Saturday, 27 October 2012 14:11

የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ቴምብር ያሳተመው ለባንዳ ሳይሆን ለአርበኛ ነው

Written by  -ኦርዮን ወ/ዳዊት-
Rate this item
(1 Vote)

“የደራሲያን ማህበር ቴምብር ለባንዳ?” በሚል ርዕስ “በምግባሩ አፈወርቅ (ከ6 ኪሎ)” በተባሉ ግለሰብ ጥቅምት 2005 ዓ.ም “ቁም ነገር” መጽሔት ላይ የወጣውን ጽሑፍ ካነበብኩ በኋላ ራሴን እንዲህ ስል ጠየቅሁት፡፡
ለመሆኑ ጸሐፊው ስለ ድርሰትና ደራሲ፣ ስለ ወንጀልና ቅጣት፣ ስለ ጥፋተኝነትና ከቅጣት በኋላ ስለሚኖር ስም፣ ስለማይጨው ጦርነትና የሽንፈቱ እውነተኛ ምክንያት፣ ወዘተ ምን ያህል ያውቃሉ?
ጸሐፊው እንዳሉት እኔም የታላቁ ማህበር አባል በመሆኔ ጳጉሜ2 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ ቴምብሩ ሲመረቅ የዝግጅቱ ታዳሚ ነበርኩ፡፡ ሆኖም በማህበሬ አርቆ አስተዋይነትና ሚዛናዊነት ኮራሁ እንጂ እንደ ፀሐፊው አልተበሳጨሁም፡፡ ለደራስያን ተገቢውን ክብር እየሰጠ ላለው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም የላቀ አክብሮት እና ከልብ የመነጨ ውዳሴ እንጂ እንደ “በምግባሩ አፈወርቅ” ወቀሳም ሆነ ክስ የለኝም፡፡


የጽሑፌ ዓላማ ለአንባቢያን ግልጽ ይሆን ዘንድ የጸሐፊውን ትችት በአጭሩ እያቀረብሁ ተገቢ ነው የምለውን መልስ በጭር በአጭሩ ላቅርብ፡፡
“ደራሲያን ማህበር አዘጋጅቶት በአዳራሽ ለምንገኘው ሰዎች የተበተነው የነጋድራስ አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ ታሪክ እኔ ከማውቀው ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የሥነጽሑፍ ሰዎች ከሚያውቁት የተለየ ታሪክ ነው” ይሉናል አቶ በምግባሩ፡፡ አያይዘውም፤
“ደራሲ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ኢትዮጵያን የወጉና በባንዳነታቸው ሀገር ያወቃቸው ፀሐይ የሞቃቸው ሰው ናቸው” ሲሉ ጉዳዩን በእሳቸው ምርምርና ጥናት ያገኙት ብርቅና ድንቅ ውጤት አስመስለው አቅረበውታል፡፡
የፕሮፌሰር አፈወርቅን ባንዳነት “አገር ያወቀው” ከሆነ ጸሐፊው ለምን ደከሙ? እንደ እርስዎ ያለ ተመራማሪ በህዝቡ ዘንድ እምብዛም ያልታወቁ ጉዳዮችን እንጂ እንዴት “አገር ላወቀው ፀሐይ ለሞቀው” ጉዳይ በከንቱ ይደክማል?
የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር የመታሰቢያ ቴምብር ያዘጋጀው በቀዳሚ ደራሲነታቸው እንጂ በፖለቲካ ተሳትፎአቸው አይደለም፡፡ ይኸው ማህበር በ2002 ዓ.ም የመታሰቢያ ቴምብር ካሳተመላቸው አራት ደራስያን መካከል አቶ ከበደ ሚካኤል ልክ እንደ ፕሮፌሰር አፈወርቅ የጣሊያንን ጋዜጣ ያዘጋጁ ነበር፡፡ ማህበሩ አቶ ከበደን ሲዘክር ለምን እንደ አሁኑ በ”አርበኝነት” “አካኪ ዘራፍ” አላሉም? ስለዚህም ሰዎችን የሚመዝኑበት የህሊና ሚዛንዎ የተዛባ አስመስሎዎታል፡፡ ከፕሮፌሰሩ ጋር የተለየ ጠላትነት ካለዎት ያ የግልዎ ጉዳይ ነው፡፡
“በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ልቦለድ መጽሐፍ “ጦቢያ” ደራሲ ተብለው የሚሞካሹት እኝህ ሰው፤ ክብሩን ያገኙት በድርሰታቸው ብቃት ወይስ ከማንም ቀድመው መጽሐፍ ማሳተም በመቻላቸው ነው?” ሲሉም አቶ በምግባሩ ጠይቀዋል፤ መጠየቅ ብቻም ሳይሆን በድርሰት ችሎታቸው ላይ ሊሳለቁ ሞክረዋል፡፡
አቶ በምግባሩ እርስዎ ወደዱትም ጠሉትም ፕሮፌሰር አፈወርቅ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ባለው መረጃ በአፍሪካዊ ቋንቋ የጻፉ ቀዳሚ ምሑር ናቸው፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፤ ፕሮፌሰሩ ከአገራቸው አልፈው በአውሮፓ ዩኒቨርስቲዎች ነጮችን ያስተማሩ፣ የሀገራቸውን ቋንቋ ለአውሮፓውያን ለማስተማር ካላቸው ጽኑ ፍላጐት የተነሳም በጣሊያንኛ - አማርኛ እንዲሁም በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች መዛግብተ ቃላትን ያዘጋጁ ሊቅ ናቸው፡፡
“አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ ለትውልድ ቦታቸው ቅድሚያ የሚሰጡ ጠባብ አመለካከት የነበራቸው ሰው ናቸው፤ ለዚህም ነው አንድ ጽሑፍ ጽፈው ሲጨርሱ ከስማቸው ቀጥለው “ዘብሔረ ዘጌ” ይሉ የነበረው” ሲሉም ጸሐፊው አስቂኝ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
የዚህ ዓይነቱ አጻጻፍ በመሠረቱ ስመ ሞክሼዎችን ለመለየት፤ አፈወርቅ የትኛው እንደሆነ እርግጠኛ ማንነትን ለመግለጽ አሁንም ድረስ የአገራችን ጸሐፍት የሚጠቀሙበት መንገድ እንጂ የፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ጠባብ ባሕርይ ያፈለቀው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡
ይህ አይነቱ የስም አገላለጽ’ኮ ከገድላትና ከስንክሳር በአጠቃላይም ከሃይማኖታዊ መጻሕፍት የሚነሳ ነው፡፡ ለዚህም ሣሙኤል ዘዋልድባ፣ ሣሙኤል ዘ ደብረ ወገግ፣ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስሜ፣ ወዘተ ብለን የምናውቃቸው ቅዱሳን በርካታ ናቸው፡፡ በጊዜያችንም አሸናፊ ዘደቡብ፣ ዘለሌ ዘግንፍሌ፣ ተዋነይ ዘጐንጅ፣ ተስፋ ገብረስላሴ ዘብሔረ ቡልጋ… ወዘተ የተለመደ የማንነት መግለጫ እንጂ የጠባብነት ማሳያ በፍጹም ሊሆን አይችልም፡፡ ቀድሞ ነገር ፕሮፌሰር አፈወርቅ በጠባብነት ታምተው አያውቁም፡፡ ለነገሩማ የፕሮፌሰሩን ጉድፍ ሲፈልጉ የራስዎ አልታየዎትም እንጂ እርስዎምኮ እንዳቅምዎ “በምግባሩ አፈወርቅ (ከ6 ኪሎ)” ብለው ነው የዘለፋ ጽሑፍዎን የጻፉት፡፡ እናም ቅዱሱ መጽሐፍ “ቅድሚያ የአይንህን ጉድፍ አውጣ” እንዳለው ወዳጄ አቶ በምግባሩ ቅድሚያ የዓይንዎን…!
“አፈወርቅ ዝንባሌያቸው ስዕል መሳል እንጂ ጽሑፍ መፃፍ አልነበረም” ሲሉም የፕሮፌሰሩን ችሎታ ያጠኑበትን “የጥናት ውጤት” አቅርበውልናል፡፡ ደራሲ ለመሆን ከውቧ ተፈጥሮ መታደል ይገባል እንጂ በትምህርት ብቻ እንደማይመጣ እርስዎን ያህል ተመራማሪ እንዴት ያጣዋል?
