Monday, 27 February 2023 00:00

“ያለ ትብብር፣ … አገር አይፈርስም!”... የሚሉ ይመስላል - በጥላቻ ሲረባረቡ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 አዲስ ውዝግብ ሳይፈጥሩ ካደሩ፣ አገርን የሚያንገጫግጭ፣ ህዝብን የሚያንጫጫና- የሚያስጨንቅ ቀውስ ሳይፈጥሩ ከሰነበቱ፣ ክብራቸው የተገፈፈ፣ ዝናቸው የተረሳ፣ ስልጣናቸውን ያስደፈሩ፣ ተቃዋሚነታቸውን ያስነጠቁ ይመስላቸዋል።
“የመጣው ይምጣ፣… አብጦ ይፈንዳ፣… የተናጠው ይደፍርስ፣… የተዳፈነው ይንደድ”… “ከዚያ የሚሆነውን እናያለን”… የሚል ፉክክርና እሽቅድምድም እየማረካቸው፣ የመጠፋፋት ውድድር እንደስራ የሚያዘወትሩ በዝተዋል።
ዛሬ፣ ስለ አድዋ የነጻነት ድልና ስለ ሕዳሴ ግድብ የምንነጋገርበት ጊዜ መሆን ነበረበት። ጊዜያችንን የምናጠፋው ግን፣ አገርን በሚያወዛግብና ሕይወትን በሚያጠፋ ክፉ ንግግር ነው።
የግዙፉ ግድብ የግንባታ ግስጋሴ የት እንደደረሰ፣ ምን ያህል ውሃ እንደያዘ ከነከፍታው እየዘረዘርን፣ በቁጥር እያነፃፀርን ብንነጋገርበት ይበዛበታል? 20 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ገደማ ነበር የደረሰው - አምና ነሐሴ ወር አጋማሽ።
በመጪው ክረምት፣ ከአምናው የበለጠ ውኃ ለመያዝ፣ ከወንዙ ወለል የግድቡ ከፍታ 120 ሜትር ወይም ከዚያ በላይ ማለፍ አለበት። በእርግጥ፣ እንዳለፉት ዓመታት፣ እኛ ስለ ግድቡ ውኃ ብንናገር፣ ከግብፅ መንግስት በኩል የውግዘት መዓት ይጎርፋል። ለነገሩ ዝም ብንልም፣ በሚቀጥሉት ወራት የግብፅ መንግስት ስሞታና ውንጀላ መበርከቱ አያጠራጥርም።
ስለ ግድቡ ግንባታና ስለ ውሃ ሙሌት እኛ ባንነጋገርም እንኳ፣ የየዓመቱ ውንጀላ ዘንድሮም መደገሙ አይቀሬ ከሆነ፣ ብንነጋገር ነው የሚሻለው።
ግን ኑሯችን በግጭት ቅስቀሳና በነውጠኞች ዘመቻ ተወጥሮ መች ለቁምነገር ጊዜ ይኖረናል? ጊዜስ ቢገኝ፣ በአተካራና በውዝግብ ሱስ ተጠምደን፣ የህዳሴ ግድብ እንዴት በሃሳባችን ይመጣል? ከአንደበታችን ዝር አይልም።
ከልብ ብናወራበትኮ፣ ለግድቡ ግንባታ ከዜጎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ብቻ አይደለም ጥቅሙ።
ሌላውን እንደተወውና፣ የአገሪቱ ትምህርት ባይራቆትና የእውቀት ልምሻ ባይፈጠር ኖሮ፣ የሕዳሴ ግድብ ለተማሪዎች የሚሰጠው ጥቅም ብዙ ነበር። ከግድቡ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በምን ምክንያት እንደሚጨምርና እንደሚቀንስ አስቡት። በውኃው ብዛትና በከፍታው ነው የሚሰላው። ለ11ኛ እና ለ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በሚያመች መንገድ፣ ቀመሩንና ስሌቱን ማሳየት አይከብድም። “m.g.h.” የሚለውን ቀመር አስታወሳችሁ?
