Saturday, 18 February 2023 20:36

ጣዖቷ (ጉምን መዝገን)

Written by  መኮንን ደፍሮ
Rate this item
(6 votes)

በሴት የመገፋት መጥፎ ጠባሳ ከአእምሮዬ ስላልተፋቀ እያመነታሁ ነበር ሄራንን የቀረብኳት። ናርዶስ አሰፋ ከሸሸችኝ በኋላ ከሴቶች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመስረት እፈራለሁ፤ በመቀራረብ ሰበብ በፍቅር ብወድቅና እንደ ናርዶስ የፍቅር ጥያቄዬን ቢገፉት በሚል ብርቱ ፍራቻ፡፡ በፍራቻዬ የተነሳም የሴት ወዳጅ ሳልይዝ ነዉ ኮሌጅ ጨርሼ የወጣሁት፡፡
ባፈቀሩት ሰዉ ዘንድ ተቀባይነትን እንደማጣት ያለ ቅስም ሰባሪ ዉድቀት የለም፡፡ በሌሎች አለመመረጥ ስዉር ጉድለትን የሚያሳብቅ ታላቅ ሽንቁር ነዉ፡፡        
ናርዶስ ትልቅ የተስፋ ስንቄን መና ያስቀረች ጣዖቴ ነበረች፡፡ ሁለት ድፍን ዓመታትን  በልቤ አርግዣት በፍቅሯ ተንገብግቢያለሁ፡፡
እኔ እና ናርዶስ የተገናኘነዉ ዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዉስጥ ነዉ፣ አስራ አንደኛ ክፍል እንደገባሁ፡፡ አስተዋዋቂያችን እሷ ሰፈር የምትኖረዉ የክፍል ጓደኛዬ አዜብ ፊሊሞን ነበረች፡፡
ናርዶስ ዝምታ የምታዘወትር ጠይም የፀደይ እሸት ናት፡፡ ከተዋወቅንበት ዕለት ጀምሮ ብዙ ጊዜያትን አብረን ስናሳልፍ፣ ፍቅሯ በልቤ ቤቱን መስራት ጀመረ፡፡ ብዙ ጊዜ ከትምህርት ቤት ስንለቀቅ ናርዶስን እና አዜብን መኖሪያ ሰፈራቸዉ ካዛንቺስ ድረስ ሸኝቼ ፀሐይ ስታቀዘቅዝ ነበር ሰፈሬ ፒያሳ የምገባዉ፡፡
1992 ዓ.ም ሚያዚያ መባቻ፡፡
እንደ ሁልጊዜዉ ናርዶስን የቀጠርኩበትን ሰዓት በቋፍ ስጠብቅ ዉዬ፣ አመሻሽ ላይ መኖሪያ መንደሯ ካዛንቺስ ሄድኩ፡፡ አርብ ተለያይተን ቅዳሜ ደርሶ ዐይኗን ለማየት የሚያስናፍቅ ታላቅ ርሀብ (ዐይኗን የማየት ርሀብ) ከተቆራኘኝ ቆየ፡፡ በየሳምንቱ ቅዳሜ ቅዳሜ ኦርጅናል የቪኤችኤስ ፊልሞችን (ፊልም ማየት በጣም ትወድ ነበር) ሰፈሯ ድረስ ይዞ መሄዱን ልማድ አድርጌዉ ነበር፡፡ በዚያ እለት ይዤላት የሄድኩት  ታይታኒክ የተሰኘዉን የወቅቱን ተወዳጅ ፊልም ነው፡፡  የፊልሙ መሪ ገጸባሕሪያት የግዙፉ መርከብ ድርዝ ላይ እጆቻቸዉን በማቆላለፍ እንደ በራሪ ንስር  ግራና ቀኝ ክንፍ ዘርግተዉ የተነሱት ፎቶግራፍ የታተመበት ቲ-ሸርት ነበር የለበስኩት፡፡ ከናርዶስ  ሰፈር ራቅ ያለ ካፌ ዉስጥ ተገናኝተን ቸኮላት ኬክ በለስላሳ እየበላን የባጥ የቋጡን ስናወጋ (ሁሌም ስንገናኝ ብዙ እማወጋዉ እኔ ነኝ) አመሸን፡፡   
