Print this page
Saturday, 04 March 2023 10:56

መልካም መርሆችን እያሟሉ በየልካቸው ማዋሃድ - የቅንጦት ጥያቄ?

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

• የጥሩ ነገሮች፣ የመልካም መርሆች የተሟላ ውህደት ነው - ወርቃማው አማካይ።
    • የጥሩና የመጥፎ ቅይጥ አይደለም።
    • ጥሩ ነገሮችን በግማሽ እየበረዙ ወይም እየበከሉ ማቀላቀልም አይደለም።
    • በተቻለ መጠን፣ ጤናማ ዱቄትና ዘይት፣ በተቻለ መጠን ጥራት ያለው ሲሚንቶና አሸዋ በትክክል እንደማዋሃድ ቁጠሩት።


“ወርቃማው አማካይ” ይሉታል - መልካምነቱን ለመግለፅና ለማድነቅ።
“ሦስተኛው የመሃል መንገድ” ብለው ይጠሩታል። የተቃና የጉዞ መስመር እንደሆነም ይመሰክሩለታል።
“መሃል ሰፋሪ” የሚል ቅጽልም ይጠቀማሉ - የሰውን ሚዛናዊ አቋም ለማመስገን።
የሦስቱም አገላለፆች የትርጉም ዝንባሌ ተቀራራቢ ነው። መልዕክታቸውም ግልፅ ይመስላል።
ታዲያ፣ ትርጉማቸው ግልፅ ከሆነ፣ ለምንድነው በርካታ ጠቢባን ማብራሪያ ለመስጠት የደከሙት?
ታዲያ ለምንድነው፣ “መሃል ሰፋሪ” የሚለው ቅፅል፣ ለስድብና ለአድናቆት ያገለገለው? ሚዛናዊነትን የሚገልፅና የሚያስመሰግን አባባል ነበር - ከመቶ ዓመት በፊት። የዛሬ 50 ዓመት ደግሞ፣ የሚያስኮንን ሆኗል። “እከሊት ወላዋይ ናት፣ አገሌ አቋም የለሽ ነው” ብለው ለመሳደብ ሲፈልጉ፣ “መሃል ሰፋሪ” የሚል ታርጋ ይለጥፉባቸዋል።
በተለያዩ ሰዎች አንደበት፣ የተለያየ ትርጉም የያዙ፣ ወይም ተቃራኒ መልዕክት የሚያስተላልፉ አባባሎች፣ ግልጽነታቸው የቱ ላይ ነው? በርካታ ጠቢባን፣ ወርቃማ አማካይ ምን ማለት እንደሆነ ለማብራራት መድከማቸውስ፣ ትርጉሙ፣ ግልጽ ባይሆን አይደል? እና የሦስቱ አባባሎች መልእክት ምን ይሆን? ትርጉማቸውስ ምንድነው?
ሳይበዛ ሳያንስ ማለት ነው አማካይ ማለት? ከግራም ከቀኝም፣ ርቀቱና ቅርበቱ እኩል ሲሆን ነው መካከለኛ የሚባለው? ከፊትም ከኋላም ያላፈነገጠ፣ ከመሃል የተቀመጠ ነው?
ሳይቀድምና ሳይዘገይ፣ ሳይፈጥንና ሳያዘግም፣ ሳይንከወከውና ሳይደነዝዝ፣ ሳይወፍርና ሳይቀጥን ማለት ነው መካከለኛ ማለት?
ቅይጥ ድብልቅ፣ የነጭና የጥቁር ቅልቅል ግራጫ መልክ፣ ብርሃንና ጨለማ መሆኑ ያልለየለት ድንግዝግዝ፣ የገሀድ እና የህቡዕ ቅይጥ፣ የግልጽና የስውር አማካይ የሆነ፣ ውልብታና ብዥታ ነው መካከለኛ ማለት?
የለየለት ውሸታም ወይም የተዋጣለት ሐቀኛ ያልሆነ፣ ግማሽ እውነት ግማሽ ሐሰት የሚናገር፣ በፈረቃ አሉቧልታ የሚያናፍስና ከዚያም የተረጋገጠ መረጃ የሚወራ ሰው፣ መካከለኛ ነው?
ለእያንዳንዱ ሰው እንደየስራው የሃቅ ዳኝነትን መስጠት እንችላለን። በዘር በጭፍን መቧደን በጅምላ መፈረጅ ለምደናል። ሁለቱንም እንደ አመቺነታቸው እያለዋወጥን፣ ከዚህ ከዚያ እያጣቀስን፣ አንዳንዴ በጤናማ የሥነ-ምግባር መርህ፣ ሌላ ጊዜ በዘረኝት ስሜት  እየቀየጥን ስናምታታ ነው ወይ አማካይ መንገድ?
