Saturday, 25 February 2023 12:09

አግባ ሲሉት ሚዜ እሆናለሁ አለ!

Written by 
Rate this item
(13 votes)

   በአንድ ሰፊ ቤት ጓዳ ውስጥ በመስኮት ሁለት ድመቶች የተንጠለጠለ ስጋ አይተው እንዴት አውርደው ሊወስዱ እንደሚችሉ መማከር ጀመሩ። “የምንችለውን ያህል እንዝለልና አንዳችን እንደምንም ብለን እንይዘዋለን፤” ተባባሉ። ሌሊቱን ሙሉ ሲዘልሉ አድረው ስጋውን ለማውረድ ለፉ። ግን አልቻሉም። ሊነጋጋ ሲል አንደኛው ድመት አንድ ዘዴ አመጣ።
“አንተ ትከሻ ላይ ልቁምና ከዚያ ልዝለል። ያኔ ወደ ስጋው እቀርባለሁና በቀላሉ አወርደዋለሁ” አለው። ሁለተኛው ድመት በሃሳቡ ተስማምቶ እንደተባለው ለጓደኛው ተንጠራርቶ ትከሻውን አመቻችቶ ሰጠው። አንደኛው ድመት ጓደኛው ትከሻ ላይ ቆመና ወደላይ ተስፈነጠረ። ያለችግር ስጋውን ይዞ ወረደ። ከዚያም ተካፍለው ድርሻ ድርሻቸውን ለመውሰድ ወደ ጓሮው ስጋውን ይዘውት ሄዱ። ሆኖም “ስጋውን ለማውረድ የተሻለ አስተዋጽኦ ያደረኩት እኔ ነኝ፣ እኔ ነኝ” በሚል ተጣሉ። በመጨረሻም መስማማት ስላቃታቸው “ጓሮ ካለው ዛፍ ላይ የምትኖር ትልቅ ጭልፊት ትፍረደን” በሚለው ሀሳብ ተስማሙና ወደሷ ሄዱ። እንዳገኟትም ምክንያታቸውን በተራ በተራ አቀረቡ።
አንደኛው ድመት፤ “ብልሃቱን ያገኘሁት እኔ፣ የዘለልኩትም እኔ፤ ስለዚህ ለእኔ ይገባኛል” አለ።
ሁለተኛው ድመት፤ “እሱ ብልሃቱን ቢያገኝም፣ ቢዘልም፣ እኔ ትከሻ ላይ ቆሞ የዘለለ በመሆኑ ዋናው የስራ ድርሻ የእኔ ነው” አለ።
ጭልፊትም ዳኝነቷን ስትሰጥ፤ “የሁለታችሁም አስተዋጽኦ ባይኖር ኖሮ ሥጋውን ለማውረድ አትችሉም ነበር። ስለዚህም እኩል ብትካፈሉ ይሻላል” አለች።
በሃሳቧ ተስማሙ። “እሺ ለማንም ሳታዳይ አንቺው አካፍይን” አሏት።
ጭልፊት ስጋውን ሁለት ቦታ ከፍላ፣ አንዱን ክፋይ በአንድ እጇ፣ ሌላኛውን በሌላ እጇ ይዛ የግራው በዛ ስትል ከግራው ቆርሳ ስትጎርስ የቀኙ በዛ ስትል ከቀኙ ቆርሳ ስትጎርስ ስጋው ተመናምኖ በጣም ጥቂት ብቻ ቀረ። በመጨረሻም የቀረውን ስጋ አንድ ላይ አድርጋ በሁለት እጇ ያዘችና፤
“ ይሄ ደግሞ እኔ የዳኝነቱን ስራ የሰራሁበት ክፍያዬ ነው” ብላ ይዛው ወደ ሰማይ በረረች።
***
መብትን፣ እድልን፣ አሳልፎ ለሌላ መስጠት የራስን ይዞታ ከነአካቴው ያስነጥቃል። በራሳችን ልናዝበት በሚገባ ጉዳይ እርስ በእርስ አንስማማ ብለን ዳኝነቱን ለሌላ በተውን ቁጥር የጭልፊት ሲሳይ እንሆናለን። በትናንሾቹ የፖለቲካ ጉዳዮቻችን በተኮራረፍን፣ በተጋጨን፣ በተጠላለፍን ቁጥር ለባላንጣችን ምቹ መደላደል እንፈጥራለን፤ ለውጭ ጣልቃ-ገብ ሃይልም ገርባባውን በር አንድያውን በርግደን እንከፍታለን። ራዕያችን (Vision) በጠበበና ሩቅ እይታችን (Far-sight) ባጠረ ቁጥር ሩቅ የታለሙ ግቦችን ማስተዋያ አይናችን ይንሸዋረራል።
