Saturday, 25 February 2023 13:33

ታላቅነታችን በተመፅዋችነታችን ኮስምኗል!

Written by  የዓባይ፡ልጅ Esleman Abay
Rate this item
(0 votes)

  ውሃ ሰማያዊ ፀጋው አረንጓዴ፤
ልጆቹ ተመፅዋች የዳቦና ስንዴ።
ባለ ጠጋዋ አህጉራችን አፍሪካ፣ እስከ 2020 በነበሩት ሁለት ዓመታት ውስጥ፣ ከአመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ አንድ ሶስተኛውን ከሩሲያ፣ 12 በመቶውን ከዩክሬይን  ማስገባቷን UNCTAD ያወጣው  ሪፖርት ይገልጻል፡፡
ባለ ፀጋይቷ አህጉረ አፍሪካ የመላው ዓለም 60 በመቶ ያልታረሰ ለም መሬት ባለቤት ናት፤ ተፈጥሮ ከለገሳት 874 ሚሊዮን ሄክታር የሚታረስ የመሬት ሃብቷ 179 ሚሊዮን ሄክታሩን ብቻ ነው እያረሰች የምትገኘው፤ ይኸውም ቢሆን ምርታማ በማያደርግ ዘዴ የሚተገበር ነው። በዚህም አፍሪካ ከምታርሰው የመሬት ስፋት አንፃር አንድ አራተኛ እንኳ የማይሞላ መሬቷን ምርታማ አድርጋ ያረሰችው ዩክሬይን፣ ለባለ ጠጋዋ  አፍሪካ ምግብ አቅራቢ ለመሆን በቅታለች፡፡  
የአህጉራችን ሕዝብ ቁጥር ባለፉት 30 አመታት በእጥፍ (በከተሞች 3 እጥፍ) አድጓል።
60 በመቶው የአፍሪካ ህዝብ ግብርና ላይ ተሰማርቶ 180 ሚሊዮን ሄክታር ያህል መሬቷ ላይ በገበሬነቱ ቢተጋም፣ የራሱን  ፍጆታ ለመሙላት ግን ከዩክሬይን መሸመት ይጠበቅባታል። ይህችው ዩክሬይን 41 ሚሊዮን ሄክታር በሚገመት መሬቷ ላይ 14 በመቶ ብቻ ህዝቧን በግብርናው ዘርፍ አሰማርታ ነው፣ ለባለጠጋዋ አህጉር ምግብ ሻጭ መሆን የቻለችው - የቆዳ ስፋቷ ደግሞ የአፍሪካን 2 በመቶ (604 ሺህ ኪ.ሜ ስኩዌር) ብቻ ነው።
ከአምስት አፍሪካዊያን አንዱ የከፋ ረሃብ ውስጥ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ያስታወቀው  የዛሬ ሁለት አመት ሲሆን፤ በዚሁ አመት አፍሪካ ለምግብ ግዢ 50 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርጋለች።
አንዳንድ ሃቆች
- ከ90 በመቶ በላይ የደቡብ ሱዳን መሬት ሊታረስ የሚችል ሲሆን፤ አዲሲቷ ሀገር የአፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ የዳቦ ቅርጫት የመሆን አቅሟ ብዙ ቢባልለትም  ጥቅም ላይ የዋለው አራት በመቶው መሬት ብቻ ሲሆን፤ አሁንም ከውጭ በሚገቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ መሆኗን ቀጥላለች።
- ኡጋንዳ 80 በመቶ መሬቷ ሊታረስ የሚችል ሲሆን፤35 በመቶው ብቻ ነው እየለማ የሚገኘው፡፡
- የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2001 ሪፖርት እንዳመለከተው፤  ናይጄሪያ ለምግብና ለግብርና ምርቶች ግዢ በዓመት 1.6 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።
- ጋና በየአመቱ ከ 300,000 ሜትሪክ ቶን በላይ ያልተጣራ (ክሩድ ፓልም ዘይት) እስከ 100 ሚሊዮን ዶላር በሚደርስ ወጪ (መንግስታዊ ድጎማ እያደረገች) ከእስያ ሀገራት ትሸምታለች።
- አፍሪካ በፈረንጆቹ 2050 ዓ.ም ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥሯ 2 ቢሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል።
