Saturday, 04 March 2023 11:05

የእርግዝና የመጀመሪያ 3 ወራት…

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(4 votes)

   በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚፈጠሩ እርግዝናዎች መካከል ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆኑ ፅንሶች በተለያየ ምክንያት የመቋረጥ አደጋ ያጋጥማቸዋል። ከዚህም ውስጥ 80 በመቶ በመጀመሪያ የእርግዝና 3 ወራት (13 ሳምንታት) ውስጥ የሚያጋጥም ነው። ማለትም ከ4 ነፍሰጡር እናቶች መካከል 1 እናት የተሸከመችውን ፅንስ ታጣለች። ከእናቶች ቁጥጥር ወይም ድርጊት ውጪ (በተፈጥሮ እንዲሁም በተለያዩ ሰው ሰራሽ ሁኔታዎች እና አጋጣሚዎች) ፅንስ የመቋረጥ ሁኔታዎች ይኖራሉ። ነገር ግን በእርግዝና ወቅት እራስን ከተለያዩ ነገሮች መጠበቅ ያስፈልጋል። በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ እንደተናገሩት ይህ የእርግዝና የመጀመሪያ 3 ወራት በተለየ መልኩ ትኩረት እና ጥንቃቄ ይፈልጋል። ምክንያቱም የፅንሱ የሰውነት ክፍሎች የሚፈጠሩት በዚህ ጊዜ ነው። ይህ ከ6 እስከ 13 ሳምንት ያለው የእርግዝና ወቅት የአካል ግንባታ ጊዜ (organogenesis) በመባል ይጠራል። ከሚገነቡት ከሰውነት ክፍሎቹ መካከል የነርቭ ስርአት [አእምሮ እና የጀርባ አጥንት ‘spinal cord’]፣ ልብ፣ ፊት፣ አይን፣ የምግብ ስርአት (digestive system)፣ እጅ እና እግር ተጠቃሽ ናቸው።
የግብረ ስጋ ግንኙነት የምትፈጽም ማንኛዋም ሴት እርግዝና እንደሚፈጠር መጠርጠር እና ወደ ህክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባት የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል። ይህም በእርግዝና የመጀመሪያ 3 ወራት ለፅንስ እና ለእናት እንክብካቤ ለማድረግ ቀዳሚው ጉዳይ ነው። በህክምና ተቋም የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት የደም፣ የሽንት እና የዘረመል ምርመራ ነው። እንዲሁም የእናት እና የቤተሰብ የህክምና ታሪክ በተለይም እናት ከዚህ ቀደም በስነተዋልዶ ጤና ዙርያ የነበራት ታሪክ ላይ መሰረት በማድረግ ህክምና ይሰጣል።  
እርግዝና እንደተፈጠረ ወደ የህክምና ተቋም መሄድ ያለው ጥቅም
ሁሉም እርግዝና ማህፀን ውስጥ ላይፈጠር ይችላል። ስለሆነም የተፈጠረው እርግዝና ከማህፀን ውጪ ከሆነ እናት የከፋ ጉዳት ሳይደርስባት ህክምና እንድታገኝ ይረዳል።
ፅንስ ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል እናት የምትጠቀመው መድሀኒት ካለ ሙድሀኒቱ እንዲቀየር ወይም እንዲቀር ይደረጋል።
አንዲት እናት በበሽታው መጠቃቷን ሳታውቅ አብሯት የቆየ በሽታ ሲኖር በሽታው እንዲታወቅ እና ህክምና እንድታገኝ ያግዛል።
የእናት አመጋገብ እንዲስተካከል ስለሚደረግ የፅንሱ አፈጣጠር ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል።
በመጀመሪያ የእርግዝና 3 ወራት ወቅት መደረግ ያለባቸው ጉዳዮች
የተመጣጠነ ምግብ መመገብ
የበሰለ ምግብ ብቻ መመገብ
የእራስ እና የአከባቢን ፅዳት መጠበቅ
ቀለል ያለ የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግ
ማንኛውንም መድሀኒት የህክምና ባለሙያ ሳያማክሩ አለመውሰድ; ቀላል ተብለው ወይም ምግብ ናቸው ተብለው የሚታሰቡትንም ቢሆን ያለ ሀኪም ማማከር ሙውሰድ አይመከርም። ለምሳሌ; የቫይታሚን መድሀኒት እንክብል…ወዘተ
እፆችን አለመጠቀም (ማቆም); ሲጋራ፣ ጫት፣ በሲርንጅ የሚወሰዱ እና ሌሎችም አድንዛዥ እፆች የተከለከሉ ናቸው።
ሙሉበሙሉ የአልኮል መጠጥ ማቆም(አለመውሰድ)
የስራ ወይም የአኗኗር ሁኔታን ማስተካከል; ከጨረር ጋር ግንኙነት ያለው ስራ መስራት፣ ከፍተኛ የሆነ ሙቀት ያለበት እንደ ስቲም እና ሳውና ባዝ መጠቀም አይመከርም። ይህም የአፈጣጠር ችግር ሊያስከትል የሚችል መሆኑን ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ተናግረዋል።