ከተራራው ወዲህ ያለችውን ትንሿን ወጥመድ ለማምለጥ ስንሯሯጥ፣ ከተራራው ጀርባ ያለውን ግዙፍ ወጥመድ እንዳናይ እንታወራለን።
በሀገራችን ተደጋግፈው ለድል የበቁ ወይም ያልበቁ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ማህበራት፣ ተቋማት፣ ግለሰቦች ውለው አድረው ሚዛን በማይደፉ ጉዳዮች ጠብጭረው፣ ተፈነካክተው፣ ተዳምተው፣ ጠላት ቢያጡም ባያጡም ራሳቸው ተከፋፍለው፣ ጎራ ለጎራ ተታኩሰው ለውድቀት የበቁ አያሌ ናቸው። አብዛኞቹ ዋናው ባለጉዳይ በሌለበት ዋና ለመሆን በሚጥሩ ወገኖች ሳቢያ የሚፈጠሩ ውድቀቶች ናቸው። “ንጉሱ እህቴ ነች ሳይል፣ እኔ የንጉስ እህት ነኝ ትላለች” እንደተባለው መሆኑ ነው። የሁልጊዜውም አዚም፣ የሁሌም አባዜያችን ይሄው ነበር፤ ነውም። ገጣሚው ሮበርት ፍሮስት እንዳለው፤ “ባልተሄደበት መንገድ ከመሄድ፣ በሄድንበት ላይ እንዳክራለን”። ታላላቅ መንግስታት ባመቻቸው በወደዱትና በጣፈጣቸው መንገድ የአፍሪካን ሀገሮች መቃኘታቸውና የእነሱን ዜማ እንዲያዜሙ ማድረጋቸው መቼም፤ ፀሀይ የሞቀው እውነት ነው። የአፍሪካ ቀንድ የማያባራ ቀውስን ቀዘቀዘ- ሲሉት- ፈላ፣ ፈላ- ሲሉት- በረደ ፖለቲካ (Volatile) በታላላቆቹ መንግስታት የማይቆረቁር መግለጫ እንደሚሆን አገራቱም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎቹም፣ ታዋቂ የፖለቲካ ሰዎችም አውቀው በድፍረት ሳያውቁ በስህተት አላይ እያሉ በየራሳቸው የወፍ-ጎጆ ውስጥ ጦርነት (War in respective pigeon-holes) እያካሄዱ ሲቃጠሉ፣ ለታላላቆቹ የጦርና የብዝበዛ መሀንዲሶች (War engineers) የጥቅምም የንድፈ ሃሳብም መፈተኛ ከመሆናቸው ባሻገር፤ የበሰለ ምግብ አልያም ማዳበሪያና ማገዶ (Cannon fodder) ይሆናሉ። ሃያላኑ መንግስታትም “ሊበሏት የፈለጓትን አሞራ ጅግራ ይሏታል” እንዲሉ “ዲሞክራሲ እየተስፋፋባቸው፣ ሰላም እየሰፈነባቸው፣ ፍትህ እያረበበባቸው ያሉ ሀገሮች) የሚል ውዳሴ ዜማቸውን ያሰሟቸዋል። ድንገት ባይመቿቸው ደግሞ እንደ ዘንድሮ ኑሮ ዘዴ “ነክ-ባትሉኝ” ማለትን ያውቁበታል። ወላይታ “ጊዜው ሲዋሽ ድመት ታመነዥጋለች” እንዲል፤ ብዙ የተገላቢጦሽ ፍርድ፣ የውል መሰረዝ፣  መሪ መሻር፣ መሪ መቅረጽ ወዘተ በማናለብኝ የሚፈጽሙት በወታደራዊ ሃይላቸው ጡንቻ (Military might) እና ከፋይናንስ ክርናቸው ግዝፈት የፈለቀ “ጥበብ” ሳይሆን ኮከባቸው የፈቀደላቸው እንዲመስል መስበካቸው አልቀረም። ይሄን መሳዩ ፍሬ- ጉዳይ በንቃት፣ በጉጉት አይን መታየት ያለበት ነገር ነው።