ወደ ኢትዮጵያ ብንመለከት፣ ከ 50 ሚሊዮን ሄክታር ሊታረስ የሚችል የመሬት ሐብቷ (ባልዘመነ ዘዴ) የምናርሰው 16 ሚሊዮን ሔክታሩን ብቻ ነው። ግዙፍ የውሃ ሀብት የተለገሳት ሲሆን 124 ቢሊዮን ኪ.ሜ. የወንዝ፣ 70 ቢሊዮን ኪ.ሜ. የሐይቅ ውሃ እና በብዙ ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሚለካ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት ተለግሷታል። የውሃ ሀብቷ  7.5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት ቢችልም፣ ጥቅም ላይ የዋለው 1.2 ሚሊዮን ሄክታሩ (የአቅማችንን 16 በመቶ ብቻ) ነው።
የአለማችን ቁጥር 2 የግብርና ምርቶች ላኪ መሆን የቻለችው ኔዘርላንድስ፤ የቆዳ ስፋቷ ከኢትዮጵያ 27 ጊዜ ያነሰ ነው፡፡ 4.2 ሚሊየን ሄክታር አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ያላት ኔዘርላንድስ፤ ከአጠቃላይ መሬቷ ግማሹን (ሁለት ሚሊየን ሄክታሩን) በተሻሻሉ ዘዴዎች ለእርሻ አውላው ነው፣ ከረሀብ ታሪኳ ተስፈንጥራ በጥቂት አስርት አመታት ውስጥ ወደ ሐብታምነት ከፍ ያለችው። ሀገሪቱ ከአመት በፊት የእርሻና የእንስሳት ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ዩሮ በላይ የውጭ ምንዛሪ አግኝታለች።
ኢትዮጵያ ለእርሻ ያዋለችው የመሬት ስፋት ኔዘርላንድስ ለግብርና ካዋለችው ጋር ሲነፃፀር ከ8 እጥፍ በላይ ብልጫ አለው። ዘርፉ የሚተገበርበት ዘዴ ያልዘመነ በመሆኑ እንጂ 16 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኢትዮጵያ እየታረሰ ነው። (ሊታረስ ከሚችለው 50 ሚሊዮን ሔክታር መሬታችን ውስጥ  መሆኑ ነው።)
በማዕድን ሐብት ከየትኛውም አህጉር የማይወዳደር ፀጋ የተለገሳት አህጉረ-አፍሪካ፤ ከ90 በመቶ በላይ የአለም የፕላቲኒየም ማዕድን፣ 50 በመቶ የወርቅ ማዕድን፣ 50 በመቶ የአልማዝ ሐብት እና  33 በመቶ የዩራኒየም ማዕድን ባለቤት ናት - ያስገኘላት ትርፍ ግን ለልጆቿ ሰቆቃና ሌቦቿን ከማደለብ የዘለለ ባይሆንም።
“አህጉራችን የተሻለ የሚታረስ መሬት እያላት በረሀብ ከተጋለጠው የዓለም ህዝብ አንድ ሶስተኛው ለምን አፍሪካዊ ሆነ? ብሎ መጠየቅ ይገባል፡፡ ለጊዜው ራሳችንን  በደንብ መመገብ ባንችልም፣ እውነታውን ለመለወጥ ግን በጋራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡” በማለት ጠ/ሚ ዐቢይ በ36ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተናገሩ ሲሆን፤ ያነሱት የመፍትሄ ሀሳብ ታዲያ በቀደሙ ፓን አፍሪካዊ መሪዎችም ሲቀነቀን የቆየ ነው።  ይህን አፍሪካዊ መፍትሄ ለመተግበር የሚቻል ቢሆንም፣ ጠልፎ የሚጥል ጣጣ ሲያመጣ ነው ታሪክ የሚነግረን። አፍሪካ ከልመና ስትላቀቅ ከሐብት ማማ ላይ ወርደው የሚፈጠፈጡ ሃያላን መኖራቸው፣ የጥቁሮችን ምኞት ሲያጨናግፍ ቆይቷል። ጉዳዩ ስውር ቀይ መስመራቸው በመሆኑ..።
