Saturday, 18 February 2023 19:24

በትግራይ ይቋቋማል የተባለው ጊዜያዊ መንግስት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞ ገጠመው

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

ከሁለት ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ የዘለቀችው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም እየሰራ መሆኑንና  ጊዜያዊ መንግስቱ የሚመሰረትበት ሰነድም በቀጣይ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ የተሰጠውን መግለጫ ተከትሎ፣ በክልሉ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ፓርቲዎቹም በሰጡት በዚሁ መግለጫም፤ በትግራይ ክልል መሰረታዊ የተባለውን ጊዜያዊውን ክልላዊ መንግስት ከሚያቋቁመው ኮሚቴ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌላቸው በመጥቀስ፤ኮሚቴውን አንቀበልም ብለዋል፡፡
“ኮሚቴው ለህወኃት የሚያደላና ገለልተኛ ያልሆነ ኮሚቴ ነው፤ ህወኃት የክልሉ መንግስት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የሚቀየር ነገር የለም” ብለዋል- ተቃዋሚዎቹ፡፡
 በክልሉ ይመሰረታል የተባለውን ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት ለመመስረት  እንዲያስችል የተቋቋመውና በሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ሊቀመንበርነት የሚመራው ኮሚቴ፣ በክልሉ ጊዜያዊ መንግስት ለማቋቋም የሚያስችል የምስረታ ሰነድ በቀጣዩ ሳምንት ይፋ እንደሚያደርጉና በዚህ ጉዳይ ላይ በክልሉ ውስጥ ከሚገኘው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከነዋሪው ህዝብ ጋር ዛሬና ነገ ሰፊ ውይይት ሊደረግ መታሰቡን ተገልጾ ነበር። ይህንን መግለጫ ተከትሎ በክልል ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኑት ሳልሳይ ወያኔ ትግራይ፣ ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ ባይቶና እና ውደብ ነፃነት ትግራይ የተባሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትላንት በጋራ በሰጡት መግለጫ ጊዜያዊ መንግስት ለመመስረት የተቋቋመውን ኮሚቴ እንደማያውቁና እንደማይቀበሉ ተናግረዋል። ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ በሰጡት በዚሁ መግለጫ፤ የውድብ ነጻነት ትግራይ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ ዶ/ር ደጀን መዝገበ እንደተናገሩት፤ “የጊዜያዊ መንግስት መስራች ኮሚቴውን ህወኃትና ሰራዊቱ አዋቅረውታል ምንም የሚመጣ  ለውጥ የለም፤ ተቃውሞ ግን ይቀጥላል” ብለዋል፡፡
ውጥ በማናመጣበት ጉዳይ ውስጥ መግባት እስፈላጊነቱ አልታየንም ያሉት ዶ/ር ደጀን፤ ኮሚቴው ለህወሃት የሚያደላ ነው የገለጹት። ብለው እንደሚያምኑ የገለፁት ዶ/ር ደጀን መዝገበ በዚህ ኮሚቴ የሚዋቀር ጊዜያዊ ክልላዊ መንግስት ለውጥ ሊያመጣ አይችልም ብለዋል፡፡
የሳልሳይ ወያኔ ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ክንፈ ሀዱሽ በበኩላቸው፤ ኮሚቴው የተደራጀበት መንገድ ግልፅ ያለመሆኑን ጠቁመው፣ “ለአንድ አካል የሚወግን ነው ብለን ስለምናምን ከኮሚቴው ጋራ ምንም ዓይነት ግንኙነት አይኖረንም፡፡ ለራሱ ህልውና የሌለው አካል ጊዜያዊ አስተዳደር ለመመስረት የሚያስችል ኮሚቴ መሆን የለበትም” ሲሉም ተቃውመዋል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በክልሉን የሚቋቋመው ጊዜያዊ መንግስት የክልሊን ህዝብ ፍላጎት መሰረት ያደረገና ሁሉንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በእኩልነት ያካተተ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡


Read 2695 times