አዝናኝ የጥያቄና መልስ ዝግጅት ሊወጣለትም ይችላል - ትንሽ ከታሰበበት። ይህን ወደ በኋላ እናቆየው። እናየዋለን። ግን ትንሽ ይቆይ። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካው መች ፋታ ይሰጣል? የሐይማኖት ተቋም ላይ የመጣው መዓትስ መች በቀላሉ ይረግባል? መወዛቢያ ተትረፍርፎ፣ ስለ ሕዳሴ ግንባታ፣ ቀመርና ስሌት እያልን ለምን እንጨናነቃለን?
ቢሆንም ግን፣ የግድቡን ስሌትና ቀመር ብናውቅም ባናውቅም፣ በጥቅሉ መነጋገር አያቅተንም ነበር - ከፈለግን። ከአዲሱ ኃይቅ ጥልቀትና ስፋት ጋር፣ ከጠረፍ ዳር እስከ መሃል አገር፣ ሁሉንም የሚያዳርስ የብርሃን ኃይል እንዴት በእውን እየደመቀ እንደሚመጣ ማውራት ነበረብን - ዛሬ። እንደ ትረካ፣ “በነዚህም ወራት” እያልን፣ ስለ ግድቡ ብናወጋ ማን ይከለክለናል? ከመዋጋት ይሻላል።
የሕይወትን በጎ ትርጉም እንድናውቅና በጨረፍታም ለማጣጣም እድል የሚሰጥ ድንቅ ፀጋ እና ውድ የጽናት ፍሬ ነው  - የሕዳሴ ግድብ ግንባታ። የአድዋ የነጻነት ድልም ነበረልን። ግን ጊዜ የለንም። ለውዝግብም በቂ ጊዜ አጥተናል።  
የጦርነትና የግጭት፣ የመከራና የትርምስ ሰበቦችን በመግታት፣ የሰላምና የእርጋታ ጭላንጭሎች እንዲፈኩና አስተማማኝ እንዲሆኑልንስ፣ መቼ እንመካከር? እስከመቼ እንጠብቅ? የበኩር ጉዳያችን እንደሆኑብን የምር የምንገነዘበውስ መቼ ነው? አበክረን እንድንሰራ፣ እናም… በሐዘንና በስጋት ምትክ፣ ሰላምና ተስፋ እንዲበዛ ዛሬ መነጋገር ነበረብን። ሰላምን ከማስፈን አልፈን እንድንሻገርና የሚያዘልቅ፣ ሕግና ሥርዓት እንዲጸና መመካከር መነጋገር ነበረብን- ዛሬ።
በጣም የተጎሳቆለው የዜጎች ኑሮ እንዲያገግም፣ የተቃወሰውና የተመሰቃቀለው ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ፣ እለት በእለት ሳናሰልስ ማሰብና መትጋት የምጀምረውስ መቼ ይሆን? የዋጋ ንረት እንዲረግብ፣ ኢንቨስትመንት ያለስጋት እንዲነቃቃና የሥራ እድሎች እንዲከፈቱ፣ የሥራ አጥነትን ማእበል እንድንቋቋም በአጽንኦት የምናስብበትና በተስፋ የምንነጋገርበት ጊዜ መሆን ነበረበት-ዛሬ።
እጅግ የተበላሸው የትምህርት ሁኔታስ የአንድ ሰሞን ወሬ፣ ጊዜያዊ ወረት ነው? ብዙ ገንዘብ እየፈሰሰበት ለምን ፍሬ አልባ እንደሆነ በቅጡ ለመገንዘብና መፍትሄ ለማበጀት የምንጣጣርበት ጊዜ መቼ ነው? ዛሬ መሆን ነበረበት።
በመላው ዓለም አስፈሪ ቅራኔዎችንና ውዝግቦችን የሚያባብስና የሚያዛምት አስፈሪ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ መግባታችንስ ልብ ብለነዋል ወይ? በየጎራውና በሁሉም ማዕዘናት ግራ መጋባትና መተራመስ የበረከቱበት፣ በወታደራዊ ኃይልና በጦር መሳሪያ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ከጎረቤት እስከ ባሕር ማዶ፣ ከቅርብ እስከ ሩቅ አደገኛ ስጋት የሚፈጥሩ መንግስታት እየበዙ የመጡበት ዘመን ነው-ዛሬ።
ታዲያ በዚህ አስፈሪ የትርምስ ዘመን ላይ ሆነን፣ በአደገኛ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ገብተን፣ በገዛ እጃችን ተደራቢ የቤት ውስጥ ግብግብ መፍጠር ነበረብን ወይ?
