኞች፤ የቴክኒክ ዲያሬክተሮች እና የዝውውር ደላሎች በብዛት እንደሚገኙ የሚገልፁት አሰልጣኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሚኖረው ውጤታማነት ትኩረት አግኝቶ ለተጨዋቾች የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት እድል እንደሚፈጠር እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡
የኢትዮዽያ ብሄራዊ ቡድን ከ3 ሳምንት በፊት ጥቅምት 4 ላይ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከ100 ደቂቃ በላይ በፈጀው አስደናቂ ተጋድሎ የሱዳንን ብሄራዊ ቡድን 2ለ0 በማሸነፍ በደርሶ መልስ ድምር ውጤት 5እኩል ቢለያይም ከሜዳው ውጭ ባስመዘገባቸው 3 ጎሎች ወደ አፍሪካ ዋንጫ ከ31 አመታት ማለፉን አረጋግጦ በአገሪቱ እግር ኳስ አዲስ ምእራፍ ተከፍቷል።
የዚህ ትውልድ ብሄራዊ ቡድን ተጨዋቾች በከፍተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት ወደ አፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያን ከ31 ዓመታት በኋላ መልሰዋታል፡፡ ዋልያዎቹና አሰልጣኞቻቸው፤ ክለቦቻችን፤ ዝናብና ፀሃይ እየተፈራረቀባቸው የኢትዮጵያን እግር ኳስ በፅናት በመደገፍ ለቆዩ ስፖርት አፍቃሪዎች ጥቅምት 4 ምንግዜም የማይረሳ ታሪካዊ ቀን ሆኖ ይዘከራል፡፡ ለ31ዓመታት ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ የራቀችው ኢትዮጵያ ሱዳን ካዘጋጀችው የመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ጀምሮ እስከ ሰባተኛው ዋንጫ ድረስ በማዘጋጀትና በመካፈል በተከታታይ ተሳታፊ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በሶስተኛውና በስድስተኛው እና በ10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ እንደነበረች ሲታወስ ከዛሬ 50 ዓመታት በፊት ሶስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በማስተናገድ ሻምፒዮን ለመሆንም በቅታለች፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አገር ውስጥ በተዘጋጀው 13ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ ለመጨረሻ ግዜ የመሳተፍ እድል የገጠመው ከ30ዓመት በፊት ሊቢያ ላይ ነበር ፡፡
በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫው ከኮትዲቯር እነ ድሮግባ፣ ካሉ፣ ጀርቪንሆ፣ የቱሬ ወንድማማቾች ፤ከናይጄርያ እነ ጆን ኦቢ ሚኬል፣ ኦዲሚውንጌ ፤ ከጋና እነ ሙንታሪ፣ ጂያንና ኤሲዬን፤ ከሞሮኮ ቻማክ፤ ፤ ከማሊ ማሀመዱ ዲያራ፤ ከቶጎ አዳባዬር፤ ከደቡብ አፍሪካ ስቴቨን ፒናርን የመሳሰሉ በአውሮፓ ትልልቅ ሊጎች ከፍተኛ ብቃታቸውን ያሳዩ ምርጥ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ይኖራሉ፡፡ የዘንድሮ አፍሪካ ዋንጫ ካመለጣቸው አገራት 28ኛውን ውድድር በጣምራ ያዘጋጁት ጋቦንና ኢኳቶርያል ጊኒ፤ ለሁለት ተከታታይ ግዜ ተሳትፎው ያመለጣት የሰባት ግዜ ሻምፒዮናዋ ግብፅ፤ አራት ግዜ ሻምፒዮን የሆነችው ካሜሮን፤ ሊቢያ ፤ ሴኔጋል፤ ጊኒ ቦትስዋና እና ሱዳን ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ደቡብ አፍሪካ 29ኛውን የአፍሪካ ዋንጫን ስታዘጋጅ ከ1996 እኤአ በኋላ ለሁለተኛ ግዜዋ ነው፡፡የመስተንግዶውን እድል አስቀድማ እንድታዘጋጅ ተመርጣ የነበረችውን ሊቢያ በመተካት ያገኘችው ነበር፡፡ የውድድሩ አዘጋጆች በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ አገራት በዓለም ዋንጫ ደረጃ መስተንግዶ እንደሚያገኙ አሳውቀዋል፡፡ ጨዋታዎቹን በ5 ከተሞች ጆሃንስበርግ፤ ደርባን፤ፖርት ኤልዛቤት፤ሩስተንበርግና ኔልስፕሪውት የሚገኙት እና ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የሞምቤላ፤የኔልሰን ማንዴላ ቤይ፤ የሮያል ባፎኬግና የሞሰስ ማዲባ ስታድዬሞች ያስተናግዷቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ግዜ በሚሳተፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በርካታ ድጋፍ እንደሚያገኝም ይጠበቃል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች በተለያዩ የንግድ ስራዎች፤በትምህርት እና በስደት የሚኖሩ እስከ 1.5 ሚሊዮን የሚገመቱ ኢትዮጵያውያን አሉ፡፡
ከሁለት ብሄራዊ ቡድን በላይ የሚወጣቸው ኢትዮጵያዊ የቀድሞ እግር ኳስ ተጨዋቾችም በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ከእነሱም መካከል እነ አስፕሪላ፤ አብርሃም እና ሌሎችም የሚታወሱ ናቸው፡፡ እነዚህ የኢትዮጵያ ልጆች ለብሄራዊ ቡድናቸው ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚሰጡት የሚጠበቅ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ 19ኛው ዓለም ዋንጫ በደቡብ አፍሪካ በተሰናዳበት ወቅት የውድድሩ ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድን ማሊያዎችን፤ ቩቩዜላዎችንና የስታድዬም መግቢያ ትኬቶችን በመሸጥ ከፍተኛ ንግድ አድርገው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ለ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድል አድራጊነት ጋና እና ኮትዲቯር ቅድሚያ ግምቱን የወሰዱ ቢሆንም አዘጋጇን ደቡብ አፍሪካ ጨምሮ ናይጄርያ፤ቶጎ፤ ሞሮኮና ሻምፒዮናነቷን ለማስጠበቅ የምትገባው ዛምቢያ ግምት እየተሰጣቸው ነው፡፡ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ 1.5 ሚሊዮን ብር ከመሸለሙም በላይ በ2013 ብራዚል በምታስተናግደው የኮንፌደሬሽን ካፕ ላይ አፍሪካን በመወከል ተሳታፊ ይሆናል፡፡
