Thursday, 16 February 2023 17:03

ቢጂአይ ኢትዮጵያ፤ ሜታ አቦ ፋብሪካን ለማዘመን ከግማሽ ቢ. ብር በላይ ማውጣቱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ቢጂአይ ኢትዮጵያ የሜታ አቦ ፋብሪካን እንደገና ለማደስና ለማስፋፋት ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን አስታወቀ፡፡
በዛሬው ዕለት የካቲት 9 ቀን 2015 ዓ.ም በሰበታ ከተማ በሜታ አቦ ፋብሪካ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀ ሥነሥርዓት ላይ የቢጂአይ
ኢዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሄርቬ ሚልሃድ፣ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ሥራዎችን በሚመለከት አጭር መግለጫ ለባለድርሻ
አካላት አቅርበዋል፡፡
የቢጂአይ የሥራ እንቅስቃሴዎች በአራት ዘርፎች ላይ ያተኮረ መሆኑን በመግለጫው የጠቆመው ኩባንያው፤ እነሱም የሰው ኃይል፣
የማምረት አቅም ግንባታ፣ ሽያጭና ሥርጭት እንዲሁም ማህበራዊ ሃላፊነት ናቸው ብሏል፡፡
አዲሱ የቢጂአይ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ባደረጉት ንግግር፤ ቢጂአይ የሜታ አቦ ፋብሪካን አቅም ለማሳደግ፣ ስሙን ለማደስና
ኩባንያውን ለመንከባከብ እንዲሁም ከሰበታ ከተማ ህዝብ፣ ከአካባቢው አስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጠበቀ ግንኙነት
ለመፍጠር የገባውን ቃል አስታውሰዋል፡፡
"የገባነውን ቃል በትክክል እንደፈጸምን ለመግለጽ በመቻሌ ደስታ ይሰማኛል" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ይህን አባባላቸውን
ለመደገፍ የንግድና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር፣ ቢጂአይ ያከናወነውን ሥራ በጥልቀት ከገመገመ በኋላ፣ በጥር ወር 2015
ዓ.ም የሰጠውን ውህደትን የመፈጸም ፍቃድ በማስረጃነት ጠቅሰዋል፡፡
ቢጂአይ ኢትዮጵያ ሜታ አቦን በወር 300ሺ ሄክቶ ሊትር ለማምረት የሚችልና ከቢጂአይ ቤተሰብ ድርጅቶች ውስጥ ትልቁ የቢራ
ፋብሪካ ለማድረግ አቅዶ መነሳቱን የጠቆመው መግለጫው፤ ለዚህም ሦስት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም
ያለው ትልቅ ጀኔሬተር ግዢን ጨምሮ በዘመናዊ ማምረቻ መሣሪያዎች ግዢ ላይ መዋዕለ ንዋዩን በማፍሰስ ላይ እንደሚገኝ
አመልክቷል፡፡
ቢጂአይ የምርት ሽያጭና ሥርጭቱን ለማስፋፋት በሚያደርገው ጥረት በተመረጡ ገበያዎች ላይ የሚያተኩረውን ሥልቱን በመከተል
ውጤታም ሥራ ለመሥራት በመቻሉ፣ በአሁኑ ወቅት የሜታ ምርቶች ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ ሆኖ መገኘቱም ተጠቅሷል፡፡

Read 2629 times