የጥሩ እና የመጥፎ፣ የመርዝና የፈውስ ውህደት፣ ልማትንና ጥፋትን ያመጣጠነ ሚዛን ነው - ወርቃማ አማካይ ማለት?
ወይስ ሁለት ስህተቶችን ማዛነቅና ሁለት ጥፋቶችን ማፈራረቅ ይሆን አማካይ ማለት?
50 በመቶ ጀብደኛ 50 በመቶ ፈሪ፣ ቀን ላይ ቆጥቋጣ፣ ወደ ማታ ደግሞ ብኩን፣ በየተራ ባሪያና ገዢ ከሆነም መካከለኛ ነው? መሃል ሰፋሪ ይባላል?
የሁለት መጥፎ ጥጎች፣ የጉረኛና የወራዳ፣ የቀበዝባዛና የፈዛዛ፣ የቀባጣሪና የዝጋታም ቅይጥ ነው መካከለኛ?
ወይስ ከሁለቱ ጽንፎች የጸዳ ማለት ይሆን መሃል ሰፋሪነት?
በዓይኑ በገሃድ ያየውን ነገር፣ ቅንጣት ሳይጨምርና ቅንጣት ሳይቀንስ፣ ሳያጋንን ሳያኳስስ የሚናገር ሰው ነው እውነተኛ ምስክር? ሁለት መጥፎ ጥጎችን የሚያዳቅል ሳይሆን፣ በሁለቱ መሃል በጠባቧ መንገድ የሚያልፍ ሰው ነው ጻድቅ?
ከጥሩና ከመጥፎ ጥጎች የተዳቀለስ?
ከውሸትና ከእውነት፣ ከቅንነትና ከመሰሪነት፣ ከአስተዋይነትና ከሞኝነት፣ ከስንፍናና ከጉብዝና፣ ከብቃትና ከድክመት፣ ከማምረትና ከማምታታት፣ ከማልማትና ከማጥፋት፣… ከሁለቱም ጥጎች ጋብቻ የሚገኝ ይሆን መካከለኛ ማለት? እየለገሙ መትጋት? ታታሪው ታካች ሰው ነው መሃል ሰፋሪ ማለት?
በክፋት የሚያለማ፣ በበጎ የሚያጠፋ፣ ለመጥፎ አላማ እውነትን የሚናገር፣ ለመልካም አላማ የውሸት ፕሮፓጋንዳ የሚነዛ ሰው ነው ሚዛናዊ?
የሁለት መልካም ጥጎች ግማሽ መንገድስ?
ግማሽ ጠንቃቃ ግማሽ ጀግና፣ በከፊል ለጋስ በከፊል ቁጥብ፣ በጣምም ቁምነገረኛ ያልሆነ፣ በጣምም ተጫዋች ያልሆነ፣ ለዘብተኛ ሰው ነው የወርቃማው አማካይ ምሳሌ?
የቻለውን ያህል ነባር መሰረቶችን ማጽናትና አሻሽሎ አዳዲሶችን መገንባት ሳይሆን፣ ግማሹን የሚያፈርስ፣ ለግንባታም የአቅሙን ግማሽ ያህል ብቻ የሚጠቀም? የአንድ ቀን ስራውን በማለዘብ፣ ለሁለት ቀን አካፍሎ የሚያከናውን ሰው ነው የወርቃማው አማካይ ምርጥ አርአያ?
በተገቢው መጠን፣ ሰውን እንደየስራው ከልብ ማድነቅና መንቀፍ፣ ማበርታትና መገሰጽ ሳይሆን፣ በግማሽ ልብ መሆን አለበት ነገረ - ስራችን? ያኛውም ተሞገስኩ ብሎ እንዳይኮፈስ፣ ያኛውም ተነቀፍኩ ብሎ እንዳያኮርፍ፣ ከአድናቆቱ ትንሽ በንፍገት እናጉድልበት? ከተግሳጹም በግማሽ ወይም እስከ ሩብ ጉዳይ ድረስ እንቀንስለት?
ዳኝነት ላይም እንደዚያው፣ ተበዳይ ባዶ እጁን እንዳይቀር ግማሽ ካሳ እንዲያገኝ ግማሹን እናስቀርበት? በዳይ እንዳይቀየም በግማሽ ቅጣት እንዲያመልጥ ከግማሽ እዳ ነፃ እንዲወጣ እንፍረድለት?