በራሳችን አንደበት ስንቀባጥር አደጋ መጥራት፣ በራሳችን ድካምና ወጪ ጥፋትን መደገስ ነበረብን?
ማለቂያ የሌለው የሰበብ ዓይነት፣ እልፍ የውዝግብና የቅራኔ መዓት እየፈለፈልን፣ በትርምስ አፋፍ ላይ ደርሰናል።
ከአንድም ሁለት ሦስቴ ወደ እንጦሮጦስ ለመውረድ ተንገዳግደን፣ ለትንሽ ድነናል፤ ለትንሽ ተርፈናል። ቢሆንም ግን፣ ጊዜ ሳናጠፋ፣ እንደገና በአዳዲስ ሰበብ ተጨማሪ ረብሻና የመጠፋፋት ግርግር ያለፋታ እንለኩሳለን። ያለማቋረጥም እያቀጣጠልን፣ ከውስጥም ከውጭም ተጨማሪ የጥፋት መዓት የምንጋብዝበት ጊዜ መሆን አልነበረበትም- ዛሬ።
አስተዋይትና ስክነት፣ ትጋትና ጽናት፣ ጥንቃቄና ጥበብ በእጅጉ የሚያስፈልጉበት ጊዜና ቦታ ላይ ነን።
ታዲያ፣ በእፍታ ርቀት ከገደል አፋፍ ላይ መሆናችንን በውል መገንዘብና ማወቅ ለዛሬ ካልሆነ ለመቼ ሊሆን ነው?
ተግባራችንን ማስተካከልና ባሕርያችንን ማቃናት የምንጀምረውስ መቼ ይሆን? ዛሬ ካልሆነ!
ነገረ ስራችን ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል። በጭፍን በድንብር ወደ ገደል መጣደፍ አብዝተናል። የዘፈቀደ አዙሪትና የስካር ቅዠት የሰፈረብን መስለናል።
ይህም ያነሰ ይመስል፤ አደገኛ አደገኛ ነገሮችን እያፈላለጉ፣ እለት በእለት እሳት ለማያያዝ፣ ነበልባሉን ከአንዱ ወደ ሌላው ለማዛመት የሚሻሙ ሞልተዋል።
ብሔር ብሔረሰብን ከፖለቲካ ጋር ይቀይጣሉ፣ ሌላ ጊዜ ከሃይማኖት ጋር ያዳቅላሉ።
እንዲያውም፣ እንደ ጀግንነት ይፎክሩበታል። “አጀንዳ እያመጣን ግራ እናጋባቸዋለን” ይላሉ- አገርን የማወዛገብ ጀብድ መሆኑ ነው።
“የመጣው ይምጣ፣… አብጦ ይፈንዳ፣… የተናጠው ይደፍርስ፣… የተዳፈነው ይንደድ፣…”… “ከዚያ የሚሆነውን እናያለን”… የሚል ፉክክርና እሽቅድምድም እየማረካቸው፣ የመጠፋፋት ውድድር እንደስራ የሚያዘወትሩ በዝተዋል።
አዲስ ውዝግብ ሳይፈጥሩ ካደሩ፣ አገርን የሚያንገጫግጭ፣ ህዝብን የሚያንጫጫና- የሚያስጨንቅ ቀውስ ሳይፈጥሩ ከሰነበቱ፣ ክብራቸው የተገፈፈ፣ ዝናቸው የተረሳ፣ ስልጣናቸውን ያስደፈሩ፣ ተቃዋሚነታቸውን ያስነጠቁ ይመስላቸዋል።
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ በጣም አደገኛ እንደሆነ ጠፍቷቸው፣ መዘዙን ሳያውቁ ቀርተው ነው ነገር የሚያጋግሉት? አዎ፣ አላዋቂዎች ይኖራሉ። ሞልተዋል። ግን ደግሞ፣ አደገኛነቱን ፈልገውት እሳት የሚለኩሱና የሚያቀጣጥሉም አሉ።
ሃይማኖትን የፖለቲካ ጉዳይ ማድረግና ሁለቱን ማቀላቀል፣ ከብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካም በላይ የከፋ መሆኑስ አያውቁም? ሃይማኖት እና ፖለቲካ፣… አንዱ የሌላው አገልጋይ መሳሪያ እንዲሆንላቸው የሚፈልጉ ነውጠኛ ባለስልጣናትም ሆኑ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች፣ የእሳት ጨዋታ የሚያምራቸው አላዋቂ ሕፃናት ናቸው ወይ?