ተላላፊ ከሆኑ በሽታዎች እራስን መጠበቅ(መከላከል)
በእርግዝና ወቅት ጥንዶች ማድረግ ስለሚገባቸው እና ስለሚከለከሉ ጉዳዮች ሲነሳ የግብረ ስጋ ግንኙነት ይጠቀሳል። የፅንስ እና ማህፀንም ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ እንደተናገሩት ማንኛዋም ጤነኛ የሆነች ነፍሰ ጡር ሴት የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀም ትችላለች። ነገር ግን ከእናት ጤና ጋር ተያይዞ የግብረ ስጋ ግንኙነት እንዳይፈፀም የሚከለከልበት ሁኔታዎች አሉ። ከዚህ ቀደም ጊዜውን ያልጠበቀ ምጥ በተደጋጋሚ ያጋጠማት እና ከ12 ሳምንት የእርግዝና ጊዜ በኋላ ፅንስ ያቋረጠች እናት ከሆነች የግብረ ስጋ ግንኙነት ባትፈፅም ይመከራል። እንዲሁም ከተፀነሰው ፅንስ (ልጅ) ቁጥር አንፃር እና በአጠቃላይ ከእናት የስነተዋልዶ ታሪክ (ጤና) ጋር በተያያዘ ሊከለከል ይችላል። በአጠቃላይ ጥንዶች ቢያማክሩ የተሻለ መሆኑን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
እናቶች በእርግዝና ወቅት አካላዊ እና ስነልቦናዊ ለውጥ ወይም ህመም እንደሚያጋጥማቸው ይታወቃል። በእርግዝና ወቅት ቀለል ያለ የእራስ ምታት ወይም የማዞር ስሜት፣ ድድ አከባቢ መድማት፣ ትንፋሽ መቆራረጥ፣ የድካም እና የእንቅልፍ ስሜት፣ ቶሎ ቶሎ መሽናት፣ ጨጓራ ማቃጠል፣ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ እንዲሁም ጡት አከባቢ ማሳከክ ወይም እብጠት ሊያጋጥም ይችላል። ነገር ግን የደም መፍሰስ፣ ከፍተኛ የሆነ የራስ ምታት፣ ሆድ እና ዳሌ አከባቢ የህመም ስሜት እንዲሁም ያልተለመዱ ወይም ከፍተኛ የህመም ስሜት ሲያጋጥም የህክምና ባለሙያ ማማከር ያስፈልጋል።
የህክምና ባለሙያዋ እንደተናገሩት በመጀመሪያ የእርግዝና 3 ወራት ብዙ ፅንሶች መፈጠራቸው እንኳን ሳይታወቅ በእራሳቸው ጊዜ ይቋረጣሉ። ነገር ግን ፅንስ የመቋረጥ(የመውረድ) ሁኔታ ጀምሮ ያለምንም ችግር ሳይጠናቀቅ ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ እና ህመም ሊያጋጥም ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የኢንፌክሽን ችግር ሊያጋጥም እና ከአፈጣጠር ችግር ጋር በተያያዘ የእንግዴ ልጅ በጣም በማደግ እንደ እጢ (molar pregnancy) ሊሆን ይችላል። ይህ እንደ እጢ ያደገው ክፍል ማህፀን አከባቢ ብቻ ወይም በሰውነት ክፍል በሙሉ ተሰራጭቶ (እንደ ካንሰር) ችግር ሊያስከትል ይችላል።
ልምዳቸውን እንዲያካፍሉን ካነጋገርናቸው ነፍሰጡር እናቶች መካከል ወ/ሮ ብሌን አሰፋ “እኔ እንኳን 2 ልጆችን በሰላም ብገላገልም እህቴ ግን 2 ጊዜ የጸነሰችው ልጅ ወርዶባታል’’ በማለት ተናግረዋል። እንደ ወ/ሮ ብሌን ንግግር ለዚህ ጽንስ መቋረጥ ምክንያት የሆነው ጽንስ መፈጠሩን ባለማወቅ ለነፍሰ ጡር እናቶች የማይመከሩ ተግባራትን [ስራዎችን] በመከናወናቸው ነው። የወ/ሮ ብሌን እህት ደም ሲፈሳቸው እና ከባድ ህመም ሲሰማቸው ወደ ህክምና ተቋም በሄዱበት ወቅት ነበር እርግዝና መኖሩን ያወቁት። ልምዳቸውን ያካፈሉን ሌላኛዋ እናት ወ/ሮ ነቢላ አህመድ ይባላሉ። የ1 ልጅ እናት የሆኑት ወ/ሮ ነቢላ በመጀመሪያው የእርግዝና 3 ወራት የማቅለሽለሽ፣ ሽታ መጥላት እና ምግብ የመምረጥ [የመጥላት] ስሜት ነበራቸው። ነገር ግን እርግዝና በተፈጠረ በ1 ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ህክምና ተቋም በመሄዳቸው እና ህክምና በማግኘታቸው ለከፋ ህመም ወይም ጉዳት አልተዳረጉም።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ “እናቶች ሁልጊዜ ነፍሰጡር ሊሆኑ እንደሚችሉ መጠርጠር ያስፈልጋል። በዚህም እርግዝና መኖሩን ቶሎ በማወቅ በንቃት ለልጅ እና ለእናት ጤና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠቅማል። አባቶችም በዚህ ወቅት የስነስልቦና እና ሌሎች ድጋፎችን ማድረግ አለባቸው።” በማለት ለእናቶች እንዲሁም ለጥንዶች መልዕክት አስተላልፈዋል።


Read 2416 times