መቼም፣ በጥንቃቄ መመርመር አለብን። ሳይመረምሩ በጥድፊያ ለመፍረድ አለመቸኮል ጥሩ ነው (ሳያረጋግጡና ሳያመዛዝኑ ላለመፍረድ)።
ግን ደግሞ፣ ሳያመነቱ ሳያድበሰብሱ እውነት መፍረድም ጥሩ ነው (ሁሉም እንደየስራው የሚገባውን እንዲያገኝ)።
እናም፣… የበደለ አላግባብ ተጠቃሚ ሆኖ እንዳይቀጥል፣ የተበደለም ተጎጂ ሆኖ እንዳይቀር፣… ትክክለኛና የተሟላ ዳኝነት ያስፈልጋል እንል ይሆናል። ነገር ግን፣ ወርቃማው አማካይ ማለት፣ ለተበደለ በከፊል ተቆርቁረን፣ ለበደለም በከፊል አድልተን፣ ፍርዳችንን ለማመጣጠን የምንጨነቅበት ጭጋጋማ ዘዴ ከሆነስ? መሃለኛው መንገድ ማለት ለየትኛውም ደንታ የሌለው ገለልተኛ ግድ የለሽነት ቢሆንስ?
ዳኝነት የግድ ከሆነ ደግሞ፣ ምገሚሱን መመርመርና ገሚሱን ማድበስበስ፣ በከፊል መቸኮልና በከፊል ማመንታት ነው ወይ፣ ወርቃማ አማካይ መንገድ? እየተምታቱ እያምታቱ ግራ መጋባት?
በቂ ምግብ ማሟላት ተገቢ ነው። የምግብ ዓይነቶችን አመጣጥኖ አስማምቶ ማዘጋጀትም ጥሩ ነው። ሁለቱ ጥሩ ቢሆኑም፣ ወደ ሁለቱ ህጎች፣ ወደ ሁለቱ ጥግ ጽንፎች ሳንሄድ፣… በጣምም ሳናሟላ፣ በጣምም ሳናመጣጥን፣ ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላው ሳናዘነብል መመገብ ነው የወርቃማው አማካይ ህግ?
በጣምም ያልጎደለና ያልተመናመለነ፣ በጣምም ያልተዛባና ያልተዘባረቀ፣ እንደነገሩ እንደማሟላትና እንደማመጣጠን የሚመስል፣ በከፊል የጎደለ፣ በመጠኑ የተዛነፈ መሆን አለበት ኑሯችን?
ጽንፍ ያልረገጠ መካከለኛውን መንገድ፣ ወርቃማውን አማካይ የምናገኘው በዚህ መንገድ ነው? መቶ በመቶ በቂ ምግብ ማሟላት፣ መቶ በመቶ በትክክል ማመጣጠን ከተቻለስ? ጽንፍ የረገጠ፣ እስከ ጥግ የተስፈነጠረ (extrimism) ይባላል?
በምልዓት ማዋሃድ የቻለ ሰው፣ የወርቃማው አማካይ ፀር ይሆናል ወይ? ይህ አንድ ጥያቄ ነው።
አሟልቶ በየልካቸው አመጣጥኖ - የቅንጦት ጥያቄ?
በእርግጥ በምልዓት ማዋሃድ፣ ሁልጊዜና በሁሉም ነገር ላይ አይቻልም የሚል ሃሳብ እንደሚመጣብን አያጠራጥርም። ግማሽ ግማሽ ማግኘትም የሰማይ ያህል እየራቀብን፣… በምልዓት ስለማዋሃድ ይጭነቀን እንዴ?
ተመጣጥኖ የተሟላ ወይም ተሟልቶ የተመጣጠነ… የሚሉት ቅንጦት ቀርቶብን፣ በቀን ሶስቴ ሳይሆን በወጉ አንዴ ከተቻለም ሁለቴ የምንበላው ነገር መች አገኘን?
በፀሎትና በምህላ፣ መሬት አርሰን ብረት ቀጥቅጠን፣ ከንጋት እስከምሽት ደክመን፣ ጠብ የሚል ነገር እየራቀን፣… ስለወርቃማው አማካኝ መንገድ፣ ወይም ስለ ምሉዕ ውሕደት ብንፈላሰፍ፣…አንዳች የሚቀመስ ፍሬ እናመጣለን?