“ጣሊያን ተምረው ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የሥዕል እንጂ የድርሰት ሙያ ይዘው ባለመምጣታቸው እቴጌ ጣይቱ አዲስ ያሠሩትን እንጦጦ የሚገኘውን የራጉኤል ቤተክርስቲያን በስዕል እንዲያስጌጡላቸው ነበር ያዘዟቸው፡፡” ያሉት ሃሳብም አራምባና ቆቦ የሚረግጥ ነው፡፡
እንግባባ እንጂ አቶ በምግባሩ! እንዴት ያለ ጽሑፍ ነው ሊያስነብቡን የደፈሩት? እቴጌ በድርሰት ፈትነዋቸው አልሳካ ብሎአቸው ወደ ሥዕል መድበዋቸው ቢሆን ኖሮ ምን አልባት እንግባባ ነበር፡፡ ግን “ድርሰት ስላላወቁ ስዕል መደቧቸው” የሚለው ግራ ገብቶት ግራ የሚያጋባ ሃሳብ ነው፡፡
“አፈወርቅ ስዕል ሊስሉ ቤተክርስቲያን ሲገቡ ከእነጫማቸው ነበር፤ በዚህም ሃይማኖታዊ ሥርዓትን የሚያፈርሱ፣ ለመጭው ትውልድም መጥፎ አርአያ የሚያወርሱትን ሰው ነው በቴምብር ለማስታወስ እየተሞከረ ያለው?” ብለውም የፕሮፌሰሩን ሃጢያት ለማብዛት ሞክረዋል፡፡
ቤተክርስቲያን በሚታደስበት ጊዜ ጽላቱ ከመንበሩ ወጥቶ መቃረቢያ ቤት ውስጥ ይቆያል፡፡ ያን ጊዜ ግንበኞቹም ሆኑ አናጢዎቹ ከእነጫማቸው እንደሚገቡና እንደሚወጡ ይታወቃል፡፡ ምክንያቱም ቤተክርስቲያኑ ክብርና ቅድስና የሚያገኘው ጽላቱ ሲኖር ነው፡፡ ስለሆነም ፕሮፌሰር አፈወርቅ ስዕል በሚስሉበት ወቅት ቤተክርስቲያኑ በዕድሳት ላይ ነበር ማለት ነው፡፡
ነገር ግን በማሳበቅ የተካኑ ደባትር ከእቴጌዋ ጋር ሊያጣሏቸው ሲሞክሩ የፈጠሩት ሰበብ ምንም አይነት መሠረት አልነበረውም፡፡ ለነገሩማ በቤተክርስቲያኗ ገቢ የተቀማጠለ ኑሮ የሚኖሩና የቤተክርስቲያኗን ዶግማ ማክበርና ማስከበር የሚገባቸው “የሃይማኖቱ ቁንጮዎች ነን” ባዮችስ አሁን ድረስ ቤተመቅደስ ውስጥ በጫማ ሲገቡ የምናስተውለው ጉዳይ አይደል! ምነው ታዲያ አቶ በምግባሩ “ከጳጳሱ ቄሱ…ሆኑሳ?”
ጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ ሲያስተምሩ ቆይተው ወደ አገራቸው ሲመለሱ ቅድሚያ ወደ ኤርትራ መሄዳቸውንም እንደ ክህደትና ለጣሊያን ያላቸውን ፍቅር ለማሳየት መሆኑን ቁጭት እያንገበገበዎት ገልፀውልናል፡፡
ለመሆኑ ከጣሊያን አገር መጥተው በወቅቱ የጣሊያን ግዛት በነበረችው ኤርትራ በኩል ወደ አገራቸው መግባት ምኑ ነው የሚያስነውራቸው? ጸሐፊው አያውቁት እንደሆነ እንጂ ኤርትራውያን’ኮ ትላንት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ወገኖቻችን የሆኑና የፖለቲካ ማዕበል ወገንነታቸውን የማያናውጠው ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው፡፡ ታዲያ ከብዙው የኤርትራ ህዝብ ምነው ጥቂት ነጭ ገዥዎች ብቻ ታዩዎት? ፕሮፌሰሩ ለጣሊያን ይህን ያህል ጥብቅ ፍቅር ካላቸው በዘመናዊቷ ሮማ ተንፈላስሶ መኖር ማን ከለከላቸው?