ፖለቲካንና ሃይማኖትን ማዳቀል፣… ራሱን የቻለ የጥፋት ምጽዓት መሆኑ ብቻ አይደለም ክፋቱ። ሌሎችም የአገር ችግሮችንና ህመሞችን የሚያባብስ፣ የሚያጦዝ አደገኛ ጥፋት እንደሆነስ አይገባቸውም? የማይገባቸው ይኖራሉ።
ግን አደገኛነቱ የሚያጓጓቸው፣ ቃጠሎ ለማየት የሚሻሙም ሞልተዋል።
አገር ሲጨስ፣ ሲነድ፣ መግቢያ መውጫ ጠፍቶበት ሲተራመስ በማየት የጥረታቸውን ውጤታማነት ለማረጋገጥ ይናፍቃሉ።
ገደል አፋፍ ላይ ባለች አገር ውስጥ፣ እየተንሸራተተችና እየተንገዳገደች ባለችበት ዘመን፣ እንዲህ አይነት አዳዲስ ክፉ ቅዠት እየተጨመረ አገር ምድሩን ሲያዳርሰው ማየት ያስጨንቃልም። ያሳዝናልም።
ግን የተሻለ ነገር ማሰብ እንችላለን። የአድዋ የነፃነት ድልን! ወይም የሕዳሴ ግድብን።
እንግዲህ፣ ከግድቡ የሚነጨውን የኤሌክትሪክ ሃይል፣ ለ11ኛ እና ለ12ኝ ክፍል ተማሪዎች በሚያመች መንገድ፣ ቀመሩንና ስሌቱን ማሳየት አይከብድም ብለን የለ!
የጥያቄና መልስ አዝናኝ ዝግጅት ሊወጣለትም ይችላል ብለናል - ትንሽ ከታሰበበት። እስቲ እንሞክረው።
ከመቶ ሜትር ከፍታ የተለቀቀ አንድ ኪሎ ግራም ክብደት፣ ወደታች ወርዶ ወለል ላይ ሲደርስ፣ ምን ያህል ጉልበት ሊፈጥር ይችላል?
ክብደት ሲባዛ፣ በግራቪቲ፣ ሲባዛ በከፍታ…
የፊዚክስ ትምህርት ውስጥ በቲዎሪ ደረጃ የተማርነው ፍሬ ሃሳብና ቀመር ነው። ነገር ግን ቀመሩን ከሚጨበጥ ጉዳይ ጋር ማያያዝ ይቻላል።
በአንድ ሴኮንድ፣ 1600 ሜትር ኩብ ውሃ፣ ከመቶ አርባ ሜትር ከፍታ እየወረደ፣ ተርባይኖችን ቢያሽከረክር፣ … ብለን ስንቀምረው፣…
ይሄም ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል ቢቀየር፣… ብለን ስናሰላው፣ ጥያቄውን ወደ ሕዳሴ ግድብ አስጠጋነው ማለት ነው።
ሜትር ኩብ ስንል፣ በሁሉም ጎኖቹ አንድ ሜትር የሆነ ጋን ልንለው እንችላለን። አንድ ሺ ሊትር ውሃ መያዝ የሚችል ጋን ብለን ብንተረጉመውም ያስኬዳል።
እናማ በሴኮንድ 1600 ሜትር ኩብ ውሃ ስንል፣ በሴኮንድ 1.6 ሚሊዮን ሊትር ገደማ እንደማለት ነው። አንድ ሊትር ውሃ ደግሞ፣ 1 ኪሎ ግራም አይደል? በነገራችን ላይ የዘይት የነዳጅ ክብደት ከውሃ ያንሳል። ይሄ ተፈጥሯዊ ባሕርይ ምን ይባላል? “specific density”? በትክክል ተመልሷል።
