Sunday, 12 March 2023 10:28

የህክምና ስህተት እና ህግ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(2 votes)

በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ በህክምና ሂደት ውስጥ ‘የህክምና ስህተት’ ተብሎ ስለሚጠራው ጉዳይ በስፋት ይነገራል። በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም ላይ ለሞት እና ለአካል ጉዳተኝነት ከሚዳርጉ 10 ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ የህክምና ስህተት ሆኖ ይመደባል። የህክምና ስህተት የሚባሉት የተሳሳተ መድሀኒት መስጠት፣ ህክምና መስጠት ሲገባው አለመስጠት፣ የታካሚውን በእውቀት ላይ የተመሰረተ የመታከም ፈቃድ አለማግኘት፡ በቀዶ ጥገና ወቅት የሚፈጸሙ ስህተቶች፣ ባእድ ነገሮችን በታካሚው አካል ውስጥ መተው፣ ዘግይቶ ህክምና መስጠት፣ በሽተኛውን ትቶ ጤነኛውን አካል ማስወገድ፣ ሰመመን (ማደንዘዣ) መጥኖ አለመስጠት እና አላስፈላጊ ቀዶ ጥገና መስጠት ናቸው። የህክምና ስህተት የሚፈጠረው በህክምና ባለሙያ፣ በህክምና መሳሪያ፣ በምርመራ ሂደት፣ በመዝገብ አያያዝ፣ በአጠቃላይ ሂደት(ሲስተም) እና በታካሚ ግንዛቤ (እውቀት) ችግር ምክንያት ነው።
“የህክምና ሙያ ውስብስብ ነው” በማለት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ተናግረዋል። ለዚህም እንደ ምሳሌ ያቀረቡት አንድ ምርት በፋብሪካ ውስጥ ሲመረት ግብአቱ እና ውጤቱን ማወቅ ይቻላል። ነገር ግን በህክምና ላይ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ በመሆን (አስቀድሞ በመተንበይ) ውጤትን መናገር አይቻልም። ሁለት ሰዎች ተመሳሳይ የሆነ ህክምና አግኝተው የተለያየ የህክምና ውጤት ሊኖራቸው ይችላል ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። የዚህ ምክንያት ደግሞ የታካሚ፣ የህክምና ባለሙያ እና የህክምና መሳሪያ ሊሆን ይችላል።
በቀላሉ ከሚሰጥ መድሀኒት ባለፈ ህክምናው ጊዜ የሚወስድ እና ውስብስብ ሲሆን ችግሩም ይበልጥ ይጨምራል። ስለሆነም “ውጤት ብቻ በመመልከት ስህተት ተፈጥሯል ማለት አይቻልም” ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። ለምሳሌ አንዲት ሙሉ ጤንነት ያላት እናት ልጅ ስትወልድ ጉዳት ቢያጋጥማት ወይም የተወለደው ልጅ አሊያም የእሷ ህይወት ቢያልፍ ሙሉ በሙሉ የህክምና ስህተት ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ጤነኛ የነበረችው ነፍሰጡር ሴት ምን እንዳጋጠማት፣ ያጋጠማትን እክል (ችግር) የጤና ባለሙያዎች የተረዱበት ፍጥነት፣ የተሰጣት የህክምና እርዳታ (ሂደት)፣ ለሂደቱ የነበረው ምላሽ፣ ምላሹ በተገቢው ጊዜ መሆን ወይም አለመሆኑን እና ሌሎችም መታየት ያለባቸው ጉዳዮች ታይተው ነው የህክምና ስህተትን መለየት የሚቻለው።
የኢትዮጵያ ፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ስለህክምና ስነምግባር እና ከህክምናው ጋር ተያይዞ ስላለው የህግ ሁኔታ ጥር 23 2015 ዓ.ም ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል። የኢትዮጵያ የፅንስ እና የማህፀን ሀኪሞች ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ የህክምና ጉዳይ የሚታይበት የህግ ማዕቀፍ ለህክምና ብቻ የተዘጋጀ አይደለም። እንደአጠቃላይ በተዘጋጀው የአስተዳደር፣ የቤተሰብ እና የወንጀል ህግ ውስጥ የተካተተ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የህግ ባለሙያዎች ስለህክምና እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች ስለህግ በቂ ግንዛቤ (እውቀት) የላቸውም። ሌላኛው በህግ እና በህክምና ባለሙያዎች መካከል ተግባቦትን ለመፍጠር አዳጋች የሚያደርገው የህክምና ቃላቶች አስቸጋሪ መሆን ነው። ስለሆነም ከህክምና ጋር በተያያዘ እራሱን የቻለ የህግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ወይም ያለውን ህግ አመቺ ማድረግ ያስፈልጋል። እንዲሁም የህክምና እና የህግ ሙያ ያላቸው ሙያተኞችን ማፍራት አስፈላጊ በመሆኑ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱን ዶ/ር ገላኔ ተናግረዋል።
ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ እንደተናገሩት የህክምና ጉዳዮችን በተመለከተ በሌሎች ሀገራት የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች (አሰራሮች) አሉ። አንድ የህክምና ባለሙያ በህክምና ሂደት ላይ ያልተፈለገ ውጤት ሲያጋጥመው ወይም ስህተት ተፈጥሯል ተብሎ ሲታሰብ የህግ እና የህክምና እውቀት(ሙያ) ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው ለጉዳዩ እልባት የሚሰጡት። እንዲሁም የህክምና ስህተት ወንጀል የሚሆነው በተለያዩ መስፈርቶች ተጣርቶ በግድ የለሽነት፣ በተለያየ ጥቅም እና በሌላ ወንጀል በሚያስብሉ ምክንያቶች መፈፀሙ ሲረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ ግን ሁሉም የህክምና ስህተት ከወንጀል ጋር የማያያዝ ሁኔታ መኖሩን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል።
