Saturday, 18 February 2023 19:46

ESOG0-------31ኛ ዓመታዊ ጉባኤ (2023)

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

የእናቶችንና የቅድመ ወሊድን ሞት ለመቀነስ የጤና አገልግሎቱን እንደገና መፈተሸ ወይንም ማስተካከል የሚል ሀሳብ ባለው መሪ ቃል የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እንደውጭው አቆጣጠር ፌብሩዋሪ 13-14/2023 በኢትዮጵያ አቆጣጠር ደግሞ የካቲት 6-7 በአዲስ አበባ 31ኛውን አመታዊ ጉባኤውን አካሂዶአል፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደው 31ኛው አመታዊ ጉባኤ ከመተግበሩ በፊት ባሉት ሶስት ቀናት የህክ ምና ባለሙያዎች ሙያዊ ማሻሻያ የሚያደርጉበት ስልጠና በተለመደው መልኩ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት በተሳተፉ ባለሙያዎች የተሰጠ ሲሆን ስነስርአቱም የተካሄደው በኢንተርኔት አማካኝነት በሚካሄደው በቨርቹዋል የመገናኛ ዘዴ ነበር፡፡ አሰልጣኞቹም ካሉባቸው የአለም ክፍሎች ሆነው በኢትዮጵያ ስልጠናውን የሚከታተሉትም በየአሉበት የስራ ቦታቸው እንዳሉ የተለያዩ ሳይንሳዊ እና ሙያዊ እንዲሁም አዳዲስ አሰራሮችን ከቴክኖሎጂ ጋር በተ ዛመደ መንገድ ቀስመዋል፡፡
31ኛው አመታዊ በተካሄደበት ወቅት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር አባላት የሆኑ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች እና ተባባሪ አካላት ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በመምጣት ጉባኤውን የተሳተፉ ሲሆን በጉባኤው ላይ በተለይም በሁለተኛው ቀን የተለያዩ ጥናታዊ ስራዎች ቀርበዋል፡፡
የወሊድ አገልግሎትን አሰራር እንደገና መፈተሸና የእናቶችንና የቅድመ ወሊድን ሞት ለመቀነስ የህክምና አገልግሎቱን ፕላን ወይም እቅድ …አሰራር ማሻሻል ያስፈልጋል የሚለው አመታዊ የጉባኤው መሪ ቃል ጥናታዊ ስራ በጉባኤው ላይ በቅድሚያ የቀረበ ሲሆን ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ቁምነገሮችም ለውይይት ቀርበዋል።
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ባካሄደው 31ኛ አመታዊ ጉባኤ በተካሄደበት ወቅት በጽንስና ማህጸን ሕክምና ዙሪያ የጎላ አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለሙያዎች በአለምአቀፋዊና ብሔራዊ ደረጃ ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቶአቸዋል፡፡
የመጀመሪያዋ ተሸላሚ ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሓ ይባላሉ፡፡ እሳቸውም ለዚህ እውቅናና የክብር ሽልማት የበቁት በአለም አቀፍ ደረጃ የህዝብ ጤና አገልግሎትን በሚመለከት ከፍተኛ እውቅና ያላቸው ባለሙያ በመሆናቸው እና በስርአተ ጾታ (Gendere) ላይ ያለውን የእኩልነት መብት በማስከበር ረገድ እና በስነተዋልዶ ጤና አጠባበቅ የህይወት ዘመን ክብር የተቀዳጁ በመሆናቸው የኢሶግ 31ኛ አመታዊ ጉባኤ የክብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡   
ፕሮፌሰር ሰናይት ፍሰሀ በአሁኑ ወቅት በቡፌት ፋውንዴሽን የዓለም አቀፍ ፕሮግራሞች ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሁም በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ (የህክምና ትምህርት ቤት) የአለም ጤና ድርጅት እና ረዳት ፋኩልቲ ዋና ዳይሬክተር እና አማካሪ በመሆን በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ሰናይት በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ  በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ የተሻሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል ቀደም ሲልም ሆነ አሁን ከሰሩባቸውና ከሚሰሩባቸው አካባቢዎች ሁኔታ ዎችን በማስተካከል በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃውን የጠበቀ፤ በእኩልነት ለሁሉም በተመሳሳይ አገልግሎት እንዲደርስ ለማስቻል ብዙ ስራዎችን የሰሩ የተከበሩ ባለሙያ በመሆናቸው ይህ ሽልማት ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ተበርክቶላቸዋል፡፡ የፕሮፌሰር ሰናይት አስተዋጽኦ በጥቂቱ እንጂ ይህ ብቻም እንዳልሆነ በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
ቀጣዮቹ ተሸላሚዎች ዶ/ር እንድርያስ ሌንቻሞ እና ዶ/ር አምባዬ ኃ/ሚካኤል ናቸው፡፡