በሀገራችን የየዘመኑ ጉዞ- ስልጣን ሰሞነኛ ፈሊጥ፣ ወንበር በያዙ ማግስት “መባረሬ አይቀርምና አሟሟቴን አሳምርልኝ። አወዳደቄን አደላድልልኝ (Soft landing እንዲል)” አይነት ከሆነ ውሎ አድሯል። ጸሎታቸው “ቆሞ አውሎ ንፋስ የማይደፍረውን ግንድ፣ ወድቆ ውሻ ይራመደዋል” የሚባለው ተረት እንዳይደርስ ነው።
ከአሸናፊዎቹም ወገን ቢሆን “ልቅደም እንጂ የሩጫ መልክ አለው ወይ” እያለ ግራ ቀኙን ሰው እየረመረመ የሚሮጠው ይበዛል። ፍርሃትና ጥርጣሬ ይዞ ያድጋል። የገዛ እብሪቱ ይጥለዋል። ባላንጣው በበኩሉ ቂም እንደያዘ ያድራል። ሲወድቅለት እርግማኑን ያወርድበታል። አገሪቱም አሸናፊም ተሸናፊም የሚሸነፍባት ሀገር ትሆናለች።
ያለፈውን ሁሉ አጋነን በማስቀመጥ ከዛሬ ጥፋት እንድን ይመስል- “ይህን ሚስጥር አውቅ ነበር፣ ያ ደባ የእኛ ነበር…” ማለት ልማድ ነው። ህዝቡም “ነበር ለካ?” በሚል ፈሊጥና “እኛም ብለን ነበር!” በሚል ኩራት አእምሮውን ሸብቦ በወግ እየተገበዘ ይቀመጣል። ምን እንደሚመጣ እንዳያይ እንደ ዱቤ-ከልል ባርሜጣ አይኑ ላይ ግርዶሽ ጥሎ ዛሬን በእንቅልፍ እንዲያሳልፍ ይገደዳል። “አንዱን ወገን ወሬ ያጠፋል፣ አንዱን ወገን ጦርነት ያጠፋል” እንዲሉ ማለት ነው። በሥነ-ልቦና ጦርነትም፣ በአካላዊ ትንቅንቅም፣ አቅሙን እያኮሰመነ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ አንድያውን ቅስሙ እንዳይነጥፍ የሚታደገው አስተዋይ ወገን፣ ፓርቲ፣ ድርጅት፣ መሪ ያሻዋል።
መብቱን የማያውቅ ህዝብ የሁሉ ጫማ መርገጫ ነው። የየትኛውም ስልጣን ኮርቻ ርካብ ነው። የጎደለው እንዲሟላ የማይጥር፣ የተድበሰበሰው እንዲገለጥለት የማይጠይቅ ህዝብ፣ በገዛ ቤቱ አዛዥ የመሆን እድል የለውም። በገዛ ዳቦው ልብ ልቡን ያጣል። ዲሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ቀርቶ ይቆይበት የረጋ ምድር፣ ይውል ያድርበት ቤት፣ ጸሀይ ይሞቅበት በርጩማ አጥቶ ብርድ ይፈደፍደዋል። ምኞትና ህልም ያጣል። ሁሉን አሳልፎ ይሰጣል። “አግባ ሲሉት ሚዜ እሆናለሁ አለ” የተባለው አይነት መሆኑ ነው።


Read 2379 times