ዝም የሚያሰኙ ጥያቄዎች ናቸው። ዝም የሚያስብሉ ጥያቄዎች ቢሆኑብንም ግን፣ ዝምታችን መፍትሔ ይሆናል ማለት አይደለም።
ደግሞም ሰዎች ዝም ብለው አይደለም የሚኖሩት። አንዳንዱን አስቀድመው፣ ሌላውን አቆይተው፣ ያለችውንና የተገኘችውን አብቃቅተው ነው ኑሯቸውን የሚገፉት። በዝምታ አይደለም። ለትንሿ እንጀራ ትንሽ ወጥ አዘጋጅተው፣ ለእፍኝ ሽሮ ጠብታ ዘይት ገዝተው፣ ጨው ቆንጥረው፣ ለኤሌክትሪክ ሂሳብና ለከሰል ተጨንቀው፣… ከኑሮ ጋር ይታገላሉ። እህሉ ከማነሱ ማስፈጫና መጋገሪያ ቢጠፋ ይታያችሁ።
አነሰም በዛ፣ እፍኝ ታህልም ብትሆን፣ ለማሟላትና ለማመጣጠን መሞከር የግድ ነው። እህል ስላነሰ ማብሰያ አያስፈልግም ማለት አይደለም። የሽሮ ዱቄት እንዳያልቅ እየተጨነቁ፣ ወጥ መስሪያ ዘይት ባይኖር አስቡት።
ምናለፋችሁ? ማምለጫ የለውም። ያለችውንና የተገኘችውን አመዛዝኖና አብቃቅቶ፣ አመጣጥኖና አዋህዶ ለማሟላት በሚደረግ ጥረት እንጂ በዝምታ አይደለም ሰው የሚኖረው። እሱም “ኑሮ” ከተባለ ነው። ግን እሱስ በዝምታ መች ይሆናል? በቀን አንዴ ብቻ ወይም ሁለቴ ለመብላት ሊሆን ይችላል የየእለቱ ትግል። አንዴ ለመብላትም ቢሆን ግን፣ ለዚህችውም ኑሮ፣… ተመጣጥነው መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ።
በዚያ ላይ አስማምተው አዋህደው ካላዘጋጁት፣ ከንቱ ልፋትና ብክነት ይሆናል። አረረ፣ ከሰል ሆነ፤… ገንፍሎ ፈሰሰ እንደማለት ነው - ያለችውንም ማጣት።
ያው፣… አሟልቶና አመጣጥኖ የማዋሃድ ጥያቄ፣ የቅንጦት ቢመስልም፣ ለሞላላቸውና ለተረፋቸው ሰዎች የምንተወው ጉዳይ ቢመስልም፣ በተቃራኒው በተቸገሩ ሰዎች ላይ ነው ጥያቄው የሚበረታው።
በሌላ አነጋገር፣ “ አመጣጥኖ ማሟላትና ማዋሃድ”፣ ሁሉንም ሰው የሚመለከት የኑሮ የሕይወት ጉዳይ ነው - የጤንነትና የጣዕም ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር ስናየው፣ “ሁሉም ልክ አለው” ከሚለው ሀሳብ ጋር ልናዛምደው እንችላለን።
አመጣጥኖ የማሟላትና የማዋሃድ መንገድ፣… ወርቃማው አማካይ መንገድ ነው ማለትም ይቻላል። አለበለዚያ ጤንነትና የሕይወት ጣዕም ይዛባል፤ ይጓደላል፤ ይበላሻል።
ሚዛኑ፣ ምጣኔው፣ ልኩ ከተዛባ፣… ወዲህ ወይም ወዲያ ካዘነበለ፣… መንገዱን ስቶ በከንቱ ይባክናል፤ ተደናቅፎ ይወድቃል። የእንጀራና የወጥ፣ የዘይትና የጨው ጉዳይ ብቻ አይደለም። አዎ፣ ሁሉም ጥሩ ናቸው። አማራጮች አይደሉም። መሟላት አለባቸው። ሲሟሉም በየልካቸው ተመጠጥነው ተስማምተው መዋሃድ ይኖርባቸዋል።
እውነትን መናገር፣ ፍሬያማ አላማ መያዝና መትጋት፣ በራስ ብቃት መተማመንና ሃላፊነትን አለመሸሽ… እነዚህም ሁሉ ጥሩ ናቸው። ሁሉንም እንደየ አቅማችንና እንደየ እውቀታችን መጠን ልናሟላቸው ይገባል። አማራጮች አይደሉም።
የአንድ ሕይወት ሦስት ገፅታዎች ናቸውና፣ አንዱን ከሌላው ስንነጥለው ሕይወትን ያጓድልብናል። አንዱን ይዘን ሌላኛውን ብንዘነጋው ወይም ብንጥለው፣ የያዝነውን ያበላሽብናል። አንዱን እያውለበለብን ሌላኛውን ላለማየት አይናችንን ብንጨፍን፣ የምናውለበልበውን ነገር ማየት እናቆማለን።
እያሟላንና እያዋሃድን ስንጓዝ ነው፣ ኑሮን የማሻሻል፣ የሕይወትን  ትርጉም የማጣጣም እድል የምናገኘው።
በተቃራኒው፣… “ለበጎ አላማ” የምትል ሰበብ ይዘን፣ የውሸት ወሬዎችንና የሃሰት ውንጀላዎችን የምናናፍስ ከሆነስ?