ከህክምና ህግ ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ (ችግር) ለህክምና እና ለህግ ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰቡም ጉዳት እንዳለው የተናገሩት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ናቸው። በህክምና ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች በተገቢው መንገድ መፍትሄ ካላገኙ በህብረተሰቡ እና በህክምና ባለሙያ መካከል ያለመተማመን ስሜት ይፈጥራል። ይህ ደግሞ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ችግር ያስከትላል።
ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ የህክምና ስርአት ማለትም በህክምና ባለሙያ እና በታካሚ መካከል ያለውን ግንኙነት ለሁለት በመክፈል አብራርተዋል።
አባታዊ/ እናታዊ የህክምና ስርአት (maternalistic principle); የህክምና ባለሙያ ለታካሚ ይጠቅማል ብሎ የሚያስበውን ነገር ይወስናል። ግላዊ የህክምና ስርአት (Autonomy principle); አንድ ሰው(ታካሚ) ስለእራሱ ህክምና እራሱ እንዲወስን የሚያደርግ አሰራር ነው።
እነዚህ ሁለቱ ስርአቶች የማይደጋገፉበት (የሚጋጩበት) አጋጣሚ መኖሩን የህክምና ባለሙያዋ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ህይወቱን አደጋ ላይ በሚጥል በሽታ ሊታመም እና ለመዳን ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ታካሚው ቀዶጥገናውን ባይፈልግ በግላዊ የህክምና ስርአት መሰረት ቀዶጥገናው አይደረግም።
የህክምና ባለሙያዋ እንደተናገሩት ታካሚዎች፣ የታካሚ ቤተሰቦች እንዲሁም ማህበረሰቡ የህክምና ውጤት ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ በህክምና ባለሙያ እና በህክምና ሙያ ላይ እምነት ያጣሉ። ይህም በህክምና ባለሙያዎች የተደረገውን ርብርብ[ህክምና] የማወቅ እድል ስለሌላቸው የሚፈጠር ነው።
እንደ መፍትሄ የህክምና ባለሙያዋ ያስቀመጡት ህክምና በሚሰጥበት ቦታ ላይ የታካሚ ቤተሰብ እንዲገኝ(እንዲመለከት)፣ ታካሚው በሚወስነው ውሳኔ ላይ ቤተሰብ እንዲያግዝ እና በአጠቃላይ የህክምናው ሂደት እንዲታወቅ ማድረግ (መፍቀድ)ን ነው። ለምሳሌ; በብዛት በቀዶ ጥገና ልጅ መውለድ በሰላም የሚጠናቀቅ እና ችግር የማያስከትል የህክምና አይነት ነው። ነገር ግን ከሚሰጠው የማደንዘዣ መድሀኒት (Anesthesia) እና ከቀዶጥገና ጋር በተያያዘ እስከ ሞት ሊያደርስ ይችላል። ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው ከታሰቡ እናቶች ውጪ ያጋጥማል። ስለሆነም ይህ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል አስቀድሞ ለታካሚዎች መንገር (በህብረተሰቡ ዘንድ መታወቅ) ያስፈልጋል።
የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የፅንስ እና ማህፀን ሀኪሞች ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ከህክምና ስህተት ጋር ተያይዞ በተለይም በማህበራዊ ድረገፆች ላይ የተሳሳቱ መረጃዎች እንደሚሰራጩ ተናግረዋል። ስለሆነም ህብረተሰቡ ሁሉንም መረጃን ከማመኑ አስቀድሞ በሁለቱም (በታካሚ እና በህክምና ባለሙያ) በኩል ያለውን እውነታ ቢያገናዝብ የተሻለ ነው። እንዲሁም ስህተት ሲፈጠር ችግሩ የሚፈታው በህግ ባለሙያዎች ዘንድ መሆኑን በመገንዘብ ለባለሙያዎች መተው ያስፈልጋል።
የጽንስ ማህጸን ህክምና እስፔሻሊስት የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ህክምና ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ህብረተሰቡ የሚያገናዝብ፣ መረጃ ያለው እና የሚከታተል ‘የነቃ ታካሚ’ እንዲሆን መልእክት አስተላልፈዋል። እንዲሁም የስነተዋልዶ ጤና ላይ ችግር ከመፈጠሩ አስቀድሞ እራስን መከላከል እንደሚያስፈልግ ዶ/ር ገላኔ ሌሊሳ ተናግረዋል።
በፍትህ ሚንስቴር የንቃተ ህግ ትምህርት እና ስልጠና ክፍል ውስጥ አቃቢ ህግ የሆኑት አቶ ተሰማ ግደይ የውይይት መርሀ ግብሩ ተሳታፊ ናቸው። የህግ ባለሙያው እንደተናገሩት ፍትህ ሚንስቴር የህክምና ስህተትን አስመልክቶ አነስተኛ ጥናት ሰርቷል። በጥናቱ መሰረት ስለ ህክምና እና ስለህግ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ለጤና ባለሙያዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ለመስራት መታሰቡን(መታቀዱን) የህግ ባለሙያው ተናግረዋል።


Read 900 times