ናርዶስን እንደተሰናበትኩ፣ ተጋፍቼ የተሳፈርኩበት ሚኒ ባስ ታክሲ አካልቦ መኖሪያ መንደሬ ፒያሳ እንዳደረሰኝ እንጃለት። ረዳቱ ጉዟችን መገባደዱን አዉጆ ከመኪናዉ እንድንወርድለት ቆፍጠን ያለ ትዕዛዝ አዘዘን። ከሚኒ ባሱ ወርጄ በእግሬ ጥቂት ከተጓዝኩ በኋላ ኤንሪኮ ኬክ ቤት በር ላይ ቆመዉ ለሚያወጉት አብሮ አደጎቼ እጄን ከፍ አድርጌ በማዉለብለብ ሰላምታ ሰጥቼ እየተጣደፍኩ (ምን እንደሚያጣድፈኝ እንጃ) ወደ ቤቴ ዘለቅኩ።
ግራ እና ቀኝ ግንብ ያጀበዉን ግራጫ ቀለም የተቀባ የግቢያችንን ብረት በር በቁልፌ ከፍቼ ገባሁ፡፡ ሳሎን ስዘልቅ፣ ጠረጴዛ ከበዉ ራት እየጠበቁ የሚቁለጨለጩ የቤተሰቦቼ ዐይኖች ተቀበሉኝ፡፡ ለመላ ቤተሰቡ የሞቀ ሰላምታ አቅርቤ መኝታ ቤቴ ገብቼ መሸግኩ (የቤተሰባችን ልማድ ዘወትር ማታ ሳሎን ተገኝቶ እራት በጋራ በልቶ ወግ መሰለቅ ነዉ)፡፡
የናርዶስ መልክ አእምሮዬ ሸራ ላይ እንደተንሰራፋ ነዉ፡፡ አልጋዬ ላይ ወጥቼ ዳህላክ ሙዚቃ ቤት አቅንቼ የገዛሁትን የሳም ኩክ ካሴት በእስክርቢቶ አጠንጥኜ ትልቅ ሶኒ ቴፔ ዉስጥ አስገብቼ ከፈትኩ፡፡ ከሳም ኩክ ልሳን የሚፈልቀዉ ቃል ለእኔ የተጻፈ ነበር የሚመስለዉ፡፡ በልቤ እኔም እንደ ሳም ኩክ የፍቅር አማልክቱ ኪዩፔድ በቀስቱ ፍላፃ የናርዶስን ልብ ወግቶ እግሬ ስር እንዲጥላት ተመኘሁ፡፡1   
ሶ፣ ኪዩፔድ፣ ድሮዉ ባክ ዩር ቦዉ
ኤንድ ሌት ዩር አሮ ጐ፡፡
ስትሬት ቱ ማይ ላቨርስ ኸርት
ፎር ሚ፣ ኖበዲ በት ሚ፡፡
ኪዩፔድ፣ ፕሊስ ሂር ማይ ክራይ
ኤንድ ሌት ዩር አሮ ፍላይ፡፡
ስትሬት ቱ ማይ ላቨርስ ኸርት ፎር ሚ፡፡
ናዉ፣ ኪዩፔድ ኢፍ ዩር አሮ ሜክ ኸር ላቭ
ስትሮንግ ፎር ሚ
አይ ፕሮሚስ አይ ዊል ላቭ ኸር አንቲል
ኢተርኒቲ፡፡
አይ ኖ ቢቲዊን ዘ ቱ ኦፍ አስ
ኸር ኸርት ዊ ካን ስቲል                     
ኸልፕ ሚ ኢፍ ዩ ዊል፡፡
ሶ፣ ኪዩፔድ፣ ድሮዉ ባክ ዩር ቦዉ
ኤንድ ሌት ዩር አሮ ጐ፡፡
ስትሬት ቱ ማይ ላቨርስ ኸርት
ፎር ሚ፣ ኖበዲ በት ሚ፡፡
ኪዩፔድ፣ ፕሊስ ሂር ማይ ክራይ
ኤንድ ሌት ዩር አሮ ፍላይ፡፡
1993 ዓ.ም ላይ አስራ ሁለተኛ ክፍልን ልናገባድ ወር ገደማ ሲቀረን፣ ናርዶስን የሸገር  ዝነኛ መናፈሻ ዉስጥ ቀጥሬአት ተገናኘን፡፡ በእዛ ዕለት ነበር የልቤን ፍቅር ለናርዶስ የዘረገፍኩት። ከቤቷ ያመጣችዉን ዘቢብ እየበላሁ (ቀለሟን የመሰለ) ዐይኖቿ ላይ ዐይኖቼን ሰፍቻለሁ፣ እንደ ቡዳ፡፡
“ናርዶስ አፍቅሬሻለሁ፡፡”   
“ኦ! ይገርማል፡፡” አለች የሰዉነቷን ሙቀት ለማርገብ አንገቷ ዙሪያ ጠምጥማዉ የነበረዉን ቡናማ የአንገት ልብስ እያወለቀች፡፡ ህዋሶቼ በጅምላ ጆሮ ሆነዉ ቀጥሎ ከአንደበቷ የሚመነጨዉን ቃል ለመስማት እንዳሰፈሰፉ ናቸዉ፡፡
“እ … ማፍቀር ታላቅ ፀጋ ነዉ፡፡ ተፈጥሯዊም ነዉ፡፡” ዐይኖቼን ዐይኖቿ ላይ እንደ ተከልኩ አንገቴን በአወንታ ነቀነቅኩ፡፡          
“ምኔ ስቦህ ወደድከኝ?” በቀኝ እጇ ከግንባሯ ወርዶ ቀኝ ዐይኗን ጋርዶ የነበረዉን ፀጉሯን ወደ ጆሮዋ ኋላ መለሰች፡፡