እና ወዳጄ! በጣሊያን ስር ወደ ነበረችው አስመራ ብቻ ሳይሆን በእንግሊዝ እና በሻዕቢያ ስር ወደነበረችው (ወዳለቸውም) አስመራም ብዙ ሰዎች ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል፡፡ የሚመላለሱበት ምክንያት አንድም ለዲፕሎማሲ፣ አለዚያም ለማህበራዊ ጉዳዮች ሊሆን ይችላል፡፡ ለግል ጉዳይ የሚሄዱትን (ለጉብኝት ሊሆን ይችላል) ግለሰቦች ዓላማ ግን የሚያውቁት ራሳቸው ተጓዦች እንጂ እኔ ወይም እርስዎ ልንሆን አንችልም፡፡
የፕሮፌሰሩ ድሬዳዋ ውስጥ የጉምሩክ ዳይሬክተር ሆነው መሾምም ከልብ አስቆጭቶዎታል፤ እንዲያውም “የስልጣን ጥም ነበረባቸው” ብለዋል፡፡
የምሁራን እጥረት በእጅጉ ያሰቃያት ለነበረችው የያኔዋ ኢትዮጵያ፣ ፕሮፌሰር አፈወርቅን የመሰለ ምሑር ማግኘት መታደል እንጂ መበደል አልነበረም፡፡ በወቅቱ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የደም ጥራታቸው እንጂ ዕውቀታቸው ዋጋ የሚሰጠው ባለመሆኑ ጥቂት “ጠብደል መሃይሞች” የአገሪቱን ህዝብ እንደፈለጉ ይነዱና ይገዙት እንደነበር አቶ በምግባሩ ይዘነጉታል ብዬ አላምንም፡፡
“የነጋድራስ አፈወርቅ ኢትዮጵያን መጥላትና የማፈራረስ ስትራቴጂ እቅዳቸው ጐልቶ የወጣው በ1928ቱ የጣሊያን ዳግም ወረራ ወቅት ነበር፡፡ አፈወርቅ በወቅቱ ባላቸው የሥነጽሑፍ ችሎታ ተመርጠው ለኢጣሊያን መንግሥት የፕሮፖጋንዳ አገልግሎት የሚሰጥ ጋዜጣ ያዘጋጁ ነበር” ሲሉም ግራ የተጋባ ሃሳብዎን ሊጭኑብን ሞክረዋል፡፡
ቀደም ሲል “የስዕል እንጂ የድርሰት ሙያ የላቸውም” እንዳላሉ ሁሉ ለውንጀላ ሲሆን ግን የ”ሥነ ጽሑፍ ችሎታቸውን” እያንገሸገሸዎትም ቢሆን ተቀብለውታል፡፡
ሌላውና ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ የፕሮፌሰር ባንዳነት ጉዳይ ነው፡፡ ለዚሁ ማጣፈጫም የዝነኛውን ገጣሚ ዮፍታሔ ንጉሤን (ስማቸውን መጥቀስ ባይፈልጉም፤ ወይም ገጣሚውን ባያውቁም)
“አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ን ጠቅሰዋል፡፡ በደንብ ካስተዋሉ’ኮ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ባንዳነታቸው ጥፋት ሆኖ ስለተገኘ የዕድሜ ልክ እስራት በንጉሡ ተወስኖባቸው፣ በጨለማ (ምድር ቤት) ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ታስረው፣ በረሃብና በስቃዩ እንዲሞቱ ተደረገ እንጂ ከንጉሡ ሹመት ወይም ሽልማት አላገኙም፡፡ ታዲያ ግጥሙን የጠቀሱት ለማን ነው? የፕሮፌሰሩን ስቃይና እንግልት እንደ ሽልማት ቆጥረውት ከሆነ ምንም ማለት አይቻልም፡፡