16ቱ ቡድኖች እና ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት የነበራቸው የውጤት ታሪክ
ምድብ 1- ደቡብ አፍሪካ፤ ኬፕቨርዴ፤ ሞሮኮ፤ አንጎላ
ደቡብ አፍሪካ ለ8ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 2 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 4 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 31 ጨዋታዎች አድርጋ 13 ድል፤ 9 አቻ እና 9 ሽንፈት
ኬፕ ቨርዴ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የምትሳተፍ ናት
ሞሮኮ ለ15ኛ ግዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 1 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 4 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች 54 ጨዋታዎች አድርጋ 19 ድል፤ 19 አቻ እና 16 ሽንፈት
አንጎላ ለ7ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 20 ጨዋታዎች አድርጋ 4 ድል፤ 9 አቻ እና 7 ሽንፈት
ምድብ 2 -ጋና፤ ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ ኒጀር፤ ማሊ
ጋና ለ19ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 4 ጊዜ ዋንጫ ስትወስድ፤ 7 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 12 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 77 ጨዋታዎች አድርጋ 43 ድል፤ 14 አቻ እና 20 ሽንፈት
ዲ. ሪፖብሊክ ኮንጎ ለ16ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡2 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 2 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 4ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 56 ጨዋታዎች አድርጋ 16 ድል፤ 15 አቻ እና 25 ሽንፈት
ኒጀር ለ2ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 3 ጨዋታ አድርጋ በሶስቱም ተሸንፋለች፡፡
ማሊ ለ8ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 5 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 34 ጨዋታዎች አድርጋ 13 ድል፤ 9 አቻ እና 12 ሽንፈት
ምድብ 3- ዛምቢያ፤ ኢትዮጵያ፤ ቡርኪናፋሶ፤ ናይጄርያ
ዛምቢያ ለ16ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 6 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 13 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 61 ጨዋታዎች አድርጋ 26 ድል፤15 አቻ እና 20 ሽንፈት
ኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 2 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 5 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 24 ጨዋታዎች አድርጋ 7 ድል፤ 2 አቻ እና 15 ሽንፈት
ቡርኪናፋሶ ለ9ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 26 ጨዋታዎች አድርጋ 2 ድል፤ 6 አቻ እና 18 ሽንፈት
ናይጄርያ ለ17ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 2 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 6 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 13 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 80 ጨዋታዎች አድርጋ 42 ድል፤ 19 አቻ እና 19 ሽንፈት
ምድብ 4- ኮትዲቯር፤ ቶጎ፤ አልጄርያ፤ ቱኒዚያ
ኮትዲቯር ለ20ኛ ግዜ ትሳተፋለች፡፡ 1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 3 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 6 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 77 ጨዋታዎች አድርጋ 34 ድል፤ 18 አቻ እና 25 ሽንፈት
ቶጎ ለ7ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 18 ጨዋታዎች አድርጋ 2 ድል፤ 6 አቻ እና 10 ሽንፈት
አልጄርያ ለ15ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡ 1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 2 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 6 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች፡፡ 57 ጨዋታ አድርጋ 20 ድል፤ 17 አቻ እና 20 ሽንፈት
ቱኒዝያ ለ16ኛ ጊዜ ትሳተፋለች፡፡1 ጊዜ ዋንጫ ስትወሰድ፤ 3 ጊዜ ሁለተኛ ደረጃን 5 ጊዜ ሶስተኛ ደረጃን አስመዝግባለች 57 ጨዋታዎች አድርጋ 18 ድል፤ 21 አቻ እና 18 ሽንፈት

Read 4674 times