“ሁሉ ነገርሽ፡፡”
ቃሌ ዉስጥ ኩሸት አልነበረም፣ ናርዶስ በሁለ ነገሯ ረታኝ ነበር፡፡ ከእሷ በፊት ሴት በዐይኔ አይሞላም ነበር፡፡  
“መስፍኔ … አፍቃሪነትህን አደንቃለሁ፤ ግን እኔ አልሆንህም፡፡” ዐይኖቿን ከዐይኖቼ ላይ አሽሽታ በዝምታ ባዶ አየር ላይ አተኮረች። ከአንደበቷ ባደመጥኩት አሉታዊ መልስ ኅሊናዬ ታወከ፡፡ ዙሪያችንን የከበቡት አበቦች ደበዘዙብኝ፤ ዉበታቸው ጎደለብኝ፣ አጠቃላይ የሥፍራዉ ገፅታ መናኛ ሆነብኝ፡፡      
አመሻሽ ላይ ናርዶስን ተሰናብቼ ወደ ሰፈሬ ፒያሳ በታክሲ ስመለስ ቅስሜ ተሰብሮ ኃያል ድብርት ተጭኖኝ ነበር፡፡  የፍቅር ጥያቄዬን ትገፈዋለች የሚል ጥርጣሬ አእምሮዬ ዉስጥ አልነበረም፡፡ እኔን የገፋች ሴት አልነበረችም። ብዙ ነበሩ ፈላጊዎቼ፡፡ ፍቅር ነዉ ኅሊናዬን አዉሮ የናርዶስ  አምላኪ ያደረገኝ፡፡
በዙሪያዬ ናርዶስን በዉበት የሚከነዱ ብዙ ጠንበለሎች ነበሩ፤ ልቤን የረታችዉ ግን እሷ ነበረች፡፡ በስብ የደደረዉ ግዙፍ ሰዉነቷ ቅርፅ አልቦ ቢሆንም፣ ጡቶቿ ያጋቱ የላም ጡቶች ቢያክሉም፣ አልፎ አልፎ ከንፈሯን ገሽልጣ ስትስቅ የሚታየዉ ድዷ ድልህ ቢመስልም ቀልቤን የሰረቀችዉ ግን እሷ ነበረች፡፡ ስንት የሸገር ጠይም አሶችን ገሸሽ አድርጌ ቀዝቃዛና ዝጋታም ሴት ለምን እንደወደድኩ አላዉቅም፡፡   
ናርዶስ ለእኔ የተፈጠረች ሴት ትመስለኝ ነበር፡፡ እዉነታዉ ግን ተቃራኒ ነበር፡፡ ናርዶስ ‘እኔ አልሆንህም’ በሚል ያልተብራራ ምላሽ ከሕይወቷ ገሸሽ አድርጋኛለች፡፡ ‘እኔ አልሆንህም’ የሚለዉ አጭር ዓረፍተ ነገር ትርጓሜ አዉዱ ሰፊ ነዉ፡፡ ‘እኔ አልሆንህም’ ማለት አልማረከኸኝም ማለት ነዉ፡፡
 በቀጥታ ‘አንተ ፈፅሞ ዓለም ላይ የምመርጥህ ወንድ አይደለህም’ ብሎ እቅጩን ከመናገር ይልቅ ‘እኔ አልሆንህም’ በሚል አጭር ቃል አፍቃሪን ገለል ማድረግ ኪነት የተሞላበት ጨዋነት ነዉ፡፡
የቃሉ ቅኔ ፍቺ ነዉ አቁሳዩ፡፡
1. ኪዩፔድ በሮም አፈ ታሪክ ዉስጥ የሚገኝ የፍቅር አምላክ ነዉ፡፡ ይህ የፍቅር አምላክ ቀስተኛ ሲሆን በፍላፃዉ የወጋዉ ሁሉ በአንዷ ወይም በአንዱ ፍቅር መዉደቅ ዕድል ፈንታዉ ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኪዩፔድ አልማዝ የተባለች ሴት አበበ በተባለ ወንድ ፍቅር እንድትንበረከክ ልቧን በቀስቱ ከወጋ አልማዝ በአበበ ፍቅር የምብርክክ ከመሄድ ውጭ ሌላ ምርጫ አይኖራትም፡፡ ኪዩፔድ የወደርየለሽ ቆንጆዋ ሳይኪ ፍቅረኛ ነዉ፡፡ ሳይኪ  ምንም እንኳ መዋቲ ፍጡር ብትሆንም የኪዩፔድን እናት ኢ-መዋቲዋን የዉበት እና የፍቅር አምላኳን ቬነስን በቁንጅና ትከነዳት ነበር፡፡ ኪዩፔድ እና ሳይኪ ከተጋቡ በኋላ የአማልክቱ ገዥ ጁፒተር ሳይኪን ኢ-መዋቲ አድርጓታል፡፡        

Read 1111 times