ዶ/ር እንድርያስ ሌንቻሞ የኢሶግ 31ኛ አመታዊ ጉባኤ ተሸላሚ ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ ዶ/ር እንድርያስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ለአንድ አመት ያህል ካገለገሉ በሁዋላ ወደሻሸመኔ በማቅናት በጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት በኃላፊነት ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም ዶ/ር እንድርያስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ክፍል ሜዲካል ዳይሬክተር በመሆን በሆሳእና መንግስታዊ ሆስፒታል ለሰባት አመት ያህል አገልግለዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ አካላት አገልግሎት ያበረከቱ ሲሆን በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅም በተመሳሳይ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አሲስታንት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር እንድርያስ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ሆስፒታል በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
በመቀጠል በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር 31ኛ አመታዊ ጉባኤ የቀረቡት ተሸላሚ ዶ/ር አምባዬ ኃ/ሚካኤል ናቸው፡፡ ዶ/ር አምባዬ በብሔራዊ ደረጃ ሽልማትን የተቀበሉ በተለይም በፊስቱላ ሕክምና ታዋቂ የሆኑ ትጉህና ታታሪ እንዲሁም ብቃት ያላቸው ባለሙያ መሆናቸው የተመሰከረላቸው ናቸው፡፡ ዶ/ር አምባዬ በአዲስ አበባ ፊስቱላ ሆስፒታል ከአስር አመት ላላነሰ ጊዜ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ በመሆን አገልግሎት የሰጡ ሲሆን ሜዲካል ዳይሬክተር በመሆንም ለ6 ዓመታት ያህል ሰርተዋል፡፡ ዶ/ር አምባዬ በተለያዩ መስተዳድሮች  እና የአፍሪካ ሀገራትም በመሄድ ሕመምተኞችን ያክሙ የነበረ ሲሆን ይህንኑ እድላቸውን ተጠቅመው ወደተለያዩ መስተዳድሮች በመሄድም ከሆስፒታሎች ጋር በመነጋገር የታማሚዎችን የጉዞ እንቅስቃሴ ወይንም እንግልት ለመቀነስ እንዲረዳ በየአካባቢው የፊስቱላ መታከሚያ እንዲፈጠር ትልቅ ስራ ሰርተዋል፡፡ ዶ/ር አምባዬ WAHA--Women and Health Alliance በሚባል መንግስታዊ ያልሆነ አለምአቀፍ ድርጅት በመግባት ከፊስቱላ ጋር በተያያዘ የቀዶ ጥገና ሐኪም፤ የሜዲካል አስተባባሪ፤ አማካሪ፤አሰልጣኝ በአጠቃላይም የፌስቱላ ቀዶ ሕክምናን በሚመለከት በሓላፊነት ደረጃ ሰርተዋል፡፡ በአጠቃላይም ዶ/ር አምባዬ ባለፉት ሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ ለብዙ ሴቶች የጽንስና ማህጸን ሕክምናን ጥራትና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲደርስ በተለይም በፊሰቱላ ታካሚ የሆኑትን ከችግራቸው እንዲላቀቁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ናቸው፡፡
ሶ/ር አየለ ደበበ እና ዶ/ር መላኩ አብርሀም በሽልማቱ የተካተቱ ነበሩ፡፡   
ዶ/ር አየለ ደበበ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ሆነው በብቸኝነት ከተመደቡበት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሴቶች በሚኖሩባት አምቦ በምትባል አካባቢ በሚገኘው የአምቦ ሆስፒታል በብቃት አገልግለዋል፡፡ ዶ/ር አየለ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ላለፉት 22 አመታት አባል ሲሆኑ የቦርድ አባል በመሆንም የሰሩ ሲሆን ለሶስት አመት ያህልም የእናቶችን ደህንነት የሚመለከተውን የኢሶግና ፊጎ የትብብር ፕሮጀክት መርተዋል፡፡ ከዚያም በኢትዮጵያ የእናቶችን ደህንነት በሚመለከት የሚዘረጉ ፕሮጀክቶች ውጤት እና የጽንስና ማህጸን ህክምናን በሚመለከት አፋጣኝ ሕክምናን መስጠት አለመቻል ከምን ጋር የሚያያዝ ችግር መሆኑን የሚያሳዩ ጽሁፎችን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር አየለ በተለያዩ ማህበራት ማለትም በኢትዮጵያ ሜዲካል ማህበር፤ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ኼልዝ ማህበር፤በኢትዮጵያ የቀይ መስቀል ማህበር እና ብሪትሽ የቀይ መስቀል ማህበር በመሳተፍ የእናቶችና ጨቅላዎቻቸው አገልግሎት የተሟላ እና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡
ሌላው ተሸላሚ ዶ/ር መላኩ አብርሀ ናቸው፡፡ ዶ/ር መላኩ በአዲግራት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የነበሩ ሲሆን ዶ/ር መላኩ ከጽንስና ማህጸን ሕክምና በተጨማሪም የፌስቱላ ቀዶ ሐኪም በመሆን የብዙ የፊስቱላ ታማሚ ሴቶችን ህይወት ወደነበረበት ለመመለስ ጥረት አድ ርገዋል፡፡ ዶ/ር መላኩ ለዚህ ለተከበረ ስራቸው በFIGO እና British Royal College እውቅና ተሰጥቶአቸዋል፡፡ ዶ/ር መላኩ እና የስራ ጉዋደኞቻቸው ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን እስከ 2020 ከፊስቱላ የጸዳች ሀገርን ለመመልከት በመቀሌ ፊስቱላ ማእከል የሚቻለውን ሁሉ በማድረግ ከህክምናው ባሻገርም ህብረተሰቡ እንዲያውቅ የሚያደርጉበት አሰራርም አላቸው፡፡ ዶ/ር መላኩ ምንም እንኩዋን በስራ አጋጣሚያቸው የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቢገጥሙ ዋቸውም የህብረተሰቡን ጤና በተለይም የፊስቱላ ታካሚዎችን አገልግሎት በተቻለ መጠን እንዳይቋረጥ እና ጥራቱን በጠበቀ መንገድ እንዲሆን የበኩላቸውን ጥረዋል፡፡



Read 575 times