የአፍሪካ ተመፅዋችነትና ድህነት ለምዕራባዊ ሀገሮች የሀብት መሠረትና የፈጣን ዕድገታቸው ምሰሶ መሆኑን የገለፁት ጎምቱው አንድሬ ጉንደር፤ “በዓለም ዙሪያ ያሉ ደሃ ሀገራት በተለይም የሰሃራ በታችና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ናቸው።” ብለውናል። ለዚህም ነው አፍሪካን ለሃምሳ በጣጥሰው እምቅ ጉልበቷ በተቃርኖ ፍትጊያዎች እየመከነ ለግልቢያ የተመቸ አህጉር ያደረጓት። ለዚህም ይመስለኛል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአፍሪካ መሪዎች በጋራ መቆማቸው የመፍትሄው ቁልፍ መሆኑን ያሰመሩበት።
በሪቻርድ ኒክሰን እንዲሁም ቀጥለው በነበሩት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች የስልጣን ጊዜ የፀጥታ አማካሪና የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዋና ፀሐፊ ሄንሪ ኪሲንጀር በግልፅ እንደተናገሩት፤ “የአለም አቀፉም የጂኦ-ፖለቲካ ሃይል የሚዘወረው የሀይል ምንጮች ላይ በሚኖር የበላይነት፣ የምግብ አቅርቦትን ብሎም አለም አቀፍ ገንዘብን መቆጣጠር በቻሉ ሀገራት ነው” (Who controls the food supply controls the people; who controls the energy can control whole continents; who controls money can control the world.)
የአፍሪካ ጠቅላላ አመታዊ ምርት 2.4 ትሪሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፤ ይህም አፍሪካን የፕላኔታችን 7ኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት የሚያደርግ ነው።
አህጉራችን ያላት የሸመታ አቅም 1.6 ትሪሊዮን ዶላር ሲሆን፤ ይህም እንደ አንድ ሀገር ቢሰላ ከአለም 11ኛው ከፍተኛ የግዢ አቅም ያደርጋት ነበር። ይህ ደግሞ የአፍሪካን የመደራደር አቅም ሃያል ባደረገው  ነበር።
የቡርኪናፋሶው ፓን አፍሪካዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንት  ቶማስ ሳንካራ ...“ዕዳ በብልጣ ብልጦች የተሰራች አፍሪካን መልሶ የመቆጣጠሪያ ሴራ ናት” ሲል በአፍሪካ አንድነት ድርጅት  ጉባዔ በ1987 ላይ የተናገረውም፣ በየዘመኑ ክስተቶች እውነትነቱ ሲገለጥ መታዘብ ተችሏል።
ጀግንነታችን በረሀብተኝነታችን ተጋርዷል፤ ታላቅነታችን በተመፅዋችነታችን ኮስምኗል፣ ክብራችንንም ድህነታችን አስረስቶናልና…ስንዴ አምርቶ ረሃብን ከራስ ጓዳ ማስታገስ ማለት ከስንዴ የተሻገረ ዋጋ እንዳለው በውል መረዳት ያስፈልጋል፡፡
ይህን ሰቆቃ በጎጥ ተበጣጥሰን ይቅርና፣ እንደ ሀገር በርትተንም ለመስበር ከባድ ነው። ከአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች ሀገር ብትኖረንም፣ ሌላው አፍሪካ ተገዢ ነበርና ዞረን የነሱው አገልጋይ ሆነናል። ሕብረትን ከሀገርም ባሻገር እስከ አፍሪካ አሻግረው የሚናፍቁ ሹማምንት እስካልተበራከቱ ድረስ ከአዙሪቱ ለመውጣት ተዓምር መጠበቅ ይኖርብናል።
ጋናዊው የፓን አፍሪካ መሪ የነበሩት ከዋሚ ንኩርማ እንዳሉት፤ “የአፍሪካ እጣ ፋንታ ወይ እውነተኛ አንድነትን እውን ማድረግ ወይም መጥፋት ነው። ያለ እውነተኛ አንድነቷ የአፍሪካ መፃኢ ዘመናት በቅኝ ገዢ ሀገራት ይሁንታና ክልከላ ስር የታነቀ ይሆናል!”



Read 923 times