ፕሮፌሰር አፈወርቅ እርግጥ ነው የጣሊያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርተዋል፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ አቶ ከበደ ሚካኤልና ሌሎች በርካታ ጸሐፍትም ለጋዜጣው ጽሑፍ ያበረክቱ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ንጉሡ ከሄዱበት ሲመለሱ በፕሮፌሰሩ ላይ የዕድሜ ይፍታህ እስራት ፈርደውባቸው ጅማ ውስጥ በሚገኝ ጨለማ ክፍል ለብቻቸው ታስረው ነበር፡፡ በጨለማው ምክንያት ዓይናቸው ጠፍቶ ሞቱ ተብሎ ተነገረ፤ በቃ ይህንን ነው የምናውቀው፡፡
ስለዚህ አንድ ሰው ወንጀል ፈጽሞ ሲገኝና ድርጊቱ በማስረጃ ሲረጋገጥ መብቱ በሚፈቅድለት ፍርድ ቤት ህጉ የሚያዝዘው ቅጣት ሊጣልበት ይችላል፡፡ ቅጣቱን ከፈጸመ በኋላ ግን በምንም ተዓምር ቢሆን በተቀጣበት ጉዳይ ዳግም ሊወቀስበትም ሆነ ሊከሰስበት አይችልም፡፡ ከሞት ፍርድ በላይስ ምን ቅጣት አለ? ወዳጄ አቶ በምግባሩ ይህንን የህግ ድንጋጌስ ያውቁ ይሆን? በስም አጥፊነት ሊጠየቁ እንደሚችሉስ?
ከአፄ ምኒሊክ ጋር ውጫሌ ላይ የተዋዋሉትን ውል በተመለከተ በተለይ አንቀጽ አስራ ሰባትን አስመልክቶ ጣሊያኖች ደባ እየሰሩ መሆናቸውን ያጋለጡና ለሃገራቸው ቀናኢ ምሁር የነበሩ መሆናቸውንስ እንዴት ሳያውቁት ቀሩ? ወይስ ለምን መካድ ፈለጉ?
በመሠረቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የጐዳው ፕሮፌሰር አፈወርቅ ያዘጋጁት የነበረው ጋዜጣ ሳይሆን ወገኑን ከጀርባ ሆኖ የወጋው የራሱ ዜጋ ድርጊት ነው፡፡ ማይጨው ላይ የተፈጸመውን አሳዛኝ ድርጊት መቸም ጸሐፊው ይዘነጉታል ብዬ አልጠረጥራቸውም፡፡
ለመሆኑ ማንበብና መጻፍ የማይችለውን የዚያኔውን ምስኪን ህዝብ የፕሮፌሰር አፈወርቅ ጋዜጣ ነው የጐዳው? ወይስ አይኑን ያወጣ የወገን ሴራና ጭካኔ? ለአስረጅ ያህል ቼኮዝሎቫኪያዊው አዶልፍ ፓርለስክና ኩባዊው ኮሎኔል ዴል ባዬ የጻፏቸውን “የሐበሻ ጀብዱ” እና “ቀይ አንበሳ” የተባሉትን መጻሕፍት ያንብቧቸውና የራስዎን የህሊና ፍርድ ይስጡ፡፡
“ለመሆኑ የኢትዮጵያን አርበኞች ማህበር የዚህ ዓይነት ሸፍጥ በቴምብር መታሰቢያ ሰበብ ሲፈፀም ምነው ዝም አለ?” ሲሉም ፀሐፊው ጥግ ፍለጋ ደክመዋል፡፡ አርበኞች ከጐናቸው ተሰልፈው “አካኪ ዘራፍ!” እንዲሉም ወትውተዋል፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማህበር አባላት የሚሰሩትን በአግባቡ የሚያውቁ፣ ላመኑበት ዓላማም በጽኑዕ የታገሉና የሚታገሉ እንጂ በመናኛ ፕሮፖጋንዳ ተነድተው ከሚያከብሩት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ጋር የሚላተሙ አይደሉም፡፡ እንዲህ ያለ ደካማ ባህርይም የላቸውም፡፡ “እነ በላይ ዘለቀን የመሳሰሉ ኢትዮጵያዊ አርበኞች ለውለታቸው መሰቀላቸው