ወደ ሕዳሴ ግድብ ስንመለስ፣ በአማካይ 1.6 ሚሊዮን ሊትር (ኪሎ ግራም) ውሃ በሴኮንድ ያወርዳል ብለን የለ? በሴኮንድ 1.6 ሚሊዮን ኪሎግራም፣ በግራቪቲ (ማለትም በ9.81) ሲባዛ፣ ስንት ይሆናል? ትክክል ነው። 15.7 ሚሊዮን ይሆናል።
ከፍታው 140 ሜትር ነው በሚል ስናባዛው፣ ከ2.2 ቢሊዮን በላይ ዋት ይሆናል።
በእርግጥ፣ አንዲት የሙቀት ሽውታ ሳያባክን ምግብ የሚያበስል ምድጃ አለ እንዴ? የለም። የተወሰነው ያህል የምድጃ ሙቀት በየአቅጣጫው እየወጣ በዙሪያችን ሲናኝ ይሰማናልኮ።
ልክ እንደዚያው፣ የኤሌክትሪክ ተርባይንም፣ እያንዳንዷን ጠብታ ተጠቅሞ ይሽከረከራል ማለት አይደለም። በጎን በኩል የሚያልፍ ውሃ ይኖራል። ሌላኛው የብክነት ሰበብ… ምንድነው? በትክክል ተመልሷል። friction ወይም ሰበቃ ይባላል።
ቢሆንም ግን፣ አብዛኛውን የውሃ ጉልበት ወደ ኤሌክትሪክ ሃይል የመለወጥ ብቃት አለው። ይሄን የምንገልጽበት ፍሬ ሃሳብ ምን ይባላል? turbine efficiency! በትክክል ተመልሷል። የተርባይን ኤፊሼንሲ ከ85 በመቶ በታች አይሆንም። ስለዚህ ከውሃው የሚገኘውን ጉልበት፣ በ.85 እናባዛዋለን።
ስሌቱን አጠናቀቅን ማለት ነው።
1.87 ቢሊዮን ዋት ወይም 1870 ሚሊዮን ዋት ይሆናል።
“ሚሊዮን” የሚለውን ቃል፣ “ሜጋ” በሚልም መተካት እንችላለን።
1870 ሜጋ ዋት እንደማለት ነው። የአገራችንን የኤሌክትሪክ ኃይል በእጥፍ እንደማሳደግ ቁጠሩት።
ታዲያ፣ ይሄ ምን ይባላል? ተጨባጭ የማመንጨት አቅም ይሉታል።
5250 ሜጋ ዋት የምንለውስ? የተርባይኖቹ ጠቅላላ የአቅም ጥግ ልንለው እንችላለን።
ግን የመኪናውን ፍጥነት እስከ ጥግ ድረስ ረግጦ ሁልጊዜ መሸምጠጥ ይቻላል እንዴ? አይቻልም። የግድብና የተርባይ የአቅም ጥግ እንደዚያ ነው።
እዚህ ላይ ቢበቃንስ? የጥያቄና መልስ አዝናኝ ዝግጅት ለመፍጠር፣ በጥንቃቄ ማሰብ ያስፈልጋል- የሚወሳሰቡ ነገሮችን ለማፍታትና ገለጥለጥ አድርጎ ለማቅረብ። ግን ቢሳካስ ምን ዋጋ አለው?
የአገሬውን የትምህርት ሁኔታ ለወሬ የሚመች አልሆነም። እንኳን ለጥያቄና መልስ ዝግጅት።
ትምህርት ገደል ቢገባስ ማን ይጨንቀዋል? ለሳምንት ያህል በወቀሳና በማስተባበያ መበሻሸቂያ ከሆነ በኋላ፣ ከአእምሯችን እናሰናብተዋለን።
እህስ? አተካራ፣ ውዝግብ፣ ውንጀላ፣ ግጭት፣ ጦርነት፣… ላይ ነው ውሎና አዳራችን።

Read 1190 times