በሌላ አቅጣጫ ደግሞ፣ “የእገሌ ንግግር እውነተኛ ቢሆንም፣ ለአጥፊ አላማ፣ በክፉ የጥላቻ ስሜት የተነገረ ነው” የምትል ሰበብ ይዘን፣ ላለመስማስ ጆሯችንን ከመድፈን ባሻገር፣ እውነትን ብናስተባብልስ?
ከዚያም አልፈን፣ እውነትን ለማፈንና ለማስፈራራት የሚሞክር ተቃዋሚ፣ ወይም ለማሳደድና ለማሰር የሚዘምት ባለስልጣን ብንሆንስ? የአገራችን ፖለቲካ፣ በዚህ አይነት ጠማማና ሰንካላ መንገድ የሚጓዝ ነው።
ጥሩ ነገሮችን ማሟላት ያስልጋል። አንዱን ብቻ ይዞ፣ በዚያ ሰበብ ሌሎች ጥሩ ነገሮችን ለማጥፋት መዝመት፣ የጥበብ መንገድ አይደለም። የጥሩና የመጥፎ ቅይጥ ሳይሆን፣ የጥሩ ነገሮች ምልዓት ነው ወርቃማ መንገድ። በየልካቸው ሟሟላትና ማዋሀድ።
ጥሩና ተገቢ ነገሮችን፣… አቅማችንን በሚመጥን ትጋት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ፣ ደረጃ በደረጃ፣ እንደየልካቸው እያመዛዘንን፣ እያሟላንና እያዋሃድን የምንጓዝበት መንገድ፣… “ወርቃማው አማካይ መንገድ” ነው ልንለው እንችላለን።
ነገር ግን፣ ጥሩ ነገሮችን በምልዓት እንደየልካቸው ለማዋሃድ፣… ሚዛንና መስፈሪያ ለመጠቀም፣… በቅድሚያ ጥሩና መጥፎ፣ ተገቢና ነውር ለይተን ማወቅ ይኖርብናል።  የወተትና የመርዝ ልዩነትን ካወቀን፣ ሚዛንና መስፈሪያ ምን ይጠቅመናል?
ምግብ ስንሰራ፣ የእህል ዱቄትና ሲሚንቶ፣ ጨውና አሸዋ የሚምታታብን ከሆነ፣ አመጣጥኖ ማሟላት ብሎ ነገር፣ ትርጉም ያጣል። ምግብ ስናዘጋጅ፣… የምናመጣጥነው የምግብ ዱቄትንና ጨው፣ ውሃና ዘይትን ነው። ቤት ስንገነባም እንደዚያው ነው - ሲሚንቶና አሸዋ በየልካቸው ተሟልተው መዋሃድ አለባቸው።
ልክ እንደዚያው፣ የስነምግባር መርሆችንም በምልዓት እንደየልካቸው ለማዋሃድ፣ መልካም የሆኑትን ለይተን የምናውቅበት መስመር ያስፈልገናል። የጥሩ ነገሮች፣ የመልካም መርሆች የተሟላ ውህደት ነው  - ወርቃማው አማካይ። የጥሩና የመጥፎ ቅይጥ አይደለም። ጥሩ ነገሮችን በግማሽ እየበረዙ ወይም እየበከሉ ማቀላቀልም አይደለም። በተቻለ መጠን፣ ጤናማ ዱቄትና ዘይት፣ በተቻለ መጠን ጥራት ያለው ሲሚንቶና አሸዋ በትክክል እንደማዋሃድ ቁጠሩት።


Read 1274 times