ሲገርመን ዓመታት ተቆጥሮ ባንዳ የሚሞገስበት ዘመን ላይ ደረስን?” ሲሉ የሰጡን መረጃ ይልቅ “ለካ በላይ ዘለቀ በንጉሡ የተሰቀለው ለሃገሩ ለከፈለው ውለታ ንጉሱ ያበረከቱለት ድንቅ ስጦታ ነው?” ብለን “የተደበቀውን ምስጢር” እንድናውቅ ረድተውናል፡፡ “የንጉሡ ፍርድ የተዛባ ነው” ተብሎ በፕሮፌሰሩ መደፈሩም ፀሐፊውን አበሳጭቶዎታዋል፡፡ ግዴለዎትም አቶ በምግባሩ! እነሱው ይተዋወቁ ነበር፤ አንደኛው ለጣሊያን ያደረ፤ ሌላው ደግሞ በፍርሃት ምጥ አገሩንና ህዝቡን ለአውሬ ጥሎ የፈረጠጠ ነው፡፡ እርስዎ የተቆጩለትን በላይ ዘለቀን የሰቀለስ ማነው? ታዲያ የማንኛቸው ይብሳል ወዳጄ? አቶ በምግባሩ ብዙ ደከሙ እንጂ የጽሑፋቸው ዐቢይ ነጥብ አንድ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ለምን ፕሮፌሰር አፈወርቅን ሸለመ? አፈወርቅኮ ባንዳ ነበሩ” የሚል!
የማህበሩ መሪዎችም ሆኑ መላ ኢትዮጵያውያን እንደሚያውቁት ፕሮፌሰር አፈወርቅ የጣሊያን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ጣሊያንን ማገልገላቸው እውነት ነው፡፡ ረጅም የፈጠራ ጽሑፍን (Novel) “ልብ ወለድ ታሪክ” ብለው የተረጐሙና ጽፈውም ያሳዩ ቀዳሚ ደራሲ መሆናቸውንም ማንኛውም የሥነ ጽሑፍ ቤተሰብ የሚረዳው ቁም ነገር ይመስለኛል፡፡
ማህበሩ የሙያ ማህበር እንደ መሆኑ መጠን የሙያ አባቶቹንና እናቶቹን ያከብራል፡፡ ለአስረጅ ያህል ከአርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት፣ ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤትና ከብራና ማተሚያ ቤት ጋር በመተባበር ያለፉና በህይወት ያሉ ደራስያን አጫጭር ታሪክና ስራቸውን የያዘ አጀንዳ ሶስት ጊዜ አሳትሟል፡፡
መንገዶች፣ አደባባዮች፣ አዳራሾችና የትምህርት ተቋማት በደራስያን ስም እንዲሰየሙም መንግስትን ከመወትወት ቦዝኖ አያውቅም፡፡ የሙያ አባቶቹንና እናቶቹን ከሚዘክርባቸው መንገዶች አንዱም ቴምብር በስማቸውና በምስላቸው ማሳተም ነው፡፡
በ2002 ዓ.ም ለሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ለአቶ ሀዲስ አለማየሁ፣ ለወ/ሮ ስንዱ ገብሩና ለአቶ ከበደ ሚካኤል መታሰቢያ ቴምብር አዘጋጅቶ፣ በማህበሩ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ተግባር አከናውኗል፡፡
በ2004 ዓ.ም ቴምብር የታተመላቸው አራት ደራስያንም በስነጽሑፍ ሙያቸው ላበረከቱት ድንቅ ተግባር እንጂ ለፖለቲካ ተሳትፎአቸው አይደለም፡፡ የፖለቲካ አቋም ሌላ የሥነ ጽሑፍ አርበኝነት ሌላ፡፡ አቶ በምግባሩ! እርስዎ “አርበኛ ነው” ብለው የሚያምኑት የሚገድል ወይም የሚሞትን ብቻ ከሆነ ተሳስተዋል፡፡ በየሙያ መስኩ ጀግኖች፣ ፈሪዎችና አሳባቂዎች አሉ፡፡
ማህበራችን መታሰቢያ ቴምብር ያሳተመላቸው ግን ለሀገሪቱ ሥነ ጽሑፍ “አንቱ” የሚያሰኝ ተግባር ላከናወኑ ጀግኖቹ ነው፡፡ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስም በአገራችንና በአህጉራችን ፋና ወጊ ተግባር ስላከናወኑ መታሰቢያውን በላቀ አክብሮት አሳትሞላቸዋል፡፡ ይህን የሙያ አባቶቹንና እናቶቹን የማክበርና የመዘከር ተግባሩን በተጠናከረ መልኩ ይቀጥልበታል የሚል የጸና እምነትም አለኝ፡፡
“አፈወርቅ ከፍርድ በኋላም ወደ ጅማ ተወስደው ለረጅም ጊዜ ታስረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥም በህመም አይናቸው ጠፍቶ የእግዚአብሔር ፍርድ የተቀበሉ ሰው ናቸው” ሲሉ የቀላቀሉት ሃሳብም የጸሐፊውን “አላዋቂ ሳሚ”ነት የሚያመላክት ነው፡፡
ፕሮፌሰር አፈወርቅ የታሰሩትና ለሞት የበቁት በንጉሡና አሽቃባጭ ባለሥልጣኖቻቸው የተጣመመ “ፍርድ” እንጂ በእግዚአብሔር ፍርድ አይደለም፡፡ እግዚአብሔርን እንዲህ ዓይነቱ ርካሽ ወንጀል ውስጥ አይቀላቅሉት ወዳጄ!
ቀድሞ ነገር “ፍርድ” የተባለውን ማደናገሪያ ተግባር ያከናወኑት አገር ጥለው የፈረጠጡ ወኔቢሶችና ለጣሊያን ፋሽስቶች ዕንቁላል ሲያቀብሉ ኖረው አገር ሰላም ሲሆን ቆዳቸውን ገልብጠው የለበሱ ነውረኞች አይደሉም እንዴ! እና ትችትም ቢሆን እየተስተዋለ ቢሆን ይሻላል፡፡
ሌላውና በጣም ያሳቀኝ ጉዳይ “ደራሲያን ማህበርስ እሺ ምርቱን ከግርዱ ሳይለይ አባል ማድረግና መሸለም ልማዱ ነው፡፡ በህዝብ ግብር የሚተዳደረው ፖስታ ቤት ግን የህዝቡን ሃብት ለህዝብ ጥቅም ላዋሉ ሰዎች ማዋል ሲገባው ለባንዳ መጠቀሚያ ማድረጉ ምን ይባላል” ያሉት መናኛ ሃሳብ ነው፡፡
የማህበሩን ምርትና ግርድ ለይተው ቢነግሩን ኖሮ “እውነታቸውንኮ ነው!” ብለን እናደንቅዎ ነበር፡፡ ይህን ደፋር ሃሳብ ሲያቀርቡ አገራችን የምታከብራቸውን፣ አቅምና ችሎታቸው የፈቀደውን ለአገራቸው በማበርከት ላይ ያሉ ብዙኅኑን ደራስያን እየዘለፉ መሆንዎ ይገባዎታል? “መሸለም ልማዱ ነው” ያሉት የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር እንደ እርስዎ የሙያ አባቶቹንና እናቶቹን በድፍረት አይዘረጥጥም እንጂ አቅሙ በፈቀደ መጠን ይሸልማል፤ ያመሰግናል፤ ደራስያንንና ድርሰትን ያበረታታል፡፡ ይህ ወንጀል ከሆነ ለእርስዎ ብቻ ነው፡፡
ማህበራዊ ግዴታውን እየተወጣ ያለው የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትም ለፈፀመው አኩሪ ተግባር ሊወደስ እንጂ በምንም ተዓምር ሊወቀስ አይገባም፡፡ ይልቅ ለሌሎች ተቋማትና ድርጅቶች በአርዓያነቱ ሊጠቀስ ይገባል፡፡ ብራቮ ፖስታ!!

Read 27615 times